(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ መስከረም 21 ቀን፣
2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
የይሖዋ ምስክሮች የተባለው ተቋም እ.ኤ.አ. በ1870 ላይ የተመሠረተ ሲኾን፥
መሥራቹም ፔንሳልቫንያ በምትባለው የአሜሪካ ግዛት እ.ኤ.አ. በ1854 ላይ የተወለደው ቻርለስ ራስል የተባለ ግለሰብ
ነው፡፡ ይኽ ሰው ከጓደኞቹ ጋር በየጊዜው እየተገናኘ መጽሐፍ ቅዱስ ያጠና ነበር፡፡ የኋላ ኋላ ግን በተለያዩ የክሕደት ትምህርቶች
ውስጥ ወደቀ፡፡ ከክሕደቶቹ መካከልም “ነፍስ ትሞታለች፤ ሥላሴ የሚባል ትምህርት የለም፤ ወልድ ፍጡር በመለኮቱ፤ ክርስቶስ በሥጋ
አልተነሣም፥ በፍጹም ሥጋም ወደ ሰማይ አላረገም፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ሊቀ መላዕክት ቅዱስ ሚካኤል ነው፤ ዘለዓለማዊቷ ገነት ይኽቺ
የምንኖርባት ምድር ነች፤ ኃጢአተኞች ፈጽመው ከመኖር ወዳለመኖር ይጠፋሉ እንጂ የዘለዓለም ስቃይ የሚባል አያገኛቸውም፥ ሰይጣንም
ቢኾን ወደአለመኖር ይጠፋል እንጂ አይሰቃይም፤ መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ኃይል እንጂ አካላዊ አይደለም” የሚሉ ይገኙበታል፡፡
ለዚኹ ትምህርቱ ይረዳው ዘንድም መጽሐፍ ቅዱስን በማጣመም “የአዲሲቱ ዓለም መጽሐፍ ቅዱስ” በማለት የራሱ የኾነ መጽሐፍ አዘጋጅቷል፡፡
በአኹኑ ሰዓትም ይኽን የክሕደት ትምህርታቸውን በተለያዩ ቋንቋዎች በማዘጋጀት ብዙ ሰዎችን እያታለሉ ይገኛሉ፡፡ እኛም፥ እግዚአብሔር
በፈቀደልን መጠን፥ እነዚኽ ተረፈ አርዮሳውያን በትምህርተ ሥላሴ ዠምረን ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች አንድ በአንድ መልስ እንሰጥበታለን፡፡
ለዚኽም እግዚአብሔር ዓይነ ልቡናችንን ያብራልን፤ አሜን!!!