(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፥ ግንቦት
፴ ቀን፥ ፳፻፮ ዓ.ም)፡ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
“ጰራቅሊጦስ” ማለት በጽርዕ ልሳን “አጽናኝ” ማለት ነው፡፡ ምንም እንኳን
በ፩ኛ ዮሐ.፪፡፩ ላይ ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ተጠቅሶ ብናገኘውም፥ አብዛኛውን ጊዜ ግን ከሦስቱ አካላተ ሥላሴ
አንዱ ለሚኾን ለመንፈስ ቅዱስ የሚሰጥ ስያሜ ነው /ዮሐ.፲፬፡፲፮/፡፡ ይኸውም የመንፈስ ቅዱስን ግብር የሚገልጥ ነው፡፡ መንፈስ
ቅዱስ በበዓለ ኃምሳ ቤተ ክርስቲያንን በአሚነ ሥላሴ አጽንቶ ዓለምንም ኹሉ ወደ እውነት እንዲመራት መውረዱን የሚያመለክት ነው፡፡
ከዚኽም በተጨማሪ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንደሚተረጕሙት ጰራቅሊጦስ ማለት መንጽሒ (የሚያነጻ)፣ መጽንዒ (የሚያጸና)፣ መስተፈሥሒ (ደስታን የሚሰጥ)፣ መስተሥርይ (ኃጢአትን ይቅር የሚል)፣ ናዛዚ (የሚያረጋጋ)፣ ከሣቲ (ምሥጢርን የሚገልጥ) የሚል ትርጕምን ይሰጣል (መጻሕፍተ ሠለስቱ
ሐዲሳት፣ ገጽ ፪፻፹፫)፡፡ ይኸውም መንፈስ ቅዱስ በኃጢአት ጭቃ የሚወድቁትን እንደሚያነጻቸው፤ በመንፈሳዊ ተጋድሎ ላሉት ኹሉ በፈተናቸውና በመከራቸው ኹሉ እንደሚያበረታቸው (እንደሚያጸናቸው)፤ የሚነዋወፁትን እንደሚያረጋጋቸው፤ ያዘኑትን እንደሚያጽናናቸው፤ የሚደክሙትን እንደሚያበረታቸው፤ የተከዙትንም ሐሴትን እንደሚሰጣቸው
የሚያስገነዝብ ነው፡፡ ሰማዕታትን ወደ ደም፣ መነኮሳትን ወደ ገዳም፣ ማኅበረ ክርስቶስንም ወደ ቤተ ክርስቲያን ልቡናቸውን የሚያነሣሣና የሚመራ እርሱ ነው፤ መንፈስ ቅዱስ /ዮሐ.፲፮፥፲፪/፡፡
ጥንተ ታሪክ - ብሉይ
እስራኤላውያን በምድረ ግብጽ ለ፬፻፴ ዓመታት በፈርዖን እጅ በባርነት ከኖሩ በኋላ፥ ጊዜው ሲደርስ እግዚአብሔር በሚያስደንቅ ተአምራት በሙሴ መሪነትና በቅዱስ ሚካኤል ተራዳኢነት ነጻ አወጥቷቸዋል፡፡
ነገር ግን የሰው ልጅ በባሕርዩ የተደረገለትን ቸርነት ለመርሳት ፍጡን ነውና፥ እግዚአብሔር ያደረገላቸውን ኹሉ እነርሱ
ራሳቸው ባለ ዘመናቸውም ኾነ ለልጆቻቸው እያስታወሱ እንዲኖሩ፥ ግብጻውያንን በሞተ በኵር የቀጣበትን ቀን፣ እስራኤላውያንን በማሳለፍ (ፓስካ - ፋሲካ) የተቤዠበትን ዕለት እንዲያከብሩ
ሥርዓት አድርጐላቸዋል፤ አዝዟቸዋልም /ዘጸ ፲፪፥፲፰-፳/፡፡ በዓለ ፍስሓን (ፋሲካን) ብቻ ሳይኾን በየጊዜው በያሉበትም ኾነ በኢየሩሳሌሙ ዋናው ቤተ
መቅደስ ተገኝተው በዓል እንዲያደርጉ እግዚአብሔር ሥርዓት ሠርቶላቸው ነበር፡፡ በዓለ ሰንበት፣ በዓለ መጸለት እንዲኹም በዓለ ፉሪም (ንግሥት አስቴር ከመርዶክዮስ ጋር
የተገናኘችበት) እስራኤላውያን እንዲያከብሯቸው ከታዘዙ በዓላት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች፥
እስራኤላውያን በምድረ ርስት በሰላም መኖር ያልቻሉባቸው ኹኔታዎች ነበሩና በተለያየ ጊዜ ፄዋዌ (ምርኮና) ስደት አጋጥሟቸዋል፡፡ በዚኽም
ምክንያት በመካከለኛውና ሩቅ ምሥራቅ እስያ፣ በሰሜን አፍሪካ እንዲኹም በሌሎች አከባቢዎች በዝርወት ይኖሩ ነበር፡፡ የእግዚአብሔርን ሥርዓትና ትእዛዝ እንዳያፈርሱ ብለውም
በእነዚኽ ግዝት በዓላት ወደ ኢየሩሳሌም እየወጡ ያከብሩ ነበር፡፡ ከሚያከብሯቸው የግዝት በዓላት አንዱም ከበዓለ ፍስሓ ቀጥሎ የሚውለው “ፔንትክሰቲ፣
ኢሜራ፣ በዓለ ኃምሳ፥ ጰንጠ ቆስጤ፣ የመከር በዓል፣ ፔንዲ ኮንዳ፣ በዓለ ጰራቅሊጦስ” የተባለው አንዱ ነው፡፡
እስራኤል ዘሥጋ በዓለ ኃምሳን
የሚያከብሩት ስለ ብዙ ምክንያት ነው፡፡ ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያኽልም፡-
፩ኛ) ከምድረ ግብጽ ከወጡ በኋላ ምድረ ከነዓን ገብተው ለመዠመርያ ጊዜ እሸት የበሉበትን የሚዘክሩበት ነው፡፡ ዳግመኛም በበረኻ ሳሉ እግዚአብሔር ከሰማያት ኅብስተ መናን አውርዶ
እንደመገባቸው ይዘክሩበታል፡፡ በመኾኑም በዚኽ በዓል ቀዳምያት፣ አስራትና በኵራት እያወጡ፣ በየዓመቱ ከሚዘሩት እኽል እሸት (በብዛት ስንዴ) እየበሉ እግዚአብሔርን ስለ ምድር ፍሬ
የሚያመግኑበት በዓል ነው፡፡
፪ኛ) እግዚአብሔር ከግብጽ ባርነት ካወጣቸው በኋላ በኃምሳኛው ቀን በደብረ ሲና ሕገ ኦሪትን
ስለተቀበሉበት ይኽን ያስቡበታል፡፡
፫ኛ) እግዚአብሔር ከምድረ ግብጽ በታላላቅ ገቢረ ተአምራት ስላወጣቸው ይኽን ያስቡበታል፡፡
ከላይ ለመግለጥ እንደተሞከረው ይኽ በዓል እኽል በሚታጨድበት በመከር ወቅት
የሚከበር በዓል ነው፡፡ መከር ሲገባ መዠመርያ ከሚሰበስቡት እኽል ለእግዚአብሔር መሥዋዕት እንዲያቀርቡ ታዝዘው ነበር /ዘጸ.፳፫፡፲፮/፡፡
በመኾኑም ከበዓለ ፋሲካ ዠምረው ሰባት ሳምንታት (፵፱ ቀናት) በየዕለቱ አንድ መስፈርያ እኽል ይሰጡ ነበር፡፡ በ፶ኛው ቀን ደግሞ ሊቀ ካህኑ ከተሰበሰበው እኽል በትልቅ
መስፈርያ አድርጎ ካቀረበ በኋላ መሥዋዕተ በግ ይሠዋ ስለነበር ታላቅ በዓል ኾኖ ይከበር ነበር /ዘሌ.፳፫፥፲-፲፯፣ ዘዳ.፲፪፥፭-፯/፡፡
አማናዊ ትርጓሜ - ሐዲስ
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ድኅነተ ዓለምን በፈጸመበት ዓመት ግን፥ እስራኤል ዘሥጋ ከላይ በገለጥነው መንገድ ከያሉበት
ተሰባስበው በዓሉን በኢየሩሳሌም ሲያከበሩ፤ ለእሥራኤል ዘሥጋና ለእሥራኤል ዘነፍስ ብርሃን እንዲኾኑ
የመረጣቸው ሐዋርያትም
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የነገራቸውን ተስፋ እየተጠባበቁ በደብረ ጽዮን በቅዱስ ማርቆስ
እናት ቤት ተሰባስበው ነበር /ሉቃ.፳፬፡፵፱/፡፡ በዓለ ኃምሳ የተባለው ቀን በደረሰ ጊዜም ከወደ ሰማይ እንደ ዓውሎ ነፋስ
ድምፅ ያለ ድምፅ ነጕዶ ተሰማ፤ መንፈስ ቅዱስ ነበር፡፡ በዚኽም ብሉይና ሐዲስ ተገናኙ፤ ተተካኩ፡፡
የነቢያት ትንቢታቸው የሐዋርያትም ስብከታቸው የኾነው ጌታችንና መድኃኒታችን
ኢየሱስ ክርስቶስ ነቢያትንና ሐዋርያትን በደብረ ታቦር ተራራ እንዳገናኛቸው፥ በዚያም ክብረ መንግሥቱን ብርሃነ መለኮቱን እንደገለጸላቸው የሚታወስ ነው /ማቴ.፲፮፡፩-፯/፡፡ በምሴተ ሐሙስም በቤተ አልዓኣዛር የብሉይ ፋሲካን እንዳዘጋጁና እርሱም መሥዋዕተ ብሉይን በመሥዋዕተ ሐዲስ እንደተካው የተጻፈ ነው
/ማቴ.፳፮፡፲፯-፳፱/፡፡ በበዓለ ኃምሳ የኾነውም ልክ እንደዚኹ ነው /ሐዋ.፪/፡፡ ይኽ ኹሉ በኢየሩሳሌም፣ በመዠመርያዪቱ ቤተ ክርስቲያን በተሰየመች በቤተ ማርያም (የማርቆስ እናት) ተፈጸመ፡፡ ቤተ ክርስቲያን ለፊተኞችም ለኋለኞችም እናታቸው
እንደኾነችም ታወቀ፤ ተረዳ፡፡
ቅዱሳን ሐዋርያት በዲድስቅልያ ፴፩
ላይ፡- “ከዕርገቱ ቀን በኋላ ታላቅ በዓል ይደረግ፤ በዚኽች ቀን በሦስተኛው ሰዓት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
ጰራቅሊጦስን ልኮልናልና እኛም በርሱ ስጦታዎች ተሞላን፤ አዳዲስ ቋንቋም ተናገርን” በማለት በዓሉን በቤተ ክርስቲያን ልናከብረው
እንዲገባ ሥርዓት የሠሩልንም ስለዚኹ ነው፡፡ በነቢያትና በሐዋርያት መሠረት የታነጸችው ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችንም
ይኽንኑ በዓል ከጌታችን ዘጠኝ ዐበይት በዓላት አንድ በማድረግ በድምቀት ታከብሯለች፡፡
በዓለ ኃምሳ በብሉይና በሐዲስ - በንጽጽር ሲቀርብ
እስራኤል ዘሥጋ የፋሲካውን በግ ሠዉተው ከግብጽ ባርነት ከወጡ በኋላ
በኃምሳኛው ቀን ሕገ ኦሪትን እንደተቀበሉ ኹሉ፥ እኛም የእግዚአብሔር በግ የተባለው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
የተወደደ መሥዋዕት ኾኖ ቀርቦ ከተነሣ በኋላ በኃምሳኛው ቀን ሕገ ሐዲስን ተቀብለናል፡፡
ሕገ ኦሪቱ በደብረ ሲና ሲሰጥ
ጢስና ጭጋግ እንደነበረ ኹሉ /ዘጸ.፲፱፡፲፰/፥ ሕገ ወንጌል በደብረ ጽዮን ሲሰጥም በእሳት ላንቃ አምሳል ወርዷል፡፡
እስራኤል ዘሥጋ በበዓለ ኃምሳ
ከአዝመራው በኵራቱን ቀዳምያቱን እንደሚሰበስቡ ኹሉ፥ አኹንም መንፈስ ቅዱስ ዓለምን ኹሉ ለእግዚአብሔር በኵራት አድርጐ ያቀርብ
ዘንድ ወርዷል፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዘር መስሎ ያስተማረበት ምሥጢርም ይኸው ነው /ማቴ.፲፫፡፩-፱፣
ዮሐ.፬፡፴፭/፡፡
እስራኤል ዘሥጋ ከግብጽ ከወጡ
በኋላ በእደ ሙሴ በእግዚአብሔር ጣት የተቀረጸውንና የተጻበትን ጽላት እንደ ተቀበሉ ኹሉ፥ እኛም ከጌታችን ሞትና ትንሣኤ በኋላ
በኃምሳኛው ቀን በምእመናን ልብ ጽላት ላይ እውነትን የሚጽፍ (የሚያኖር) የእግዚአብሔር ጣት የተባለ መንፈስ ቅዱስን
ተቀብለናል፡፡
ርደተ መንፈስ ቅዱስ
ጌታችን እንደነገራቸው መቶ ኻያው ቤተ ሰብእ በቤተ ማርያም ኃይልን
ከአርያም እስኪለብሱ ድረስ ተሰብስበው ነበር፡፡ በትዕግሥት ከመጠበቅ ውጪ መንፈስ ቅዱስ መቼ እንደሚወርድም አያውቁም ነበር፡፡
ወንጌላዊው ሉቃስ “ድንገት እንደሚነጥቅ ዓውሎ
ነፋስ …” የሚለንም ስለዚኹ ነው /ሐዋ.፪፡፪/፡፡ ጌታችን ባረገ በዐሥረኛው ቀን ግን እኔና እናንተ እንደምንሰማው ዓይነት
ያይደለ፥ ነገር ግን ከወደ ሰማይ እንደ ዓውሎ ነፋስ ድምፅ ያለ ድምፅ ነጕዶ ተሰማ፡፡ ያሉበትን ቤት ሞላው፡፡ ላንቃ ላንቃ
ያለው እሳት ኾኖ ታያቸው፡፡ በበደልን ጊዜ ከእኛ ርቆ ነበርና አኹን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሞት ስለታረቅን በኹሉም
አደረባቸው፡፡ መጥምቁ ዮሐንስ “በመንፈስ ቅዱስም በእሳትም ያጠምቃችኋል” ያለው ደረሰ፤ ተፈጸመ /ማቴ.፫፡፲፩/፡፡ ኃይል
የሚኾናቸው ሀብትን፣ ሀብት የሚኾናቸው ዕውቀትን ገንዘብ አደረጉ፡፡
ኹሉም በየራስ በየራሳቸው በሰብዓ ኹለት ቋንቋ መናገር ዠመሩ፡፡ በዔቦር ዘመን የሰው ልጆች ልሳን በሥላሴ ተደባልቆ ነበር፡፡ የሰው ልጆችም አንድነትን አጥተው
ተከፋፍለው ነበር /ዘፍ.፲፡፳፭/፡፡ አኹን ግን የተበታተኑትንና የተከፋፈሉት የሰው ልጆችን አንድ መንጋ ያደርጉ ዘንድ (ሐዋርያት)
በሰብዓ ኹለት ቋንቋ እንዲናገሩና ወንጌለ መንግሥትን እንዲያስተምሩ ተደረገ፡፡ ይናገሩ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ ሀብቱ እንዳደላቸው መጠን በሐዋርያት ፸፪ ቋንቋ
አልተከፈለባቸውም፡፡ የቀሩት ግን ከዐሥራ አምስት በታች የወረደ የለም እንጂ እንደ መጠኑ ኻያም፥ ኻያ አምስትም፥ ሠላሳም፥
አርባም፥ አምሳም፥ ስሳም ተገልጦላቸዋል፡፡
ከሰማይ በታች ባለ በአራቱ ማዕዘን ካሉ አሕዛብ
ተለይተው መጥተው በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ደጋግ ሰዎች ነበሩ፡፡ ከመግቢያችን እንደገለጥነው ከሚጠት በኋላ እስራኤል በወደዱት ሀገር
በሕጋቸው ይኖሩ ስለ ነበር በዓለ ፋሲካን አክብረው ከዚያ አያይዘው ሰባት ሱባኤ ቈጥረው በኃምሳኛይቱ ቀን በዓለ ሰዊትን
ለማክበር ሀገር የቀረበው በየሀገሩ ይኼዳል፥ ሀገር የራቀበትም ሥንቁን ይዞ ከዚያው ይሰነብታል፡፡ በዚኽች ቀንም የኼዱት
ተመልሰው ያሉትም ተሰባስበው ባንድነት ሳሉ በሰባ ኹለት ቋንቋ ሲናገሩ ሰምተዋቸው የአንክሮ ድንጋጤ እየደነገጡ ተሰብስበዋል፡፡
ከእናንተ መካከል፡- “በአዲስ ቋንቋ መናገር ማለት
ምን ማለት ነው? በአኹኑ ሰዓት አንዳንድ ሰዎች በአዲስ ቋንቋ ተናግርን ከሚሉት ጋርስ ግኑኝነት አለውን?” ብሎ የሚጠይቅ ሊኖር
ይችላል፡፡ እኛም እንዲኽ ብለን እንመልስለታለን፡- “ደቀ መዛሙርቱ ከዚኽ በፊት በማያውቁትና ባልተማሩት አዲስ ቋንቋ
እንደተናገሩ ርግጥ ነው፡፡ ነገር ግን በአኹኑ ሰዓት በልሳን ተናገርን እንደሚሉት የፊደላት ቅጥልጥል ሳይኾን በሰሚዎቹ ዘንድ
የሚሰማና መልእክት ማስተላለፍ የሚችል ልሳን ነበር /ሐዋ.፪፡፰/፡፡ ሐዋርያት በአዲስ ቋንቋ እንዲናገሩ የተደረገው በዚያ
የነበሩ ሰዎች ልሳኑ የእግዚአብሔር የጸጋው ስጦታ እንደኾነ ተረድተው ድኅነት አንድ ቋንቋ ለሚናገሩት ለእስራኤላውያን ብቻ
ሳይኾን ለሰው ልጆች በሙሉ እንደመጣች እንዲገነዘቡ ነበር፡፡ ደቀ መዛሙርቱ በአዲስ ቋንቋ ሲናገሩ መንፈስ ቅዱስ ስለገለጠላቸው
እንጂ አስቀድመው ተለማመድዉት አልነበረም፡፡ ከዚኽም የተነሣ አኹን አኹን እንደምንሰማው ስለ ራሳቸው ታሪክ የሚናገሩበት አልነበረም፤
የእግዚአብሔርን ዓላማ ብቻ የሚያስተላልፉበት እንጂ፡፡ ዳግመኛም ሐዋርያት በአዲስ ቋንቋ ሲናገሩ የእግዚአብሔር የማዳን ሥራ
ለሰው ልጆች በሙሉ እንደተገለጠች ማሳየት እንጂ ዛሬ ዛሬ እንደምናየው ውዳሴ ከንቱን ለማግኘት አልነበረም፡፡ ብጹዕ የሚኾን
ጳውሎስ ብዙ ልሳን እንደሚናገር ጽፎልናል /፩ኛ ቆሮ.፲፬፡፲፰/፡፡ ነገር ግን እንዲኽ መናገር ስለቻለ ብቻ ማኅበሩን በማያንጽ
መልኩ ሊናገር አልወደደም፡፡ ጥቂት የሚያንጹ ቃላትን ብቻ ቢናገር ይመርጥ ነበር እንጂ፡፡ በአጠቃላይ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳለው
በልሳን መናገር ለማያምኑ ምልክት (ማቅረቢያ) እንጂ በምእመናን መካከል የሚነገር አይደለም /፩ኛ ቆሮ.፲፬፡፳፪/፡፡ ሰውስ
ይቅርና እግዚአብሔር ስንኳ በሰዉኛ ቋንቋ ካልተናገረ የሚሰማው የለምና፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለገበሬው በዘር፣ ለሴቷ
በእርሾ፣ ለነጋዴው በዲናር እየመሰለ ማስተማሩም ይኽን የሚያስረዳ ነው፡፡”
አኹንም ከእናንተ መካከል፡- “መንፈስ ቅዱስ በሚታይና
በሚሰማ ትእምርት መውረዱ ስለ ምንድነው?” ብሎ የሚጠይቅ ሊኖር ይችላል፡፡ እኛም እንዲኽ ብለን እንመልስለታለን፡- “ጸጋ መንፈስ ቅዱስ በሚታይና በሚሰማ ትእምርት
መውረዱ ለአይሁድ ጥቅም ነው፡፡ አይሁድ፥ ሰምተውና ዐይተው ሐዋርያት ወዳሉበት ኅብረት እንዲመጡና የእውነት መንፈስ የሚላቸውን እንዲሰሙ፣ እዝነ
ልቡናቸውንም እንዲከፍቱ ፈቃደ እግዚአብሔር ስለነበረ ነው፡፡ በሐዋርያት የሚሰጠው ትምህርት እውነትነቱ እንዲረጋገጥ በትእምርት የታጀበ ነበር፡፡
ይኸውም በሰማያዊ ኃይል እንጂ በምድራዊ ጥበብ እንዳልኾነ ያረጋግጥላቸው ዘንድ ያደረገው ነበር፤ አይሁድ ምን ያኽል ከማመን
የዘገዩ እንደ ነበሩ ቅዱስ መጽሐፍ የሚመሰክረው ሐቅ ነውና፡፡ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም
የማቴዎስ ወንጌልን በተረጐመበት በ፲፪ኛው ድርሳኑ ላይ እንዲኽ ይላል፡- በበዓለ ኃምሳ የታየውና የተሰማው ኹሉ ስለ መቶ ኻያው
ቤተ ሰብ የኾነ አይደለም፤ ስለ አይሁድ እንጂ፡፡ ምንም እንኳን እንደ አውሎ ነፋስ ያለ ድምጽ፥ ላንቃ ላንቃ ያለው እሳትም ባይወርድ
አኹን እኛ ስንጠመቅ የሚኾነውም እንደዚኹ ነው፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእደ ዮሐንስ በፈለገ ዮርዳኖስ ሲጠመቅ መንፈስ
ቅዱስ በርግብ አምሳል መውረዱ ለጌታችን ወይም ለዮሐንስ ሳይኾን በዙርያ የነበሩት ሰዎች ስለ ሀልዎተ መንፈስ ቅዱስ እንዲረዱ
እንደነበረ ኹሉ አኹንም መንፈስ ቅዱስ እንዲኽ በነፋስና በእሳት አምሳል መውረዱ እንደተናገረን ስለ አይሁድ ረብሕ ነበር፡፡
ዳግመኛም እኛ ስንጠመቅ መንፈስ ቅዱስ እንዲኽ በእኛ እንደሚያድር እንድናውቅ እንድንረዳ ነው፡፡ ነገር ግን አኹን እንዲኽ ያለ
ትእምርት አያሻንም፤ በእምነት እንቀበሏለንና፡፡ ዳግመኛም ብጹዕ የሚኾን ሐዋርያ ጳውሎስ እንደተናገረ ይኽ ዓይነት ትእምርት
ለማያምኑ እንጂ ለሚያምኑ አይደለምና /፩ኛ ቆሮ.፲፬፡፳፪/፡፡”
አኹንም ከእናንተ መካከል፡- “መንፈስ ቅዱስ ለአይሁድ ጥቅም እንዲኽ በሚታይና በሚሰማ ትእምርት
ለአይሁድ እንደወረደ ተማርን፡፡ በእሳትና በነፋስ አምሳል መውረዱስ ስለምንድነው?” ብሎ የሚጠይቅ ሊኖር ይችላል፡፡ እኛም
እንዲኽ ብለን እንመልለታለን፡- “ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲጠመቅ በርግብ አምሳል መውረዱ በ፵ና በ፹ ቀናችን
ስንጠመቅ ይኽን የትሕትና መንፈስ ገንዘብ እንደምናደርግ ሲያስረዳን ነው፡፡ በእሳት አምሳል መውረዱም ይኽን የእውነት መንፈስ
የተቀበልን ክርስቲያኖች በእምነታችን ለዓለም ኹሉ ብርሃን ልንኾን እንደሚገባ ሲያስተምረን ነው፡፡ አንድም ምእመናን እምነታቸውን
እስከ እሳት (ሰማዕትነት) ድረስ መመስከር እንዳለባቸው ያስረዳል፡፡ አንድም እሳት በምልዓት እያለ ከክብሪቱ ካልወጣ በቀር
አይታወቅም፤ መንፈስ ቅዱስም በምልዓት ሲኖር መኖሩ የሚታወቀው ትንቢት ሲያናግር፣ ምሥጢር ሲያስተረጕም፣ ለሰው በሚሰማ በሚረዳ
በሐዲስ ልሳን ሲናገር ነው፡፡ እሳት ከክብሪቱ ሲወጣ መጠነኛ ነው፤ መንፈስ ቅዱስም በ፵ና በ፹ ቀን እንደየኹኔታው በሌላም ጊዜ
ሲሰጥ በመጠኑ ነው፡፡ ከዚኽ በኋላ በገድል፣ በትሩፋት ማለትም በጦም፣ በጸሎት፣ በተጋድሎ፣ በአጠቃላይ በበጐ ሥራ እየጸና
ይኼዳልና፡፡ እሳት በመጠን ከሞቁት ሕይወት ይኾናል፤ መንፈስ ቅዱስም በተጻፈው ቃለ እግዚአብሔር የመረመሩትና የተረዱት እንደኾነ
ሕይወተ ሥጋ ሕይወተ ነፍስ ይሰጣል፡፡ እሳት ወንዝ ገደል ካልከለከለው በቀር ኹሉን ሊያጠፋ ይችላል፤ መንፈስ ቅዱስም ቸርነቱ ካልከለከለው
በቀር ኹሉን ማጥፋት ይቻሏል፡፡ እሳት ከብረት ዝገትን ሳይሳተፍ ብረቱን እንዲጠራ ያደርጓል፤ መንፈስ ቅዱስም ከኃጢአት ሳይሳተፍ
ምእመናንን ያነጻል፡፡ ስለዚኽ ይኽ በመቶ ኻያው ቤተ ሰብእ የወረደው እሳት የሚባላ እሳት ሳይኾን የኃጢአትን እሾኽና አሜኬላ
የሚበላ እሳት ነው፡፡ በንፋስ መልኩ መውረዱ ደግሞ ነፋስ ረቂቅ እንደኾነ ኹሉ መንፈስ ቅዱስም ረቂቅ መኾኑን ለማሳየት ነው፡፡
አንድም ነፋስ ኃያል ነው፤ መንፈስ ቅዱስም ኃያል ነው፡፡ ነፋስ ገለባን ከፍሬ ይለያል፤ መንፈስ ቅዱስም ኃጥአንን ከጻድቃን
ይለያል፡፡ ነፋስ በምልዓት ሳለ ሀልዎቱ የሚታወቀው ባሕር ሲገሥጽ፣ ዛፉን ሲያንቀሳቅስ ነው፤ መንፈስ ቅዱስም በምልዓት ሳለ
መኖሩ የሚታወቀው ትንቢት ሲያናግር ምሥጢር ሲያስተረጕም ነው፡፡”
ጰራቅሊጦስና እመቤታችን
ጸጋ
መንፈስ ቅዱስ በመቶ ኻያው ቤተ ሰብእ በምልዓት ሲወርድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም በመካከላቸው ነበረች፡፡ ይኸውም
እመቤታችን ባለችበት ኹሉ ጉባኤ መንፈስ ቅዱስ የሚገለጥ መኾኑን የሚያስረዳ ነው፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፥
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚኽ ምድር በነበረበት ወራት ተለይታው አታውቅም፡፡ በቤተ ክርስቲያን ልደትም እንደዚኹ
አልተለየችም፡፡ ይኸውም እመቤታችን አማናዊት ታቦት መኾኗ ምስክር ነው፡፡
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በመቶ ኻያው ቤተ ሰብእ መካከል ነበረች
ማለት ግን መንፈስ ቅዱስን የተቀበለችው በዚኽ ዕለት ነው ማለት አይደለም፡፡ መንፈስ ቅዱስ አስቀድሞ ከርሷ ጋር ስለነበረ
እንደሌሎቹ ደቀ መዛሙርት አኹን በበዓለ ኃምሳ የተቀበለች አይደለችም፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ሲያበሥራት “ተፈስሒ ፍስሕት ኦ
ምልዕተ ጸጋ” ያላትም ስለዚኹ ነው፡፡ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ እንደነገረን፥ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዓለም ሳይፈጠር
በአምላክ ኅሊና ታስባ ትኖር ስለነበር ጸጋ መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያት ሲሰጥ የተቀበለች አይደለችም፡፡
ከእናንተ
መካከል፡- “መንፈስ ቅዱስ ከበዓለ ኃምሳ በፊት ከሰዎች ጋር ነበርን?” ብሎ የሚጠይቅ ሊኖር ይችላል፡፡ አዎ! ምንም እንኳን
የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ከኹሉም ፍጥረት የተለየ ቢኾንም መንፈስ ቅዱስ ከሰው ልጆች ፈጽሞ ርቆ አያውቅም፡፡ መንፈስ
ቅዱስ ከዓለም ቢርቅ አንድ ስንኳ በሕይወት መቈየት የሚቻለው የለምና፡፡ ምንም እንኳን አዳም በበደለው በደል በሰውና
በእግዚአብሔር መካከል የቆመ ትልቅ የኃጢአት ግድግዳ የነበረ ቢኾንም /ዘፍ.፮፡፫/ በጣም ውሱን በኾነ መልኩ ግን በተወሰኑ
ቅዱሳን ሰዎች በረድኤት አብሮ ነበር፡፡ ቅዱሳን ነቢያት በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝተው ስለ መጻእያት ትንቢት የተናገሩት ቅዱሳት
መጻሕፍትንም ሊጽፉ የቻሉት ስለዚኹ ነው፡፡ እንደ ቅዱስ ዳዊት የመሰሉ ነቢያትም ፯ ሀብታት የተሰጣቸውና በገናን በመደርደር ክፉ
መናፍስትን ሲያርቁ የነበሩትም ስለዚኹ ነው፡፡
የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ግን ከዚኽ ኹሉ የተለየ ነው፡፡
ሰማይና ምድር የማይሸከሙትን ጌታ ፱ ወር ከ፭ ቀን በማኅፀኗ ለመሸከም የተመረጠች በመኾኗ ቅድስተ ቅዱሳን፥ ንጽሕተ ንጹሐን
ናት፡፡ የሰው ልጆች በአዳም በደል ምክንያት በደረሰባቸው ድቀት (ጉድለት) ከጸጋ መንፈስ ቅዱስ በአፍአ የነበሩ ሲኾን
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ግን አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በእሑድ አርጋኖኑ ላይ እንዳስተማረው መንፈስ ቅዱስ ከእናቷ
ማኅፀን አንሥቶ ስለ ጠበቃት ከዚኽ ድቀት (ጉድለት) ነጻ ነበረች፤ የዓለም ብርሃን ክርስቶስ ወደዚኽ ምድር ሳይመጣ ገና ምልዕተ
ጸጋ ነበረች፡፡ ይኸውም አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም እንዳስተማረው በቅታ ብትገኝ እግዚአብሔር የሰጣት ጸጋ ነው፡፡ ስለዚኽ
ምንም እንኳን በበዓለ ኃምሳ በመቶ ኻያው ቤተ ሰብእ መካከል የነበረች ቢኾንም መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል ግን አልነበረም፡፡
መንፈስ ቅዱስ
መንፈስ ቅዱስ ከሦስቱ አካላተ ሥላሴ አንዱ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ከአብና
ከወልድ ጋር የሚሠለስ የሚቀደስ የባሕርይ አምላክ ነው፡፡ እንደ አብና ወልድ ፍጹም ገጽ፣ ፍጹም መልክዕ፣ ፍጹም አካል አለው፡፡
መንፈስ ቅዱስ አካላዊ እንጂ ሕጹጽ (ብትን፣ ዝርው) አይደለም፡፡ በተለየ ግብሩም መሥረፅ (መውጣት) ነው፡፡ መሥረጹም ከአብ
ብቻ እንጂ አንዳንዶች (ካቶሊኮችና መካነ ኢየሱሶች) እንደሚሉት ከወልድም ጭምር አይደለም /ዮሐ.፲፭፡፳፮/፡፡ መንፈስ ቅዱስ
ቢሠርፅ እንጂ አያሠርጽም፤ አይወልድም፤ አይወለድም፡፡
ሠለስቱ ምዕት “በመንፈስ ቅዱስም እናምናለን፤ እርሱም
ጌታ ሕይወትን የሚሰጥ ከአብ የሠረፀ ከአብና ከወልድ ጋር በአንድነት እንሰግድለታለን፤ እናመሰግኗለን፡፡ እርሱም በነቢያት አድሮ
የተናገረ ነው” ብለው እንዳስተማሩን በባሕርይ፣ በመለኮት፣ በሥልጣን፣ በሕልውና፣ በአገዛዝ፣ ዓለማትን በመፍጠርና በማሳለፍ
ከአብና ከወልድ ጋራ የተካከለ ነው /ጸሎተ ሃይማኖት/፡፡ ቀዳሚነትም ኾነ ተቀዳሚነት የሌለው ይልቁንም ከአብና ከወልድ ጋር የተካከለ
(ዕሩይ) ነው፡፡
“መንፈስ ቅዱስ” እንደ አርዮስ “አካል አልቦ፣ ዝርው ኃይል ነው”፤ እንደ
መቅዶንዮስም “ፍጡር፣ ሕጹጽ ነው” የሚል እንግዳ ትምህርት በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ተቀባይነት የለውም፡፡
እንዲኽ ያለ ትምህርትም ሥርየተ ኃጢአት የማይገኝበት በደል ነው /ማቴ.፲፪፡፴፪/፡፡
እኛና ጰራቅሊጦስ
ይኽቺ ዕለት በዓለ ሰዊት (እሸት)
በበዓለ ጰራቅሊጦስ የተተካባት፣ ኹሉንም አንድ የምታደርግ ቤተ ክርስቲያን የተገለጠችባት ዕለት ናት፡፡ እንደ ቅዱስ ዮሐንስ
አፈወርቅ አጠራርም ቤተ ክርስቲያን የተወለደችባት፣ የክርስቶስን ትእዛዝ ተቀብላ ወንጌልንም ተሸክማ ወደ ዓለም እርሻ መሰማራት
የዠመረችባት ዕለት ናት፡፡
ይኽቺ ቀን በኋለኛይቱ ቀን በልቡናችን እርሻ የተዘራው የወንጌል ዘር በቅሎ፥
ፍሬ ሊሰበሰብበት የተዠመረበት የመሠረት ዓውድማ ቀን ናት /ሐዋ.፪፡፵፩/፡፡
ይኽቺ ዕለት ቤተ ክርስቲያን፥ በምሥጢረ ንስሐ፣ በምሥጢረ ጥምቀት፣ በምሥጢረ ጸጋ መንፈስ ቅዱስ ስጦታ (አስቀድሞ በአንብሮተ እድ ኋላ ላይም በሜሮን የኾነው) ወኀበ ዘተርፈ ተልእኳን የዠመረችበት ዕለት ናት፡፡
ይኽቺ ዕለት በዔቦር ዘመን ለኃጢአት ሥራ የዋለውና በሥላሴ የተደበላለቀው ቋንቋ፥
ለስብከተ ወንጌል ከ፲፭ እስከ ፸፪ ልሳን ኾኖ ለሐዋርያት የተሰጠባት ዕለት ናት፡፡
ውሉደ እግዚአብሔር የኾንን እኛም በ፵ና በ፹ ቀናችን የዚነኽ ኹሉ ስጦታዎች ተካፋዮች
ኾነናል፡፡ በመኾኑም እግዚአብሔር ስላደረገልን ኹሉ እያመሰገንን ጸጋችንን በአግባቡ ልንጠቀምበት፣ በኃጢአት ጭቃ ስንወድቅ ልንነጻበት፣ በመንፈሳዊ ተጋድሎአችን ኹሉ በፈተናችንና በመከራችን ልንበረታበት፣ ስንነዋወጥ
ልንረጋጋበት፣ ስንተክዝ ልንጽናናበት፣ ስንደክም ልንበረታበት፣ ስንተክዝም ሐሴት ልናደርግበት፣ ከምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን እየተካፈልንም የሚገባ
ፍሬም ልናፈራበት ይገባል፡፡
ዳግመኛም አኹን በኢትዮጵያችን
ከሚታየውና እየባሰበት ከመጣው የባቢሎን ሥራ (በቋንቋ፣ በዘር፣ በወንዝ መለያየት) ራሳችንን ልንጠብቅ ሌሎችንም ከዚኹ ክፉ
መንፈስ እንዲወጡ በርትተን ልናስተምር ይገባል፡፡ የተቀበልነው መንፈስ አንድ የሚያደርግ መንፈስ እንጂ የመለያየት መንፈስ
አይደለምና፡፡ አስቀድመን እንደተናገርን እስከ ፸፪ ቋንቋ ድረስ ለሐዋርያት የተሰጠው በበደሉ ምክንያት ተበታትኖ የነበረው የሰው
ልጅ ወደ እግዚአብሔር ለማቅረብ (አንድ መንጋ ለማድረግ) እንጂ አኹን ዲያብሎስ እንደሚያድገው “እኔ የአጵሎስ ነኝ፤ እኔ የኬፋ
ነኝ” ብለን እንድንከፋፈል አይደለምና፡፡
እናስተውል
መጽሐፍ ቅዱሳችን እንደሚነግረን በመጨረሻው ዘመን በግ
ሳይኾኑ የበግ ለምድ ለብሰው የሚመጡ ብዙ ሐሰተኛ ነቢያት አሉ፡፡
እነዚኽ ሐሰተኛ ወንድሞችም ማኅበረ ክርስቶስን ማወክ ተቀዳሚ ዓላማቸው ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ከ፳ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ወዲኽ
በቅዱሳን አባቶቻችን የተወገዙትን አስተምህሮዎች እንደ አዲስ በማምጣት “የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ነው” በማለት ታይቶና ተሰምቶ
የማይታወቅ የመጽሐፍም ልማድ ያልኾነ እንግዳ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ምእመናንን (በተለይ ወጣቶችን) ሲያታልሉ ይታያል፡፡ ይኽ
ኹሉ ግን የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት (ከሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን አንዱ በሚኾን በምሥጢረ ጥምቀት እንደሚታደል)
እንዲኹም ጸጋ መንፈስ ቅዱስን (ሀብተ መንፈስ ቅዱስ ሥልጣነ ክህነት በሌለው ሰው እንደማይሰጥ) አለማወቅ ነው፡፡ በመኾኑም
ምእመናን ከላይ ይኽን ከመሰለ እንግዳ ትምህርት ይጠበቁ ዘንድ የመቅረዝ ዘተዋሕዶ መልእክት ነው፡፡
ይኽን እንድናደርግ በቤቱ ጸንተንም ለእግዚአብሔር
በኵራት (ቀዳምያት) ኾነን እንድንቀርብ ጸጋ መንፈስ ቅዱስ አይራቀን፡፡ አሜን!!! ከበዓሉ በረከትና ረድኤት ይክፈለን!!!
kale hiwoten yasemalen
ReplyDeleteQale Hiwet Yasemalin
ReplyDeleteQale hiwot yasemalen
ReplyDelete