(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሰኔ ፪ ቀን፥ ፳፻፮ ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ.
ምእመን ኾኖ ስለ ጾም ምንነትና አስፈላጊነት የማያውቅ አለ ማለት አይቻልም፡፡ ከ፯ ዓመታችን አንሥተን አብዛኞቻችን
ከጾም ጋር ተዋውቀናልና፡፡ ጾም የሥጋን ምኞት እንደምታጠፋ፣ የነፍስን ቁስል እንደምትፈውስ፣ ጽሙናንና ርጋታን
እንደምታስተምር፣ ከእንስሳዊ ግብር እንደምትጠብቅ፣ ሰውን መልአክ ዘበምድር አድርጋ መንፈሳዊ ኃይልን እንደምታስታጥቅ
አብዛኞቻችን ተምረነዋል፤ በቃላችንም እናውቀዋለን፡፡ ነገር ግን በተግባር እግዚአብሔር እንደወደደው የሚጾሙት እጅግ
ጥቂቶች መኾናቸው በጣም አሳዛኝ ነው፡፡ ብዙዎቻችን የሥጋ ፈቃዳችንን ሳንተው “ስለምንጾም” በሕይወታችን ለውጥ
አይታይብንም፡፡
አባቶቻችን
ጾም ሲመጣ ደስ ይላቸዋል፤ እኛ ግን (አብዛኞቻችን) ባናዝንም ደስ አይለንም፡፡ አባቶቻችን ጾም ሲፈታ ያዝናሉ፤
የጾሙ ወራት ቢራዘምም ደስ ይላቸዋል፡፡ እኛ ግን ጾሙ ሲገባ ሳይኾን ሲፈታ የበለጠ ደስ ይለናል፤ ወራቱም ቢያጥር
ደስታችን ነው፡፡ በጾም ጊዜ ብዙው ትኵረታችን የሚወስደው ምሳችንን የምንበላበት ሰዓትና ደቂቃ፣ የምግቡ ዓይነት
(የጾም አለው ወይስ የለውም፥ ዛሬ ምን ዓይነት ብፌ ነው የምበላው የሚለው) እንጂ እግዚአብሔር አይደለም፡፡ እኛ
በሕይወቱ ስለሌለንበትም “ቅዱሳን ይኼን ያኽል ቀን፣ ይኽን ያኽል ወር እኽልና ውኃ ሳይቀምሱ ሰነበቱ” ሲባል
እንደነቃለን፡፡ ይኼ ኹሉ የጾምን ዓላማ ምን ያኽል እንደሳትነው ያሳያል፡፡ ዲያብሎስም በገዳመ ቆሮንቶስ በምን ድል
እንደተደረገ ጠንቅቆ ስለሚያውቅ /ማቴ.፬/ ይኽን የእግዚአብሔር ስጦታ እጅግ ረቂቅ በኾነ ጥበቡ እንዴት አድርጐ
እንዳስጣለን ያመለክታል፡፡
“ጾምን ቀድሱ” /ኢዩ.፩፡፲፬/
“መቀደስ” ማለት “መለየት” ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር ሙሴን፡- “በእስራኤል ልጆች ዘንድ ከሰውም ከእንስሳም ማሕፀንን የሚከፍት በኵር ኹሉ ለእኔ ቀድስልኝ፤
የእኔ ነው” ሲለው /ዘጸ.፲፫፡፩/ በኵራቱ ለእግዚአብሔር አገልግሎት መለየት እንዳለባቸው ሲነግረው ነው፡፡ እነዚኽ
በኵራት በአሮንና በአሮን ልጆች ፊት ኾነው እግዚአብሔርን ከማገልገል ውጪ ሌላ ሥራ አልነበራቸውም፡፡ ለእግዚአብሔር
ስለተለዩ ሌላ ሥራ መሥራት አይፈቀድላቸውም፡፡ የእንስሳቱ በኵራትም ለመሥዋዕትነት የተለዩ ናቸው፡፡ እነዚኽን
በኵራት፥ ሰዎች በቤታቸው አርደው ሊበልዋቸው አይችሉም፤ ለእግዚአብሔር የተለዩ ናቸውና፡፡
በቤተ
ክርስቲያን ውስጥ ያሉ ንዋያተ ቅዱሳትም ለአምልኮተ እግዚአብሔር የተለዩ (የተቀደሱ) ስለኾነ ንጉሡ ብልጣሶር
እንዳደረገው ለሌላ ዓላማ ማዋል አይቻልም /ዳን.፭/፡፡ አንድ ቤተ ክርስቲያንም ተባርኮ ለአምልኮተ እግዚአብሔር
ከተለየ በኋላ “ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች” ተብሎ እንደተነገረ ለሌላ ዓላማ ማዋል አይቻልም /ማቴ.፳፩፡፲፫/፡፡
እግዚአብሔር “የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ” ሲልም በዚኹ ዕለት መንፈሳዊ ግብራትን አብልጣችኁ ሥሩበት፤ ከእግዚአብሔር ጋር ተገናኙበት፤ ከሥጋዊ ሥራም ዕረፉ ሲል ነው /ዘጸ.፳፡፰/፡፡
ጾምን
መቀደስ ማለትም ጾምን ለእግዚአብሔር መለየት፣ ፈቃደ እግዚአብሔርን ለመሥራት መለየት ማለት ነው፡፡ ጾማችንን
ለእግዚአብሔር ስንለይ በጾማችን ውስጥ ዋናው ትኵረታችንን የሚወስደው እግዚአብሔር እንጂ ሌላ አይኾንም፡፡
ታድያ ጾማችንን እንዴት እንቀድሰው?
ከምንም በፊት የጾምን ዓላማና ጥቅም ልንረዳ ያስፈልጋል፡፡ የጾም
ዓላማ ሰው እንዲራብና እንዲጠማ ማድረግ አይደለም፡፡ የጾም ዓላማ ሰው ከእንስሳዊ ባሕርዩ ከፍ ብሎ መልአካዊ
ባሕርዩን እንዲለማመድ ማድረግ ነው፡፡ አዳም የሞት ሞት የሞተው ይኽን ማድረግ ሲያቅተው ነውና፡፡ ከአዳም የተወለደ
ኹሉ የሥጋውን ፈቃድ እየተከተለ በኃጢአት ላይ ኃጢአትን እየጨመረ የኼደውም ስለዚኹ ነው /ሮሜ.፰:፩/፡፡ ክብር ይግባውና ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚኽ ምድር መጥቶ ይኽን ወደ ጥንተ ተፈጥሮው ሲመልሰው አገልግሎቱን በጾም የዠመረውም ስለዚኹ ነው /ማቴ.፬፡፬/፡፡
አምላካችን እግዚአብሔር በመንፈሳዊ ሕይወታችን ዘወትር እንድናድግ ምን እንደሚያስፈልገን ያውቃል፡፡ እንደ አፍቃሪ አባትነቱ ለእኛ ለልጆቹ ያለው ጥቅም እንደምን ታላቅ እንደኾነ ስለሚያውቅም ጾም የተባለ ስጦታ ሰጠን፡፡ በመኾኑም ጾም እንዲኹ ትእዛዝ ብቻ ሳይኾን መለኮታዊ ስጦታ እንደኾነ ማወቅና መረዳት አለብን! ይኽን የተረዳን እንደኾነ ጾማችንን ቅዱስ ለማድረግ አንቸገርምና፤ ቢያንስ ቢያንስ ቅዱስ ለማድረግ እንጥራለንና፡፡
ለምንድነው
የምንጾመው? ስንጾም ምንን ዓላማ አድርገን ነው? የምንጾመው ቤተ ክርስቲያን ጾም ነው ብላ ስላወጀች ነውን?
እንዲኽ ከኾነ ጾማችን የተሟላ አይደለም፡፡ ለሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን መታዘዝ ጥሩ ነው፤ ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን
ጾምን ስታውጅልን ከእግዚአብሔር ጋር እንድንገናኝ ብላ እንጂ በእኛ ላይ ሸክም ለመጫን እንዳልኾነ ግን መገንዘብ
አለብን፡፡
ለምንድነው
የምንጾመው? ፈቃደ ሥጋችንን ለማድከም? ፈቃደ ሥጋን ማድከም በራሱ ግን ግብ አይደለም፤ ወደ ቀጣዩ ደረጃ
ልንሸጋገር ይገባናል እንጂ፡፡ እርሱስ ምንድነው? ፈቃደ ነፍሳችንን ማበርታት፡፡ ፈቃደ ነፍስስ ምንድነው?
እግዚአብሔርን ዓላማ ያደረገ ጾም መጾም፡፡ ፈቃደ ነፍሳችን ሲበረታ ለጸሎት እንነሣሣለን፡፡ ቃለ እግዚአብሔርን
ለማንበብ እንበረታለን፡፡ ለተራቡና ለተጠሙ ማዘንን እንማራለን፤ መማር ብቻ ሳይኾን ቸርነትን (ምጽዋትን) ማድረግ
እንለማመዳለን፡፡ ከንስሐ አባቶቻችን ጋር ያለን ግንኙነት የጠበቀ ይኾናል፡፡ በሌላ አገላለጥ ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነት ይጠነክራል፡፡
ብዙዎቻችን የምንታለለው እዚኹ ደረጃ ላይ ስንደርስ ነው፡፡ ጾም ሥጋን ለማስራብ ሳይኾን ነፍስን ለመመገብ መኾኑን እንዘነጋለን፡፡
አንዳንዶቻችን
ጓደኞቻችን ስለሚጾሙ ብቻ እንጾማለን፡፡ አንዳንዶቻችን “ሰው ምን ይለኛል?” ብለን እንጾማለን፡፡ አንዳንዶቻችን
ሐኪም “ሥጋ መብላት የለብኽም” ስላለን ብቻ እንጾማለን፡፡ ክብደት ለመቀነስ የምንጾምም ጥቂቶች አይደለንም፡፡
የምንጾመው ከእነዚኽ በአንዱ ምክንያት ከኾነ ባንጾም ይሻለናል፡፡ ምክንያቱም በእነዚኽ ውስጥ አንድም ቦታ
እግዚአብሔር የለበትምና፡፡ እግዚአብሔርን ዓላማ ያላደረገ ጾምም ሥጋችንን ከመጕዳቱም በላይ ለነፍሳችን አንዳች
የሚያተርፈው ጥቅም የለውም፡፡ በሌላ አገላለጥ ብንጾምም ጾማችን የተቀደሰ (ለእግዚአብሔር የተለየ) አይደለም፡፡
በመኾኑም ስንጾም የምግብ ለውጥ ሳይኾን የሕይወት ለውጥ ሊታይብን ይገባል፡፡
እድፈታችንን አስወግደን ከእግዚአብሔርና ከሰዎች ጋር ያለንን ፍቅር (ኅብረት) የምናጐለምስበት መኾን አለበት፡፡
እንዲኽ ካልኾነ ለምን እንጾማለን? እስኪ ራሳችንን እንጠይቀው፡፡ ስንት አጽዋማት አለፉ? እኛስ ምን ያኽል
ተለወጥን? ያው ከኾንን ስለምን ራሳችንን እንጐዳለን? ቤተ ክርስቲያናችን በዓመት ፯ የአዋጅ አጽዋማት እንዳሏት
አብዛኞቻችን ጠንቅቀን እናውቃለን፡፡ ታድያ ምን ያኽሎቻችን ነን በእነዚኽ አጽዋማት የተለወጥነው? ምን ያኽሎቻችን
ነን ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ኅብረት ያጠነከርነው?
ጾም ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ማክበር ብቻ አይደለም፤ ከዚያ ባለፈ ራሳችንን የምንለውጥበት መሣሪያ ነው እንጂ፡፡ ርግጥ ነው ኹል ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት የጠበቀ መኾን አለበት፡፡ በወርኃ ጾም ግን የበለጠ ሊኾን ይገባል፡፡ ለምን? በዚኽ ወራት የበረታን እንደኾነ በሌላው ጊዜ አንቸገርምና፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!
No comments:
Post a Comment