በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
የታሪክ መዛግብት እንደሚናገሩት አንድ ንጉሥ ወደ አንድ አከባቢ ከመሄዱ በፊት መንገዱን ያዘጋጁ ዘንድ አስቀድሞ መልእክተኞችን ይልካል፡፡ የፍጥረታት ሁሉ ጌታ እና ንጉሥ የሆነው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስም እኛን ለማዳን ወደዚህ ዓለም ከመምጣቱ በፊት መንገዱን ይጠርጉ ዘንድ ብዙ ነቢያትን ልኳል፡፡ መጥምቁ ዮሐንስም በበረሐ ተገድዶ ሳይሆን የጌታ ፍቅር አስገድዶት ላንቃው እስኪሰነጠቅ ድረስ እየጮኸ መልእክተኛ ሆኖ የመጣ ታላቅ ነቢይም ሐዋርያም ነው፡፡ ለዚህም ነው ወንጌላዊው፡- “እነሆ፥ መንገድህን የሚጠርግ መልክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ የጌታን መንገድ አዘጋጁ ጥርጊያውንም አቅኑ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ ተብሎ በነቢዩ በኢሳይያስ እንደ ተጻፈ” ያለው /ማር.1፡2-3/፡፡
ወንጌላዊው ስለዚሁ የጌታ መልእክተኛ የተነገሩትን ሁለቱም ትንቢቶች እያነሣ ይናገራል /ሚል.3፡1፣ ኢሳ.40፡3/፡፡ ሚልክያስ “የጌታ መልእክተኛ” ብሎ የጠራው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለድኅነተ ዓለም ከመምጣቱ በፊት ሕዝቡን በንስሐ መንገድ እየጠረገ ስለ ነበረ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ጌታን ለመጀመርያ ጊዜ ያየው በሥጋ ማርያም ሳይሆን በዐይነ እምነት ነበረ፡፡ ምንም እንኳን በእናቱ ማሕፀን ውስጥ የነበረ ቢሆንም ጌታውን በዐይነ እምነት ሲመለከተው ግን በደስታ ዘሏል /ሉቃ.1፡44/፡፡
ጠርጡለስ የተባለ የሁለተኛው ክፍለ ዘመን ምሁር “መዝሙረኛው ዳዊት፡- ለቀባሁትም ሰው መብራትን አዘጋጃለሁ እንዳለ መጥምቁ ዮሐንስ መልእክተኛ ብቻ ሳይሆን መብራትም ነበረ” ብሏል፡፡ በእርግጥም መስማትን ለሰሙት ወገኖች የሚያበራ ፋና ነበረ፡፡
“ወንጌላዊው” ኢሳይያስም ዮሐንስን “በምድረ በዳ የሚጮህ ድምጽ” ብሎታል፡፡ እርሱ አዳኙን ክርስቶስ ለመግለጥ እንደ ተላከ የምሕረት መልአክ፣ እንደ አንበሳ በበረሐ እየጮኸ በኃጢአት የጠነከረውን ልባችንን ይሰብር ዘንድ የመጣ መልእክተኛ ነውና፡፡ ሰውነታችንን መልእክተኛ ለሆነለት ለእግዚአብሔር በግ ለክርስቶስ ማኅደር እንድንሆን ያዘጋጅ ዘንድ የመጣ ነብይ ነውና፡፡
“ዓምደ ተዋሕዶ” የተባለው ታለቁ ሊቅ ቅዱስ ቄርሎስም “መጥምቁ ዮሐንስ ከንጋቱ ኰከብ በፊት የነበረ ፀሐይ” ይሏል፡፡ ምክንያቱም ዮሐንስ ፀሐየ ጽድቅ ኢየሱስ ክርስቶስ እስኪመጣ ድረስ የሚያበራ ፋና ነበረና፡፡ በጨለማ ውስጥ ይመላለሱ ለነበሩት ሁሉ ወደ እውነተኛው ብርሃን ይደርሱ ዘንድ ያዘጋጅ ነበረና፡፡
ዮሐንስ ያዘጋጀው የነበረው ጥርግያ የጌታን ወንጌል ነበረ፡፡ የትምህርቱ መሠረታዊ ዓላማም እያንዳንዱ ሰው የንስሐ ፍሬ እንዲያፈራ ማድረግ ነበር፡፡ የንስሐ ፍሬ ሲባልም የሠሩትን ኃጢአት መተው ብቻ ሳይሆን ፍሬም ጭምር ማፍራት ነው፡፡ ለምሳሌ፡-በሰረቁበት እጅ አለመስረቅ ብቻ ሳይሆን በዚያ ወዶ መስጠት፣ በዘፈኑበት ከንፈር ዘፈንን መተው ብቻ ሳይሆን በዚያ መዘመር፣ አመንዝረን እንደ ሆነም ይኸን መተው ብቻ ሳይሆን ከሕጋዊ ሚስታችንም ቢሆን ለተወሰነ ጊዜአት መቆጠብን የመሳሰለ ሁሉ ነው፡፡
መጥምቁ ዮሐንስ በቃሉ ብቻ ሳይሆን በልብሱም ጭምር ይሰብክ ነበር፡፡ ምግባራችን እንደ ሞተ እንስሳ ቁርበት ጠፍር፣ ኃጢአታችንም እንደ ግመል ጠጉር ለበዛብን ለእኛ ክብር ይግባውና የእግዚአብሔር በግ እርሱ ክርስቶስ ይቆስልልን ዘንድ እንደ መጣ ይመሰክር ነበር፡፡
እኛ ሁላችን ወደ ገዛ መንገዳችን ስናዘነብል፤ በከንቱም የማይበላውን በልተን ስንሞት እርሱ በ30 ብር ተሸጦ እኛን ግን በማይተመን ዋጋ ገዝቶ ከዓለቱ ማር
በልተን እንደሚያጠግበን ያውጅ ነበረ /መዝ.81፡16/፡፡
የመጥምቁ ረድኤትና በረከት አይለየን! የንስሐ ፍሬም እንድናፈራ ሰውን በመውደድ ሰው የሆነው ክርስቶስ ይርዳን አሜን!