(ከቻሉ በጸሎት ጀምረው በሰቂለ ሕሊና ሆነው ያንቡት!)
“ኢየሱስም። አንቺ ሴት፥ ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም አላት” /ቁ.4/፡፡ ወንጌላዊው ሉቃስ ጌታችን ለዮሴፍና ለድንግል ማርያም “ይታዘዝላቸው ነበር” ይለናል /ሉቃ.2፡51/፡፡ አሁን ግን እንዲህ የሚላት ምንም እንኳን ልጇ ወዳጇ ቢሆንም በአምላክነቱ ሰው የሚያዘው አለመሆኑን ለማጠየቅ ነው፡፡ እግዚአብሔር የራሱን ሥራ የሚሠራበት የራሱ ጊዜ አለውና፤ በቀን የሚሠራውን በሠለስት አይሠራውም፤ በሠለስት የሚሠራውም በነግህ አይሠራውምና /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ ድርሳን 22/፡፡ እመቤታችንም ይህንን ስለምታውቅ፡- “ልጄ ወዳጄ! አንተ ከጊዜና ከቦታ ቀመር ውጪ እንደሆንክ አውቃለሁ፤ ሁሉም በጊዜው ውብ አድርገህ የምትሠራ ኤልሻዳይ መሆንህንም አላጣውም፡፡ ልጄ ወዳጄ! አሁን የምለምንህ ወገኖቼን ከሐፍረት እንድትታደጋቸው እንጂ በአምላክነትህ ለማዘዝ አይደለም፤ ከባቴ አበሳ አምላክ መሆንህን አሳምሬ አውቃለሁና፡፡ ልጄ ሆይ! ለዓለም ሁሉ መድኃኒት ሆነህ የመጣህ ከሦስቱ ቅዱስ አንዱ ቅዱስ እንደሆንክማ መልአኩ አክብሮ ከነገረኝ ቃል አውቃለሁ፤ በሕግ በአምልኮ ለሚቀርቡህ ግን ሰማዔ ጸሎት ነህና እባክህን ራራላቸው” ብላ በአራኅርኆ ማለደችው፡፡ ሰው ወዳጁ ጌታም፡- “እናቴ ሆይ! አንቺ ሴት የምልሽ ኃይለ አርያማዊት እንዳልሆንሽ ለመግለጽ ነው፡፡ ይልቁንም አስቀድሞ በአንተና በሴቲቱ መካከል በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ ተብሎ የተነገረልሽ የአዳም ልጅ መሆንሽን ለማስገንዘብ እንጂ ውኃውን ጠጅ አድርግላቸው ብትዪኝ አይሆንም እልሽ ዘንድ ካንቺ ጋር ምን ፀብ አለኝ” ብሎ መለሰላት፡፡ እመቤታችንም ለአገልጋዮቹ፡- “የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ” አለቻቸው /ወንጌል ቅዱስ አንድምታ/፡፡
“አይሁድም እንደሚያደርጉት የማንጻት ልማድ ስድስት የድንጋይ ጋኖች በዚያ ተቀምጠው ነበር፥ እያንዳንዳቸውም ሁለት ወይም ሦስት እንስራ ይይዙ ነበር፡፡ ጌታችን ኢየሱስም እኔህን ጋኖች ውኃ ሙሉአቸው አላቸው። እስከ አፋቸውም ሞሉአቸው” /ቁ.6-7/። ወንጌላዊው “አይሁድ የማንጻት ልማድ የሚያደርጉባቸው የድንጋይ ጋኖች በዚያ ነበሩ” የሚለን ያለምክንያት አይደለም፡፡ ይልቁንም ምክንያትን የሚፈልጉ ከሐድያን “ጠጁ አላለቀም ነበር፤ ቀርቶ የነበረውን አበርክቶ ሰጣቸው እንጂ” ብለው ምክንያት እንዳያገኙ ነው፡፡ ምክንያቱም በኦሪቱ ሕግ መሠረት ጋኖቹ ለማንጻት የሚጠቀሙባቸው ጋኖች ከሆኑ ለመጠጥ የሚሆን ወይን ጠጅ ፈጽሞ አይቀዳባቸውምና /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ ዝኒ ከማሁ/፡፡
ቀጥሎም “አሁን ቀድታችሁ ለአሳዳሪው ስጡት አላቸው፤ ሰጡትም። አሳዳሪውም የወይን ጠጅ የሆነውን ውሃ በቀመሰ ጊዜ አደነቀ፤ ከወዴት እንደ መጣ ግን አላወቀም፤ ውኃውን የቀዱት አገልጋዮች ግን ያውቁ ነበር፤ አሳዳሪው ሙሽራውን ዶኪማስ ብሎ ጠራው። ሰው ሁሉ አስቀድሞ ሸሎውን፣ በርዳዳውን፣ መልካሙን የወይን ጠጅ ያቀርባል፥ ከሰከሩም በኋላ ተራውን፣ መናኛውን ያጠጣል፡፡ አንተ ግን ሸሎውን፣ በርዳዳውን መልካሙን የወይን ጠጅ እስከ አሁን አቆይተሃል አለው” /ቁ.8-10/። አንዳንድ ልበ ስሑታን “ሠርገኞቹ ሁሉም ሰክረው ስለ ነበር የወይኑን ጣዕም ሊያውቁ አይችሉም፤ ስለዚህ የጠጡት የተለወጠው መልካሙን ወይን ሳይሆን መናኛውን ነው” ብለው ለማጥላላት ይሞክራሉ፡፡ ወንጌላዊው ግን የእነዚህን ነቀፋ አስቀድሞ ስለሚያውቅ “መጀመርያ ሠርገኞቹ ሁሉ ቀመሱት” አላለንም፡፡ አስቀድሞ የቀመሰው ያልሰከረው ሊሰክርም የማይችለው አሳዳሪው ብቻ ነው፡፡ እንደውም ወንጌላዊው ትንሽ ቆየቶ፡- “ኢየሱስም ውኃውን የወይን ጠጅ ወደ አደረገባት ወደ ገሊላ ቃና ዳግመኛ መጣ” በማለት ወይኑ በተአምራት የተለወጠ መሆኑን ነግሮናል /ምዕ.4፡46፣ ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ ዝኒ ከማሁ/፡፡
“ኢየሱስ በሦስት ዓመት ከሚያገርገው ይህን የምልክቶች መጀመሪያ በገሊላ ቃና አደረገ፤ ክብሩንም ገለጠ፡፡ ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ” /ቁ.11/። አስተውላችሁ ከሆነ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ውኃውን ወይን ለማድረግ ሲጸልይ ወይም ሲለምን አንመለከተውም፡፡ ይልቁንም ሠራተኞቹ ለአሳዳሪው እንዲሰጡት ነገራቸው እንጂ እስኪ ልቅመሰው እንኳን አላለም፡፡ እኛ እንደምናውቀው ተራ ወይን ሳይሆን እጅግ መልካም የሆነ ወይን እንደሰጣቸው ያውቃልና፡፡ በዚህም ጌትነቱን ገለጠ፤ ከአባቱ ጋር ያለውን መተካከል አሳየ፡፡ ደቀ መዛሙርቱም አመኑበት፡፡
ወንድሞቼ ሆይ! ዛሬም እግዚአብሔር እንደ ውኃ ጣዕም ያጣው ሕይወታችንን ወደ መልካም ወይንነት ፍጹም ሊለውጠው ይፈልጋል፡፡ እንግዲያስ እንደ ውኃ የቀዘቀዘው፣ የደከመው ማንነታችን ወደ እርሱ እናቅርበውና ፈቃዳችንን ተመልክቶ ወደ ወይን ይቀይርልናል፡፡ ከዚያ በኋላ በቃና እንደሆነው ለራሳችን ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም የደስታ ምክንያት እንሆናለን፡፡ ይህን ሁሉ እንድናደርግ እንደ ነነዌ ሰዎችም እንድንለወጥ እግዚአብሔር ይርዳን!!!