(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፥ መስከረም ፲፮ ቀን፥ ፳፻፮ ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ
አሓዱ አምላክ አሜን!!!
በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ. ሥርዓት መሠረት ከመስከረም ፲፮ እስከ መስከረም ፳፭
ያለው ሳምንት “ዘመነ መስቀል” ይባላል፡፡ በዚህ ሳምንት ስለ መስቀል ክብር ይነገራል፤ መዝሙረ መስቀልም ይዘመራል፡፡ መስቀል ማለት
“ሰቀለ” ከሚል የግእዝ ግሥ የተገኘ ሲኾን ትርጓሜውም “የተመሳቀለ፣ መስቀለኛ” ማለት ነው፡፡
መቅድመ
ወንጌል እንደሚነግረን፥ አዳም የማይበላውን በልቶ ከእግዚአብሔር አንድነት ከተለየ በኋላ አብዝቶ ያለቅስ ነበር፡፡ በኀጢአቱ ከማዘንና
ከማልቀስ በቀርም ሌላ ግዳጅ አልነበረውም፡፡ በልብ መታሰቡ በቃል መነገሩ ከፍ ከፍ ይበልና ብዙ መጨነቁን፥ ጸዋትወ መከራዉን ያየው
ቸሩ እግዚአብሔር ግን አዘነለት፡፡ “እቤዝወከ በመስቀልየ ወበሞትየ - በመስቀሌና በሞቴ አድንኀለኹ” ብሎም ቃል ኪዳን ገባለት
/ኪዳነ አዳም ፫፡፫-፮፣ ዘፍ.፫፡፲፭/፡፡ መጽሐፈ ቀሌሜንጦስ እንደሚነግረንም ከ፭ ቀን ተኵል በኋላ እንደሚያድነው ተስፋ ሰጠው፤
ከ፭ ሺሕ ፭ መቶ ዓመታት በኋላ ሲል ነው፡፡ “ነገረ መስቀል” የምንለውም ይኸው ለአዳም የተሰጠው ተስፋ ነው፡፡