የትሕትናን ነገር ከወዴት እንፈልጋት? ከወዴት እናግኛት? ከማንስ እንማራት? ወደ ግብረ ገቦች ከተማ፣ ወደ ቅዱሳኑ በዓት፣
ወደ ተራራዎቹ፣ ወደ ዱር ዋሻው፣ ወደ ጋራውና ሸንተረሩ እንሂድን?
አዎ ወደዚያ እንሂድና የትሕትናን ብዛት፣ የትሕትናን ዋጋ፣ የትሕትናን ክብር ከመነኰሳቱና ከመነኮስያቱ ዘንድ እንመልከታት፤ መመልከት
ብቻም ሳይሆን እኛም ገንዘብ እናድርጋት፡፡
ወደዚያ ስንሄድ ቅዱሳኑ ግማሾቹ የሞቀ ወንበራቸውን (ሥልጣናቸውን)፣ ግማሾቹ የሞቀ ሀብት ንብረታቸውን ትተውና ንቀው
ሁለንተናቸውን ዝቅ አድርገው በአለባበሳቸው፣ በአኗኗራቸው፣ በአገልግሎታቸውም ትሕትናን ሲለማመዷት ሲኖሯት እናገኛቸዋለን፡፡
የትዕቢት ሐሳብ፣ ያማረ ልብስን የመልበስ ሐሳብ፣ የተዋበ ቪላን የመሥራት ሐሳብ፣
ብዙ ሠራተኞችን የማስተዳድር ልቡና እንዲሁም ሌሎች ወደ ትዕቢት የሚወስዱ ነገሮች በእነዚህ ቅዱሳን ዘንድ ቦታ የላቸውም፡፡ እነርሱ
ራሳቸው እሳቱን ያቀጣጥላሉ፣ እነርሱ ራሳቸው ምግባቸውን ያበስላሉ፣ እነርሱ ራሳቸውም የመጣውን እንግዳ ያስተናግዳሉ፡፡
በእነዚህ ቅዱሳን ዘንድ የሚሳደብ የለም የሚሰደብም የለም፤ ትእዛዝ የሚቀበል
የለም ትእዛዝ የሚሰጥም የለም፤ ከዚያ ይልቅ ሁሉም አገልጋዮች ናቸው፡፡ የመጣውን እንግዳ እግሩን ለማጠብ ይሽቀዳደማሉ፡፡ ይህን
ሲያደርጉም አስቀድመው የሰውዬውን ማንነት አይጠይቁም፡፡ ባርያም ይሁን ጌታም ይሁን በእነርሱ ዘንድ ልዩነት የለውምና፡፡ ሰው መሆኑ
በቂያቸው ነውና፡፡ በእነርሱ ዘንድ ታላቅ የለም ታናሽም የለም፡፡ ለምን? ማወቅ ተስኖአቸው ተደነጋግሮአቸው ነውን? በፍጹም! ያንን
የሚመለከቱበት ልብ ያንን የሚያደርጉበት ሕሊና ስለሌላቸው እንጂ፡፡ ከእነርሱ አንዱ በጣም ታናሽ ነኝ ብሎ የሚያስብ ከሆነ ሌሎቹ
እንደዚያ ታናሽ ነው ብለው አይመለከቱትምና፡፡ እነርሱ ራሳቸው ከእርሱ በታች ታናሽ እንደሆኑ የሚያስቡ ናቸውና፡፡
ለሁላቸውም አንድ ማዕድ አላቸው፡፡ አገልጋዩም ተገልጋዩም አንድ ዓይነት ምግብ፤
አንድ ዓይነት ልብስ፤ አንድ ዓይነት በዓት፤ አንድ ዓይነት የአኗኗር መርሕ አላቸው፡፡ ትንሹን ሥራ የሚሠራ እርሱ በሁላቸውም ዘንድ
ታላቅ ነው፤ የከበረ ነው፡፡ ይህ የእኔ ነው ያም የአንተ ነው የሚባል ነገር አይታወቅም፡፡ ለብዙ ሰዎች መጥፋት ምክንያት ለብዙ
ዓለማቀፍ ጦርነቶች መነሻ የሆነው ይህ አገላለጽ (ይህ የእኔ ነው ይህ የአንተ ነው የሚል አገላለጽ) በእነርሱ ዘንድ ቦታ ካጣ ሰነባብቷል፡፡
አንድ ዓይነት መዓድ፣ አንድ ዓይነት ልብስ፣ አንድ ዓይነት በዓት፣ አንድ ዓይነት
የኑሮ መርሕ ስላላቸው ትደነቃላችሁን? ምን ይሄ ብቻ? ልባቸውም አንዲት ናት፤ ነፍሳቸውም አንዲት ናት፡፡ በተፈጥሮ እንዲያ ሆኖ
አይደለም፤ በፍቅር ስለተሳሰረ እንጂ፡፡ አንዲት ነፍስ ካለቻቸውስ እንደምን አንዱ የበላይ አንዱ የበታች አድርጎ ሊያስብ ይችላል?
አንዲት ነፍስ ለራሷ እኔ የበላይ ነኝ አንቺም የበታች ነሽ ልትል ትችላለችን? በፍጹም!
በእነዚህ ቅዱሳን ዘንድ ባዕለ ጸጋ የለም ደሀም የለም፤ ክቡር የለም ሕሱርም
የለም፡፡ እንዲህ ያለ ነገር ከሌለስ ትዕቢትና ኩራት እንደምን መግቢያ ቀዳዳ ሊያገኙ ይችላሉ? በእውነቱ እነዚህ መነኰሳት መነኰሳይያትም
ታናናሾችም ታላላቆችም ናቸው፡፡ ሆኖም ግን አስቀድሜ እንደነገርኳችሁ ይህ ነገር ለእነርሱ አይታያቸውም፡፡ ታናሽ