Showing posts with label የዮሐንስ ወንጌል የ26ኛ ሳምንት ጥናት. Show all posts
Showing posts with label የዮሐንስ ወንጌል የ26ኛ ሳምንት ጥናት. Show all posts

Friday, June 8, 2012

ከዮሐንስ ምስክር የሚበልጥ ምስክር አለኝ- የዮሐንስ ወንጌል የ26ኛ ሳምንት ጥናት (ዮሐ.5፡30-ፍጻሜ)!


     በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

 አንድ ምንም እውቀቱና ልምዱ የሌለው ሰው ዝም ብሎ መሬት ስለ ቆፈረ ብቻ ወርቅ አያገኝም፡፡ ከዚያ ይልቅ ምንም ረብሕና ጥቅም የሌለውን ድካም ያተርፋል እንጂ፡፡ ባስ ካለም የቆፈረው ጉድጓድ ተደርምሶበት ሕይወቱን ሊያጣ ይችላል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንዴት እንደሚነበብና እንዴት መረዳት እንዳለበት ያለወቀ ሰውም ይህን ሰው ይመስላል፡፡ ይህንን የምንለው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ይልቁንም ቀጥለን የምንመለከተው ቃል በቀላሉ ሊረዱት የማይችሉና ሰም ለበስ ወርቅ ስለሆነ እንጂ፡፡ ጌታችን “እኔ ከራሴ አንዳች ላደርግ አይቻለኝም፤ እንደ ሰማሁ እፈርዳለሁ ፍርዴም ቅን ነው፥ የላከኝን ፈቃድ እንጂ ፈቃዴን አልሻምና።  እኔ ስለ እኔ ስለ ራሴ ብመሰክር ምስክሬ እውነት አይደለም” ስላለ ብቻ እንዲሁ ጥሬ ንባቡን በመያዝ ብዙ ሰዎች ይደናበራሉ /ቁ.30-31/፤ እውነት የሆነው “ክርስቶስ ስለ ራሱ የመሰከረው ምስክርነት እውነት አይደለም” ለማለት ይደፍራሉ፡፡ ሆኖም ግን ጌታችን ይህንን ሲል እነርሱ እንደሚሉት ማለቱ አልነበረም፡፡ አይሁድ “እግዚአብሔር አባቴ ነው፤ ከአባቴ ጋር የተስተካከልኩ ነኝ፤ አባቴ እስከ ዛሬ እንደሚሠራ እኔም በአንድ ፈቃዲት በአንዲት ሥልጣን እንዲህ አደርጋለሁ” ቢላቸው “አንተ ስለ ራስህ ትመሰክራለህ፤ ምስክርነትህ እውነት አይደለም፡፡ ስለዚህም አናምንህም” /ዮሐ.8፡13/ ስለሚሉትና ሊገድሉት ስለሚፈልጉ፡- “እኔ ምንም ምን ከራሴ ብቻ አንቅቼ አላስተምርም፤ በህልውና እንደሰማሁ የሰማሁትን አስተምራለሁ እንጂ፡፡ ትምህርቴም እውነት ነው፤ የእኔ ፈቃድ ከአባቴ ፈቃድ ልዩ ሆኖ የእኔ ፈቃድ ብቻ ሊደረግ አልወድም፤ ወልድ ያልወደደው አብም አይወደውም” ነው የሚላቸው /ወንጌል ቅዱስ አንድምታ ገጽ 481/፡፡

   ሰው ወዳጁ ጌታ ንግግሩን በዚህ አያቆምም፤ ይልቁንም እንዲህ ብሎ ይቀጥላል እንጂ፡- “የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ስላልሁ፣ አብ ልኮ ያዋሐደኝ አምላክ ነኝ ብላችሁ እናንተ ግን ትሳደባለህ ትሉኛላችሁ፡፡ ሆኖም እኔ የአባቴን ሥራ ባላደርግ፣ የአምላክነትን ሥራ ባላደርግ አትመኑኝ፤ ምስክርነቴንም አትቀበሉ፤ ባደርገው ግን እኔን እንኳ ባታምኑ አብ በእኔ ህልው እንደሆነ እኔም በአብ ህልው እንደሆንሁ ታውቁና ታስተውሉ ዘንድ ሥራውን እመኑ”/ዮሐ.10፡36/፤ አብ ሙታንን እንደሚያነሣ ሕይወትም እንደሚሰጣቸው እኔም ለምወዳቸው ለሚያምኑብኝ ሕይወትን የመስጠት ኃይልና ሥልጣን እንዳለኝ እመኑ፡፡ አንተ ስለራስህ የምትመሰክረው ምስክርነት አንቀበልም ብትሉ እንኳን አብ ስለ እኔ የሚመሰክረውን ለመቀበል አትቸገሩ፤ የማደርገውን ሥራ አይታችሁ እመኑ፡፡ እናንተ ወደ ዮሐንስ ልካችሁ አልነበረምን? እርሱስ፡-እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔረ በግ ብሎ እውነት ነግሯችሁ አልነበረምን? /ዮሐ.1፡29/:: እንግዲያውስ ዮሐንስ የመሰከረላችሁ ምስክርነት እመኑ፡፡ ስለ ራስህ ምን ትላለህ? ሳይሆን ስለ ክርስቶስ ምን ትላለህ? ብላችሁ ጠይቁትና እመኑ፡፡ እናንተ እንድትድኑ ይህን እላለሁ እንጂ እኔስ  ከሰው ምስክር አልቀበልም፡፡ እናንተ ትወዱት ስለ ነበረ እንደ ነብይም ታዩት ስለ ነበረ የእርሱን ትምህርት አድምጣችሁ በእኔ ታምኑ ዘንድ ትምህርቱን አስታወስኳችሁ እንጂ አምላክነቴን ለማረጋገጥስ የማደርገው ተአምራት ራሱ በቂ ነው /ቁ.34፣ Saint John Chrysostom  Homilies on ST. John, 41/፡፡

FeedBurner FeedCount