Wednesday, May 28, 2014

ዕርገተ ክርስቶስ

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ግንቦት ፳ ቀን፣ ፳፻፮ ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ከተነሣ በኋላ ዕለቱን ወደ ሰማይ አላረገም፡፡ ወንጌላዊው ሉቃስ እንደሚነግረን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያረገው ከሙታን ተለይቶ ከተነሣ በኋላ በ፵ኛው ቀኑ ላይ ነው፡፡ በእነዚኽ ፵ ቀናት ውስጥም ብዙውን ጊዜ ለደቀ መዛሙርቱ እየተገለጠ ብዙ ምሥጢርና ሥርዓተ ሐዲስ አስተምሯቸዋል፡፡ የተማሩትን ኹሉ እንዲጠብቁ፣ ዓለምን ኹሉ በወንጌል መረብ እንዲያጠምዱ ትእዛዝ ሰጥቷቸዋል፡፡



  ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ከተነሣ በኋላ ዕለቱን ያላረገው ስለ ብዙ ምክንያት ነው፡፡ አንደኛውና ዋነኛው ግን ለደቀ መዛሙርቱ ትንሣኤውን ያረጋግጥላቸው ዘንድ ነው፡፡ ወንጌላዊው ሉቃስ “… ከሕማማቱ በኋላ ሕያው ኾኖ ለእነርሱ ራሱን አሳያቸው” የሚለውም ስለዚኹ ነውና /ሐዋ.፩፡፫/፡፡ የተወለደው፣ መከራ መስቀልን የተቀበለው፣ የሞተው እርሱ የተነሣው ነውና ይኽን ያረጋግጥላቸውና ያሳያቸው ዘንድ ፵ ቀን ቈየ፡፡ አንድም ደቀ መዛሙርቱ በሞቱ ምክንያት ተስፋ ቈርጠው ነበርና ሙስና መቃብር እንዳላገኘው ይልቁንም እንደተናገረው እንደተነሣ ያጽናናቸው ዘንድ ቈየ፡፡ አንድም የትንሣኤ ክብር እንደምን እንደኾነ ያሳያቸው ዘንድ ቈየ፡፡ አንድም ሞት ከእንግዲኽ ወዲኽ አስፈሪነቱ እንደቀረ ያሳያቸው ዘንድ ቈየ፡፡ ወእለ ዘተርፈ…፡፡ በእነዚኽ ፵ ቀናት ሕያው ኾኖ መነሣቱም በመብላት አረጋገጠላቸው፡፡ እንዲዳስሱት በማድረግ አረጋገጠላቸው፡፡
    
እናንተ ግን ከላይ ኃይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ /ሉቃ.፳፬፡፵፱/
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከማረጉ በፊት ለሐዋርያት ካዘዛቸው ትእዛዛት አንዱ፥ አጽናኝ እንዲኹም ከሣቴ ምሥጢር (ምሥጢር ገላጭ) መንፈስ ቅዱስን እስኪለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ እንዲቆዩ ነው፡፡ ይኽ ለምን እንደኾነ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ግብረ ሐዋርያትን በተረጐመበት በቀዳሚው ድርሳኑ ላይ ሲያብራራው፡- “አንድ ወታደር ለጦርነት የሚያስፈልገውን ትጥቅ ሳይታጠቅ ወደ ጦር ሜዳ አይኼድም፡፡ አንዲት ሠረገላም ችሎታ ያለው መሪ ከሌላት በቀር እንዲኹ እንድትኼድ አይደረግም፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ደቀ መዛሙርቱ ኃይለ መንፈስ ቅዱስን ሳይታጠቁ ወደ ዓለም እንዲኼዱ አላደረገም፡፡ ይኸውም ዓለም ድል አድርጋ እንዳታስቀራቸው ነው፡፡
 ይኼ ብቻ አይደለም፤ ዳግመኛም ሐዋርያት ወደ አሕዛብ ከመኼዳቸው በፊት በኢየሩሳሌም ወንጌለ መንግሥት መማር የነበረባቸው ሰዎች ስለነበሩ ነው፡፡ ዳግመኛም ‘ወገኖቻቸውን ሳያስተምሩ ባዕዳንን ያስተምሩ ዘንድ ኼዱ’ ብለው በኋላ የሚነሡ መናፍቃን ምክንያት እንዳያገኙ ነው፡፡… ዳግመኛም ብሉያት ናቸውና ‘እኛ ደካሞች ስንኾን እንደምን ኃያላንን ማሳመን ይቻለናል?’ ‘በቍጥር እጅግ ጥቂቶች ስንኾን እንደምን ዓለምን ኹሉ ወደ አሚነ ክርስቶስ ማምጣት ይቻለናል?’ ‘የንግግር ችሎታ የሌለን ስንኾንስ እንደምን ማስተማር ይቻለናል’ ብለው ፍርሐት እንዳያድርባቸው ፍርሐትን የሚያርቅና አጽናኝ (ብርታትን የሚያድል) መንፈስ ቅዱስን እንዲልክላቸው ስለ ወደደ ነው …” ይላል /Homily on Acts, Hom.1/፡፡


“ዐርገ እግዚአብሔር በይባቤ ወእግዚእነ በቃለ ቀርን”
 የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዕርገት ወደዚኽ ምድር የመጣበትን ዓላማ ጨርሶ ምርኮም ማርኮ ወደ ቀደመ ክብሩ የተመለሰበት ነው፡፡ ምርኮ የተባልነውም እኛው ነን፡፡ ይኽስ እንደምንድነው? ያሉ እንደኾነም፥ በበደልነው በደል ምክንያት ለ፭ ሺሕ ፭፻ ዘመናት በእግረ አጋንንት ስንጠቀጠቀጥ ኖረናል፡፡ ክብር ይግባውና ጌታችን መድኃኔ ዓለም በከበረ ደሙ ቤዛ ሲኾነን ግን ከጥንተ ጠላታችን ግዛት ከዲያብሎስ ማርኮናል፡፡ ወደ ጥንተ ተፈጥሯችን መልሶናል፡፡ ከኃጢአታችን ነጻ አውጥቶናል፡፡ ዳግም ልጆቹ እንባል ዘንድ አድሎናል፡፡ የሠጠን ሥልጣን “ልጅ” መባል ብቻ እንዳልኾነ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሲያስተምርም፡- “ …እርሱም (ከሰማያት ኹሉ በላይ የወጣው ክርስቶስ) አንዳንዶቹ ሐዋርያት ሌሎቹም ነቢያት ሌሎቹም ወንጌል ሰባኪዎች ሌሎችም እረኞችና አስተማሪዎች እንዲኾኑ ሰጠ” ብሏል /ኤፌ.፬፡፲፩-፲፪/፡፡
 ዳግመኛም “ምርኮ” የሚለው ቃል ቅዱስ ጐርጐርዮስ ዘኑሲስ ሲተረጕሞው እንዲኽ ይላል፡- “ከመስቀሉ ወደ ሲዖል በመውረዱ አዳነን፡፡ በአባታቸው በአዳም በደል በሲዖል ተግዘው የነበሩ ጻድቃንን ፈታ፡፡ ከሙታን ተለይቶ አስቀድሞ በተነሣ በእውነተኛ ትንሣኤውም አስነሣን፡፡ የንስሐንም በር ከፈተልን” /ሃይ.አበ.፴፮፡፴/፡፡ ይኸውም ቃል ከቅዱስ ጳውሎስ ጋር የተስማማ ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰማያት ያረገው ከዚኽ ምርኮ በኋላ ነው፡፡ እኛም በዚኽ ቃል ጸንተን የቈየን እንደኾነ፣ ዳግመኛም ወደ ዲያብሎስ ምርኮ ባንመለስ የሐዋርያትና የሌሎች ቅዱሳን ጸጋ እንደማይለየን አረጋግጦልናል፡፡
 የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደቱ፣ ጥምቀቱ፣ ሕማሙ፣ ሞቱ፣ ትንሣኤው፣ ዕርገቱ፣ ወእለ ዘተርፈ ድንገት የመጣ ሳይኾን አስቀድሞ በነቢያት ትንቢት የተነገረ ነው፡፡ መዝሙረኛው ቅዱስ ዳዊት ስለ ጌታችን ዕርገት ሲናገር፡- “ዐርገ እግዚአብሔር በይባቤ ወእግዚእነ በቃለ ቀርን - አምላክ በዕልልታ፣ እግዚአብሔር በመለከት ድምጽ ዓረገ ዘምሩ ለአምላካችን ዘምሩ፤ ዘምሩ ለንጉሣችን ዘምሩ” ያለውም ስለዚኹ ነው /መዝ.፵፮ (፵፯)፥፭)/፡፡
 በዚኽ ኃይለ ቃል እጅግ ብዙ ቁምነገሮችን እንማራለን፡፡ አንደኛ በመለኮታዊ ባሕርዩ “እዚኽ አለ፤ እዚኽ የለም” የማይባለው እግዚአብሔር “ዐረገ” መባሉ በለበሰው ሥጋ መኾኑን ያስረዳል፡፡ ኹለተኛ የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነትን ለሚጠራጠሩ ኹሉ ግሩም የኾነ ትምህርትን የሚሰጥ ነው፡፡
የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዕርገት እንዲኹ የተፈጸመ አልነበረም፡፡ ሊነገር በማይችል አኳኋን ዕፁብ ድንቅ በኾነ የምስጋና ሰልፍ እጅግም በሚያስደነቅ ሰማያዊ ሰልፍ የታጀበ ነበር እንጂ፡፡ ለዚያ ጠላት ዲያብሎስን ገድሎ በድል ሲያርግ የነበረው አምላካቸው፥ ቅዱሳን መላእክት በየነገዳቸው ኾነው በሰልፍ ዘምረዉለታል፤ ሰማያዊ ውዳሴን አቅርበዉለታል፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን መጻሕፍት የነበረውን ኹናቴ እጅግ ሰፋ አድርገው መዝግበዉታልና ከብዙ በጥቂቱ ከረዥሙ በአጭሩ ኹናቴው ምን ይመስል እንደነበር እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
  ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደሚያርግባት ስፍራ ከሰማይ ወደ ምድር ብርሃናዊ ሰዋስው ተዘረጋ፡፡ ጌታም እጆቹን ዘርግቶ ሐዋርያትን ባረካቸው፡፡ እፍ ብሎም ጸጋዉንና ሥልጣንና ሰጣቸው፡፡ በኪሩቤል ላይ የተጫነ ብርሃናዊ ሠረገላም ከሰማይ ወረደ፡፡ ከእርሱም ጋር አእላፋት ወትእልፊተ መላእክት ነበሩ፡፡ ክንፍ ያላቸው ሱራፌልም አብረው ነበሩ፡፡ እጅግ በሚመስጥ ጥዑም ዜማና ብርሃናዊ ቃላትም ኹሉም በየሥርዓቱ ያመሰግኑት ነበር፤ ያወድሱት ነበር፣ ይቀድሱት ነበር፡፡ ከዚኽም ጋር እጅግ ልብን የሚሰርቅ የመለከት ድምጽ በየሥርዓቱ ይሰማ ነበር፡፡ አንዳንዶቹ ብሩክ ውእቱ እግዚአብሔር እምቀዳሚ ወእስከ ለዓለም አሜን” እያሉ ስብሐት ያቀርቡ ነበር፡፡ ከእነርሱ አንዳንዶችም “ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር ጸባዖት ፍጹም ሰማያተ ወምድር ምሉእ እምስብሐቲሁ ፤ ሆሳዕና በአርያም ዘውእቱ ቡሩክ ዘመጽአ ወውእቱ ዘይመጽእ በስመ እግዚአብሔር” እያሉ ያመሰግኑት ነበር፡፡ ዳግመኛም ሌሎች ቡሩክ ስሙ ለእግዚአብሔር እምይእዜ ወእስከ ለዓለመ ዓለም አሜን” ይላሉ፤ ሌሎቹም “ቅዱስ አንተ እግዚአብሔር ቅዱስ አንተ ኃያል፡ ቅዱስ አንተ ሕያው፡ ዘኢይመውት መሐረነ” እያሉ ይቀድሱት ነበር፡፡ ሌሎችም “ስብሐት ለአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለመ ዓለም አሜን” እያሉ ያመሰግኑት ነበር፡፡ 

 ከዚኽ በላይ ያሉት ደግሞ እጅግ ግሩምና ነጐድጓዳዊ በኾነ ድምጽአርኅዉ ኆኃተ መኳንንት፡ ወይትረኃዋ ኆኃት እለ እመፍጥረት ወይባእ ንጉሥ ክብር ወስብሐት” ሲሉ ዠመሩ፡፡ በብርሃናዊው መንጦላዕት ውስጥ የነበሩ ማኅበረ ልዑላን ደግሞ “መኑ ውእቱ ዝንቱ ንጉሠ ክብር ወስብሐት” ብለው ጠየቁ፡፡ የቀደሙትም “ዝንቱ ውእቱ እግዚአብሔር ኃያል ውጽኑዕ” እያሉ መለሱላቸው፡፡ ከዚኽ በኋላ ቃላተ መኳንንት ወሥልጣናት ኃይላት ተሰማ፤ እንዲኽም አሉ፡- “አርኀዉ ኆኃተ መኳንንት ወይትረኃዋ ኆኀት እለ እምፍጥረት ወይባእ ንጉሠ ክብር ስብሐት፡፡” ዳግመኛም ከመናብርትና አጋዕዝት ሌላ ድምጽ ተሰማ፡፡ እንዲኽ ሲል፡- “መኑ ውእቱ ዝንቱ ንጉሠ ክብር ወስብሐት፡፡” ሌሎችም እንዲኽ ሲሉ መለሱላቸው፡- “ዝንቱ ውእቱ ንጉሠ ክብር ዐቢየ እስከ ለዓለመ ዓለመ፡፡” ኹሉም ልብን በሚመስጥ ጥዑም ዜማ ያመሰግኑት ነበር፡፡ ብርሃናዊ ትዕይንትና ጥዑምዕጣን መዓዛም ከያዙት ሙዳይ ይወጣ ነበር፡፡

  እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ለእርሷ ተብሎ በተተከለ ብርሃናዊ ደብተራ (ድንኳን) ነበረች። ሐዋርያቱን ካናገረ በኋላም ወደ እርሷ ኼደ፤ ምድር ተንቀጠቀጠች፡፡ ኹሉም ሰገዱለት፡፡ ጌታ ወደ ሰማያዊ ሠረገላ ወጣ፡፡ ሊቃነ መላእክት ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል በሚመርዋቸው እልፍ አእላፍ ሠራዊተ ሰማይ በኹሉም መዓዘናት በየመልካቸው በየነገዳቸው በየሥርዓታቸው ቆመው ነበር፡፡ ወዮ! በዚኽ ዕለት የታየው ሰማያዊ ሰልፍ የሰው ልጅ ደካማ ቋንቋ ፈጽሞ ሊገልጸው አይችልም፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት ዐርገ እግዚአብሔር በይባቤ ወእግዚእነ በቃለ ቀርን- አምላክ በዕልልታ፡ እግዚአብሔር በመለከት ድምጽ ዐረገ። ዘምሩ ለአምላካችን ዘምሩ” የሚለን ይኽን ግሩም ምሥጢር አይቶ ነው፡፡

የጌታችን ዕርገት ፍጹም የተለየ ነው!!!

 ከጌታችን ዕርገት በፊት ወደ ሰማይ የወጡ፣ የተነጠቁ፣ እንዲኹም የተሰወሩ ብዙ ቅዱሳን እንዳሉ የታወቀ ነው፡፡ የጌታችን ዕርገት ግን ከእነዚኽ ኹሉ የተለየ ነው፡፡ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዕርገት እንደ ኄኖክ በመሰወር፣ እንደ ኤልያስም በእሳት ሠረገላ የተፈጸመ አይደለም፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ እስከ ሦስተኛው ሰማይ እንደተነጠቀው ዓይነትም አይደለም፡፡
 ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲያርግ አጋዥ (አሳራጊ) አላስፈለገውም፡፡ ቅዱሳን ቢያርጉ፣ ቢሰወሩ፣ ቢነጠቁ እግዚአብሔር በሰጣቸው ጸጋ ነው፡፡ ያለ እግዚአብሔር ምንም ማድረግ አይቻላቸውም፡፡ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የጌታችንና የኤልያስን ዕርገት እያነጻጸረ ሲናገር እንዲኽ ይላል፡- “እንዲኽ ድል መንሣት ባለበት የነጋሪት ድምጽ እግዚአብሔር ዐረገ አለ (መዝሙረኛው ዳዊት)፡፡ እርሱ ዐረገ አለ እንጂ መላእክት አሳረጉት አላለም፡፡ በፊቱ መንገድ የሚመራ አልፈለገም፡፡ በዚያው ጐዳና እርሱ ዐረገ እንጂ፡፡ ኤልያስ በዚያ መንገድ እንደ ክርስቶስ እንዲኽ ሊያርግ አልቻለምና፡፡ የኤልያስ ባሕርይ በዚኽ መንገድ ሊያርግ አልቻለም፡፡ መላእክት ወደ ታዘዙበት ቦታ ወሰዱት እንጂ፡፡ አንድ አካል አንድ ባሕርይ የሚኾን የእግዚአብሔር ቃል ግን መላእክትን የፈጠረ ነውና በሥልጣኑ ዐረገ፡፡ ስለዚኽም ወንጌላዊው ሉቃስ የሐዋርያትን ሥራ በሚናገር መጽሐፉ ወደ ሰማይ ሲያርግ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ አቅንተው ያዩ እንደነበረ ተናገረ፤ አሳረጉት አላለም፡፡ ወይም ተሸከሙት አላለም፡፡ ያረገበት ቦታ ገንዘቡ ነውና” /ሃይ.አበ.፷፯፡፲፪-፲፬/፡፡ ኄኖክም ቢኾን “እግዚአብሔር ስለወሰደው” ተባለለት እንጂ በራሱ ሥልጣን ያረገ አይደለም፡፡

የጌታችን ዕርገት በርቀ’ት ሳይኾን በርሕቀት የተፈጸመ ነው!!!
 ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰማይ ያረገው በጥቂት በጥቂቱ እየራቀ፣ ከፍ ከፍ እያለ ወደ ሰማይ ዐረገ እንጂ በርቀት (ረቂቅ በመኾን) አይደለም፡፡ ይኽም ማለት አስቀድሞ የተዋሐደው ባሕርያችንን (ግዙፍነቱን) አጥፍቶ ሳይኾን ከመለኮታዊ ባሕርዩ ጋር አንድ አካል አንድ ባሕርይ የኾነው ግዙፍነቱን ሳይለቅ ከዓይን እየራቀ በመውጣት ነው፡፡ ሐዋርያት ዓይናቸውን ወደ ሰማይ አንሥተው ሲያዩት የነበረውም ይኸውን ነው፡፡ ከተዋሕዶ በኋላ ምንታዌ (ኹለትነት፣ መለያየት) የለም፡፡ በመግቢያችን ላይ እንደተናገርነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ እንዲዳስሱት ያደረገበት አንዱ ምክንያትም ይኸው ነው፡፡ በመኾኑም የጌታችን ዕርገት በርሕቀት (በመራቅ) እንጂ በርቀት (በመርቀቅ) አይደለም፡፡

ወነበረ በየማነ አቡሁ
 ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መዝሙረኛው ቅዱስ ዳዊት አስቀድሞ፡- “እግዚአብሔር ጌታዬን፡- ጠላቶችኽን በእግርኽ መረገጫ እስካደርግልኽ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው” ብሎ እንደተነበየ /መዝ.፻፱ (፻፲)፡፩/ በአብ ቀኝ ተቀምጧል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ይኽ ትንቢት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እንደተፈጸመ አስተምሯል /ዕብ.፲፡፲፪/፡፡
 ይኽም ማለት ወልደ አብ በመለኮቱ ወልደ ማርያም በትስብእቱ የኾነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከዕርገቱ በኋላ በአብ ዕሪና (ትክክል) መቀመጡን የሚያስረዳ ነው፡፡ ነገር ግን ይኽ ለመለኮት የተነገረ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ወልድ ከአብ በባሕርየ መለኮቱ ዝቅ ያለበት ጊዜ የለምና፡፡ ስለዚኽ ደካማ የነበረው ባሕርያችን በተዋሕዶ ከብሮ በአብ ዕሪና መቀመጡን ለማስረዳት የተነገረ ነው፡፡ መጽሐፍ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአብ ቀኝ ተቀመጠ ሲል /ማር.፲፮፡፲፱፣ ዕብ.፩፡፫፣ ዕብ.፰፡፩/፥ እኛም ደጋግመን ወደ ቀደመ ክብሩ ተመለሰ ስንል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚኽ ምድር መመላለሱን መናገራችን እንጂ ከባሕርየ መለኮቱ ተለይቶ ያውቃል ማለታችን እንዳልኾነ መረዳት አለብን፡፡
 አካላዊ ቃል ወደዚኽ ምድር ወረደ ስንል ምሉዕነቱን ሳይለቅ ወልድ በተለየ አካሉ ከባሕርያችን መመኪያ ከቅድስት ድንግል ማርያም ሥጋንና ነፍስን ነሥቶ (ተዋሕዶ)፥ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ፥ ፍጹም ሰው ኾኖ፥ ስለ ድኅነታችን የመጣ መኾኑን መናገራችን እንደኾነ ኹሉ፥ ወጣ ስንልም የመጣበትን ዓላማ ፈጽሞ የተዋሐደውን ሥጋንና ነፍስን ሳይተው ስለ እኛ ክብር እንዳረገ መናገራችን ነው፡፡ ዓምደ ሃይማኖት የተባለው ቅዱስ ቄርሎስ ዘእስክንድርያ የሉቃስ ወንጌልን በተረጐመበት ፳፬ኛው ምዕራፍ ላይ ይኽን በተመለከተ ሲናገር እንዲኽ ይላል፡- “ደቀ መዛሙርቱን ከባረካቸው በኋላ ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡ በአባቱ ዕሪናም ተቀመጠ፡፡ የተቀመጠውም በባሕርየ መለኮቱ ብቻ አይደለም፤ በተዋሐደው ሰውነቱም ጭምር እንጂ፡፡ አካላዊ ቃል ባሕርያችንን ሲዋሐድ እኛን ወደዚኽ ክብር ለመመለስ ነበርና፡፡ … እግዚአብሔር ሲኾን ስለ እኛ ሰው ኾነ፡፡ በፍቃዱ መከራ መስቀልን በተዋሐደው ሰውነቱ ተቀበለ፡፡ በተዋሐደው ሰውነቱ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፡፡ በተዋሐደው ሰውነቱም ዐረገ፡፡ በሕያዋንና በሙታን ላይ ይፈርድ ዘንድም ዳግመኛ በክበበ ትስብእት ይመጣል” /Commentary on Luke, Chap.24/፡፡
 “ተቀመጠ” ሲባልም ለመለኮት መቀመጥና መነሣት ኑሮበት አይደለም፡፡ ከክብሩ ርቆ ከጸጋው ተራቁቶ የነበረው ባሕርያችን (ሥጋ) በተዋሕዶ ከመለኮት ጋር መክበሩን መናገር ነው እንጂ፡፡ የመለኮት ገንዘብ ለሥጋ እንደኾነ መናገር ነው፡፡ “በሰማያዊው ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን” የተባለውም ስለዚኹ ነው /ኤፌ.፪፡፮/፡፡

ዕርገቱና እኛ
 ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞታችንን በሞቱ ደምስሶ ተነሥቶ በማረጉ ያገኘነው ጸጋ እንዲኽ ነው ተብሎ በቃላት የሚገለጥ አይደለም፡፡ በዕርገቱ ተስፋችን ጽኑ ኾኗል፡፡ ፍጹም የኾነ ክብርን አግኝተናል፡፡ “አፈር ነኽና” ተብሎ ተፈርዶበት የነበረው ባሕርያችን በጌታችን ዕርገት ምክንያት በአብ ዕሪና እስከ መቀመጥ ደርሶ እጅግ ክቡር ኾኗል፡፡ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይኽን በማስመልከት፡- “… ክርስቶስ ሥጋውን መሥዋዕት አድርጐ አቀረበ፡፡ ሊቀ ካህናችን ነውና ወደ እርሱ ስላቀረበው በሥልጣኑ ስለ ዐሳረገው ስለ ሥጋው ስለደሙ ወደርሱ መቅረብ ከተቻለው ከዚኽ መሥዋዕት የተነሣ አብ አደነቀ፡፡ በቀኜም ተቀመጥ አለው፡፡ ይኽ ሥጋ ቀድሞ አንተ መሬት ነኽ፤ ወደ መሬትነትኅም ትመለሳለኽ የሚል አዋጅን ሰምቶ ነበር፡፡ ዛሬ ግን ለዚኽ ሥጋ ከሰማያት መኾን ብቻ አልበቃውም፤ በመላእክት ቦታም አልተወሰነም፡፡ ይኽም ክብር አልበቃውም፡፡ ከመላእክት በላይ ኾነ ከሱራፍኤልም በላይ ከፍ አለ፡፡ ወጥቶ ከሊቃነ መላእክት በላይ ኾነ እንጂ፡፡ ወደ ላይ መውጣት ብቻ አልበቃውምና፤ ወደ መንግሥት ዙፋን ወጥቶ እስከ መቀመጥ ደረሰ እንጂ፡፡ በሰማይና በምድር መካከል ያለውን የርሕቀት መጠን አታውቅምን? ና አኹን ከበርባሮስ ጀምረኅ ሥፈር፤ አስተውል፡፡ በገሃነምና በምድር መካከል ያለው የርቀት መጠን ምን ያኽል ነው? ዳግመኛም ከምድር እስከ ጠፈር ያለውን ርቀት ሥፈር፤ አስተውል፡፡ ከዚኽ ሰማይ እስከ ኹለተኛው ሰማይ ያለው የርቀት መጠን፣ ከኹለተኛው ሰማይ እስከ ሦስተኛው ሰማይ ያለውን የርቀት መጠን፣ በሰማያውያን መላእክትና  በአርያም ባሉ መላእክት መንበረ መንግሥትም መካከል ያለው የርኅቀት መጠን ምን ያኽል ነው? እግዚአብሔር የእኛን ባሕርይ ከዚኽን ከፍተኛ ያኽል የርቀት መጠን በላይ አውጥቶ አኖረው፡፡ ቀድሞ ሰውን ካወረደበት ቦታ በታች (መሬት ከመኾን የሚያንስ) ምንም ምን የለምና፤ ዛሬም ሰውን ካወጣበት በላይ (አምላክ ከመኾን የሚበልጥ) ምንም ምን የለምና፡፡… ቀድሞ ትቢያ አመድ ነበርንና፡፡ ይኽንንም የምናገር ባሕርያችንን ለመንቀፍ አይደለም፤ ከማይናገሩ ከእንስሳት ይልቅ ዕውቀትን አጥተን ስለ ነበርን ነው እንጂ” ይላል /ሃይ.አበ.፷፰፡፳፫-፳፰/፡፡
 ዳግመኛም ይኽ ሊቅ በሌላ አንቀጽ እንዲኽ አለ፡- “አስተውል! ከዚኽ (በአብ ዕሪና ከመቀመጥ) የሚበልጥ ነገር አለን? ከዓሣ ይልቅ ቃሉ አይሰማ የነበረ፣ ለአጋንንትም መዘባበቻ የነበረ ሰውን እስከዚኽ መዓርግ ከፍ ከፍ አደረገው፡፡ ይኽ ለአምላክነቱ የሚገባ ደግ ክብር ነው” /ሃይ.አበ.፷፯፡፳፪/፡፡ ለማይመረመር ለዚኽ ክብር አንክሮ ይገባል! ከኹሉ በታች ቁጫጭ ስንኾን ከኹሉም በላይ አድርጐናልና፡፡
 ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን “ዐርገ እግዚአብሔር ከመ ያለቡ ዕርገተ ጻድቃን - እግዚአብሔር ዕርገተ ጻድቃንን ያስረዳ ዘንድ ዐረገ” እንዲሉ የጌታችን ዕርገት ለእኛ ለምናምን ታላቅ ተስፋንና ብሥራትን የሰጠ ነው፡፡ እርሱን መስለን ተነሥተን ወደ ላይኛይቱ አገራችን ወደ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት እናርጋለንና፡፡
 ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ያገኘነው በጌታችን ዕርገት ነው፡፡ በመኾኑም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች እንደተናገረው /ኤፌ.፪፡፯/ በክርስቶስ በሰማያዊ ስፍራ ተቀምጠናልና ሰማያዊ ግብራችንን ረስተን በምድራዊ ግብር ብቻ ልንያዝ አይገባንም፡፡ በክርስቶስ ያገኘነውን ክብር ድጋሜ ልናቆሽሸው አይገባንም፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ዘወትር በቅዳሴዋ “ላዕለ ይኩን ኅሊናክሙ፥ በሰማይ የሀሉ ልብክሙ፥ አእምሩ ኀበ ትቀውሙ፥ ስምዑ ቃለ ጽድቅ ወአስምዑ ዜና ሰናይ” እያለች የምታሳስበንም ስለዚኹ ነው፡፡
በዓለ ዕርገት
  በዓለ ዕርገት ከትንሣኤ በዓል በኋላ በ፵ኛው ቀን ስለሚውል ሐሙስን አይለቅም፡፡ በዓለ ዕርገት ከዘጠኙ የጌታችን ዓበይት በዓላት አንዱ እንደመኾኑ መጠንም በኹሉም አብያተ ክርስቲያናት በቅዳሴ ይከበራል፡፡ ታቦቱ ባላቸው አብያተ ክርስቲያናትም ታቦቱ ወጥቶ በዑደት በድምቀት ይከበራል፡፡ አንዳንድ ምእመናንም በዓለ ዕርገትን ምክንያት በማድረግ ጸበል ጸዲቅን በማድረግ ያከብሩታል፡፡
 ይኹን እንጂ ብዙ ሰው ሌሎቹን የጌታችን ዓበይት በዓላትን እንደሚያከብረው ለበዓለ ዕርገት ሲሰጠው አይታይም፡፡ ይኸውም ልምድ እየኾነ የመጣ ጥሩ ያልኾነ ልማድ ነው፡፡ በመኾኑም በዓሉን እንደ ጥንቱ አባቶቻችን በድምቀት ልናከብረው እንደሚገባ የመቅረዝ መልእክት ነው፡፡
 ወስብሐት ለእግዚአብሔር!

3 comments:

FeedBurner FeedCount