“በሦስተኛውም ቀን በገሊላ ቃና ሰርግ ነበረ”/ቁ.3/፡፡ ሰርጉ የሆነው የይሁዳ ዕጣ ከምትሆን ከኢየሩሳሌም ሳይሆን ነብዩ “የአሕዛብ ገሊላ” ባላት በቃና ነው /ኢሳ.9፡1/፡፡ ጌታ በዚያ መገኘቱ የአይሁድ ምኵራብ አማናዊውን ሙሽራ እንዳልተቀበለችው የአሕዛብ ቤተክርስቲያን ግን በደስታ እንደተቀበለችው ያሳያል /ቅ.ቄርሎስ ዘአሌክሳንድርያ Commentary on the Gospel of John 2:1/፡፡ ይህም የሆነው ከተጠመቀ በሦስተኛው ቀን ነው፡፡ የመጀመርያው ቀን እንድርያስና ዮሐንስን የጠራበት ቀን ሲሆን ሁለተኛው ቀን ደግሞ ፊሊጶስና ናትናኤልን የጠራበት ቀን ነው /ቴዎዶር ዘሜውፕሳስትያ Commentary on John 1:2:1/፡፡ አንድም ጌታ የጾመው 40 ቀንና 40 ሌሊት እንደ አንድ ቀን ተቆጥሮ ነው፡፡
“እመቤታችንም ቤተ ዘመድ ናትና በዚያ ነበረች፡፡ ኢየሱስም ደግሞ ደቀ መዛሙርቱም ወደ ሰርጉ ታደሙ” /ቁ.2/፡፡ “ባልና ሚስት አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ሁለት አይደሉም፤ እግዚአብሔር አንድ ያደረገውን እንግዲህ ሰው አይለየው” እንደ ተባለ ፈጣሪ በፍጥረት መጀመርያ በአዳምና በሔዋን የመሠረተውን የጥንቱን ሥርዓተ ጋብቻ በአዲሱ የምሕረት ኪዳን በኪዳነ መንፈስ ቅዱስም መጽናቱንና መቀደሱን ጌታ በመዋዕለ ሥጋዌው አንዴ ብቻ በተገኘበት በዚሁ ሠርግ አረጋግጦልናል /ቅዱስ ቄርሎስ ዝኒ ከማሁ/፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከራሱ ክብር ይልቅ ስለ ሰዎች መልካምነት የሚገደው ነውና በዚያ ተገኘ፡፡ የባርያዎቹን መልክ ለመያዝ እንኳን ያላፈረ ጌታ በባሮቹ ሠርግ መገኘት አላሳፈረውም፤ እንኳንስ ከዚህ ቅዱስ ጋብቻ “ከኃጢአተኞች” ጋር እንኳን ሳያፍር ለመመገብ ተቀምጧል /ፊል.2፡7፣ማቴ.9፡13 ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ ድርሳን 20፡1/፡፡
ከዚያ በኋላ የወይን ጠጅ አለቀ፡፡ እመቤታችንም “የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም አለችው” /ቁ.3/፡፡ ይህንንም ያደረገችው ልጇ ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ መሆኑን ስለምታውቅ ነው፡፡ ነገር ግን ከዚያች ቀን በፊት ሁሉንም በልቧ ትጠብቀው ነበር እንጂ “የአምላክ እናት ነኝ፤ እርሱም አምላክ ነው” እያለች ራሷን ከፍ ከፍ አታደርግም ነበር፡፡ በዚሁ ሰዓት ግን የሆነው ነገር አሳፋሪ ነውና ሁልንም ለሚችል ልጇ በቀስታ አናገረችው፡፡ ከራሷ ፍላጎት ይልቅ ስለ ምእመናን የምትጨነቅ እናት መሆኗንም ያመለክታል፡፡ ልመናዋም “ሊያደርግ ይችል ይሆናል” በሚልና ጥርጣሬ በተሞላበት አኳኋን ሳይሆን በእርግጠኝነት እንደሚያደርግላት በማመን ነበር፡፡ በእርግጥም እግዚአብሔር እንዲህ ዓይነቱን ልብ ይፈልጋል /ቅ.ቄርሎስ ዘአሌክሳንድርያ/፡፡
ሌለው የምረዳው ነገር ደግሞ ጌታ ከተጠመቀ በኋላ ራሱን ለሕዝቡ መግለጥ ስለ ነበረበት ይህ ተአምር የአስተርእዮ አካልም እንደ ነበር ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ የተገለጠው የእርሱ አምላክነት ብቻ ሳይሆን የእናቱ እመ አምላክነትንም ጭምር ነበር፡፡
“ኢየሱስም። አንቺ ሴት፥ ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም አላት” /ቁ.4/፡፡ ወንጌላዊው ሉቃስ ጌታ ኢየሱስ ለዮሴፍና ለድንግል ማርያም “ይታዘዝላቸው ነበር” ይለናል /ሉቃ.2፡51/፡፡ እዚህ ቦታ ግን ለእመቤታችን እንዲህ የሚላት በአምላክነቱ አገብሮ ተአዝዞ እንደሌለበት ለማጠየቅ ነው፤ እግዚአብሔር የራሱን ሥራ የሚሠራበት የራሱ ጊዜ አለውና፤ በቀትር የሚሠራውን በሠለስት አይሠራውም፤ በሠለስት የሚሠራውም በነግህ አይሠራውምና፡፡ ይህ ቢሆንም ግን “እመቤታችን ለአገልጋዮቹ። የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ ትላቸዋለች” /ቁ.5/፡፡ ልጇ ምን ያህል እንደሚያከብራት ደግሞም የጠየቀችውን እንደሚያደርግላት ታውቃለችና /ቅ.ቄርሎስ ዝኒ ከማሁ/፡፡
ይቆየን!!