ገ/እግዚአብሔር ኪደ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ ነሐሴ ፭ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም.)፡- ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም እመቤታችን
ከባረከችው በኋላ ምስጋናውን የጀመረው “ፈቀደ እግዚእ…” ብሎ ነው፡፡
፩. በመቅድመ ወንጌል “ወአልቦቱ ካልእ ሕሊና ዘንበለ ብካይ ላዕለ ኃጢያቱ - በኃጢአቱ
ከማዘን፣ ከማልቀስ በቀር ሌላ ግዳጅ አልነበረውም” እንዲል ጌታ ፭ ሺህ ከ፭፻ ዘመን በግብርናተ ዲያብሎስ ያዝን ይተክዝ የነበረ አዳምን ነጻ ያደርገው (ያድነው) ዘንድ ወደደ፡፡ ምድራዊ ንጉሥ የተጣላውን አሽከር “ሰናፊልህን (ልብስህን) አትታጠቅ፤ እንዲህ ካለ ቦታም አትውጣ” ብሎ ወስኖ ያግዘዋል፡፡ በታረቀው ጊዜ ግን ርስቱን፣ ጉልበቱን፣ ቤቱን፣ ንብረቱን እንደሚመልስለት ኹሉ ንጉሠ ሰማይ ወምድር እግዚአብሔርም
“ጥንቱንም መሬት ነህና ወደ መሬት ተመለስ” /ዘፍ.፫፡፲፱/ ብሎ ፈርዶበት የነበረ አዳምን ይቅር ብሎ ወደ ቀደመ ቦታው ወደ ገነት፣ ወደ ቀደመ ክብሩ ወደ ልጅነት ይመልሰው ዘንድ ወደደ
/ሉቃ.፳፫፡፵፫/፡፡