Showing posts with label በአዲሲቷ ቆሮንቶስ መኖር. Show all posts
Showing posts with label በአዲሲቷ ቆሮንቶስ መኖር. Show all posts

Wednesday, August 22, 2012

በአዲሲቷ ቆሮንቶስ መኖር(ለሕፃናት)!


  እንደምን አላችሁ ልጆች? ጾመ ፍልሰታ እንዴት አለፈ? ጾማችኋል አይደል? ጐበዞች!
ለዛሬ አንድ በጣም ጣፋጭ ታሪክ ይዤላችሁ ቀርቤአለሁ፡፡ ለመስማት ዝግጁ ናችሁ አይደል? ጐበዞች!
   ከዕለታት በአንዲቱ ቀን ማርቆስ ሁል ጊዜ ከሚያጠናባት ክፍል ተቀመጠና መጽሐፍ ቅዱስን አንሥቶ የቅዱስ ጳውሎስ መልእክት ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች ምዕራፍ 13 ላይ ስለ ፍቅር ማንበብ ጀመረ፡፡ ነገር ግን ደጋግሞ ቢያነበውም ፍቅር ምን ማለት እንደሆነና እንዴት ተግባራዊ እንደሚደረግ አልገባ አለው፡፡ እያሰላሰለ ሳለም በተቀመጠበት ወንበር እንቅልፍ ወሰደውና ደስ የሚል ሕልም አየ፡፡ ከነቃ በኋላም ያየውን ሕልም በወረቀት እንዲህ ብሎ ጻፈው፡-
“የሆነ አንድ ፌርማታ ላይ የአውቶብሳችንን መምጣት እየጠበቅኩ የነበርኩ ይመስለኛል፡፡ ከጎኔም አንድ ሰውዬ እንደኔ አውቶብስ ሲጠብቅ ቆሞ አየሁኝ፡፡ ሰውዬውም፡- እኔ ጋር ና አለኝ፡፡ እኔም ሄድኩና አንድ ላይ ተሳፈርን፡፡ ፊት ለፊትም እየተያየን ተቀመጥን፡፡ አውቶብሳችን መንቀሳቀስ ጀመረች፡፡ ከተወሰኑ ደቂቃዎች በኋላም አውቶብሳችን የመጀመርያው ፌርማታ በምትሆን “አዲሲቷ ቆሮንቶስ” በምትባል ስፍራ ደረስን፡፡ ሁለታችንም ወረድን፡፡ አንድ ላይ በእግር እየተንሸራሸርን ሳለ (Walk እያረግን ሳለ) ሰውዬውን ቀና አልኩና ትኩር ብዬ ተመለከትኩት፡፡ እርሱም ፈገግ ብሎ አየኝ፡፡ በፊቱ የሆነ የሐሴትና የደስታ ነገር ይነበባል፡፡ እኔም በውስጤ ደስ የሚል ስሜት ተሰማኝ፡፡ በዚያ አከባቢ እንደኛ ሲንሸራሸሩ የማያቸው ሰዎች ሁሉም በእርጋታ ቀስ ብለው ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ሳስተውላቸው አንድ ሰው ስንኳ ፊቱ የተቋጠረ የለም፡፡ እኛም ከትንሽ ደቂቃዎች በኋላ የፍቅር አደባባይ ወደተባለ አደባባይ ደረስን፡፡ በአደባባዩ መኻከል ላይ አንድ ትልቅ የውኃ ፏፏቴ (ፋውንቴን) ይታያል፡፡ አደባባዩ ዙርያው በትልልቅ ሥዕሎች (ቢል ቦርዶች) ተሞልቷል፡፡ ሰውዬም በጣቱ ወደ አንድ ሥዕል እየጠቆመ፡- “እዛ ጋር ያለው ትልቁን መስቀል አየኸው? ይህ ሥዕል የክርስቶስን ነገረ ስቅለት የሚያሳይ ሥዕል ነው” አለኝ፡፡ እኔም ክርስቶስ የተሰቀለበትን ሥዕል ለማየት ቀና ስል ወዲያው እንዲህ የሚል ጽሑፍ ከስሩ አነበብኩኝ፡- “ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም” /ዮሐ.15፡13/፡፡ ከአጠገቡ ወደ ነበረው ሌላ ሥዕል ስመለከት ቀዳሜ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ በጉልበቱ ተንበርክኮ ሲጸልይ አየሁት፡፡ ሲጸልይ የተናገራቸው ቃላትም ከሥዕሉ ግርጌ እንዲህ ተጽፈዋል፡- “ጌታ ሆይ ይህን ኃጢአት አትቁጠርባቸው” /ሐዋ.7፡60/፡፡ ዐይኔን ወደ ሌላኛው ማዕዘን ሳሻግረው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልጇ ወዳጇን ታቅፋ አየኋት፡፡ እመቤታችን ያቀረበችው የምስጋና መዝሙርም እንዲህ ተብሎ ተጽፏል፡- “ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች፡፡ መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደረጋለች፡፡ የባርያይቱን ውርደት ተመልክቷልና፡፡… ብርቱ የሆነ እርሱ በእኔ ታላቅ ሥራን አድርጓልና ስሙም ቅዱስ ነው” /ሉቃ.1፡46-49/፡፡ ወደ ሌላኘው ማዕዘን ዐይኔን ሳማትር የጠፋው ልጁን ለመቀበል ሐሴት የሚያደርገውን አባት ተመለከትኩት፡፡ በዚያም እንዲህ የሚል ጽሑፍ ነበረ፡- “እንብላ ደስም ይበለን፤ ይህ ልጄ ሞቶ ነበርና ደግሞም ሕያው ሆኗል፤ ጠፍቶም ነበር ተገኝቷልም” /ሉቃ.15፡23-24/፡፡
  ከዚያ በኋላ የሆነ መቀመጫ አገኘንና አንድ ላይ ተቀመጥን፡፡ ሰውዬውን “አደባባዩን በጣም ወደድኩት” አልኩት፡፡ ሰውየውም ሐሳቤን በአወንታ ተቀብሎ ራሱን ነቀነቀና እንዲህ አለኝ፡- “አየህ ልጄ! በዚህ አደባባይ ቂም በቀል የሚባል ነገር አይታወቅም፡፡ አንዱ በአንዱ አይቀናም፡፡ ሰላም ሲባባሉ ራሳቸውን ጐንበስ አድርገው በትሕትና ነው፡፡ ፍቅራቸው በጣም ልዩ ነው፡፡ ጌታ እንዳስተማረው እዚህ የምታየው ሰው ሁሉ ባደረገው ነገር “እኔ እኮ እንዲህ አደረግኩ” ብሎ አይመካም፡፡ ሁሉም ተራ በተራ ይደማመጣሉ እንጂ አንድ ሰው ስንኳ ድምጹን ከፍ አድርጎ አይናገርም፡፡ አንድ ስንኳ ተቈጥቶ የሚናገር የለም፡፡ እንደ አንተ ዓይነት ሕፃን በዚህ ቦታ ወይም በመማርያ ክፍል ከጓደኞቹ ጋር ከተቀመጠና እየተናገረ ከሆነ ሁሉም በጽሞና ያደምጡታል፡፡ እርሱም ሌሎች ሕፃናት ሲናገሩ በጽሞና ያደምጣቸዋል፡፡ ከጓደኛቸው አንዱ ምናልባት የተለየ ሐሳብ እንኳን ቢኖረው ያሳምናቸዋል እንጂ የእኔ ብቻ ነው ትክክል አይላቸውም፡፡ አሁንም ሌላ ሕፃን ምናልባት… ምናልባት ተሳስቶ ልክ ያልሆነ ነገር ቢናገር ቀስ አድርገው ልክ የሆነውን ይነግሩታል እንጂ ማንም ስለተሳሳተ አይስቅበትም፡፡ በቃ! እንዲህ እያደረጉ እከሌስ ጥሩ ልጅ አይደለም ተብሎ ሰው ሲያወራለት የነበረው ልጅ በአንዴ ይለውጡታል፡፡ እርሱም ጐበዝ ልጅ ይሆናል፡፡ ተራ በተራ ሁሉም ከተናገሩ በኋላ በአንድ ሐሳብ ተስማምተው ይጨርሳሉ፡፡ ሲጨርሱም ሁሉም ተቃቅፈው እየተጫወቱ ይሄዳሉ፡፡ ሲጫወቱ ደግሞ ሐቅ ሐቁን ብቻ ይነጋገራሉ እንጂ አይወሻሹም፡፡ የሚደባበቁት ምንም ነገር የላቸውም፡፡ አንዱ በሚናገረው ነገርም ሌላው ያምኗል፡፡ እናም በቃ ሁሉም ነገር የሚያደርጉት በፍጹም ፍቅር ነው፡፡ ወደየቤታቸው ሲገቡም ተጨባብጠው ደኅና እደሩ ተባብለው ይለያያሉ፡፡”
 ከዚህ በኋላ ሰውዬውን፡-“ወይኔ! ሁል ጊዜ እዚህ በሆንኩኝ? ከእነዚህ ልጆች ጋር መጫወት እፈልጋለሁ?” አልኩት፡፡ ሰውዬውም ልብ ውስጥ በሚዘልቅ ፈገግታ ራሴን እየዳበሰ እንዲህ አለኝ፡- “ይህን በሕይወትህ ማድረግ እኮ በጣም ቀላል ነው፡፡ ሁሉም ነገር የምትወስነው አንተ ነህ፡፡ ልብህ በእነዚህ ልጆች እንዳየኸው አድርገህ ሁሉም ሰው እኵል የምታፈቅር ከሆነ በጣም ቀላል ነው፡፡ እንዲህ የምታደርግ ከሆነ እዚህ ያየሃቸው ሁሉም በአንተ ሕይወት ይከናወናሉ፡፡ እንዲህ ስታደርግ ሁሉም ነገር በፍቅር ማየት ትጀምራለህ፡፡ ሊደርሱብህ የሚችሉ ችግሮች እንኳን በጣም ጠቃቅንና በቀላሉ የምትፈታቸው ይሆናሉ” አለኝ፡፡ እኔም ንግግሩን አቋረጥኩትና፡- “የሆነ የሰፈራችን ልጅ ዝም ብሎ የሚሰድበኝ ከሆነ ምንም ነገር ሳልመልስለት እንዴት እችላለሁ? እንዲህ ዓይነቱን ልጅስ እንዴት ልወደው እችላለሁ?” ብዬ ጠየቅኩት፡፡ ሰውዬውም እንዲህ ሲል መለሰልኝ፡- “አየህ! ፍቅር ከሁሉም ይበልጣል የተባለው ለዚህ ነው፡፡ አንተ በአዲሲቷ ቆሮንቶስ ከእነዚህ ልጆች ጋር መኖር ከፈለግክ ሁል ጊዜ ፍቅርን በተግባር በመግለጥ መለማመድ አለብህ፡፡ አንተ በምትኖርባት መንደር ሆነህ በልብህና በሐሳብህ እዚች ከተማ መኖር ትችላለህ፡፡ ፍቅር ከስጦታዎች ሁሉ እንደምትበልጥና የመልካም ምግባር ሁሉ እናት እንደሆነች ታውቃለህ?” ሲለኝ ከእንቅልፌ ብንን ብዬ ነቃሁ፡፡ ዓይኔን አሻሽቼ ዙርያዬን ስመለከት ሰው የለም፡፡ ባየሁት ሕልም ግን በጣም ተደሰትኩኝ፡፡ መጽሐፍ ቅዱሴንም ሳዬው 1ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 13 ላይ እንደተገለጠ ነበር፡፡ 

 ልጆች! ታሪኩን ወደዳችሁት አይደል? ጐበዞች! “እኛም እንደ አዲሰቱ ቆሮንቶስ ልጆች እንሆናለን” እንደምትሉ እርግጠኛ ነኝ፡፡ በሉ ሌላ ጊዜ ሌላ ታሪክ ይዤላችሁ እስክመጣ ድረስ ደኅና ሰንብቱ! እወዳችኋለሁ እሺ?!
(ምንጭ፡-The Coptic Orthodox Diocese of the Southern USA, Sunday school Curriculum, Grade 8)
   

FeedBurner FeedCount