Wednesday, July 20, 2016

አንተ ሰው እስኪ ንገረኝ!


በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሐምሌ 13 ቀን 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
አንድን የሥጋ ቁስል ለመፈወስ ለእያንዳንዱ ሰው ከባድ ነው፤ የነፍስን ቁስል መፈወስ ግን ለኹሉም ቀላል ነው፡፡ የሥጋ ቁስል ለመፈወስ መድኃኒት ብሎም ገንዘብ ያስፈልጋል፤ ነፍስን ለመፈወስ ግን ቀላል ብሎም ወጪን የማይጠይቅ ነው፡፡ ሥጋን ከዚያ ከሚያሰቃይ ቁስሉ ለመፈወስ አድካሚ ነው፡፡ ምክንያቱም በቀዶ ጥገና ምላጭ መቀደድ አለበት፤ መራራ መድኃኒቶችም ሊጨመሩበት ይገባል፡፡ ነፍስን ለመፈወስ ግን እንዲህ ዓይነት ነገር አያስፈልግም፡፡ ፈቃደኛ መኾን ብቻ በቂ ነው፤ ፍላጎቱ ካለ ኹሉንም ነገር ለማድረግ ቀላል ነው፡፡ የእግዚአብሔር መግቦቱም እስከ አሁን ድረስ ይህ ነው፡፡
ሥጋ ቢቆስል ያን ያህል ከባድ ጉዳትን አያመጣብንም፤ ምክንያቱም ምንም ባንታመምም እንኳን ሞት መጥቶ ይህን ሥጋችን ያፈርሷል፤ ያበሰብሷልምና፡፡ ነፍሳችን ብትታመም ግን ጉዳቱ ብዙ ነው፡፡ እግዚአብሔር የነፍስን ሕመም ለመፈወስ መድኃኒቱ ቀላል፣ ምንም ወጪና ስቃይ የሌለበት ያደረገውም ስለዚሁ ነው፡፡ ታዲያ ምንም እንኳን በሕመሙ ምክንያት የሚያገኘን ጉዳት ያን ያህል ብዙ ባይኾንም የገንዘብ ወጪን የሚጠይቀው፣ ሐኪም የሚያስፈልገው፣ ብዙ ስቃይ ያለበት ሥጋችን ሲታመም እርሱን ለማከም እጅግ የምንደክም ኾነን ሳለ፥ እጅግ ብዙ ጉዳት የሚያመጣውን፣ እርሱን ለመፈወስ ወጪ የማይጠይቀውን፣ ለማስታመም ሌሎች ሰዎች የማያስቸግረውን፣ እንደ ምላጩና እንደ መራራ መድኃኒቱ ስቃይ የሌለበትን ይልቁንም ከእነዚህ አንዱስ እንኳን ሳይፈልግ በእኛ ኃይል ባሉ ምርጫና ፈቃድ ብቻ መዳን የሚችለውን፣ ይህን ማድረግ ሳንችል ስንቀርም ከባድ ፍርድና ቅጣት ስቃይም እንደሚያገኘን በእርግጥ እያወቅን የነፍሳችንን ቁስል ችላ የምንል ከኾነ ሊደረግልን የሚችል ምሕረት እንደ ምን ያለ ምሕረት ነው? እኮ የምናገኘው ይቅርታ እንደ ምን ያለ ይቅርታ ነው?
© አሁን እየተተረጎመ ካለው የሊቁ አንድ መጽሐፍ የተወሰደ

No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount