Pages

Wednesday, May 30, 2012

አብ የሚያደርገውን ሁሉ ወልድ ደግሞ ይህን እንዲሁ ያደርጋል- የዮሐንስ ወንጌል የ25ኛ ሳምንት ጥናት (ዮሐ.5፡18-28)=+=


     ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እነርሱ መዳን ብሎ ወደ ቤታቸው ቢመጣም፣ በኃይልና በሥልጣን የሚያደርገውን ሁሉ ሲያደርግ ቢመለከቱትም መጻሕፍትን ከመመርመር ይልቅ፣ ትንቢተ ነብያትን ከማገናዘብ ይልቅ አይሁድ የራሳቸውን ወግ በመጥቀስ ሊገድሉት ይፈልጉ ነበር፡፡ የሚናገረውን እንኳን ባያምኑ የሚያደርገውን አይተው ወደ እርሱ እንዲመጡ በተገባ ነበር፡፡ ነገር ግን ይባስኑ ውስጣቸው በቅናት ይቆስል ነበር፡፡ ስለዚህም “ሰንበትን ስለሻረ ብቻ ሳይሆን ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር ስለሚያስተካክል ይህ ሰው ከእግዚአብሔር አይደለም” ለማለት ደፈሩ /ቁ.18/፡፡ ጌታችን ግን አንዳንድ ልበ ስሑታን እንደሚሉት “ስለምን ልትገደሉኝ ትፈልጋላችሁ? እኔ ከአብ ጋር የተካከልኩ አይደለሁም” ወይም “አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል እኔም አገለግላለሁ” ሳይሆን “አባቴ እስከ ዛሬ (ቅዳሜ ቅዳሜ) ይሠራል (አንዳንድ ድውይ ይፈውሳል) እኔም እንዲሁ እሠራለሁ (መጻጉዕን ፈወስኩ)” ይላቸዋል /ቁ.17/፡፡ ወንጌላዊው እዚህ ጋር የአይሁዳውያኑ አባባል ትክክል ስለነበረ በሌላ ቦታ /ዮሐ.2፡19/ እንደሚያደርገው ማስተካከያ አላደረገበትም፤ ከዚህ በፊት እንዳደረገውም “አይሁድ ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር እንዳስተካከለ ቢያስቡም ክርስቶስ ግን እንዲህ ማለቱ ነበር” አይልም /Saint John Chrysostom Homilies on St. John, Hom 38./፡፡

   ከዚህ በኋላ ስለ ሰው ልጆች መዳን አብዝቶ የሚሻ ጌታችን እንዲህ ይላቸዋል፡- “እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ ወልድ ከራሱ ሊያደርግ ምንም አይችልም” /ቁ.19/፡፡ ምን ማለት ይሆን? እውነት “ነፍሴን ላኖራትም ላነሣትም ሥልጣን አለኝ” ያለው ጌታ ምንም ሊያደርግ አይችልምን? /ዮሐ.10፡18/፡፡ ወንድሞቼ ይህን በጥንቃቄ ልናስተውለው ይገባል፡፡ ይህ መለኰታዊ ቃል አንዳንዶች እንደሚያስቡት ሳይሆን እንዲህ ማለቱ ነው፡- “እኔ ከራሴ ብቻ አንቅቼ ምንም ምን ሥራ አልሠራም፤ ከአብ በሕልውና ያየሁትን በህልውና ያገኘሁትም እሠራለሁ እንጂ፡፡ የአብ ፈቃድ የእኔ ፈቃድ ናት፤ የአብና የእኔ ፈቃድ እርስ በእርሷ የምትለያይ አይደለችም፡፡ እስከ ዛሬ አብ የወደደውን ሲያደርግ እንደነበረ እኔም እንዲሁ (በተመሳሳይ ሥልጣን በተመሳሳይ ዕሪና) የወደድኩትን አደርጋለሁ፡፡ አብ ይፈውስ እንደነበረ እኔም እፈውሳለሁ፡፡ ስለዚህ አብ አባቴ ነው ስላልኳችሁ አትደነቁ፤ ከአባቴ ጋር የተካከልኩ ነኝ ስላልኳችሁ አትበሳጩ፡፡ እናንተን ለማዳን ብዬ ምንም ከአባቴ ጋር ያለኝን መተካከል እንደመቀማት ሳልቆጥረው የእናንተ የባርያቼን መልክ ብይዝም አብ የሚያደርገውን ሁሉ እኔ ደግሞ ይህን እንዲሁ አደርጋለሁና /ፊል.2፡6/፤ የአብ የሆነ ሁሉ የእኔ ነውና፤ የእኔም የሆነ ሁሉ የአብ ነውና /ዮሐ.17፡10/፡፡ የሆነው ሁሉ በእኔ የሆነው አብ መፍጠር የማይችል ሆኖ ሳይሆን በሥላሴ ዘንድ የፈቃድ ልዩነት ስለሌለ ነው” /ዮሐ.1፡3 Saint AmbroseOf the Holy Spirit Book 2:8:69/። በእርግጥም ክርስቶስ አልዓዛርን ከሞት ሲያስነሣው አብ ምንም አላደረገም አይባልም /ዮሐ.11፡42/፤ ክርስቶስ የዓይነ ሥውሩን ብርሃን ሲመልስለት መንፈስ ቅዱስ ምንም አላደረገም አይባልም /ዮሐ.9፡3/፡፡ የሥላሴ ሥራ በአንድነት በአንድ ፈቃድ የሚደረግ እንጂ በተናጠል የሚደረግ አይደለምና /Saint Augustine. Sermon on N.T. Lessons, 76:9/፡፡

    ከእናንተ መካከል “ታድያ ስለምን በቀጥታ የአብና የእኔ ፈቃድ አንድ ናት አይላቸውም ነበር?” የሚል ሊኖር ይችላል፡፡ እኛም እንዲህ ብለን እንመልስለታለን፡- ተወዳጆች ሆይ! “አይችልም” የሚለው አገላለጽ ድካምን ብቻ የሚያመለክት አድርጋችሁ አትዩት፡፡ ለምሳሌ “እግዚአብሔር ሊዋሽ አይችልም” ሲባል ድካምን የሚያመለክት አገላለጽ አይደለም /ዕብ.6፡18/፤ ፍጹም የሆነ ኃይልንና ሥልጣንን እንጂ፡፡ ስለዚህ አስቀድመን እንዳልነው ጌታችን “ወልድ ከራሱ ሊያደርግ ምንም አይችልም” ሲል “የአብና የእኔ ፈቃድ አንድ ነው፤ እርስ በእርሱ የሚለያይ አይደለም፤ የባሕርይ አንድነታችን የተለያየ ፈቃድ እንዲኖረን አያደርግም፤ የማደርገውን ሁሉ በፍጹም ኃይልና ሥልጣን አደርገዋለሁ” ማለቱ እንደሆነ እንወቅ እንረዳ፡፡ “ይህማ እንዲህ ማለት አይደለም” ብሎ የሚከራከረን ሰው ካለም ክርስቶስ ራሱ ምን ማለቱ እንደሆነ ይንገረው፤ እርሱም ያድምጥ፡- “ያ (አብ) የሚያደርገውን ሁሉ ወልድ ደግሞ ይህን እንዲሁ ያደርጋል”። “እንዲሁ” የምትለዋን አገላለጽ በጥንቃቄ እንመልከታት፡፡ እንግዲያውስ ወንድሞቼ የጌታችን ንግግር በአንክሮ ልንመለከተው የሚገባ እንጂ በቸልታና በአባባል ደረጃ የሚታለፍ አይደለም፡፡ 

    ሰው አፍቃሪው ጌታ አንዳንዴ ጠለቅ መጠቅ ባለ አነጋገር ሌላ ጊዜ ደግሞ ዝቅ ባለ አነጋገር የሚናገረው የሰማዕያኑን ድካም ለማገዝ ነው /ዮሐ.5፡34፣ 11፡42፣ 12፡30/፡፡ ለምሳሌ “አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል እኔም ደግሞ እሠራለሁ” ይልና እንዳይረቅባቸውና እንዳይደነጋገሩ ደግሞ “አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ ወልድ ከራሱ ምንም ሊያደርግ አይችልም” ብሎ በጥበብ ይነግራቸዋል፡፡ ይህችን ጫፍ ይዘው “ዕሩቅ ብእሲ ነው፤ ወልደ ከአብ ያንሣል” እንዳይሉ ደግሞ መልሶ “አብ የሚሠራውን ሥራ ወልድ ደግሞ ይህን እንዲሁ ይሠራዋል” ይላቸዋል፡፡ አሁንም እንዳይጠጥርባቸው “አብ ወልድን ይወዳልና፥ የሚያደርገውንም ሁሉ ያሳየዋል፤ እናንተም ትደነቁ ዘንድ ከዚህ የሚበልጥ ሥራ ያሳየዋል” ይላቸዋል /ቁ.20/፡፡ እንዲህ ማለቱ ነበር፡- “መጻጉዕን ፈወሰ፤ በሰንበትም አልጋውን ተሸክሞ እንዲሄድ አደረገ ትላላችሁ፡፡ ነገር ግን ገና ከዚህ የሚበልጥ ታያላችሁ፡፡ ሙታንን ሲያነሣ ታያላችሁ፤ ሙታንን ማንሣት ብቻ ሳይሆን በራሱ ሥልጣን ከሙታን ተለይቶ ሞትን ድል አድርጐ ሲነሣ ታያላችሁ፤ በአብ ዕሪና በዙፋኑ ሲቀመጥ ታዩታላችሁ”፡፡ ስለዚህ ንግግሩን በጥንቃቄ ካስተዋልነው “አብ ያሳየዋል ወልድም ይህን ማድረግ ስለማይችል ያየውን ብቻ ያደርጋል” ወደሚለው ደምዳሜ የሚያደርስ አይደለም /Saint John Chrysostom Ibid/፡፡ 

   “አብ ሙታንን እንደሚያነሣ ሕይወትም እንደሚሰጣቸው፥ እንዲሁ ወልድ ደግሞ ለሚወዳቸው ሕይወትን ይሰጣቸዋል” /ቁ.21፣ 1ነገ.17፡22፣ ዮሐ.11፡14/፡፡ በእርግጥም አስቀድመን እንደተነጋገርነው ይህ የትሕትና ንግግር ካልሆነ በስተቀርና “ወልድ ከራሱ ምንም ሊያደርግ አይችልም” ካልን (ስሙ ከፍ ከፍ ይበልና!) አብ እንደወደደ እንጂ ወልድ እንደወደደ ለሚወዳቸው ሕይወትን ሊሰጣቸው አይችልም፡፡ ጌታችን ግን ይህን ግልጽ ሲያደርግልን “እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ” ብሏል /ዮሐ.6፡40/፤ ይህ ብቻ ሳይሆን “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ” ብሏል /ዮሐ.11፡25፣ Saint John Chrysostom Ibid/፡፡ 

   ስለዚህ “ወልድ ከአብ ያንሣል” ብለው አፋቸውን የሚያላቅቁ መናፍቃን ይፈሩ፡፡ አብ ኃጢአትን እንደሚያሥተሰርይ ወልድም እንዲሁ ያሥተሰርያል፤ አብ ሙታንን እንደሚያነሣ ወልድም እንዲሁ በአንዲት ሥልጣን በአንዲት ፈቃድ ሙታንን ያነሣል፤ አብ ሕይወትን እንደሚሰጥ ወልድም እንዲሁ በአንዲት ሥልጣን በአንዲት ፈቃድ ለሚወዳቸው ሕይወትን ይሰጣቸዋል፡፡ እንደ እኛ ደካማ ፍልስፍና ሳይሆን የሕይወት መጽሐፍ እርሱ እንደነገረን እንመን፡፡ በእርሱ ፊት የምናፍር እንዳንሆን ዛሬውኑ እንመለስ /Saint John Chrysostom, Hom 39 /፡፡ 

  ስለ እኛ ዝቅ ብሎ የሞተው ይህ ንጉሥ ዳግም በግርማው ለፍርድ ይመጣል፡፡ ሰዎች ሁሉ አብን በሚያከብሩበት ክብር መጠን ወልድን ያከብሩት ዘንድ፥ ታይቶ መግዛትን ታይቶ መፍረድን ሁሉ ለወልድ ሰጠው እንጂ አብ ታይቶ ማንንም ማንን አይገዛም፤ አብ ታይቶ በአንድ ሰው ስንኳ አይፈርድም  እንዲህ ሲባል ግን አብ ጭራሽ አይፈርድም ማለት ሳይሆን በወልድ ህልው ሆኖ ይፈርዳል ማለት ነው፡፡ ወልድን የማያከብር የላከውን አብን አያከብርም፤ አብን የባሕርይ አባት ወላዲ ብሎ ወልድን የባሕርይ ልጅ የማይል እርሱ አብን ያህዌ ነው ሊል አይገባም /ቁ.22-23፣ ወንጌል ቅዱስ አንድምታ ገጽ 480/፡፡ 

   ስለዚህ “ክብሬን ለማንም አልሰጥም” ያለው አብ “ለወልድ ክብርን በመስጠት ከፍ አደረገው” ብለን ከመናገር እንፈር፡፡ ከተዋሕዶ ውጪ ያላችሁ ወንድሞቼ! አብ አባት ያልሆነበት ቅጽበት እንደሌለ ሁሉ ወልድም ልጅ ያልሆነበት ቅጽበት እንደሌለ እወቁ ተረዱ፤ በአብና በወልድ መካከል የጊዜ መቀዳደም እንደሌለ እወቁ ተረዱ፡፡ አብ እስከ ዛሬ እንደሚሠራ ሁሉ ወልድም እንዲህ እንደሚሠራ እወቁ ተረዱ፤ አይሁድ በቅናት ተነሣስተው ሊገድሉት ሲፈልጉ ፈርቶ ሳይሆን ስለ እነርሱ ድካም ብሎ በደካማ አገላለጽ “አብ ሲያደርግ ያየውን እንጂ ወልድ ከራሱ ምንም ሊያደርግ አይችልም” እንዳለ እወቁ ተረዱ፡፡ በጊዜው የነበሩ አይሁድ እንዲድኑ ይህን ሁሉ ደካማ አገላለጽ እንደተጠቀመ እወቁ ተረዱ።  “የላከ እና የተላከ እንዴት እኩል ይሆናሉ?” በማለት ሥጋዊ አመክንዮ የምታመጡ አትሁኑ፡፡ ፀሐይ ብርሃኗን ብትልክልን ብርሃኑ ከፀሐይዋ ዘግይቶ መጣ አይባልም፡፡ ስለዚህ በአርዮስ ደዌ የምትለከፉ አትሁኑ (አርዮስ ወልድ ዓለምን ለማዳን የተፈጠረ ፍጡር ነው ይላልና)፡፡ አሁንም ጌታችን “አንዳንዶች ይህ ሰው ሰንበትን አያከብርምና ከእግዚአብሔር አይደለም” ብለው ስለተደናበሩ እነርሱን ለማገዝ የተናገረው ሰውኛ አገላለጽ እንደሆነ እወቁ ተረዱ /ዮሐ.9፡16/፡፡ እንዲህ ባይሆን ኖሮ አገላለጹን የገባቸው አይሁድ ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር አስተካክሎእግዚአብሔር አባቴ ነው” ስላለ ሊገድሉት አብዝተው ባልፈጉ ነበር፡፡ እኛ እንዲገባን፣ ሥጋ መልበሱን ለማስረዳት እንጂ ሙሉዕ በኵለሄ የሆነው እግዚአብሔርስ ከዚህ ወደዚያ ሄደ ተብሎ የሚነገርለት አይደለም /Saint John Chrysostom, Ibid/፡፡ 

   እውነት እውነት እንላችኋለን፥ የወልድን ቃል (እግዚአብሔር አባቴ ነው ያለውን) የሚሰማ የላከውንም አብን የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው (የማታልፍ መንግሥተ ሰማያት ይወርሳል)፥ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም (ወደ ሞት ከተማ ወደ ገሃነም አይሄድም)፡፡ የወልድን ማንነት በትክክል ማወቅ ለእርሱ ምንም አይጨምርለትም፤ ለእኛ ግን ከፍርድ ለማምለጥ ወደ ዘላለማዊ ተድላም ለመግባት በእጅጉ ይጠቅመናል /ቁ.24፣ Saint Ambrose, Of the Christian Faith, 5:6:68-69/። እውነት እውነት እንላችኋለን፥ ሐዋርያው “ጌታ ራሱ በትእዛዝ በመላእክትም አለቃ ድምፅ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳልና፥ በክርስቶስም የሞቱ አስቀድመው ይነሣሉ” እንዳለው /1ተሰ.4፡16/ ሙታን የእግዚአብሔርን ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል እርሱም አሁን ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ ሙታነ ሕሊና የእግዚአብሔር ልጅ ወንጌል የሚቀበሉበት ጊዜው ዛሬ ነው /ኤፌ.5፡14/፤ የሚሰሙትም በሕይወት ይኖራሉ፤ በሁለተኛው ትንሣኤ ዕድል ፈንታ አላቸው /ቁ.25፣ ራዕ.20፡6፣ ST. Augustine:Sermon on N.T. Lessons, 77:7-8/። አብ የባሕርዩ ሕይወትነት እንዳለው እንዲሁ ደግሞ ለወልድ የባሕርዩ ሕይወት እንዲኖረው ሰጥቶታል /ቁ.26/። የሰው ልጅም ስለ ሆነ (ሥጋን ስለተዋሐደ) ታይቶ ይፈርድ ዘንድ ሥልጣን ሰጠው፡፡ በሌላ አገላለጽ ሰዎችን ያድን ዘንድ በተለየ አካሉ ከቅድስት ድንግል ማርያም እንደተወለደ፣ በሥጋው እንዳረገ ዳግመኛም ያድናቸው ዘንድ ለሚጠባበቁት ሁለተኛ ጊዜ ሊማልድላቸው ሳይሆን ሊፈርድላቸው ያለ ኃጢአት ይታይላቸዋል፤ ይመጣላቸዋል /ቁ.27፣ ዕብ.9፡28፣ ዘካ.12፡10/። በመቃብር ያሉቱ ሁሉ ድምፁን ይሰማሉ፤ መልካምም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉና በዚህ አታድንቁ /ቁ.28/። ስለዚህ መጥምቁ እንደተናገረው “በወልድ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም” ብለን እንመሰክርላችኋለን /ዮሐ.3፡36/። አሁንም መልሰን መላልሰን እንነግራችኋለን “በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል” /ዮሐ.3፡18/። አሁንም መዳን በእምነት ብቻ ነው እንዳትሉ ደግመን ከወንጌላዊው ጋር “መልካምም ያደረጉ በሕይወት በሚያኖር ትንሣኤ ክፉ ያደረጉ ግን በስቃይ ለመኖር ለፍርድ ትንሣኤ ይነሣሉና በዚህ አታድንቁ” እንላችኋለን /Saint John Chrysostom.Ibid/

 ወዮ አባት ሆይ! ከዚህ በረት ውጪ የሆኑትን ቃልህን አብራላቸው! ከዚህ እውነት ውጪ የሆኑትን እውነትህን አሳያቸው! በፍርድ ዙፋንህ ከመቆማቸው በፊት በጸጋው ዙፋንህ ፊት በእምነት እንዲቆሙ እርዳቸው፡፡ እኛንም በምግባር በሃይማኖት አጽናን አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment