Showing posts with label ከእናንተ የሚፈለገው… በቅ/ዮሐንስ አፈወርቅ. Show all posts
Showing posts with label ከእናንተ የሚፈለገው… በቅ/ዮሐንስ አፈወርቅ. Show all posts

Thursday, July 26, 2012

ከእናንተ የሚፈለገው… በቅ/ዮሐንስ አፈወርቅ!


 
… ይህ ቃል (“ለዚህ ክፉ ትውልድ ደግሞ እንዲሁ ይሆንበታል” የሚለው ቃል) በየወቅቱ ሊነገር የሚገባው እንጂ ለአይሁድ ብቻ ተነግሮ የሚያበቃ አይደለም፡፡ ዛሬ ብዙዎቻችን ብርሃን ከወጣልንና /ዕብ.6፡4/ ከብዙ ደዌዎቻችን ከተፈወስን በኋላ መልሰን ወደ ከፋ ዐዘቅት እንገባለን፡፡ ስለዚህም የሚያገኘን መከራ ከድሮ ደዌአችን በጣም የባሰ ነው፡፡ ጌታ ሽባውን ከፈወሰው በኋላ “ናሁኬ ሐየውከ- እነሆ አሁን ከደዌህ ድነሀል፤ ዑቅ ኢተአብስ ዳግመ እንከ ከመ ዘየአኪ ኢይረክበከ- ከዚህ የሚብስ እንዳይደርስብህ ወደ ፊት ኃጢአትን አትሥራ” ነበር ያለው /ዮሐ.5፡14/፡፡ 38 ዓመት ሙሉ ለተሰቃየው መጻጕዕም እንደዚሁ ነግሮታል /ዮሐ.5፡14/፡፡ ከእናንተ መካከል “ከዚህ የሚብስ ምን ያገኟል?” ብሎ የሚጠይቅ ሊኖር ይችላል፡፡ ከዚህ የባሰ እማ አለ እንጂ፡፡ ደዌ ነፍስ ይቅርና በዚህ ምድር እንኳን ሊቋቋመው የማይችል ደዌ ሥጋ ሊያገኘው ይችላል፡፡ አያድርስብን እንጂ መቋቋም የምንችለው መቋቋም የምንችለውን ብቻ ነው፡፡…

 ጌታ ኢየሩሳሌምን ሲወቅሳት እንዲህ ብሎ ነበር፡- “በአብርሃም አድሬ ወዳንቺ መጣሁ  በደመ ጣዖትም ተበክለሽ አየሁሽ፣ በደምሽ እንዳለሽ በሕይወት ኑሪ አልሁሽ፤ አዎን በደምሽ እንዳለሽ በሕይወት ኑሪ አልሁሽ…ወሐጸብኩኪ በማይ- በውኃም አጠብሁሽ፣ወአጽረይኩ ደመኪ- ከደምሽም አጠራሁሽ፣ ወቀባእኩኪ በዘይት- በዘይትም ቀባሁሽ…ባንቺ ላይ ካኖርኋት ከክብሬ የተነሣ ውበትሽ ፍጹም ነበረና ዝናሽ በአሕዛብ መካከል ወጣ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር…ወዘመውኪ ምስለ ውሉደ ግብጽ አግዋርኪ እለ ዐብይ ሥጋሆሙ- ሥጋቸውም ከወፈረ ከጐረቤቶችሽ ከግብጻውያን ጋር አመነዘርሽ፥ ወአብዛኅኪ ዝሙትኪ ከመ ታምዕዕኒ- እኔንም ታስቈጭ ዘንድ ግልሙትናሽን አበዛሽ” /ሕዝ.16፡6፣9፣14፣26/፡፡ አዎን! ሁል ጊዜ በኃጢአት ተለውሰን ለምንኖር ለእኛም ወቀሳው ይህን የመሰለ “አሌ ለክሙ” ነው፡፡

…ትላንት ወደ ሠራነው ኃጢአት ስንቴ ተመለስን? ስንቴስ የባሰ ነገር አገኘን? ወንድሞቼ! ይህን ሁሉ የምላችሁ እንድትማሩበት እንጂ ተስፋ እንድትቆርጡ አይደለም፡፡ ፎርዖንን ታስታውሳላችሁ አይደል? እርሱ ከመጀመርያው መቅሰፍት ተምሮ ቢሆን ኖሮ ከነሙሉ ሠራዊቱ ጋር በባሕረ ኤርትራ ሰጥሞ የዓሳ ቀለብ ሁኖ ባልቀረ ነበር፡፡ እኛ እኮ አሁን ከፊታችን የምንሻገረው ቀይ ባሕር የለንም፤ ነገር ግን በዓይነቱም ይሁን በመጠኑ የቀይ ባሕርን የሚያክል ሳይሆን በጣም ግዙፍና ሙቀቱ ኃይለኛ የሆነ፣ ማዕበሉም ታይቶ የማይታወቅ አስጨናቂ የእሳት ባሕር ነው፡፡ በዚህ እንጦርጦስ እሳቱ የማይጠፋ ትሉ የማያንቀላፋ ስቃይ አለ፡፡ በዚህ የእሳት ባሕር ውስጥ በየትኛውም አቅጣጫ እንደ አረመኔ የበረሀ አውሬ በቅጽበት የሚዞር ወላፈን አለ፡፡ እኛ የምናውቀው የዚህ ዓለም እሳት እንኳ ከሩቅ የነበሩትን የናቡከደነጾር መልእክተኞች ለመፍጀት ኃይለኛ ከሆነ /ዳን.3፡22/ ይህ እሳት ያውም ወደ ራሱ የተጣሉለትንማ ምን ያህል ይፈጃቸው ይሆን?
…ወንድሞቼ ያኔ ከዚህ እቶን እንኳንስ ሊያድነን ቀርቶ ምላሳችንን የምናርስበት የውኃ ጠብታ ሊሰጠን የሚችል ማንም የለም፡፡…አሁን ወደ እግዚአብሔር ቀርቦ መለመን ከፍርድም ነጻ መሆን ይቻላል፡፡ ያኔ ግን ጌታ ይህን ስለማይፈቅድ በሚያንገበግብ እሳት እየተጨነቁ ቃላትም ሊገልጹት በማይችሉ እሳትና ጭንቅ መጣል ብቻ ነው፡፡ አሁን በዚህ ዓለም ወደ እሳት የሚጣሉትና የሚቃጠሉት ቃጠሎ ቃላት አይገልጸውም አይደል? ይህ ግን በጣም ቀላል ነው፡፡ “እንዴት?” ብትሉኝ ከጊዜ አንጻር ሲታይ በጣም አጭር ነውና፡፡ በዚያ ያለው ቃጠሎ ግን መጨረሻ የለውም፡፡…

 በምነግራችሁ ነገር እያበሳጨኋችሁና እያሳመምኳችሁ እንደሆነ ይገባኛል፡፡ ግን ምን ላድርግ? እኔም እናንተም በምግባር በሃይማኖት የታነጽን እንሆን ዘንድ ብቻ ሳይሆን ከዚያም እናመልጥ ዘንድ ነው፡፡ ነገር ግን በኃጢአት ከመጨማለቃችን የተነሣ እንዴት አድርጌ ላሳምማችሁ እችላለሁ? ብትሰሙኝና ብተለወጡስ እኔም ማረፍ እንኳን በቻልኩ ነበር፡፡ ስለዚህ እስካልተለወጣችሁ ድረስ እናንተን መገሰጼና መምከሬ አላቆምም፡፡… ስለ ገሀነመ እሳት ተደጋግሞ ሲነገር የሚበሳጭ ሰው ሊኖር ይችላል፡፡ እኔ ግን “ከዚህ በላይ አስደሳች ትምህርት የለም” እለዋለሁ፡፡ “እንዴት ይህ አስደሳች ትምህርት ነው ትለናለህ?” ልትሉኝ ትችላላችሁ፡፡ እኔም “ወደዚያ መጣል ከደስታ ሁሉ የራቀ ነውና” ብዬ እመልስላችኋለሁ፡፡ ስለዚህ ነፍሳችን ከመታሰሯ በፊት የነቃን እንሆን ዘንድ ይህን ደጋግሜ እነግራችኋለሁ፡፡…

 እንግዲያውስ ማንም ለራሱ ንስሐ ይግባ እንጂ እንደተወቀሰ አያስብ፤ በንግግሬም የሚቆጣ አይሁን፡፡ ሁላችንም ወደ ጠባቢቱ መንገድ እንግባ፡፡ እስከ መቼስ በስፍና አልጋ እንተኛለን? ዛሬ ነገ ማለት አይበቃንምን? ሰማያዊ ቪላችንን ቀና ብለን ብንመለከት እኮ በዚህ ምድር ይህንን ለመሥራት ባልደከምን ነበር፡፡ እሰኪ ንገሩኝ! ሩጫችን ስንጨርስ ከሬሳ ሳጥንና ከመግነዝ ጨርቅ ውጪ ይዘነው የምንሄድ ነገር አለን? ታድያ ለምን እንከራከራለን?

ስለዚህ ተወዳጆች ሆይ ከዛሬ ጀምረን አዲስ ሕይወትን እንጀምር፡፡… አሕዛብ ምን ያህል በረከት እንደራቃቸው እናሳያቸው፡፡ በእኛ ዘንድ መልካምነትን ካዩ መንግሥተ ሰማያትን በእኛ ውስጥ ያይዋታል፡፡ አዎ! ጨዋ ስንሆን፣ ከክፋት፣ ከክፉ ምኞት፣ ከቅናትና ከጠበኝነት ርቀን ሲመለከቱን፡- “እነዚህ ክርስቲያኖች ገና እዚህ ምድር እያሉ መላእክትን ከመሰሉ ወደዚያኛው ዓለም ሲሸጋገሩ ወደ እውነተኛው ሀገራቸው ሲሄዱ ምን ይመስሉ ይሆን? በእንግድነት ዘመናቸው እንዲህ ብርሃን ከለበሱ ወደ ትውልድ ሀገራቸው ሲሄዱማ እንዴት ይሆኑ ይሆን?” ይላሉ፡፡ በእኛ ምክንያት እነርሱ ይለወጣሉ፤ የእግዚአብሔር ቃል ከእኛ የተነሣ ይከብራል /2ተሰ.3፡1/፤ ወንጌል ከሐዋርያት ዘመን በላይ ይፋጠናል፡፡ ሐዋርያት አሥራ ሁለት ብቻ ሆነው ዓለምን ከለወጡ ከእነርሱ በቁጥር የበዛን እኛማ በመልካም ምግባራችን አስተማሪዎች ብንሆን እግዚአብሔር ምን ያህል ሊወደስ ሊቀደስ እንደሚችል አስቡት፡፡ አሕዛብ ራስን ከመግዛት በላይ ሙት ማስነሣትን አይማርካቸውም፡፡ ምክንያቱም ሙት ሲነሣ ይገረማሉ፤ በመልካም ምግባራችን ግን ይጠቀማሉ፡፡ ሙት ሲነሣ የአንድ ጊዜ ክስተት ነው፤ መልካም ምግባር ግን ሁል ጊዜ ከነፍሳቸው ጋር ተዋሕዶ የሕይወት ልምድ ይሆንላቸዋል፡፡

 ስለዚህ እነሱንም እናመጣ ዘንድ እንፍጨርጨር፡፡ ደግሞም እኮ ከባድ ነገር አልተናገርኳችሁም፡፡ አትጋቡ አላልኳችሁም፤ ከሰው ተለይታችሁ ከማኅበራዊ ኑሮ ራቁም አላልኳችሁም፤ ከእነርሱ ጋር ሆናችሁ መልካምነትን አሳዩ እንጂ፡፡ አዎ! በከተማ መሀል ሆነው መልካም ምግባርን የሚያሳዩ ክርስቲያኖች በገዳም ካሉ መነኰሳት ይበልጣሉ፡፡ ምክንያቱም በከተማ ያሉት ሊሰወሩ አይቻላቸውም፤ መብራታቸውንም አብርተው ከእንቅብ በታች ሊያኖሩት አይችሉም /ማቴ.5፡15፣ ሉቃ.11፡33/፡፡

 ስለዚህ ከዛሬ ጀምረን ለመብራታችንን ዘይት እንጨምርበት፤ በጨለማ ላሉትንም ከስሕተታቸው ይወጡ ዘንድ ምክንያት እንሁንላቸው፡፡ “ትዳር አለኝ፤ ልጆችን አሳድጋለሁ፤ የቤት አባወራ ስለሆንኩኝ ይህንን ማድረግ አልችልም” አትበሉኝ፡፡ ከእናንተ የሚፈለገው ፈቃዳችሁ ብቻ ነውና፡፡ ዕድሜም ቢሆን፣ ባለጸግነትም ቢሆን፣ ማጣትም ቢሆን ሌላም ቢሆን ይኸን ሁሉ ከማድረግ አይከለክላችሁምና፡፡ ምክንያቱም ሽማግሌዎችም፣ ወጣቶችም፣ ሚስቶችም፣ ሕፃናት አሳዳጊዎችም፣ ዕደ ጥበቦኞችም፣ ወታደሮችም ይህን ሁሉ ፈጽመውታልና፡፡ ዳንኤል ወጣት ነበር፤ ሠለስቱ ደቂቅ ሕፃናት ነበሩ፤ ዮሴፍ ባርያ ነበር፤ ሉቃስ ሐኪም ነበር፤ ሊድያም ሐር ሻጭ ነጋዴ ነበረች፤ ጳውሎስንና ሲላስን በወኅኒ ሲጠብቅ የነበረውም ፖሊስ ነበር፤ ቆርነሌዎስ ደግሞ አሥራ አለቃ ነበር፤ ጢሞቴዎስ በሽተኛ ነበር… ነገር ግን ይኸን ከማድረግ የከለከላቸው አንዳችም ምክንያት አልነበረም፡፡ እነዚህ ሁሉ እንደ እኛ ሴቶች፣ እንደ እኛ ወጣቶች፣ እንደ እኛ ሽማግሎች፣ እንደ እኛ ነጋዴዎች፣ እንደ እኛ አሠሪዎች፣ እንደ እኛ ሠራተኞች፣ ወታደሮችና ሲቪል ነበሩ፡፡

 እንግዲያስ መልካም ፈቃድ ይኑረን እንጂ ከንቱ ሰበብን የምናበዛ አንሁን፡፡ ምንም ዓይነት ማንነት ይኑረን ፈቃደኞች ከሆንን ከእግዚአብሔር ጋር መልካምነትን መያዝ እንችላለን፡፡ ይህንን ሁሉ እንድናደርግና በቸርነቱ መንግሥቱን እንዲያወርሰን ሰውን በመውደድ ሰው የሆነው ክርስቶስ ይርዳን፡፡ አሜን!!



FeedBurner FeedCount