Thursday, May 17, 2012

HOW IS IT THAT JESUS CHRIST MAKETH INTERCESSION FOR US? =+=


 IN THE NAME OF THE FATHER, THE SON, AND OF THE HOLY SPIRIT ONE GOD AMEN!
 
A lot of Reformers here in Ethiopia and other Sister Churches used to misinterpret this verse of the Apostle Paul in Hebrews 7:25 & Rome 8:34. But what does it mean in its Orthodox meaning? What does the Ancient Fathers say about it? Let’s hear its interpretation from one of our Oriental Orthodox Holy Fathers, St. John Chrysostom, the Arch Bishop of Constantinople and liveth from 347-407 AD.   

For as there were many a, because they were mortal, so [here is] The One, because He is immortal. “By so much was Jesus made a surety of a better covenant,” inasmuch as He sware to Him that He should always be [Priest]; which He would not have done, if He were not living. “Wherefore He is able also to save them to the uttermost, that come unto God by Him, seeing He ever liveth to make intercession for them.” Thou seest that he says this in respect of that which is according to the flesh. For when He [appears] as Priest, then He also intercedes. Wherefore also when Paul says, “who also maketh intercession for us” ( Rom. viii. 34 ), he hints the same thing; the High Priest maketh intercession. We have clearly seen this when Our Lord was saying ‘’Father, forgive them; for they know not what they do’’ (Luk.23:34).

 The question is that for He “that raiseth the dead as He will, and quickeneth them,” ( John v. 21 ), and that “even as the Father” [doth], how [is it that] when there is need to save, He “maketh intercession”? ( John v. 22.) He that hath “all judgment,” how [is it that] He “maketh intercession”? He that “sendeth His angels” ( Matt. xiii. 41, 42 ), that they may “cast” some into “the furnace,” and save others, how [is it that] He “maketh intercession”? Wherefore (the Apostle says) “He is able also to save.” For this cause then He saves, because He dies not. Inasmuch as “He ever liveth,” He hath (he means) no successor: And if He have no successor, He is able to aid all men. For there [under the Law] indeed, the High Priest although he were worthy of admiration during the time in which he was [High Priest] (as Samuel for instance, and any other such), but, after this, no longer; for they were dead. But here it is not so, but “He” saves “to the uttermost.” What is “to the uttermost”? He hints at some mystery which is the Holy Eucharist. Not on the day of the Good Friday only (the Apostle says) but there also He saves them that “come unto God by Him” through confession and this Holy Communion. If you asketh How does He save? I say unto you “In that He ever liveth” (the Apostle says) “to make intercession for them.” Thou seest the humiliation? Thou seest the manhood? For he says not, that He obtained this, by making intercession once for all, but continually, and when so ever it may be needful to intercede for them.

“To the uttermost.” What is it? Not for a time only, but there also in the future life. ‘DOES HE TEHEN ALWAYS NEED TO PRAY? Yet how can [this] be reasonable? Even righteous men have oftentimes accomplished all by one entreaty, and is He always praying? NO! If He need to pray always why then is He throned with [the Father]?’ Thou seest that it is a  condescension. The meaning is: Be not afraid, nor say, Yea, He loves us indeed, and He has confidence towards the Father, but He cannot live always. For He doth live always. “For such an High Priest also became us, who is holy, harmless, undefiled, separate from the sinners.” Thou seest that the whole is said with reference to the manhood. (But when I say ‘the manhood,’ I mean [the manhood] having Godhead; not dividing [one from the other], but leaving [you] to suppose what is suitable.) Didst thou mark the difference of the High Priest? He has summed up what was said before, “in all points tempted like as we are yet without sin.” (Heb. iv. 15.) “For” (the Apostle says) “such an High Priest also became us, who is holy, harmless.”

“Harmless”: what is it? Without wickedness: that which another Prophet says: “guile was not found in His mouth” ( Isa. liii. 9 ), that is, [He is] not crafty. Could anyone say this concerning God? And is one not ashamed to say that God is not crafty, nor deceitful? Concerning Him, however, in respect of the Flesh, it might be reasonable [to say it]. “Holy, undefiled.” This too would anyone say concerning God? For has He a nature capable of defilement? “Separate from sinners.” Does then this alone show the difference, or does the sacrifice itself also? How? “He needeth not” (he says) “daily, as the High Priest,  to offer up sacrifices for his sins, for this He did once for all, when He offered up Himself” ( Heb.7: 27) .“This,” what? Here what follows sounds a prelude concerning the exceeding greatness of the spiritual sacrifice and the interval [between them]. He has mentioned the point of the priest; he has mentioned that of the faith; he has mentioned that of the Covenant; not entirely indeed, still he has mentioned it. In this place what follows is a prelude concerning the sacrifice itself through the Holy Eucharist. 

 Do not then, having heard that He is a priest, suppose that He is always executing the priest’s office. For He executed it once, and thenceforward “sat down.” ( Heb. x. 12.) Lest thou suppose that He is standing on high, and is a minister, he shows that the matter is [part] of a dispensation [or economy]. For as He became a servant, so also [He became] a Priest and a Minister. But as after becoming a servant, He did not continue a servant, so also, having become a Minister, He did not continue a Minister. For it belongs not to a minister to sit, but to stand.

Glory be to God Amen!

( Source:-
1.St. John Chrysostom: Homily on the Epistle of Hebrews, Homily 13:6-9, English Version).
2.ድርሳን ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ድርሳን 13123-191(Dirsan zekidus Yohans Afewerk)- which is the Ethiopic Version of the above reference.)



Wednesday, May 16, 2012

ስለ ብርሃን እንዲመሰክር ስለ ተላከው መብራት (የዮሐንስ ወንጌል የሦስተኛው ሳምንት ጥናት)!

(ቢቻልዎት አስቀድመው ይጸልዩና በተመስጦ ሆነው ያንቡት)!
“ከእግዚአብሔር የተላከ ስሙ ዮሐንስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ ሁሉ በእርሱ በኩል እንዲያምኑ ይህ ስለ ብርሃን ይመሰክር ዘንድ ለምስክር መጣ። ስለ ብርሃን ሊመሰክር መጣ እንጂ፥ እርሱ ብርሃን አልነበረም። ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም ይመጣ ነበር።” ዮሐ.1፡6-9
 አካላዊ ቃል ከአባቱ ዕሪና ሳይለይ ሰው ሆኖ ተገልጧልና ስለዚሁ ድንቅ ነገር ይመሰክር ዘንድ መልአክ ሳይሆን ዮሐንስ የሚባል ሰው ተላከ /አውግስጢኖስ/፡፡ ሌሎች ነብያት ክርስቶስ “ይወርዳል ይወለዳል” ብለው ትንቢት ቢናገሩም ክርስቶስን ሊያዩት ወደዱ እንጂ አላዩትም /ማቴ.13፡16-17/፤ ሐዋርያትም “ወረደ ተወለደ” ብለው አስተማሩ እንጂ “ከእኛ በኋላ ይመጣል” አላሉም /ሐዋ.4፡2/፡፡ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከእርሱ የሚበልጥ የሌለ መጥምቁ ዮሐንስ ግን እንደ ነብይ “ከእኔ በኋላ ይመጣል”፤ እንደ ሐዋርያም “ይመጣል ያልኳችሁ እርሱ ነው” እያለ ያስተምር ነበር /ዮሐ.1፡15፣30፣ ሄሬኔዎስ/፡፡ ወንጌላዊው ስለ አካላዊ ቃል ቀዳማዊነት እየመሰከረልን ቆይቶ አሁን ደግሞ ስለ መጥምቁ ዮሐንስ ምስክርነት ጨምሮ የሚነግረን ምስክርነት በሁለት ወይም በሦስት ስለሚጸና ነው /ዘዳ.19:15፣ ቅ.ቄርሎስ/፡፡
 መጥምቁ ዮሐንስ ስለ ክርስቶስ የመሰከረው ምስክርነት እውነተኛው ብርሃን የሰው ምስክርነት አስፈልጐት ሳይሆን ሰዎች ስለ ብርሃን በሚረዱትና እነርሱን በሚመስል አገልጋይ (ዕሩቅ ብእሲ) ሲነገራቸው አምነው እንዲድኑ ስለተፈለገ ብቻ ነው /ዮሐ.5፡34፣ ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ/፡፡ በእርግጥም ዮሐንስ ሲመሰክርለት የነበረው ብርሃን ዓለም (የሰው ልጅ) በመላ አጥቶት የነበረ ብርሃን ነው /ኢሳ.9፡2፣ አርጌንስ/፡፡ አዎ! ዮሐንስ ከአማናዊው ብርሃን የተነሣ የሚያበራ መብራት ነበር እንጂ እርሱ ራሱ ብርሃን አልነበረም /ዮሐ.5፡35/፤ አማናዊው ብርሃንስ በመስቀል ላይ የዓለምን ጨለማ ያስወገደው የእግዚአብሔር በግ ነው /ኤፌ.2፡13-17፣ አውግስጢኖስ/፡፡ ለዚህም ነው ሐዋርያው “ዓለምን የፈጠረ እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም ሥጋ ለብሶ መጣ፤ ተገለጠ፤ ረቂቅ ሲሆን ገዝፎ ታየ፤ ዳሰስነውም” ያለን /1ዮሐ.1፡1-2፣ ቅ.አትናቴዎስ/፡፡ በእውነቱ ለዚህ አንክሮ ይገባል! እርሱ የማይደፈር ግሩም ነው፣ በእኛ ዘንድ ግን ትሑት ነው፡፡ እርሱ የማይመረመር ልዑል ነው፣ በእኛ ዘንድ ግን አርአያ ገብር ሥጋን ተዋሐደ፡፡ እርሱ የማይያዝ የማይዳሰስ እሳት ነው፣ እኛ ግን ያዝነው ዳሰስነውም /አባ ሕርያቆስ/፡፡
 ነገር ግን እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም ቢመጣም ሆን ብለው ዓይነ ልቡናቸውን ለጨፈኑ አላበራም፤ አያበራምም /ማቴ.13፡14-15/፡፡ እነዚህ ዓይነ ስዉራን (ልበ ስሑታን) የእግዚአብሔር ነገር ሲነገራቸውም እንደ ሞኝነት ይቆጥሩታል /1ቆሮ.2፡14፣ ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ/፡፡ እኛም ብንሆን ልቡናችን በኃጢአት ጨለማ ከተጋረደ ብርሃኑን ማየት አንችልም፤ ኃጢአትን ከእኛ ስናርቅ ግን ወደ እውነተኛው ብርሃን እየቀረብን እንሄዳለን /ማቴ.5፡8፣ ቅ.ጐርጐርዮስ ዘኑሲስ/፡፡ ይህንን ብርሃን ለማየት ዓይነ ልቦናችን የተከፈተ ሲሆን በብርሃኑ እንመላለሳለን /ቅ.ቄርሎስ/፡፡ በእርግጥም በጽድቅ ጐዳና የሚሄድ ሰው መላ ዘመኑ የብርሃን ሕይወት ነው /ዓይነ ስወሩ ዲዲሞስ/፡፡
“በዓለም ነበረ፥ ዓለሙም በእርሱ ሆነ፥ ዓለሙም አላወቀውም። የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፥ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም። ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም።” ዮሐ.1፡10-13
 እንዴት ያለ ድንቅ ቸርነት ነው?! አካላዊ ቃል በዓለም የነበረ ቢሆንም ከዓለም ጋር እኩል ዕድሜ አልነበረውም /መዝ.90፡2/፡፡ አመጣጡም እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውኃ ፈሳሽ በዓለሙ የሌለ ሁኖ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ወንጌላዊው እንዲህ እንዳናስብ “ዓለሙም በእርሱ ተፈጠረ” ብሎ ይቀጥላልና፡፡ በዚሁ ቃል መሠረት ማንም ሰው ይመንም አይመንም የወልድ ቅድመ ዓለም መኖር አያስቀረውም፡፡ የቃልን እግዚአብሔርነት አያጐድለውም፡፡ በዚህ ዓለም ጥበብ የሚመላለስ ሰውስ ይህ ምሥጢር እንዴት ሊገባው ይችላል /1ቆሮ.2፡14/?! የሚገርመው ደግሞ ዓለም ያላወቀችው ወልድን ብቻ ሳይሆን አባቱንም ጭምር መሆኑን ነው /ዮሐ.17፡25፣ ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ/፡፡
 ሰው ወዳጅ የሆነው አምላካችን እኛ በፈቃዳችን የማይበላውን በልተን ብንቆሽሽም እንደ ቆሸሽን እንቀር ዘንድ አልወደደም፡፡ ስለዚህ እርሱ ራሱ በደሙ ካልወለወለን በስተቀር መልአክም ይሁን ሰው ሊያስታርቀን ስላልቻለ ፍቅሩ አስገድዶት የእኛን ባሕርይ ባሕርይ አድርጐ መጣ /ቅ.አትናቴዎስ/፡፡ ፍቅር ሰሐቦ ለወልድ ኃያል እመንበሩ ወአብጽሖ እስከ ለሞት- የሰው ፍቅር ወልድን ከዙፋኑ ስቦ ጎትቶ አወረደው፤ እስከ ሞት ድረስም አደረሰው /አባ ሕርያቆስ/፡፡ አንድ ዐይነ ስውር ሰው ፀሐይን ባያይ ፀሐይዋ ስለሌለች ሳይሆን እርሱ ሊያያት ስላልቻለ ነው፡፡ ይህንን የክርስቶስ ፍቀር ያላወቁ ሰዎችም እንዲህ ናቸው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ፡- “የእግዚአብሔር ምሳሌ የሆነ የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል ብርሃን እንዳያበራላቸው፥ የዚህ ዓለም አምላክ (ዲያብሎስ) የማያምኑትን አሳብ አሳወረ” እንዲል /2ቆሮ.4፡4፣ ቅ.ቄርሎስ/። የሰው ልጅ በሙሉ ለእግዚአብሔር በእግዚአብሔር ቢፈጠርም የዚህ ዓለም ገዢ የተባለው ዲያብሎስ ግን እስራኤል ከእግዚአብሔር የተሰጣቸውን ሕግ በማስተው፣ አሕዛብን ደግሞ በአምኮተ ጣዖት በማሳወር ፈጣሪያቸውን እንዳያውቁት አደረገ /ኢሳ.1፡2-4/፡፡ መዝሙረኛው ይህ ነገር ቢያስደንቀው “አእምሮ የሌለው ክቡር ሰው እንደሚጠፉ እንስሶች መሰለ” አለ /መዝ.49፡20፣ ቅ.ቄርሎስ/፡፡
 ተወዳጆች ሆይ! እነሆ እግዚአብሔር እንዴት እንደወደደን ታስተውሉ ዘንድ እንማልዳችኋለን /1ዮሐ.3፡1/፡፡ ወልድ እኛን ወንድሞቹ ያደረገን ብቻውን ስለሆነ አልነበረም ፡፡ ወንድሞቹ ያደረገን ፍቅሩ ብቻ ነው፤ ወንድሞቹ ያደረገን የዘላለምን ሕይወት እንድንወርስ ስለወደደ ብቻ ነው፤ እርሱ ከእኛ ይጠቀም ዘንድ አላዳነንም /ዮሐ.3፡16/፡፡ እርሱ የመጣው ለተቀበልነው ሁሉ በጸጋው የእግዚአብሔር ልጆች እንሆን ዘንድ ሥልጣን ሊሰጠን ነው /ዮሐ.1፡12/፡፡ ታድያ እርሱ ሊያነሣን ወዶ ሳለ እኛ አንነሣም የምንለው ለምንድነው? ልጅነትን አንቀበልም ብለንስ ወድቀን እንቀር ዘንድ ለምን እንመርጣለን? /አውግስጢኖስ/፡፡ እርሱ “አማልክት ዘበጸጋ ናችሁ” ብሎ የልዑል ልጆች ሊያደርገን ፈልጐ ሰው ሲሆንልን እኛ እንደ ዲያብሎስ ለምን ወድቀን እንቀራለን? /መዝ.81፡6-7፣ ቴዎዶር ዘስይርጥ/፡፡ ስለዚህ ከተዋሕዶ ብርሃን ርቃችሁና ክርስቶስን ባለማወቅ ጨለማ ውስጥ ያላችሁ ሁሉ ዛሬ የእግዚአብሔር ልጆች ሆናችሁ ሥልጣንን እንድታገኙ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም ተጠመቁ /ማቴ.28፡19፣ ቅ.ባስልዮስ/፡፡ በክርስቶስ ስታምኑና መዳናችሁን ወደምትፈጽሙበት ልምምድ ስትገቡ ከወንድና ከሴት ፈቃድ ሳይሆን ከሥላሴ ፈቃድ ዳግመኛ ትወለዳላችሁ /ዮሐ.1፡13/፡፡ እግዚአብሔር ዛሬም ይወዳችኋል፤ ይጠራችኋልም፡፡ ሰማይና ምድር የማይወስኑት አምላካችሁ በጠባብ ደረትና በአጭር ቁመት ከሴት የተወለደው እናንተ ከእርሱ ትወለዱ ዘንድ ነው፡፡ የሞተላችሁም እናንተ ሞት ይቀርላችሁ ዘንድ ነው /አውግስጢኖስ/፡፡
 የሥላሴን ልጅነት አግኝታችሁና ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን ለተጋባችሁ ለእናንተም  ወንጌላዊው ሲናገር “የእግዚአብሔርን ልጅነት ሰጣቸው” ሳይሆን “የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው” እንዳለ አስተውሉ፡፡ ምክንያቱም በጥምቀት የተከፈተልንን መዳን የምንፈጽመውና እግዚአብሔርን ወደ መምሰል ሙላት የምንደርሰው ልጅነታችንን እስከ መጨረሻ ያለነቀፋ ስንይዝ ብቻ ነው /ማቴ.10፡22/፡፡ ምክንያቱም ልጅነታችንን ከእኛ ንዝህላልነት ካልሆነ በስተቀር ማንም መልሶ ሊወስዳት አይችልምና /ማቴ.25፡1-13፣ ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ/፡፡ አዎ! ይህን ስናደርግ ከእንግዲህ ወዲህ ወዳጆች ነን እንጂ ባሮች አይደለንም፤ ልጆችም ከሆንን ደግሞ በክርስቶስ የእግዚአብሔር ወራሾች ነን /ሮሜ.8፡17፣ ገላ.4፡7፣ ቅ.ዮሐንስ ዘደማስቆ/፡፡
 ስለዚህ ሁላችንም የመዳናችን ቀንድ ወደ ሆነው ወደ ክርስቶስ እንመለስ፡፡ እርሱ በጨለማና በሞት ጥላ ሥር ተቀምጠን ለነበርን ለሁላችን ዓይን ያላየችው ጆሮም ያልሰማው በሰውም ልብ ያልታሰበው እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀውን ያወርሰን ዘንድ የመጣ እውነተኛ ብርሃን ነው /ሉቃ.1፡79፣ 2ቆሮ.2፡9/፡፡ እንግዲያስ ሰው ብቻ መሆን ይብቃን፤ የእግዚአብሔር ልጆች ለመሆንም ልጅነትን እንቀበል፡፡ ከተቀበልን በኋላም ሁል ጊዜ እንደ መላእክት ክብሩን እናይ ዘንድ ልበ ንጹሐን እንሁን /ማቴ.5፡8፣ አውግስጢኖስ/፡፡
 መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ እኛ ሥራ ሠርተን አንበቃምና ሰውን በመውደድ ሰው የሆነው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቸርነቱ ብዛት መንግሥቱን ያድለን፡፡ አሜን /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ/!!
  ሰላም ወሰናይ!

የቃል ቀዳማዊነት (የዮሐንስ ወንጌል የሁለተኛው ሳምንት ጥናት)!

(ቢቻልዎት አስቀድመው ይጸልዩ!!)
“በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ።ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ።” ዮሐ.1፡1-2
ዓሣ አጥማጁ ሐዋርያ ጌታ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደውን ደኃራዊ ልደቱ በሌሎች ወንጌላውያን የተነገረ ስለሆነ ቀዳማዊ ልደቱን ይነግረን ዘንድ ይቻኰላል /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ/፡፡ በእርግጥም “የድንግል ማርያም ልጅ” ብሎ የሚያቆም ካለ እኛ እርሱን አንሰማውም፤ “በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ” ሊለንም ይገባዋል እንጂ /ሄላሬዎስ/፡፡ አንዳንድ ሰዎች “ወልድ ልጅ ሆኖ ሳለ እንዴት ከአባቱ አያንስም?” ብለው ይጠይቁናል፡፡ እኛም የማይመረመር መሆኑንና የነብዩን ቃል ጠቅሰን እንዲህ ብለን እንመልስላቸዋለን፡- “መኑ ይነግር ልደቶ- ከአብ ያለ እናት የተወለደበት ቀዳማዊ ልደቱን ማን ይናገራል? እንዴትስ ሊመረመር ይችላል? እኛ፡ አብ ለልጁ አባት ሲባል አገኘነው እንጂ እንደምን እንደወለደው አናውቅም” /ኢሳ.53፡8፣ አውግስጢኖስ፣ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ/፡፡ ሐዋርያው “በመጀመርያው” ብሎ ሲነግረንም ከእርሱ በፊት ማንም እንዳልነበረ ለመግለጽ ነውና /ቅ.ቄርሎስ/፡፡ ምንም እንኳን “በመጀመርያ” የሚለው አገላለጽ በመጽሐፍ ቅዱስ የተለያየ ትርጕም ቢኖረውም አሁን ወንጌላዊው እየነገረን ያለው ግን ቀዳማዊ ቃል ተራሮች ሳይወለዱ፥ ምድርም ዓለምም ሳይሠሩ፥ ከዘላለም አንሥቶ እንደ ነበረ ነው /መዝ.90፡2፣ አርጌንስ/፡፡ ዮሐንስ “በመጀመርያው” የሚል ደካማ አገላለጽ ከመጠቀም ውጪ ሌላ የተሻለ ቋንቋ ማግኘት አልቻለም /ቅ.ቄርሎስ/፡፡ ሊቀ ነብያት ሙሴ “በቀዳሚ ገብረ እግዚአብሔር ሰማየ ወምድረ- በመጀመርያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ” ካለው ጋር ንባብ ቢያሳብረውም ምሥጢር አያሳብረውም፡፡ ነብዩ “በቀዳሚ ዕለት፣ በቀዳሚ ሰዓት ሰማይና ምድር ተፈጠሩ” እያለን ነው፡፡ ይህም ማለት ለእነዚህ ፍጥረታት በዕለተ እሑድ መነሻ፣ መጀመርያ አላቸው፤ ቀዳማዊ ቃል ወልደ እግዚአብሔር ግን ለዘመኑ ጥንት፣ መነሻ፣ መጀመርያ ለሕይወቱም ፍጻሜ የለውም፤ እርሱ አልፋና ኦሜጋ ነው /ዕብ.7፡3፣ ራዕ.22፡13፣ ቴዎዶር ዘሜውፕሳስትያ/፡፡ ለዚህም ነው ሐዋርያው “ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ” በማለት ለዓይን ጥቅሻ ታህል ቅጽበት እንኳን የባሕርይ አባቱ የባሕርይ ልጁን በዘመን እንደማይቀድመው የነገረን /ቅ.ቄርሎስ፣ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ/፡፡ መሴም ቢሆን “በመጀመርያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ” አለን እንጂ (ሎቱ ስብሐትና) “ወልድን ፈጠረ” አላለንም /ዘፍ.1፡1/፡፡ አካለዊ ቃል ወልድማ ሁሉንም የፈጠረ እግዚአብሔር ነው /ቆላ.1፡16/፡፡ የማያምኑበት ባያምኑበትም እኛስ ሙሴ ስለ እርሱ የጻፈለትን ቀዳማዊ ቃል ያህዌ-Johovah እንደ ሆነ እናምናለን /ዮሐ.5፡46፣ ዮሐ.8፡25፣ አውግስጢኖስ/፡፡

ይህ የተሰወረባቸው ሰዎች የማይቀላቀለውን ሲቀላቅሉ “ነበረ” እና “ተፈጠረ” አንድ ነው ሊሉን ይሞክራሉ፡፡ ነገር ግን “ነበረ” የሚለው አገላለጽ ለሰዎች ሲቀጸል ኃላፊ ጊዜን የሚያመለክት ሲሆን ለእግዚአብሔር ሲቀጸል ግን ዘላለማዊነትን የሚያለመክት መሆኑን እንነግራቸዋለን፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር ከጊዜና ከቦታ ቀመር ውጪ ነውና /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ/፡፡ ይህንንም የምናውቀው ሐዋርያው “በመጀመሪያው ቃል ነበረ” እያለን መልሶ ደግሞ “ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፤ ቃልም ራሱ እግዚአብሔር ነበረ” ስለሚለን ነው /አርጌንስ/፡፡

ወንጌላዊው እየነገረን ያለው ዓይነት “ቃል” እኛ እንደምንናገረው ዓይነቱ ዝርው (ብትን) ቃል ሳይሆን አካል ያለውን ቃል ነው /ቅ.አግናጥዮስ ምጥው ለአንበሳ/፡፡ የእኛ ቃል ወዲያው እንደተናገርነው ወደ አለመኖር ይለወጣል፤ አካላዊ ቃል ወልደ እግዚአብሔር ግን ሁሌ ያው ነው፤ አይለወጥም /ሚል.3፡6፣ ቅ.አትናቴዎስ/፡፡ የእኛ ዝርው ቃል ከልብ ተገኝቶ ህልው ሆኖ ሲኖር አማርኛም ይሁን ትግርኛ አይታወቅም፡፡ ነገር ግን ልገለጽ ባለ ጊዜ በአንደበት እንደሚገለጽ ሁሉ አካላዊ ቃል ወልድም ከአብ ተገኝቶ በአብ ህልው ሆኖ ሲኖር ልገለጽ ባለ ጊዜ በሥጋ ተገልጧል /ዮሐ.14፡9፣ ገላ.4፡4፣ ቅ.ኤፍሬም/፡፡ እግዚአብሔር ወልድ ከዘላለም አንሥቶ ከባሕርይ አባቱ ጋር አለ /ቅ.ጐርጐርዮስ ዘእንዚናዙ/፤ ነገር ግን አሁን እየተመለከትን ያለነው በሥልጣን ሳይሆን በአካል ከአባቱ የተለየ መሆኑን ነው /ቅ.ቄርሎስ/፡፡

እንዴት ይደንቃል?! ሙሴ በጊዜ ውስጥ ተወስኖ ይጽፋል፤ ይህ ዓሣ አጥማጅ ሐዋርያ ግን ከምናየው ሰማይና ምድር ያልፍና በደቂቃና በሴኮንድ ወደማይቆጠረው ዘላለማዊነት ያስገባናል፤ ሙሴ ከነገረን መጀመርያ አስወጥቶም መጀመርያ ወደሌለው መጀመርያ ይወስደናል /ሄላሬዎስ/፡፡ ወደዚያ ስንሄድም አካላዊ ቃል አምላክ ወልደ አምላክ፣ ከብርሃን የተገኘ ብርሃን፣ ከጥበብ የተገኘ ጥበብ፣ ከእውነት የተገኘ እውነት፣ ከማይቸገር የተገኘ የማይቸገር፣ ከማይጠፋ የተገኘ የማይጠፋ፣ ከማይፈርስ የተወለደ የማያረጅ፣ ከማያንቀላፋ የተገኘ የማይተኛ፣ ከማይጨልም የተገኘ የማይጠቁር፣ ከማይመረመር የተወለደ የማይለይ፣ ድካም ከሌለበት የተወለደ የማይደክም፣ ከማይበቀል የተወለደ የማይቀየም፣ ከማይጐድል የተወለደ የማይጐድል፣ ከማያድፍ የተገኘ የማይረክስ መሆኑን እንረዳለን /አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ/፡፡ ይህ ምን ማለት እንደ ሆነ ግን በእኛ ደካማ ቃላት መግለጽ አይቻለንም /አውግስጢኖስ/፡፡ የምናውቀው ሁሉ በከፊል ነውና /1ቆሮ.13፡12/፡፡ በእምነት መሠላል ብቻ ወደዚህ እንደርሳለን /ቅ.ጐርጐርዮስ ዘኑሲስ/፡፡
“ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም። በእርሱ ሕይወት ነበረች፥ ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረች። ብርሃንም በጨለማ ይበራል፥ ጨለማም አላሸነፈውም።” ዮሐ.1፡3-5

አዎ! የወንጌላዊው ዓላማ ሥነ-ፍጥረትን ሳይሆን የየሥነ-ፍጥረት ሁሉ ምንጭ ማን እንደሆነ ማስተዋወቅ ነው፡፡ እነዚህ ፍጥረታት ከመፈጠራቸው በፊት አልነበሩም፤ እርሱ ግን ከዘላለም አንሥቶ በእግዚአብሔር ዘንድ አለ /ዘጸ.3፡14፣ ቴዎዶር ዘሜውፕሳስትያ/፡፡ ሁሉንም የፈጠረ ፈጣሪ “ፍጡር ነው” ይሉት ዘንድ አንዳንዶች እንዴት ደፈሩ?! /አውግስጢኖስ/፡፡ ወልድ ፍጡር ከሆነስ ከእርሱ በፊት የነበረችውን ጊዜ ማን ሊፈጥራት ነው? ወንጌላዊው ግን “ከተፈጠረውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ የተፈጠረ የለም” ነው ያለን፡፡ በአመክንዮም (By Logic) ሸክላ ከሸክላ ሠሪው አይቀድምም /ዕብ.1፡8፣ ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ/፡፡

አንድ ነገር ግን ታስተውሉ ዘንድ እንማልዳችኋለን፡፡ ወንጌላዊው፡-“ሁሉ በእርሱ ተፈጠረ፥ ከተፈጠረውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልተፈጠረም” ስላለ ጣዖት፣ ኃጢአትና ክፋት ሁሉ በእግዚአብሔር ተፈጠሩ ማለት አይደለም /አርጌንስ/፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ሁሉ የኃጢአት ውጤቶች ናቸውና /ቅ.አትናቴዎስ/፡፡ ስለዚህ ፈጣሬ ዓለማት አካላዊ ቃልን ማመን ሕይወትን ይሰጣል /አርጌንስ/፡፡ አዎ! እርሱ ከሕይወት የተገኘ የሕይወት ሁሉ ምንጭ ነው /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ/፤ ከእውነት የተገኘ እውነት እንጂ እውነትን ቆይቶ የተማረ ፍጡር አይደለም /ሄላሬዎስ/፡፡ እርሱ፡ ሲሞት እንኳን ሕይወትን የሚሰጥ ዕፀ ሕይወት ነው /አውግስጢኖስ/፡፡ ዕፀ ሕይወቱም እንበላው ዘንድ አደለን፤ ይኸውም እኛን ስለ መውደድ መጥቶ ያዳነን ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ነው /ቅ.ኤፍሬም/፤ በበላነው ጊዜም ክፋንና ደጉን የምናውቅበት ዕውቀትን አገኘን /አርጌንስ/፡፡
እርሱ ብርሃን ብቻ ሳይሆን ብርሃን ሰጪም ነውና /ቅ.ቄርሎስ/ በአካላዊ ቃል ሞትና ትንሣኤ ብርሃን ወጣልን /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ/፡፡ ዐይነ ስውር የሆነ ሰው (የማያምን) ፀሐይ ብትኖርም እርሱ ስለማያያት እስከ አሁን ድረስ በጨለማ ውስጥ አለ /አውግስጢኖስ/፡፡ እኛም ቅዱስ ጳውሎስ እንደነገረን ቀድሞ ጨለማ ነበርን፥ አሁን ግን በጌታ ብርሃን ነን /ኤፌ.5፡8፣ አርጌንስ/፡፡ ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲህ “ወልድ ፍጡር ነው” ከሚሉት ጋር በጨለማ ውስጥ አንኖርንም፡፡ አካላዊ ቃልን ስናምን ጨለማ ከእኛ ተገፎ ይጠፋል፤ ሞት ከእኛ ይርቃል፣ ክህደት ከእኛ ይወገዳል፤ በአማናዊው ብርሃን ተሸንፏልና ሞት በእኛ ላይ ድል የሚያደርግበትን ሥልጣን ያጣል /1ቆሮ.15፡55-57፣ ቅ.ማር ይስሐቅ፣ ቅ.ጐርጐርዮስ ዘእንዚናዙ፣ ቅ.ቄርሎስ/፡፡

እንግዲያስ ተወዳጆች ሆይ! ይህ አካላዊ ቃል፣ ከዘላለም አንሥቶ ከአባቱ ጋር የነበረው ወልድ፣ ከጊዜና ከቦታ ከመታየትም ውጪ የሆነው አምላክ፣ አሁን ስለ እኛ ብሎ የእኛን ሥጋ ለብሶ ስለ ታየ፤ ልዑል ሲሆን ዝቅ ስለ አለ፤ ያድነንም ዘንድ በጊዜና ቦታ ተወስኖ ስለ መጣ፤ ከፀሐይና ከጨረቃ አቆጣጠር ውጪ ሆነን ከእርሱ ጋር ለዘላለም እንኖር ዘንድ ዘመን ስለ ተቆጠረለት በእርሱ ዘንድ ጽርፈትን (ስድብን) ከመናገር እንቆጠብ /ቅ.ቄርሎስ/፡፡

የዮሐንስ ወንጌል (የመጀመርያ ሳምንት ጥናት)!!

በአዳራሽ ገብቶ ወደ እልፍኝ ማለፍ፣ እርካብ ተረግጦ ወደ ኮርቻ መውጣት እንደሚመች ሁሉ እኛም ለዛሬ መቅድሙን ተምረን ከቀጣይ ሳምንት በኋላ ወደ ወንጌሉ እንሄዳለን፡፡ የጸሐፊው ዜና መዋእል በአጭሩ፡-
የዮሐንስ ወንጌል ጸሐፊ ዮሐንስ ወልደ ነጐድጓድ ነው /ቅዱስ ኤጲፋንዮስ/፡፡ ዮሐንስ ማለት “ጸጋ እግዚአብሔር” ማለት ነው፡፡ አባቱ ዘብዴዎስ የሚባል የሲዶና ሀገር ገሊላዊ ሲሆን ዓሣ አጥማጅ ሳለ ከወንድሙ ከያዕቆብ ጋር ሰዎችን እንደ ዓሣ በወንጌል መረብ ከዚሁ ዓለም ባሕር ለማጥመድ ተጠራ /ማቴ.4፡21/፡፡ እናቱም ማርያም ባውፍልያ ትባላለች /ማቴ.28፡1/፡፡ ወንድሙ ያዕቆብ በ44 ዓ.ም በሄሮድስ ዘአግሪጳ ተገደለ /ሐዋ.12፡1-2/፡፡ ብዙ ቅጽል ስሞችም አሉት፡- የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት በመግለጡና ለጌታችን ባለው ቅንዓት ባሳየውም የኃይል ሥራ “ወልደ ነጐድጓድ” /ማር.3፡17/፣ የእግዚአብሔርን አንድነትና ሦስትነት ስለሚናገር “ታዖሎጐስ- ነባቤ መለኰት”፣ ኃላፍያትንና መጻእያትን ስለሚናገር “አቡቀለምሲስ-ረአየ ኅቡአት- ባለ ራዕይ”፣ እንዲሁም የጌታን ጸዋትወ መከራ አይቶ ፊቱ በኃዘን ተቋጥሮ ይኖር ስለ ነበር “ቁጹረ ገጽ- ፊቱ በኃዘን የተቋጠረ” ይባላል፡፡ ጌታ ግርማ-መንግሥቱን ሲገልጥ /ማቴ.17፡1/፣ የኢያኢሮስን ልጅ ሲያነሣ /ማር.5፡37/፣ በጌቴሴማኒ የአታክልት ቦታ ሲጸልይ /ማቴ.26፡37/፣ ስለ ኢየሩሳሌም መጥፋት ትንቢት ሲናገር /ማር.13፡3/ ዮሐንስ አብሮ ስለ ነበር “የምሥጢር ልጅ”ም ይባላል፡፡ ጌታ ሲጠራው የ25 ዓመት ወጣት ነበር /ቅዱስ ሄሬኔዎስ/፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ “Pillars of the Church- አዕማደ ቤተ ክርስቲያን” ብሎ ከሚጠራቸው ሐዋርያት አንዱ ዮሐንስ ነው /ገላ.2፡9/፡፡ ከሌሎቹ ደቀ መዛሙርት በተለየ አኳኋንም ጌታን ይወደው ስለ ነበር ሁሌ ከእቅፍ አይለይም ነበር፡፡ በዚህም የጌታ ወዳጅ-ፍቁረ እግዚእ ተብሏል /ዮሐ.13፡23/፡፡ ጌታን እስከ መስቀል ድረስ የተከተለ እቸኛ ሐዋርያ ነው፡፡ ጌታም ዮሐንስ ካሳየው ፍቅር ከ100 ዕጥፍ በላይ እናቱን እናት አድረጐ ሰጠው /ቅዱስ አውግስጢኖስ/፡፡ ምንኛ የታደለ ሐዋርያ ነው? /ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ/፡፡ ለእርሱ ብቻ ሳይሆን በዮሐንስ ሃይማኖት እስከ መስቀል ድረስ ለምንሄድ ምእመናንንም ሁሉ ጌታ እመቤታችንን እናት አድርጐ ሰጥቶናል /ዮሐ.19፡20-27/፡፡ ዮሐንስ ከጌታ ትንሣኤ በኋላ ወንጌልን በታናሽ ኤስያ (ልዩ ስሙ ኤፌሶን) ያስተምር ነበር፡፡ ትምህርቶቹም ፍቅርን አብዝተው ይሰብካሉ /ቅዱስ ጀሮም/፡፡ ደቀ መዛሙርቱ በአንድ ቀን፡- “አባታችን ሁል ጊዜ አንድ ዓይነት ትምህርት (ስለ ፍቅር) የምታስተምረን ለምንድነው?” ሲሉት “እርሷ የጌታ ትእዛዝ ናት፤ እርሷን ከጠበቃችሁ ይበቃችኋል” ይላቸው ነበር /ዮሐ.15፡12/፡፡ በሽምግልናው ጊዜ እንኳን እንደ ወጣት ለስብከተ ወንጌል አብዝቶ ይፋጠን ነበር /አውሳብየስ ዘቂሳርያ፣ ቀለሜንጦስ ዘአሌክሳንድርያ/፡፡ በጊዜው በነበረው ጨካኙ የሮም ቄሣር በድምጥያኖስ ወደ ፍጥሞ ደሴት ተሰደደ፡፡ በዚያም የራዕይን መጽሐፍ ጻፈ፡፡ እንደ ቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ዮሐንስ ተሰውሯል እንጂ አልሞተም፤ ነገር ግን ጌታ ሲመጣ ይሞታል /ዮሐ.21፡22-23/፡፡ወንጌሉ የተጻፈበት ቋንቋ፣ ቦታና ጊዜ፡-
ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌሉን ከፍጥሞ ደሴት ከግዞት ሲመለስ በኤፌሶን በ96 ዓ.ም አከባቢ በዮኖናውያን ቋንቋ ጽፎታል /ቅዱስ ሄሬኔዎስ ዘልዮን/፡፡ምክንያተ ጽሒፍ- መጽሐፉ የተጻፈበት ዋና ዓላማ በአጭሩ፡-
v ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጅ እንደ ሆነ እናምን ዘንድ፥ አምነንም በስሙ ሕይወት ይሆንልን ዘንድ መጽሐፉ ተጽፎአል /ዮሐ.20፡31/፡፡
v በጊዜው ለነበሩ ኢስጦኢኮች ተብለው ለሚጠሩ የግሪክ ፈላስፎች መልስ ለመስጠት ተጽፏል፡፡ በሌላ አገላለጽ ለዕቅበተ-እምነት (Apology)፡፡ ፈላስፎቹ:- “ነፍስን፣ መላእክትን እና ሌሎች ረቂቃን ፍጥረታትን የፈጠረ Logos-ቃል የሚባል ደግ አምላክ አለ፡፡ ደግሞም ግዙፉን ዓለም እና የሰውን ሥጋ የፈጠረ ሌላ ክፉ አምላክ አለ፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ በደጉ አምላክ የተፈጠረችውንና በሰው ውስጥ ያለችውንና ነፍስ ነጻ ለማውጣት የተላከ “ፍንጣሪ-Ion” ነው፡፡ ሥጋ የክፉ አምላክ ፍጥረት ስለሆነም እርሱ ሥጋ አልለበሰም” ብለው ስለሚያስተምሩ ዮሐንስ “ወልደ እግዚአብሔር በመጀመሪያው Logos- ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር አብ ዘንድ ነበረ፥ ቃልም ራሱ እግዚአብሔር ነበረ። ይህ በመጀመሪያው ከዘላለም ጀምሮ በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ። እናንተ የደጉ አምላክ ፍጥረትና የክፉ አምላክ ፍጥረት የምትሉት (የሚታየውም የማይታየውም) ሁሉ በእርሱ ተፈጠረ፥ ከተፈጠረውም አንድስ እንኳ ያለ እርሱ ቃልነት የተፈጠረ የለም” እያለ ይቀጥልና “ያ ቀዳማዊ Logos-ቃልም በመምሰል ሳይሆን በኩነት ሥጋን ተዋሕዶ በእኛ አደረ፤ አማኑኤል ሆነ” እያለ አስፍቶና አምልቶ በጥልቀት የሎጐስን እውነተኛ ትርጓሜ ጽፎላቸዋል፡፡
v በሌሎች ወንጌላውያን ያልተዳሰሰው ጥልቅ ነገረ-መለኰትን (Theology) ለማስተማር በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ጽፎታል /አውሳብዮስ ዘቂሳርያ፣ ቅዱስ ጀሮም/፡፡
v ሰማየ ሰማያትን ሰንጥቀን ወጥተን፤ ሱራፍኤል፣ አለቆችንና ሥልጣናትን አልፈን ወደ ዘባነ-ኪሩብ እንድንወጣና ባለ ግርማውን ንጉሥ እንገናኝ ዘንድ ይህን ጻፈልን (ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ)፡፡
v ሐዋርያው “እኛስ ሀገራችን በሰማይ ነው” እንዳለ /ፊል.3፡20/ ወደዚያ ወደ እውነተኛው ቤታችን ይመራን ዘንድ ይህን ጽፎልናል (ቅዱስ አምብሮስ)፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

FeedBurner FeedCount