(ከቻሉ ጸልየው በትዕግሥትና በሰቂለ ሕሊና ሆነው ያንቡት)!!
“ከፈሪሳውያንም ወገን የአይሁድ አለቃ የሆነ ኒቆዲሞስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ እርሱም በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጣ” /ቁ.1/። ብዙ የዘመኑ የስነ መለኰት ተማሪዎች ኒቆዲሞስን የማታው (Extension) ተማሪ ይሉታል፡፡ ይህ ሰው አስቀድሞ በኢየሩሳሌም የፋሲካ በዓል የጌታችንን ተአምራት አይተው ካመኑት የፈሪሳውያን ወገን አንዱ ነው /ዮሐ.2፡23/፡፡ ኒቆዲሞስ በአንድ ቦታ ስለ ክርስቶስ አይሁዳውያኑን፡- “ሕጋችን አስቀድሞ ከእርሱ ሳይሰማ ምንስ እንዳደረገ ሳያውቅ በሰው ይፈርዳልን?” ብሎ ሲከራከራቸው እናገኘዋለን /ዮሐ.7፡51/፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ጌታችን ስለ ሰው ልጆች ፍቅር በመስቀል ላይ ከተሠዋ በኋላ ቅዱስ ሥጋውን አውርዶ ከአርማትያሱ ዮሴፍ ጋር በመሆን ገንዞ በክብር ሲቀብረው እንመለከተዋለን /ዮሐ.19፡39/፡፡ አሁን ግን ጌታችንን ገና በትክክል ማን መሆኑን ስላልተረዳ አብልጦ ይማር ዘንድ በሌሊት መጣ፡፡ በሌሊት መምጣቱም አይሁዳውያኑን ፈርቶ ነው፡፡ አይሁዳውያኑ አስቀድመው “እርሱ ክርስቶስ ነው ብሎ የሚመሰክር ቢኖር ከምኵራብ እንዲያወጡት ተስማምተው ነበርና” /ዮሐ.9፡22/፡፡ ሰው ወዳጁ ጌታም ተቀብሎታል፤ ለእርሱ ብቻ ሳይሆን ለእኛም የሚተርፍ ታላቅ ምሥጢርን አስተምሮታል /St. John Chrysostom, Homily on the Gospel of John 24/፡፡
ኒቆዲሞስ “ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ” በማለትና ጌታ ያደረጋቸውን ተአምራት በማድነቅ ብቻ ድኅነት የሚገኝ መስሎት ነበር፡፡ ስለዚህም “መምህር ሆይ፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣህ እናውቃለን” ይለል /St. Cyril of Alexandria, Commentary on the Gospel of John 2/፡፡
ጌታችንም “ኒቆዲሞስ! መምህር ሆይ፣ ጌታ ሆይ በማለትህ ብቻ ድኅነትን እንደምታገኝ አድርገህ አታስብ፤ መዳንህን ወደምትፈጽምበት ሕይወት ለመግባት አስቀድመህ ዳግመኛ ልትወለድ ያስፈልገሀል፡፡ እውነት እነግረሃለሁ፥ አንተ ብቻ ሳትሆን ማንም ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም” ይሏል /ቁ.3/። በሌላ አገላለጽ “ዳግመኛ ካለተወለድክ በቀር፣ ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ ካልታደስክ በቀር /ቲቶ.3፡5/ ስለ እኔ የምታስበው ሁሉ ሥጋዊና ደማዊ ነው፡፡ እኔ ግን አሁን አንተ እንደምታስበው ከዚህ በፊት ወደ እናንተ እንደላክሁላችሁ ነቢያትም መምህራንም አይደለሁም፡፡ ይልቁንም እነዚህ አንተ የምታውቃቸው ነቢያት ይወርዳል ይወለዳል ብለው ትንቢት የተናገሩልኝ መሲሕ መሆኔን ልትረዳ አትችልም፡፡ ዳግመኛም ካልተወለድክ በቀር የልጅነትን ማኅተም ስለማይኖርህ ከእኔ ጋር በመንግሥተ ሰማያት ዕድል ተርታ አይኖርህም፤ መንፈስ ቅዱስ ካላደረብህ በቀር እኔ የባሕርይ አምላክ ነው ብለህ ልታምን አትችልም” ይሏል /1ቆሮ.12፡3፣ St. John Chrysostom, Ibid/፡፡
አዎ! በሰሌዳ ላይ በተሠራ ሥዕል ከውጭ በመጣ ቆሻሻ ሲዝግና ሲበላሽ የእርሱ ምስል የሆነው ሰው ስለ ሥዕሉ ሲል ሰሌዳውን ይወለውለዋል፤ ይሰነግለዋል፡፡ ይህም ሥዕሉ ያለበትን እንጨት በመጣል ሳይሆን ከውጭ መጥቶ ሥዕሉን ያበላሸውን ቆሻሻ በማስወገድ ወደ ጥንት ሁኔታው ይመልሰው ዘንድ የሚቻለውን ያደርጋል፡፡ ንጹሐ ባሕርይ የሆነው እግዚአብሔር ቃልም በአርአያው ተሠርቶ የነበረውን ሰው ያድሰው ዘንድ ፣ በኃጢአቱ የጠፋውን ኃጢአቱን በማስተስረይ ይፈልገውና ያገኘው ዘንድ መጣ፡፡ ራሱ በወንጌል “እኔ የጠፋውን ልፈልግና ላድን መጥቻለሁ” እንዲል /ሉቃ.19፡10/፡፡ ስለዚህ ሰው እንደገና ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር “አፈር ነህና” የሚለው አሮጌ ማንነቱን ይዞ ይቀጥላል፡፡ ዳግመኛ መወለድ ማለትም እንደገና ከሴት መወለድ ማለት ሳይሆን ነፍስ በእግዚአብሔር አርአያና አምሳል እንደገና መፈጠሯንና መወለዷን የሚያመለክት ነው /St. Athanasius, On The Incarnation 14:1-2/፡፡
በእርግጥም ከመንፈስ ቅዱስ አዲስ ልደትን፤ ከአዲሱ ልደታችንም አዲስ የተፈጠረውን ሰውነትን፤ አዲስ ሰውነት ስናገኝም ክርስቶስ እርሱ ማን መሆኑን በትክክል እናውቃለን /St. Gregory of Nazianzus, On the Holy Spirit, Theological oration 5:28/፡፡
ስለዚህም ጌታችን፡- “ኒቆዲሞስ ሆይ! እኔ ከእግዚአብሔር መምህር ሆኜ እንደተላክሁ ካወቅክ፤ ያደርኳቸው ተአምራትም ይህንን ካረጋገጡልህ አሁንም አንድ ነገር ይቀራሃል፡፡ ይኸውም ሰው ሟች ሆኖ ማለትም ዳግመኛ በማይበሰብስ ባሕርይ ሳይነሣ የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊወርስ አይችልም /1ቆሮ.15፡50/፡፡ ስለዚህ ከእኔ ጋር ልትነሣ ከወደድክ እኔ እንደምሞተው ሞት ልትሞት እንደምነሣውም ትንሣኤ ልትነሣ ያስፈልጋሃል፡፡ ይህንንም የምትፈጽመው በጥምቀት በኩል ነው፡፡ ዳግመኛ ወደ ሥላሴ ማኅፀን ልትገባ ያስፈልገሀል፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር መንፈስ ስለሆነ ይህን የምትፈጽመው በጥምቀት ውኃ በኩል ነው፡፡ ይህ ወደ ሥላሴ ማኅፀን የምትገባበት ውኃ እንደ ድሮ አጠራርህ ውኃ አይምሰልህ፡፡ እዚህ ማኅፀን ውስጥ ስትገባ የሥላሴን እንጂ የውኃውን ስም የማትጠራውም ለዚሁ ነው፡፡ አንድ ሕፃን በእናቱ ሽል /ማኅፀን/ እንደሚፈጠረው ሁሉ አንተም በዚሁ ማኅፀን ዳግም ካልተፈጠርክ በቀር የእኔን ሞትና ትንሣኤ አትተባበርም” ይሏል /ሮሜ.6፡5፣ Theodore of Mopsuestia, Commentary on John 2:3.3/፡፡
ኒቆዲሞስ ግን ሰው ከአዳምና ከሔዋን ሲወለድ እንጂ ከቅድስት ሥላሴ፣ ከቤተ ክርስቲያን (በምሥጢረ ጥምቀት በኩል) የሚገኘውን ረቂቁን ልደት ምን እንደሆነ ስለማያውቅ ይደናገራል፡፡ ኒቆዲሞስ የሚያውቀው ሞትን የሚወልዱ እንጂ ሕይወትን የሚወልዱ ወላጆችን አይደለም፤ ምድራዊውን እንጂ ሰማያዊውና ረቂቁን ልደት አያውቅም፤ ከወንድና ከሴት ፈቃድ የሚገኘውን ልደት እንጂ ከአብ፣ ከወልድና ከመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ የሚገኘውን ልደት አያውቅም /Augustine, Tractes on the Gospelof John, 11:6/፡፡
ስለዚህም “ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል? ሁለተኛ ወደ እናቱ ማኅፀን ገብቶ ይወለድ ዘንድ ይችላልን?” ይላል /ቁ.4/።
የሚገርመው ዛሬም ብዙ ሰዎች እንደ ኒቆዲሞስ ተቸግረው ማየታችን ነው፡፡ “እንዴት ቅድመ ዓለም ከአብ ተወለደ ትሉናላችሁ”፤ “እንዴት እግዚአብሔር ሰው ይሆናል?” ፤ “እንዴት ሰው ውኃ ውስጥ ገብቶ ዳግም ይወለዳል?” በማለት ፍጥረታዊ አመክንዮ ለማምጣት ይጥራሉ፡፡ ጌታ ሰማያዊ ነገር ሲነግረው ኒቆዲሞስ ግን ምድራዊ ነገርን ያወራል፡፡ ዛሬም ሰማያዊዉን ምሥጢር የተረዳነውን ያህል ስንነግራቸው ምድራዊ ማረጋገጫ ይፈልጋሉ፡፡ በሕጻን አእምሮአቸውም “እንዴት ሆኖ” በማለት ራሳቸውን ያስጨንቃሉ፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ለመሰሉ ሰዎች እንዲህ ብሎ ነበር፡- “ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም” /1ቆሮ.2፡14/፡፡
ወንድሞቼ! ሰማያዊውን ምሥጢር በምድራዊ አመክንዮ ለመረዳት አንሞክር፡፡ እግዚአብሔር “ይሆናል፤ ይደረጋል” ካለን “አሜን፤ ይሁን፤ ይደረግ” ብለን መረታት እንጂ ሽሽት አያስፈልገንም፡፡ እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ይህ አስተሳሰባችን እሾክ ይሆንብንና “ኢየሱስ ጌታ ነው፤ ክርስቶስ መምህር ሆኖ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣ እናውቃለን” እያልን ነገር ግን ወደ መንፈሳዊ መረዳት ሳንደርስ እንደተደናበርን እንቀራለን፡፡ የሚያስፈልገው ግን እምነት ብቻ ነው፡፡