Thursday, January 2, 2014

ነቢዩ ሐጌ

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ታኅሳስ ፳፪ ቀን፣ ፳፻፮ ዓ.ም.)፡-በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
 ሐጌ ማለት በዓል፣ ደስታ ማለት ነው፡፡ የስሙ ትርጓሜ ሕዝቡ ከምርኮ የሚመለሱ ስለኾነ ይኽን ደስታ የሚያስረዳ ነው፡፡
 በብሉይ ኪዳን በመጨረሻ የምናገኛቸው ሦስቱን መጻሕፍት ማለትም ትንቢተ ሐጌ፣ ትንቢተ ዘካርያስና ትንቢተ ሚልክያስ ከምርኮ በኋላ ስላለው ጊዜ እንዲኹም አይሁድ ከምርኮ እንዴት ወደ አገራቸው እንደተመለሱ የሚያስረዱ ናቸው፡፡ በዚያ አንጻር ግን ደቂቀ አዳም ከዲያብሎስ ምርኮ እንደምን ወደ እግዚአብሔር እንደተመለሱ የሚያረዱ ናቸው፡፡

 ነቢዩ ሐጌ የተወለደው በምርኮ በባቢሎን ሲኾን ትንቢቱን ሲናገር የ፸፭ ዓመት ሽማግሌ ነበር፡፡ የእስራኤል ቅሪቶች ወደ ኢየሩሳሌም በዘሩባቤል አማካኝነት ሲመለሱ ነቢዩ ሐጌም ከተመለሱት ጋር አንዱ ነበር፡፡
 በ፭፻፴፰ ቅ.ል.ክ. ላይ የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ አንድ አዋጅ አስነግሮ ነበር፡፡ አዋጁም አይሁድ ወደ አገራቸው እንዲመለሱና ቤተ መቅደሱን እንዲሠሩ የሚፈቅድ ነበር /ዕዝራ ፩፡፩-፲፩/፡፡ በዚኽም መሠረት የቤተ መቅደሱን ሥራ በ፭፻፴፮ ላይ የቤተ መቅደሱን ሥራ ዠምረዋል፡፡ ነገር ግን አይሁድ ወደ አገራቸው ሲገቡ አገራቸው ባድማ ኾና ስለነበር፣ የዘር ፍሬ በአገሩ ስላልነበረ፣ እንዲኹም በሌሎች ችግሮች ምክንያት ቤተ መቅደሱን መሥራት ትተው ወደየግላቸው ተግባር ተሰማርተው ነበር፡፡ በመኾኑም መንፈሳዊ ሕይወታቸው ዝሎ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ነቢዩ ሐጌንና ነቢዩ ዘካርያስን የላከበት ዋና ምክንያትም የተዠመረውን ቤተ መቅደስ እንዲያጠናቅቁት ለማሳሰብ ነበር፡፡
 ነቢዩ ሐጌ በሚያገለግልበት ወራት የነበረው ንጉሥ ዘሩባቤል ሲኾን፤ በዚያ ሰዓት የነበረው ሊቀ ካህናት ደግሞ ኢያሱ ይባላል /፩፡፩/፡፡
ትንቢተ ሐጌ
 ነቢዩ ሐጌ በእግዚአብሔር ሰዓት የእግዚአብሔር ሰው ኾኖ የተገኘ ነቢይ ነው፡፡ አገልግሎቱን በ፭፻፳ ቅ.ል.ክ. ላይ ሲዠምር ጠንካራና ፬ ተከታታይ ስብከቶችን በመስጠት ነበር፡፡ ለሕዝቡ የቤተ መቅደሱ ሥራ እንደተቋረጠ ነገራቸው፤ ሕዝቡ ከቤተ እግዚአብሔር ይልቅ የራሳቸውን ቤት በመሸላለም እንደተሳቡ ገለጠላቸው፡፡ አራቱን ስብከቶቹም እንደሚከተለው የቀረቡ ናቸው፡-
1.     የቤተ መቅደሱን ሥራ እንዲያጠናቅቁት አሳሰባቸው /ምዕ. ፩/፡፡ በዘሩባቤል አማካኝነት ቅሪቶቹ ከባቢሎን ምርኮ ሲመለሱ የእግዚአብሔርን ቤት መሥራት ዠምረው ነበር፡፡ ነገር ግን ሥራው ብዙም ሳይቈይ ቆመ፤ ለ፲፮ ዓመት ያኽልም ተስተጓጐለ፡፡ ሕዝቡ የራሳቸውን ቤት ሸላልመው የመሥራት ችግር አልነበረባቸውም፤ ቤተ መቅደሱን ለመሥራት ግን “ጊዜ አልነበራቸውም”፡፡ እንደዉም፡- “ኢኮነ ጊዜኹ ለሐኒፀ ቤተ እግዚአብሔር - የእግዚአብሔር ቤት የሚሠራበት ዘመን አኹን አይደለም” እያሉ ያመካኙ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ግን በቀጥታ በነቢዩ ሐጌ፣ በአለቃቸው በዘሩባቤልና በሊቀ ካህናቱ በኢያሱ በኵል ተናገራቸው፡፡ እነርሱም ሰሙ፤ ከ፳፫ ቀን በኋላም የቤተ መቅደሱን ሥራ በድጋሜ ዠመሩት፡፡
2.    የኹለተኛው ቤተ መቅደስ ክብር እንዴት እንደኾነ አስረዳቸው /፪፡፩-፱/፡፡ ሕዝቡ የቤተ መቅደሱን ሥራ ለጥቂት ሳምንታት ከቀጠሉ በኋላ ግን አኹንም ተስፋ መቊረጥ ዠመሩ፡፡ ሽማግሌዎቹ የቀድሞው የሰሎሞን ቤተ መቅደስ እንዴት እንደነበረ አስታወሱና ይኽ አኹን የሚሠሩትን ቤተ መቅደስ አቃለሉት፡፡ ነቢዩ ሐጌ ግን የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን አስታወሳቸው፡፡ እግዚአብሔር በዚኽ ቤት ያለው ዓላማ ሲገልጥም፡- “ከፊተኛው ይልቅ የዚኽ የኹለተኛው ቤት ክብር ይበልጣል ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር” አላቸው /፪፡፱/፡፡ በዚኽ ቤተ መቅደስ አንጻርም በክርስቶስ ስለምትሠራውና በደሙ ስለምትከብረው ቤተ ክርስቲያን ትንቢት ሲናገር ነው፡፡ እንደዉም ቊጥር ፭ ላይ በግልጥ ስለ መንፈስ ቅዱስ የሚናገር ነው፡፡
3.    የመታዘዛቸው ውጤት የኾነ በረከትን እንደሚባረኩ ነገራቸው /፪፡፲-፲፱/፡፡ ነቢዩ ሐጌ አንድ ሰው ኃጢአት ሲሠራ የእግዚአብሔር በረከት እንዴት እንደሚርቀው ለካህናቱ አስተማራቸው፡፡ አኹን ግን ሕዝቡ ቤተ መቅደሱን ለመሥራት ስለታዘዙ ከዚያች ቀን ዠምሮ እንደምን ባለ በረከት እንደሚባርካቸው አስተማራቸው፡፡
4.    በመታዘዛቸው ምክንያት ሊመጣ ያለው በረከት እንዴት እንደኾነ አስታወቃቸው /፪፡፳-፳፫/፡፡ ነቢዩ ሐጌ ሕዝቡ ለእግዚአብሔር በመታዘዛቸው እንደምን ባለ የአኹን በረከት እንደሚባርካቸው ከገለጠ በኋላ ዳግመኛም ለዘሩባቤል እንዲኽ አለው፡- “ሰማያትንና ምድርን አናውጣለኹ፤ የመንግሥታትንም ዙፋን እገለብጣለኹ፤ የአሕዛብንም መንግሥታት ኃይል አጠፋለኹ” /፪፡፳-፳፩/፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንደሚያስተምሩት ዘሩባቤል የመሲሑ የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡ በዘሩባቤል አንጻር፡- “ዘሩባቤል ሆይ! በዚያ ቀን እወስድኻለኹ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፡፡ እኔ መርጬኻለኹና ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ እንደ ቀለበት ማተሚያ (እንደ ዳዊት) አደርግኻለኹ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር” ማለቱም ይኽን የሚያስረዳ ነው /ቊ. ፳፫/፡፡
በአጠቃላይ የነቢዩ ሐጌ ዓላማ ሕዝቡ የትኛው ማስቀደም እንዳለባቸው ለማሳሰብና ምንም ነገር ከመጠበቃቸው በፊት የቤተ መቅደሱን ሥራ እንዲጨርሱት ለማስገንዘብ ነበር፡፡ ነቢዩ ሐጌ እንደነገራቸው ሕዝቡ ከእግዚአብሔር በፊት የራሳቸውን ነገር ሲያስቀድሙ ነገሮች እንዴት ከባድ እንደኾኑባቸው ነግሯቸዋል፡፡ ለእግዚአብሔር ታዝዘው እግዚአብሔርን ሲያስቀድሙም እንደምን ባለ በረከት እንደሚባርካቸው ግልጽ አድርጐ ነግሯቸዋል፡፡
እኛስ ከዚኽ ምን እንማራለን?
vመጽሐፉን በጥንቃቄ አንብበነው ከኾነ ቃሉ መጣ የሚለው “በነቢዩ በሐጌ እጅ” ነው የሚለው /፩፡፩፣ ፪፡፩፣ ፪፡፲/፡፡ የእግዚአብሔር ቃል የሚመጣው በነቢያት አፍ ነው፤ እዚኽ ግን የተገለጠው በነቢዩ እጅ ነው፡፡ ምን ለማለት ነው? ጄሮም የተባለ የጥንታዊቷ ቤተ ክርስቲያን ሊቅ እንዲኽ ይላል፡- “እጆቻችንን ለመልካም ሥራ ስናነሣ ክርስቶስም በኹለንተናችን ላይ ይነግሣል፤ ዲያብሎስን ከእኛ ያርቅልናል፡፡ እጅ ሲባል መልካም ሥራን የሚያመለክት ነው፡፡ … እግዚአብሔር ወደ ሕይወታችን የሚመጣው ስለ ተናገርን አይደለም፤ መልካም ሥራን ስንሠራ እንጂ፡፡”
vአይሁድ ቤተ መቅደሱን ላለመሥራት ሲያመካኙ የነበረው “ኢኮነ ጊዜሁ - ጊዜው ገና ነው” በማለት ነበር፡፡ ተወዳጆች ሆይ! ብዙዎቻችን በዚኽ መንፈስ የተያዝንበት ዘመን ቢኖር አኹን፡፡ “ጊዜው ገና ነው፤ ቤተ መቅደሱን የምሠራበት ጊዜ አይደለም፤ ገና ወጣት ስለኾንኩ አኹን ወደ እግዚአብሔር የምቀርበብበት ዘመን አይደለም” እያልን እናመካኛለንና፡፡ ነገ በሕይወት ለመኖራችን ግን እርግጠኞች አይደለንም፡፡ እንኪያስ ሰባኪው እንዳለው የጭንቅ ቀን ሳይመጣ፣ በጕብዝናችን ወራት፣ አፈርም (ሥጋችን) ወደ ነበረበት ምድር ሳይመለስ ፈጣሪያችንን እናስብ እንጂ በማመካኘት ጊዜአችንን አናጥፋ /መክ.፲፪፡፩፣፯/፡፡     
vበተራራው ስብከቱ ላይ ጌታ፡- “አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፤ ይኽም ኹሉ ይጨመርላችኋል” እንዳለን /ማቴ.፮፡፴፫/ በሕይወታችን ላይ እግዚአብሔር የማናስቀድም ከኾነ ግን ብዙ ብንዘራም የምናስገባው ጥቂት ነው፤ ብንበላም አንጠግብም፤ ብንጠጣም አንረካም፤ ብንለብስም አይሞቀንም፤ ደመወዛችንን ብንቀበልም በቀዳዳ ኪስ እንደማስቀመጥ ነው /ሐጌ.፩፡፮/፡፡ አዝመራውን በእርሻው ሳለ ባየነው ጊዜ ብዙ ቢመስለንም ወደ ቤታችን ሲገባ በረከት የለውም፤ ሰማይ ዝናም ለዘር ጠል ለመከር ይነሣል (ይከለክላል)፤ ምድር የዘራንባትን አታበቅልም፤ የተከልንባትን አታጸድቅም፡፡ በአጭር ቃል በረከት ከእኛ ይርቃል /ሐጌ.፩፡፱-፲፩/፡፡
vበወልድ ውሉድ በክርስቶስ ክርስቲያን ተብለን ተጠርተን ሳለ፣ በጥምቀት ከማይጠፋ ዘር ተቈጥረን ሳለ ምድራዊ ቤትን (ፈቃደ ሥጋን) ለመሥራት አማናዊው መቅደሳችንን (ፈቃደ ነፍሳችንን) የምንረሳ ከኾነ በዚኽ ምድር ከእኛ የባሰ ጐስቋላ ሰው የለም /ሐጌ.፩፡፲-፲፩/፡፡
vቤተ መቅደሱን (ፈቃደ ነፍሳችንን) የምንሠራ ከኾነ ግን እግዚአብሔር በረድኤቱ ከእኛ ጋር ይኾናል፤ ጸጋ መንፈስ ቅዱስ በእኛ ላይ ትበዛለች፡፡ “ቤተ እግዚአብሔርን ከሠራችሁበት ቀን ዠምሮ እኽሉን ወይኑን በአውድማ ትርፍርፍ ብሎ ታዩታላችሁ፤ በለሱን ሮማኑን ዘይቱን የሚያፈራውን እንጨት ኹሉ ከዛሬ ዠምሮ አበረክታለኹ” ሲል ይኽን ያመለክታል /ሐጌ.፪፡፳/፡፡

ይኽን እንድናደርግ ሰውን በመውደዱ ሰው የኾነው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይርዳን አሜን!!!

No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount