Thursday, May 8, 2014

የቀኝ ዐይን - ድንግል ማርያም

እንኳን ለበዓለ ልደታ ለማርያም ወይም ለግንቦት ልደታ በሰላም አደረሳችሁ፡፡
በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ           
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
አፍጣኒተ ረድኤት ማርያም በጊዜ ምንዳቤ ወአጸባ፤ ለዐይን እምቀራንባ፤ አንቲ ዉእቱ ረዳኢተ ያዕቆብ በቤተ ላባ፤ በኩሉ ኅሊናሃ ወበኩሉ አልባባ፤ዘኢታፈቅረኪ ነፍስ ትሠሮ እምሕዝባ፡፡

የነገረ ማርያም ሊቅ(Marian Doctor)እየተባለ የሚጠራዉ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ እመቤታችንን በብዙ ምሳሌ እየመሰለ፣ እየተረጎመና እያመሰጠረ ብዙ ጊዜ አመስግኗታል፡፡ ምንም እንኳ እኛ የምናዉቀዉ የምስጋና ድርሰቱ ለጸሎት የምንጠቀምበት ዉዳሴ ማርያም ቢሆንም ከትርጓሜና ከስብከቶቹ ዉጪ ከሦስት ሚሊዮን በላይ ስንኝ ያላቸዉ የምስጋና ድርሰቶች(Hymns) መድረሱን ታሪክ ጸሐፊዉ ሶዝመን መዝግቦልናል፡፡ ከነዚህ የምስጋና ድርሰቶቹ መካከልም ‹‹በእንተ ልደት››(On Nativity) እና ‹‹በእንተ ቤተ ክርስቲያን››(On the Church)በተባሉ ትልልቅ ድርሰቶቹም እመቤታችንን ደጋግሞ ያመሰግናታል፡፡
በተጠቀሱት ሁለቱም ድርሰቶቹ ዉስጥ እመቤታችንን ለማመስገን ከተጠቀመባቸዉ ምሳሌዎች ዉስጥ አንዱ ዐይን ነዉ፡፡ ሊቁ ስለ ቤተክርስቲያን በደረሰዉ የምስጋና መዝሙሩ ዉስጥ እንዲህ ይላታል፤ ‹‹ዐይን ጥርት የሚለዉ ከፀሐይ ብርሃን ጋር ተዋሕዶ ከብርታቷ ኃ ይልን ከዉበቷም ነጸብራቅን ሲቀበል ነዉ፤ በዚህ ጊዜ በግለቷ ይሰነገላል፣ያበራል፤ በዉበቷም ያጌጣል፤… ልክ እንደዚሁ ማርያም ዐይን ናት፤ብርሃን (ጌታ) ማደሪያዉን በእርሷ አዘጋጀና መንፈሷን ጽሩይ አደረገ፤አሳቦቿን አጠራ፣ኅሊናዋንም ንጹሕ አደረገ፤የድንግልናዋንም ክብር አበራዉ ››/Hymns on the Church, 36, 1-2/፡፡ ሊቁ በዚሁ ድርሰቱ ዉስጥ ሌላ ቦታ ላይ ደግሞ፤ ‹ለዚህ ዓለም ሁለት ዐይኖች ተሰጡት፤ ማየት ያልተቻላት የግራ ዐይን ሔዋን ስትሆን፣ የምታበራዉ የቀኝ ዐይን ደግሞ (እመቤታችን) ማርያም ናት፡፡በማታየዉ በጨለማዋ ዐይን ምክንያት መላዉ ዓለም ጨለመ፤ ስለዚህም ሰዎች በጨለማ ጥላ ዉስጥ ሆነዉ ሲዳብሱ ያገኙት ሁሉ አምላክ ፣ ሐሰቱም እዉነት መሰላቸዉ፡፡ነገር ግን ዓለም እንደገና በሌላ ዐይኑ ባበራና (ባየና) ሰማያዊዉ ብርሃንም በዚች ዐይን ሰሌዳ ዉስጥ ባንጸባረቀ ጊዜ ሰዎችም ቀድሞ ያገኙትን(ያመለኩትን) የኑሮአቸዉ ዉድቀት(የባሕርያቸዉ መጎስቆል) መሆኑን ተረድተዉ ወደ ማንነታቸዉ ተመለሱ (አንድነታቸዉን አገኙ)›› ይላል /Ibid, 37, 5-7/::
በዚህ መሠረት የእመቤታችን ልደት ዓለም ማየት የጀመረበት ዕለት ነዉ ማለት ነዉ፡፡ በርግጥም በነገረ ማርያም መጽሐፋችን ላይ እንደተገለጸዉ እመቤታችን በቴክታና በጥሪቃ(ሰባተኛ ቅድመ አያቶቿ) በታየዉ ሕልም መሠርት ዓለምን ሰፍኖበት ከነበረዉ ድቅድቅ የኃጢኣት ጨለማ እፎይታ የሰጠችዉ ጨረቃ እርሷ ናት፡፡ በጨለማ ሲያዩት የሚያስፈራዉና ሌላ ሌላ የሚመስለዉ ጉቶዉ፣ ቁጥቐጦዉ ፣ ድንጋዩ ፣ ጉብታዉ….ሁሉ ተራ ነገር መሆኑ የተጋለጠባት፤ ሰዎችም የሰገዱለት ሁሉ አምላክና ጌታ መሆኑ ቀርቶ ድንጋይ ጉብታ መሆኑን ማየት የጀመሩባት፣ ከደገኛዉ ፀሐይ ክርስቶስ መዉጣታ በፊት ከረጂሙ ዘመን ጨለማ ጭንቀት የተገላገልንባት ጨረቃ፣ ብርሂት የቀኝ ዐይን እመቤታችን ማርያም ናት፡፡ ስለዚህም ልደቷን የጨለማችን መገፈፍ፣ የዐይናችን ማየት፣ የብርሃናችንም መዉጣት ነዉና በፍጹም ደስታ እናስበዋለን፤ እናከብረዋለንም፡፡
ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬምን የምናስታዉሰዉም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ብዙ በማመስገኑ ብቻ ሳይሆን ግሩም አደርጎ በማመስጠሩና እንዲህ ያለ ልዩ ልዩ ነገር በማምጣቱም ጭምር ነዉ፡፡ ለነገሩ ሰዉ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ከሆነ በኋላ ይህን ሁሉ ማድረጉ አያስደንቅም፡፡ የሆነዉ ሆኖ የእርሱን ያህል በልዩ ልዩ ሕብረ-አምሳል ያመሰገናት ያለ አይመስልም፡፡ሊቁ በልደት ድርሰቱም‹‹እናትህ አስደናቂ ናት፤ ጌታ ወደ እርሷ ገባና አገልጋይ ሆነ፤ እየተናገረ ገብቶ በእርሷ ዉስጥ ግን ዝም አለ፤ ወደ እርሷ በነጎድጓድ ድምፅ ገብቶ በእርሷ ዉስጥ ጸጥታን አሳደገ፤ የዓለሙ እረኛ ገብቶ በግ ሆኖ ተወለደ፤ እንደ በግም ‹ባ› እያለ ተገለጠ ››/On Nativity, 11, 6/ እያለ አስደናቂነቷን እየደጋገመ ይናገርላታል፡፡አንድ ብቻ ጨምሬ ወደ በዓሉ ልመለስ፡፡ቅዱሱ ሊቅ ጌታን እንዲህ ይለዋል፤ ‹‹አንተና እናትህ ብቻ ተወዳዳሪ የሌላችሁ ዉቦች ናችሁ፤ በአንተ ላይ ምንም ምን ትንታ(mark) በእናትህም ላይ እንከን(stain) የለም››/Carmina Nisibena, 27,8/፡፡ምንኛ ግሩም ምስጋና፣ እንዴትስ ያለ ፍቅር፣ እነደምንስ ያለ መረዳት ነዉ? መብቃት ነዋ! መብቃት! ከሌላ ከምን ይገኛል? እርሱ ካልገለጸ፡፡
ከቅዱስ ኤፍሬም ሌሎች ድርሰቶች የተነሳሁትና ርእሴንም በእርሱ ምስጋና ያደረገሁት እንዲሁ አይደለም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ዉዳሴ ማርያም እየተጣጣለና ድርሰቱም የእርሱ ሳይሆን የኢትዮጵያዉያን ነዉ (ምነዉ በሆነና ነበር) ፤ ወይም ደግሞ እርሱ ስለ ሌላ የደረሰዉን የእኛ ሰዎች የማርያም ምስጋና ነዉ ብለዉ ነዉ እንጂ እርሱስ እንዲህ አይልም መባል ስለተጀመረ እረሱ ስለ እርሷ ከደረሰዉ ወደ ግእዝ የተተረጎመዉ ትንሽ መሆኑንና ከላይ ለምሳሌነት ካቀርብኳቸዉ በላይ በዉዳሴ ማርያም ምን አዲስ ነገር አለ ለማለት ነዉ፡፡ ይህችን ታህል ጥቆማ ከሰጠሁ ቦታዉም ጊዜዉም የጽሑፉም ዓላማ በዚህ ጉዳይ ላይ መከራከር አይደለምና ወደ እናታችን በዓለ ልደት በረከት ላምራ፡፡
በርግጥም ፍጹም ልዩ
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በማይጠረጠር መልኩ ከፍጥረት ሁሉ ልዩ ናት፡፡ በድንድልና ላይ እናትነት፣ በክብረ ድንግልና ላይ ክብረ ወሊድ፣ በድንጋሌ ሥጋ ላይ ድንጋሌ ነፍስና ድንጋሌ ኅሊና የተሰጣት ከእርሷ በቀር ማንም የለም፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፤ ምንም እንኳ ‹‹በልቧ ትጠብቀዉ ነበር››/ለቃ.2፣51/ ተብሎ እንደተጻፈዉ አትናገረዉ እንጂ ከፍጥረት ወገን እንደ እመቤታችን እርሱን ለማወቅ የተቻለዉ ፍጥረት የለም፡፡ ሊቁ ኦሪገን በሉቃስ ወንጌል ትርጓሜዉ ላይ እንደገለጸዉ ስለ አምላክ ፍጥረት ሊያዉቀዉ የሚቻለዉ የመጨረሻዉ የእዉቀት ደረጃ ላይ የደረሰችዉ እመቤታችን ብቻ ናት፡፡ እንደ እርሱ ትርጓሜ እመቤታችን ፍጡር ለፈጣሪዉ ክብር ሊጨምርለት እንደማይቻለዉ እያወቀች ‹‹ተዐብዮ ነፍስየ ለእግዚአብሔር - ነፍሴ እግዚአብሔርን ታከብረዋለች›› ያለችዉ ፍጡር ሊረዳዉ የሚቻለዉ የመጨረሻዉ ደረጃ ላይ ደርሳ በዚያ መጠን ማመሰገኗን ስትገልጽልን ነዉ ይላል፡፡በርግጥም በዚህ መጠን ከርሷ በላይ ሊደርስ የሚቻለዉ እንዴት ሊኖር ይችላል? ይህ የሚያመለክተዉም ገና በምድር ሳለች ለፍጥረት የሚገባዉ ለዚህ የመጨረሻ ብቃት ከደረሰች ከዚህ ዓለም ከሔደች በኋላማ ይልቁንም እንዴት ያለዉን የተወደደዉንና ከፍጥረት ሁሉ የላቀዉን ምስጋና ታቀርብልን ይሆን? ምን ጥርጥር አለዉ? ልዩ የሆነዉን ልታቀርብ የሚቻላት ልዩ እናት፡፡
ለዚህም የበቃችዉ ራሷን ለሰዉ በሚቻለዉ ከፍተኛዉ መጠን እንደምትጠብቅ አስቀድሞ የሚያዉቅ ፈጣሪ እርሱም ደግሞ ጠበቃትና ከፍጥረት ወገን ልዩ ሆነች፡፡ ቀድም ብለን የተመለከትናቸዉ የቅዱስ ኤፍሬም ጥቅሶች የሚያረጋግጡልንም ይህንኑ ነዉ፡፡ ብርሂት የሆነች ዐይን ለሰዉነት መብራት የምትሆነዉ የፀሐይ ብርሃን ሲዋሐዳት እንደሆነዉ ሁሉ እርሷም በራሷ ብርሃነ ዐይን ንጽሐ ሥጋ ወኅሊና ላይ የብርሃን ጌታ ብርሃን የተባለ ጸጋዉን አሳድሮ ንጽሕናዋን ወደር የለሺ አደረገዉ፡፡ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ርብቃ ለይስሐቅ የታጨችበትን የሚናገረዉ አንቀጽ ላይ ‹‹ብላቴናይቱም መልክዋ እጅግ ያማረ፥ ወንድ የማያውቃት ድንግልም ነበረች››/ዘፍ. 24፣16/ የሚለዉን ሲተረጉም ‹ወንድ የማያዉቃት› የሚለዉን ለሥጋ ድንግልናዋ ከሰጠ በኋላ ‹ድንግልም ነበረች› ያለዉ ደግሞ ለመደጋገም ሳይሆን በኅሊናዋም ያልባከነች የተጠበቀች ነበረች ሲል ነዉ ይላል፡፡ ይሁን እንጂ እንደዚህ ያለችዉ ድንግል ርብቃ ድንገት(ለርሷ) ያገኘችዉና ማንነቱን እንኳ በዉል የማታዉቀዉ ሽማግሌ (የአብርሃም መልክተኛ) ቤተሰቦቿን በጠየቀዉ መሰረት ወላጆቿ ጠርተዉ ‹‹ከዚህ ሰው ጋር ትሄጃለሽን?›› ብለዉ በጠየቐት ጊዜ ሳታንገራግር ‹‹እሔዳለሁ›› አለች፤ መሰስ ብላም ተከተለችዉ፡፡/ዘፍ 24፣58/ እመቤታችን ግን የከበረ መልአክ ተገለጾ ሲያነጋግራት እንኳ የልቡናዋ በር ለወሊድ አልተንኳኳም፡፡ ለልማዱ ሴት ልጅ ‹‹ትጸንሻለሺ፣ ትወልጂያለሺ›› ቢሏት ምንም ብትመንን መልአክ ተግልጾ ከነገራት ‹‹ይህ እንዴት ይሆናል?›› ልትል አትችልም፤ እንዴት እንደሚሆንማ ጠንቅቃ ታዉቃለችና፡፡ እመቤታችን ከነዚህ ሁሉ ልዩ ስለሆነች ‹‹እፎኑ ይከዉነኒ ዝንቱ›› ስትል ፈጽሞ በታተመና እርሱን በሚያልፍ ኅሊና መልአኩን አስጨነቀችዉ፡፡ እርሱም‹‹ለእግዚአብሔር የሚሳነዉ ነገር የለም›› የምትል ጥቅስ አግኝቶ ፈተናዉን ተገላገለ፡፡ ሌላዉ ቀርቶ በዚህ ጥቅስ ተረትታ ብሥራቱን ስትቀበልም ‹‹ይኩነኒ በከመ ትቤለኒ- እንዳልከዉ ይሁንልኝ›› ያለች አንተ እንዳልከዉ የአምላኬ ፈቃዱ ሆኖ እንበለ ዘርዕ፣ እንበለ ሩካቤ ከሆነና ተጸንሶ የሚወለደዉም እርሱ ከሆነ ይሁን ይደረግ አለቺ እንጂ ለሌላዉ ነገርማ ኅሊናዋ እንደታተመ ነዉ የቀረዉ፡፡‹‹ ልጄ ሆይ ስሚ፣ እዪ ጆሮሺንም አዘንብዪ፤ ወገንሺን የአባትሺንም ቤት እርሺ፣ ንጉሥ ዉበትሺን ወድዶአልና፤ እርሱ ጌታሺ ነዉና›› (መዝ 44÷12) ሲል አባቷ ዳዊት በትንቢት እንደተናገረዉ እርሷ ከሔዋናዊ ጠባይ ተለይታለችና፡፡ ሰሎሞንም‹‹ወዳጄ ሆይ ሁለንተናሺ ዉብ ነዉ ፤ ነዉርም የለብሺም፤ ልቤን በፍቅር አሳበድሺዉ….›› ያለዉ ለዚህ ነበር፡፡
ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ ‹‹የታተመች ደብዳቤ›› ያላትም ለዚህ ነዉ/ኢሳ 28 ፤ 12/፡፡ ምክንያቱም ለልማዱ ደብዳቤ ከተጻፈ በኋላ ይታሸጋል፡፡ ስለ እርሷ የተነገረዉ ግን ከታተመ ወይም ከታሸገ በኋለ ተጻፈበት የሚል ነዉ፡፡ አብ በድንግልና አትሞ ሲያበቃ በዉስጧ አካላዊ ቃልን የጻፈባት ማንበብ የሚችሉም(እሥራኤል) ማንበብ የማይችሉም(አሕዛብ) እናነበዉ ዘንድ አንችልም ታትሟልና (በድንግልና በንጽሕና በክብር በምስጢር) አሉ ብሎ የተናገረላት ደብዳቤ እርሷ ናትና፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ጸጋ ለተሰጣቸዉ ሰዎች ብሥራት ሊያደርስ ሲመጣ ይህ የመጀመሪያዉ አልነበረም፤ ይሁን እንጂ ለዳንኤልም ሆነ ለጻድቁ ካህን ለዘካርያስ ለእርሷ እንዳደረገዉ ለእነርሱ መች አደረገ? እነርሱ እጅ ነሱት ሰገዱለት እንጂ እርሱ መቼ እጅ ነሳ ሰገደላቸዉ? ከዚህ በላይ ልዩ መሆን በእዉነት ወዴት ይገኛል፡፡
ፍጹም ልዩ መሆኗን ለማስረገጥ ያህል አንድ ነገር ብቻ ላክል፡፡ የጥንቶቹ የቤተክርስቲያን ሊቃዉንት ጌታ ለሐዋርያት ቤተ ክርስቲያንን ይጠብቛት ዘንድ የሰጠዉ ሁለት ጊዜ ነዉ ይላሉ፡፡ አንደኛዉ ብዙ ጊዜ ሲጠቀስ የምንሰማዉ ለቅዱስ ጴጥሮስ የተሰጠዉ ነዉ፡፡ይህም ‹‹በጎቼን አሰማራ፣ ጠቦቶቼን ጠብቅ እና ግልገሎቼን አሰማራ››/ዮሐ 21፣15-17/የሚለዉ ነዉ፡፡ ሁለተኛዉ ደግሞ ከዚህ ቀደም ብሎ በመስቀል ላይ የሰጠዉ ነዉ፤ በመስቀል ላይ ጌታ ለዮሐንስ ‹‹እነኋት እናትህ›› ሲል የሰጠዉ እርሷን ብቻ ሳይሆን ቤተ ክርስቲያንንም ነዉ ይላሉ፡፡ በነዚህ ሊቃዉንት ትርጓሜ መሠርት ሁለቱም ራሳቸዉን የቻሉ ምስጢራትን ይዘዋል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ሕጋዊ ስለነበር(በጋብቻ የተወሰነ ማለት ነዉ) የተሰጠዉም አደራ ይህንኑ የሚመለከትና በጎቹን እስከ ገላግልቶቻቸዉ(ምእመናን) የሚመለከት ነዉ፡፡ጌታ በወንጌል ‹‹በጎቼ ድምጼን ይለያሉ›› እንዳለዉ እነዚህ ድምጽ እንጂ ቃል መለየት የማይቻላቸዉ ምእመናን ናቸዉ፡፡ የቅዱስ ዮሐንስ ግን ከዚህ ሁሉ በእጅጉ ይለያል፡፡ምክንያቱም እመቤታችን ራሷ የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ብቻ ሳትሆን የፍጹማን ደናግልም ምሳሌ ናት፡፡ ስለዚህ ከደምጽ ያለፈ ቃላትን ምስጢራትን መለየት የሚቻላቸዉ ፍጹማንን የሚመለከተዉ አደራ የተሰጠዉ ለበቃዉ ብቻ ሳይሆን ለፍጹሙ ድንግል ለዮሐንስ ነዉ፡፡ ስለዚህ እመቤታችንን መግፋት ቤተክርስቲያንን መግፋት ነዉ፡፡ እርሷንም መቀበል የሚቻለዉ ዮሐንስን የመሰለ ንጹሕ ድንግል ነዉ፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስ እንደሚለዉ ጌታ የሰጠዉ ድንግሊቱን ለድንግል፣ ድንግሉንም ለድንግል፤ ንጹሕንም ለንጹሕ ነዉ፡፡ መላእክት ሲጠብቐት ከኖሩ በኋላ መልአክ ለመሰለ ሰዉ ሰጣት እንጂ ለሌላ አልተሰጠችም፤ ሊቀበላት የሚቻለዉም የለም፡፡በተለይ ኦሪገን ይህንኑ በተረጎመበት አንቀጹ ስለ ቅዱሱ ብቃት ሲናገር ለእርሷም ‹‹እነሆ ልጅሽ›› አላት እንጂ ‹‹ልጅ ይሁንሽ›› አላላትም፤ ምክንያቱም ዮሐንስ በዚያ የመከራና የጭንቀት የፍርሃት ቀን በዕለተ ስቅለት ሳያፈራ ሳይሰቀቅ በእግረ መስቀሉ የተገኘዉ ቅዱስ ጳዉሎስ ‹‹እኔም አሁን ሕያዉ ሆኜ አልኖርም፤ ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል›› /ገላ 2፣20/ እንዳለዉ ዮሐንስ ራሱን ክዶ ስለነበር ለራሱ እየኖረ አይደለምና በእርሱ የሚኖረዉ ጌታ ነዉ፡፡ ‹‹አነሆ ልጅሽ›› ያላትም በእርሱ አድሬ ያለሁት እኔ ነኝ ማለቱ ስለሆነ ከእርሷ ሰዉ ከሆነ በኋላ ለማንም አልሰጣትም፤ በዮሐንስ አድሮ የተቀበላትም ራሱ ነዉ፤ ከዚያ በኋላ እርሷን ሊቀበል የሚቻለዉ የለምና ይላል፡፡ ስለዚህ አንድ ሰዉ እንኳንስ የእርሷን ነገር ለመንቀፍ ቀርቶ ለማመስገንም ትሰጠዉ ዘንድ ከፈለገ እንደ ዮሐንስ ራሱን በንጽሕና ይጠብቅ ፣ራሱንም ፈጽሞ ይካድ ባይ ነዉ፡፡
የአሁኖቹ ሰዎች እርሷን ባይቀበሉ፣ በእርሷ አማላጅነት ባያምኑ ለምን እንደነቃለን? እነዚህ በትንሽ ነገር እንኳ መታመን የማይቻላቸዉ የእርሷን ነገር ይረዱ ዘንድ ታላቁንና ሰማያዊዉን ምስጢር ማን አደራ ሊሰጣቸዉ ይችላል? አንዳንድ የዋኃን ደግሞ መሠርይ ተሐድሶዎች ስለ እርሷ የዘመሯቸዉን መዝሙር ተብየ ዘፈኖች እየተመለከቱ የታለላሉ፡፡ ይህ መናፍቃኑ ስለ እርሷ የሚሉትን መንገድ የተከተለ በእነርሱ ወዝ የታሸ ስለሆነ ተወዳጅ መሥዋዕት አይደለም፡፡ በኦሪት አንበሳዉ፣ ተኩላዉ፣ ቀበሮዉ፣ … የመሳሰለዉ አዉሬ የገደለዉን ሁሉ እንኳን ለመሥዋዕት ልናቀርበዉ ቀርቶ ልንበላዉም የተከለከለ ነዉ፡፡ ይህም ማለት በመጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀሱት አዉሬዎች የተባሉት (አጋንንት፣ ርኩሳን መናፍስት፣ መናፍቃን፣…. ደሙን ያፈሰሱትን ወይም በእነርሱ) የተሰዋዉን ሁሉ እንኳን ለእግዚኣብሔር ማቅረብ ለእኛም መንካት መርከስ ነዉ ማለት ነዉ፡፡ ‹አወሬ የቧጨረዉንም አትንካ› የሚል ንባብም ይገኛል፤ ይህ ሁሉ ከእነርሱ የተነካካዉን በዚህ ዓለም የዘፈንና የረከሰ መንፈስ የጎሰቆለዉን ምንም ለዐይንህ ቢያምርህ (በዘፈን ላደገ ሁሉ የእነርሱ የሚያምረዉ መሆኑ አይጠረጠርም) ፈጽመህ አትንካ ተብለን ታዘናልና መልከስከስ አስፈላጊ አይደለም፡፡ ግጥሙ በኑፋቄ ዜማዉ በዘፈን ርኩሰት የተቧጨረ ርኩስ ነዉና፡፡እርሷ ቤተ ክርስቲያን ናት፤ የቤተክርስቲያናችንም ስጦታ ስለሆነች በእዉነት ልዩ ናትና ይህን በመሰለ መልኩ የተቧጨረዉን አናቀርብም፡፡
እንግዲህ ዛሬ ተወለደች የምንለዉ ይህችን ልዩ ድንግል ነዉ፡፡ስለዚህም የእርሷን በዓለ ልደት ማክበር ከዚህ ሁሉ በረከት መሳተፍ ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔር በእርሷ በኩል ለባሕርያችን ያደረገዉንም ክብር ማወቅና መቀበል ጭምር ነዉ፡፡
ከበዓሉ ምን እናገኛለን? የእርሷስ በዓል አልበዛምን?
አንዳንድ ሰዎች በእኛ ቤተክርስቲያን የጌታ በዓል አንሶ የእመቤታችን የበለጠ፤ እኛም ከርሱ ይልቃ ለርሷ የምናደላ የሚመስላቸዉ ቁጥራቸዉ በርከት ማለት ጀምሯል፡፡ ያለማወቅ ነዉና አይፈረድባቸዉም፡፡ ለነቀፋም የተሰለፉ ስለሆነ በ‹ምሰለ ፍቁር ወልዳ-ከተወደደዉ ልጇ ጋራ› በምንለዉ ሥዕል ዉስጥ እንኳ በሥዕሉ መጠን እየመሰላቸዉ ጌታ ያነሰ የሚመስላቸዉ ማስተዋል የራቃቸዉ ስለሆኑ በእነርሱ አንገረምም፡፡በቤተ ክርስቲያናችን ከመስከረም ፳፮ እስከ ኅዳር ፮ ድረስ ከእናቱ ጋር መስደዱን፣ ከኅዳር ፲፬ ጀምሮ እስከ ልደቱ ይወርዳል ይወለዳል ሲሉ ትንቢት የተናገሩ የነቢያትን ጾም እየጾምን እርሱን እናስባለን፡፡ ከልደት እስከ ዐቢይ ጾም ድረስም በሥጋዌ፤ በአንድነት በሦስትነት መገለጡ አስተርእዮ እየተባለ ይታሰባል ይሰበካል፡፡ ከዚያም ዐቢይ ጾም ይገባል፤ ሁለንተናችን እርሱን በማሰብ ይሰበሰባል፤ ቃለ እግዚአበሔሩም ይህንኑ ያዘክራል፡፡ በትንሣኤዉም ሃምሳ ቀናትን እንደ አንድ ቀን እንደ ዕለተ ትንሣኤዉ በመቁጠር ትንሣኤዉን እንሰብካለን፡፡ ከዚህ በማሰከተልም ርዕደተ መንፍስቅዱስን በዓለ ጰራቅሊጦስን በጾም እናከብራለን፡፡በየወሩም በዓለ እግዚእ፣ መድኃኔዓለም፣ ኢየሱስ፣ አማኑኤል…. እያልን ከዘጠኙ ዓበይትና ከዘጠኙ ንዑሳን በዓላት በተጨማሪ በየአጥቢያቸዉ የሚታሰቡት ትዝ አይሏቸዉም፡፡ ሌላዉ ቀርቶ በየሳምንቱ ሁለት ቀናትን (ረቡዕ እና አርብ) በጾም ሁለት ቀናትን (ቀዳሚትንና እሑድን) በበዓል ለክርስቶስ መታሰቢያ የሰጠች ብቸኛ ቤተ ክርስቲያን የእኛይቱ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ብቻ መሆኗን አያስተዉሉም፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ ሳለ የማርያም በዓል ከጌታ በዓል ይበልጣል ማለትን ምን ዓይነት አለማስተዋል ልንለዉ እንችላለን? ቢሆንስ በቅዱሳን በዓል ዋናዉ ተከባሪ ተመሰጋኝ ማን ሆነና ነዉ ይሄ ሁሉ ጩኸት? ስለዚህ በዚህም ስም አደረግነዉ በዚያ እግዚአብሔር በአከበራቸዉ ቅዱሳን ስም እስካደረግነዉ ድረስ በዓሉ ሁሉ የእግዚአብሔር ነዉ፡፡
የእመቤታችን በዓለ ልደትም በዚሁ መንፈስ የሚከበር በዓል ነዉ፡፡ነቢዩ ኢሳይያስ ቀደም ብሎ ‹‹ትወጽእ በትር እምሥርወ እሴይ-ከእሴይ ሥር ወይም ግንድ በትር ትወጣለች››/ኢሳ 11፤6/ ብሎ ስለ ልደቷም ተናግሮላታል፡፡ ይህንንም ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም በዉዳሴ ማርያም ዘቀዳሚት ድርሰቱ፤ ‹‹ በትረ ሃይማኖት ዘኢትጸንን ምስመኮሙ ለቅዱሳን-የቅዱሳን መደገፊያቸዉ ግያዝ የሱነማዊቷን ልጅ ከሞት ያስነሣባት ዘንድ ከነቢዩ ከኤልሳ ተቀብሎ እየተጠራጠረ እንደወሰዳት ያይደለሺ ጽነት ጥርጣሬ የሌለብሽ የሃይማኖት በትር አንቺ ነሽ›› ብሎ ተርጎሞልናል፡፡ አባ ጀሮምም ይህን የነቢዩን ትንቢት በትር ከግንዱ ላይ ተስተካክሎ የሚወጣ ግዳጂ ለመፈጸም የሚፈልግ ስለሆን የእመቤታችን ልዩ መሆን ያሳያል ይላል፡፡ በርግጥም ሊቃዉንቱ እንዳሉት ለቅዱሳን መደገፊያ ለአጋንንት ለመናፍቃን ደግሞ ማባረሪያ የሆነች በትር፤ ድንግል ማርያም፡፡ስለዚህ የእርሷን በዓል ማክበር ከዚህ ጥርጣሬ ከሌለዉ በረከት መሳተፍ ነዉ፡፡ ይሁን እንጂ በአጠቃላይ የበዓላት ይልቁንም በክርስትና ጥቅማቸዉ ምንድን ነዉ የሚለዉን እንመልከትና እንፈጽም፡፡
በዓላትን በብዛት እንድናከብር ያዘዘን እግዚአብሔር ነዉ፡፡የምናከብራቸዉም ዝም ብለን አይደለም፡፡በተለይም በብሉይ ኪዳን በዓላት ብዙ የመሥዋዕት እንስሳትን ማቅረብና መሠዋት በጥብቅ የሚፈጸም ተእዛዝ ነበረ፡፡ የዚያ ሁሉ መሥዋዕትም ዓላማ ሥርየተ ኃጢኣትን ማስገኘት ነበር፡፡/ዘሌ ፲፯፣፲፩/ በአጭሩ በዓላቱን የማክበሩ ዓላማ ሥርየተ ኃጢኣትን ማሰገኘት ነዉ ማለት ነዉ፡፡በዚህ መሠረታዊ ምክንያት በእያንዳንዱ የኦሪት በዓል እጅግ ብዙ የመሥዋዕት እንስሳት ይቀርቡ ነበር፡፡በኦሪት በየዕለቱ ሁለት ሁለት ጠቦቶች፣ በየሰንበቱ ሁለት ተጨማሪ የበግ ጠቦቶች፣በየመባቻዉ ደግሞ ለየዕለቱ ከሚቀርበዉ በተጨማሪ ሁለት ወይፈኖች፣ አንድ አዉራ በግ፣ ሰባት የአንድ ዓመት የበግ ጠቦቶች፣ አንድ ፍየል ይቀርብ ነበር፡፡ የዓመታዊ በዓላት ደግሞ ከዚህ ሁሉ ይለያል፡፡ለምሳሌ የዳስ በዓሉን ብቻ ብንመለከት ከዕለቱ፣ ከሰንበቱና ከመባቻዉ እንዲሁም በፈቃድ ከሚቀርቡት በተጨማሪ 73 ወይፈኖች፣ 136 አዉራ በጎችና ጠቦቶች፣ 10 አዉራ ፍየሎች ይቀርቡ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ግን የእህሉን ቁርባንና ሌላዉን መሥዋዕት(ለኃጢኣት ፣ ለበደል፣….የሚባሉትን) ሳይጨምር ነዉ/ዘጸ ፳፱፣፴፰፣ ዘሌ ፳፬፣፭-፱፣ ዘኁ ፳፰፣፱-፲፭፣ዘኁ ፳፱/፡፡
‹‹ሕጉ ሊመጣ ያለው የበጎ ነገር እውነተኛ አምሳል ሳይሆን የነገር ጥላ አለውና››/ዕብ 10፣1 / ተብሎ እንደተጻፈ እነዚህ ሁሉ ግን ምሳሌዎች ነበሩ፡፡ ሐዋርያዉ ቅዱስ ጳዉሎስ ‹‹ከጊዜው የተነሳ አስተማሪዎች ልትሆኑ ሲገባችሁ፥ አንድ ሰው ስለ እግዚአብሔር ቃላት መጀመሪያ ያለውን የሕፃንነትን ትምህርት እንዲያስተምራችሁ እንደ ገና ያስፈልጋችኋልና፤ የሚያስፈልጋችሁም ወተት ነው እንጂ ጠንካራ ምግብ አይደለም።ወተት የሚጋት ሁሉ ሕፃን ስለ ሆነ የጽድቅን ቃል አያውቅምና፤ጠንካራ ምግብ ግን መልካሙንና ክፉውን ለመለየት በስራቸው የለመደ ልቡና ላላቸው ለፍጹማን ሰዎች ነው።›› /ዕብ 5፣ 12-15/ እንዳለዉ ሊቃዉንቱ ለእኛ ወተት ወተቱን እየመገቡ ጠንካራዉን ምግብ አላቀረቡልንም ነበር፡፡ አሁን ግን እስኪ ይህን እንኳ እንሞክረዉ፡፡
በኦሪት እንደተጻፈዉ በፋሲካ የሚሠዋዉ ልዩ የደኅንነት መሥዋዕት በግ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነዉ፡፡‹‹በነገው ደግሞ ዮሐንስ ከደቀ መዛሙርቱም ሁለት ቆመው ነበር፥ኢየሱስም ሲሄድ ተመልክቶ። እነሆ የእግዚአብሔር በግ አለ›› /ዮሐ 1፣ 26/።ተብሎ ተጽፎአልና፡፡በሌሎቹ በዓላት የምናቀርባቸዉ ደግሞ ቀደም ብለን እንዳየነዉ ወይፈኑ፣ አዉራበጉ፣ ፍየሎቹ(ወንድም ሴትም ነዉ የሚቀርበዉ)፣ ሌላዉ ሁሉ የማን ምሳሌ ነዉ ማለታችን አይቀርም፡፡ ይህ ሁሉ የበዓል መሥዋዕት የቅዱሳን ምሳሌ ነዉ፡፡ ‹‹እንደ በጎች ሊበሉን ሰጠኸን፥ ወደ አሕዛብም በተንኸን›› /መዝ 44፣12/ ተብሎ ትንቢትም ተነግሮላቸዋልና።ጌታም በወንጌል ‹‹ስለዚህ፥ እነሆ፥ ነቢያትንና ጥበበኞችን ጻፎችንም ወደ እናንተ እልካለሁ፤ ከእነርሱም ትገድላላችሁ ትሰቅሉማላችሁ፥ ከእነርሱም በምኵራባችሁ ትገርፋላችሁ ከከተማም ወደ ከተማ ታሳድዳላችሁ፤ከጻድቁ ከአቤል ደም ጀምሮ በቤተ መቅደስና በመሠዊያው መካከል እስከ ገደላችሁት እስከ በራክዩ ልጅ እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ በምድር ላይ የፈሰሰው የጻድቅ ደም ሁሉ ይደርስባችሁ ዘንድ።እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ በዚህ ትውልድ ላይ ይደርሳል›› /ማቴ 23፣35/ ሲል እንደተናገረዉ ቅዱሳን ለእምነታቸዉ መሥዋዕት ሆነዉ ቀርበዋል።ደማቸዉንም አንዱ እንደ ፍየል፣ ሌላዉ እንደ ወይፈን፣ ሌላዉም እንደ አዉራ በግ አፍስሰዋል፡፡ እነዚህ ሁሉ የመሥዋዕት ዓይነቶች ለተለያየ የኃጢኣት ማስተሥረያ እነደነበሩት እነዚህም ደኅነትን ለመፈጸም ከተሰዋዉ በግ ከጌታ በኋላ ለምናምና ሁሉ ሥርየተ ኃጢኣትን እናገኝ ዘንድ የሚማልዱ ስለኛም ጭምር ደማቸዉን ያፈሰሱ ናቸዉ፡፡ ይሁን እንጂ የሌላዉ ጊዜ የመሥዋዕት እንስሳ የፋሲካዉን በግ ሊተካዉ እንደማይችልና የመሥዋዕቱም ዓይነት ፈጽሞ የተለያየ እንደ ሆነዉ ሁሉ የቅዱሳኑ መሥዋዕትነትና ሰማዕትነትም እንዲሁ የተለያየ መሆኑና የእነርሱም የእርሱን ሊተካ የማይችል መሆኑ ሊዘነጋ አይገባዉም፡፡እርሱ ኃጢኣትህ ተሠረየልህ(ሽ) እያለ ይቅር ሲል እነርሱ ግን የሚያስተሠርዩልን እየጸለዩ ነዉና፡፡ ከዚህ በመለስ ግን የጥንቶቹ ሊቃዉንት እንደተረጎሙልን የእነርሱ ተጋድሎና ሰማዕትነት የእኛ የሐዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች መሥዋዕቶች ናቸዉ፤ ስለእነርሱም ሥርየተ ኃጢኣትን እንቀበላለን፡፡ ሐዋርያዉ ቅዱስ ጳዉሎስም ‹‹በመሥዋዕት እንደሚደረግ፥ የእኔ ሕይወት ይሠዋልና፥ የምሄድበትም ጊዜ ደርሶአል ››/ዕብ 4፣6/ ሲል የተናገረዉ ይህን የሚያረጋግጥልን ነዉ፡፡ ቀደም ብለን እንዳየነዉ የመሥዋዕቱ እንስሳት የበዙት ለእሥራኤል ለኃጢኣታቸዉ አስፈላጊ በመሆኑ እንደሆነዉ ሁሉ በሐዲስ ኪዳን ለምንኖር ለእኛም ብዙ ቅዱሳን መኖራቸዉ ይጠቅመናል፣ ኃጢኣታቸንም ያስተሠረይልናል፡፡ የመሥዋእቱ እንስሳት በሙሉ የተቆጠሩና የታወቁ እንደሆነዉ ሁሉ ቅዱሳኑም ምን ቢበዙም እንዲሁ የታወቁና የተቆጠሩ ናቸዉ፡፡

ዳዊት አባታችን ‹‹ዘይኌልቆሙ ለክዋክብት በምልኦሙ፣ ወይጼዉዖሙ ለኩሎሙ በበአስማቲሆሙ- ክዋክብትን በምልዓት ይቆጥራቸዋል፣ ሁሉንም በየስማቸዉም ይጠራቸዋል››/መዝ 146፣4/ ሲል እንደተናገረዉ ክዋክብት የተባሉ ቅዱሳን ሁሉ በእርሱ ዘንድ በባለሟልነት በቃል ኪዳን የታወቁ በመሥዋዕትነትም የተቆጠሩ ናቸዉ፡፡ ያ ሁሉ የ መሥዋዕት እንስሳ ፣ የጧቱና የሰርኩ፣ የሰንበቱና የመባቻዉ፣ የዓመት በዓላቱ፣ የየግለሰቡ የኃጢኣቱ፣ የበደሉ፣ የመንጻቱ፣…በዓይነት በዓይነት እንደሚታወቅ በእረሱም ዘንድ ተቀባይነት እነዳለዉ ሁሉ የየዕለቱ ቅዱሳንም እንዲሁ ይተወቃሉ፤ ጸሎታቸዉና ምልጃቸዉም በእርሱ ዘንድ የከበረ ነዉ፡፡ እመቤታችን ደግሞ ከነዚህ ሁሉ በግንባር ቀደምነት የምትጠራ ልዩ መሥዋዕታችን ናት፡፡በሁለተኛዉ ክፍለ ዘመን መጨረሻ የነበረዉ የሰረዴሱ መልይጦን/Melito of Sardis/ በፋሲካ መዝሙሩ ላይ እመቤታችንን የመሥዋዕቱን በግ የወለደችልን ንጽሕት ሴት በግ (fair ewe) ይላታል፡፡ ስለዚህ የእመቤታችን በዓለ ልደት ከብሉይ ኪዳን ሰዎች የተሻለ ሥርየተ ኃጢኣት የምናገኝበት ነዉና ከነዚያ በተሻለ በዓላችንን መንፈሳዊ አድርገን እናክብር፤ ከመንፈሳዊ በረከትም እንካፈል፡፡የደራሲዉንም ምስጋናና ምልጃ በመሰለ ምስጋና እንዲህ እንበላት፤‹‹ምንተኑ አዐስየኪ ዕሴተ፤በእንተ ኩሉ ዘገበርኪ ሊተ፤ማርያም ሠናይት ዘታፈቅሪ ምሕረተ፤ሶበሰ ተታአቀቢ ዘዚኣየ ኃጢኣተ፤ እምኢሐየዉኩ አሐተ ሰዓተ›› እያልን ለእርሷ በሚገባ ምስጋና እናመስግናት፡፡ ከዚህ የወጣ ሰዉ በመጀመሪያ እንደተመለከትነዉ ብርሂት ቀኝ ዐይኑን እንደገና እያሳወረ መሆኑን ሊገነዘብ ይገባዋል፡፡ እኛስ ለባሕርያችንን መመኪያ እርሷን የሰጠንን እግዚአብሔርን ‹‹ብርሂት የቀኝ ዐይን ድንግል ማርያምን ›› በዚህ ዕለት የሰጠኸን፣ ከዚህ ዓለም የድንቁርናና የኃጢኣት ጨለማም የገላገልከን ክብር ምስጋና ለአንተ ይሁን፤ አንተ ለመረጥካትና ላከበርካት ለእናትህም ምስጋና ይድረሳት እያልን አፋችንን ሞልተን እናመሰግናለን፡፡ ቀይ ዕንቁ እምነት ገንዘባቸዉ ያልተሰረቀባቸዉ ወይም በአዉሬዉ ዲያብሎስ ያልተቧጨሩት ሁሉ አብረዉን ያመሰግናሉ፡፡ ቀኝ ዐይናችን ሆይ ዛሬም በአንቺ ብርሃን እናያለንና እናመሰግንሻለን፡፡ እንኳን አንቺን አባትሺን አብርሃምን የሚባርኩት እንደሚባረኩ ልጂሽ አስቀድሞ በሙሴ በኩል በኦሪት ነግሮናልና፡፡
ወስብሓት ለእግዚአብሔር፡፡

© ይህ ጽሑፍ በቀጥታ ከዲ/ን ብርሃኑ አድማስ የምጽሐፈ ገጽ አድራሻ የተወሰደ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount