Showing posts with label ጾም. Show all posts
Showing posts with label ጾም. Show all posts

Tuesday, June 5, 2012

ጾም!!


ጾም መድኃኒት ናት፡፡ አወሳሰድዋን በትክክል ላላወቁ ግን ጥቅም የላትም፡፡ ይህችን መድኃኒት የሚወስድ ሰው በየስንት ሰዓቱ እንደምትወሰድ፣ በምን ያህል መጠን (Dosage) እንደምትዋጥ፣ ለምን ዓይነት በሽታ እንደምትጠቅም፣ በየትኛው ወራትና በየትኛው የአየር ሁናቴ እንደምትወሰድ፣ ከእርሷ ጋር የሚሄዱና የማይሄዱ ምግቦችን እንዲሁም ሌሎች ከእርሷ ጋር የማይስማሙ ነገሮችን ለይቶ ማወቅ አለበት፡፡ እነዚህን ግምት ውስጥ አስገብተን የማንወስዳት ከሆነ ግን ከጥቅሟ ይልቅ ጉዳቷ ያመዝናል፡፡ አንድ በሐኪም የታዘዘልንን የደዌ ሥጋ መድኃኒት በትክክል ከወሰድነው ከሕመማችን እንፈወሳለን፤ የነፍሳችንን ደዌ ለመፈወስ ብለን በምንወስደው መድኃኒት ደግሞ ከዚህ የበለጠ መጠንቀቅ አለብን፡፡

ጾም ሁለመናችንን የምንለውጥበት መሣርያ ነው፡፡ ምክንያቱም የጾም መሥዋዕት ማለት ከምግብ ብቻ መከልከል ሳይሆን ከኃጢአት ሁሉ መከልከል ነውና፡፡ ስለዚህ እየጾምኩ ነው እያለ ራሱን ከምግብ ብቻ የሚከለክል ሰው ካለ እርሱ ጾምን እያቃለለና እያጥላላ ነው ማለት ነው፡፡ እየጾማችሁ ነው? እንግዲያስ መጾማችሁን በተግባር አሳዩኝ፡፡ “እንዴት አድርገን እናሳይህ?” ልትሉኝ ትችላላችሁ፡፡ እኔም እንዲህ ብዬ እመልስላችኋለሁ፡- ደሀው እርዳታችሁን ፈልጎ እንደሆነ ቸርነትን አድርጉለት፤ የጠላችሁት ሰው ካለ ፈጥናችሁ ታረቁ፤ ባልጀራችሁ ተሳክቶለት ስታዩት በእርሱ ላይ ቅናት አትያዙ፤ ቆነጃጅትን በመንገድ ሲያልፉ ስታዩ በዝሙት ዓይን አትመኙ፡፡ እንዲህ እንዲህ እያደረጋችሁ በትክክል መጾማችሁን አሳዩኝ፡፡

 በሌላ አገላለጽ አፋችሁ ብቻ ሳይሆን ዐይኖቻችሁ፣ እግሮቻችሁ፣ እጆቻችሁና የሰውነታችሁ ሕዋሳቶች በሙሉ መጾም አለባቸው፡፡ እጆቻችሁ ከመስረቅና የእናንተ ያልሆነውን ከመውሰድ ይጹሙ፤ እግሮቻችሁ የኃጢአት ሥራን ለመፈፀም ከመፋጠን ይጹሙ፤ ዐይኖቻችሁ ውጫዊ በሆነ ውበት ምክንያት ከመቅበዝበዝ ይጹሙ፡፡ ጥሉላትን (የፍስክ ምግብ) እየበላችሁ አይደለም አይደል? እንግዲያስ በዐይኖቻችሁም ክፉ ነገርን አትብሉ፡፡ የሚታዩ ነገሮች ለዐይን ምግቦች ናቸውና፡፡ ጀሮዎቻችሁም ይጹሙ፡፡ የጀሮ ጾም ሐሰተኛ ወሬንና ሐሜትን አለመስማት የመሳሰለ ነው፡፡

 አንደበታችሁም ከከንቱ ንግግር ይጹም፡፡ ዓሣንና ሌሎች ጥሉላትን ከመብላት ተከልክለን ሳለ ነገር ግን ወንድሞቻችንን በሐሜት የምናኝካቸውና የምንበላቸው ከሆነ ምን ጥቅም አለው? ወንድሙን የሚያማና የሚነቅፍ ሰው እርሱ የወንድሙን አካል ያቆስላል ሥጋውንም ይበላል፡፡ ለዚህም ነው ሐዋርያው ይህን አስመልክቶ  እጅግ የሚያስደነግጥ ንግግርን እንዲህ ሲል የተናገረው፡- “እርስ በእርሳችሁ ብትነካከሱና ብትበላሉ እርስ በእርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ” /ገላ.5፡15/፡፡ ስታሙ በጥርሳችሁ የወንድማችሁን ሥጋ አትነክሱም፡፡ በክፉ ንግግራችሁ ግን የወንድማችሁን ነፍስ ትነክሳላችሁ፤ ታቆስሉትማላችሁ፡፡ እንዲህ በማድረጋችሁ ራሳችሁን፣ ወንድማችሁንና ሌሎች ብዙ ሰዎችን ትጎዳላችሁ፡፡” 

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ!

FeedBurner FeedCount