(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሐምሌ ፭ ቀን፣
፳፻፮ ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
በዛሬው ዕለት የምናከብረው በዓል ኹለቱም ታላላቅ ሐዋርያት በሰማዕትነት ያረፉበትን
በዓል ነው፡፡ ይኽ ዕለት በየዓመቱ አይለዋወጥም፡፡ የሐዋርያትን ጦም ከጨረስን በኋላ የምናከብረው ነው፡፡ በዚኽ ዕለት ቅድስት ቤተ
ክርስቲያናችን በቅዳሴዋም በትምህርቷም ኹሉ እነዚኽን ታላላቅ ሐዋርያት ታነሣለች፤ ታወድሳለች፤ ሰማዕትነታቸውንም ለልጆቿ ታስተምራለች፡፡
ምንም እንኳን በእነዚኽ ሐዋርያት ስም የተሰየመ ቤተ ክርስቲያን በብዛት ባይገኝም በአዲስ አበባ ግን “ብርሃናተ ዓለም ቅዱስ ጴጥሮስ
ወጳውሎስ” የሚባል ቤተ ክርስቲያን አለ፡፡
ወደ ሰሜኑ የአገራችን ክፍል ስንሔድ ይኽ ዕለት “ሓወርያ” ተብሎ ይጠራል፡፡
ስያሜውም የእነዚኽን ሐዋርያት ሰማዕትነት ለመግለጥና ለማሰብ የተሠጠ ነው፡፡ እረኞች ጅራፋቸውን ገምደው በቡድን በቡድን እየኾኑ
ያስጨኹታል፡፡ የጅራፉ ጩኸት የእነዚኽ ሰማዕታት መገረፍ፣ መቁሰል፣ መሰየፍ፣ መሰቃየት፣ መሰቀል የሚያስታውስ ነው፡፡ አባቶቻችን
ክርስትናውን ማንበብና መጻፍ ወደማይችለው ማኅበረ ሰብእ ምን ያኽል እንዳሰረጹትም ከዚኽ እንገነዘባለን፡፡ እኛ ግን እንኳንስ ለተማረው
ማስተማር ይቅርና አባቶቻችን የሠሩትን እንኳን መጠበቅ አቅቶናል፡፡