(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሚያዝያ ፲፱ ቀን፣ ፳፻፮ ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
የዚኽ ትምህርት መሠረታዊ ዓላማ ክርስቲያኖች ከትንሣኤ እስከ ጰራቅሊጦስ ባለው ወራት ውስጥ መንፈሳዊ ሕይወታቸው እንዳይቀዘቅዝ ማበረታታት ነው፡፡
በቤተ
ክርስቲያናችን ሥርዓት መሠረት ከትንሣኤ እስከ ጰራቅሊጦስ እሑድ ባለው ወራት ረቡዕንና ዓርብን ጨምሮ አይጦምም፤
አይሰገድምም፡፡ ይኽም ሠለስቱ ምዕት በ፫፻፳፭ ዓ.ም. በጉባኤ ኒቅያ ሲሰበሰቡ በኻያኛው ቀኖኗቸው የወሰኑት ቀኖና
ነው /ሃይ.አበ.፳፡፳፮፣ The Oxford Dictionary of the Christian Church, pp 1250,
1738/፡፡ ይኽን ቀኖና ሲወስኑም ያለ ምክንያት አይደለም፤ ይኽ ወራት ከትንሣኤ ዘጉባኤ በኋላ ያለውን ሕይወታችን
የሚያሳይ ስለኾነ ነው እንጂ፡፡ ከትንሣኤ ዘጉባኤ በኋላ ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ ለማስገዛት ተብሎ የሚደረግ ጦምም
ኾነ ስግደት የለም፡፡ ሥጋ ሙሉ በሙሉ በዲያብሎስ ከመፈተን፣ ከእግዚአብሔር ውጪ የኾነ ሌላ ሐሳብን ከማሰብ ነጻ
የሚወጣበት ወራት ነው፡፡ በዚያ ሰዓት ፈቃደ ሥጋ ከፈቃደ ነፍስ ጋር የተስማማ ነው፡፡ ሥጋ ሙሉ ለሙሉ ከድካሙ ነጻ
ስለሚኾን እግዚአብሔርን ለማመስገን ትጉኅ ነው፡፡ እንደ አኹኑ እንቅልፍ እንቅልፍ አይለውም፤ ዘወትር የቅዱሳን
መላእክትን ምግብ ለመብላት ማለትም ለማመስገን የተዘጋጀ ነው እንጂ፡፡