Monday, May 12, 2014

መንፈሳዊ ሕይወት ከትንሣኤ እስከ ጰራቅሊጦስ - ክፍል ፭



(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ግንቦት ፬ ቀን፣ ፳፻፮ ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

4. እንገለጣለን፡፡
  እስከ ፍጻሜ ድረስ በዚኽ በተቀመጥንበት ስፍራችን የምንቈይ ከኾነ ክርስቶስ በክብር በሚገለጥበት ወራት በክብር እንገለጣለን፡፡ ከተቀመጥንበት ሰማያዊ ስፍራችን ለቅቀን የምንነሣ ከኾነ ግን የምንገለጠው ከክርስቶስ ጋር በክብር አይደለም፤ የዲብሎስን መልክ ይዘን በሐሳር ነው እንጂ፡፡ ስለዚኽ አኹን ከዚያ ስፍራ ለቅቆ መኖር የእኛ መገለጫ አይደለም፡፡ ይኽ ሕይወት ሌላ፣ ያም ሕይወት ሌላ ነውና፡፡ ክርስቶስ አኹን አልተገለጠም፡፡ የእኛም ሕይወት ገና አልተገለጠም፡፡ ስለዚኽ በክብር እስክንገለጥ ድረስ እዚያ ልንቈይ ያስፈልጋል፡፡ መቼ ነው ታድያ የምንገለጠው? ሕይወታችን ክርስቶስ በክብር ሲገለጥ፤ ዳግም ሲመጣ፡፡ እርሱ ሲገለጥ ሕይወታችን ይገለጣል፤ ክብራችን ይገለጣል፤ ደስታችን ይገለጣል፡፡

  ብዙ ሃብትና ንብረት፣ እንዲኹም ሥልጣን ያለው ሰው የቅምጥልነት ኑሮ ደስ ያሰኟል፡፡ ብዙ ልብላ ልጠጣ ስለሚልም በብዙ በሽታዎች ይያዛል፡፡ ለእርሱ አብዝቶ መብላቱና መጠጣቱ እንጂ በበሽታ እየተያዘ መኾኑን አያስተውለውም፡፡ ይኽን የተረዱ ወዳጆቹ ከዚኽ በሽታ ሊያስለቅቁት ቢሞክሩ እንኳን ሊጠላቸው ይችላል፡፡ “የእኔን ጥሩ ነገር የማይሻ፣ ቀናተኛ” ብሎም ሊሰድባቸው ይችላል፡፡ ታድያ ይኼ ሰው እንደምን ክብርን አገኘ፤ እንደምን ደስታን ገንዘብ አደረገ ልንለው እንችላለን? ይኽ ሰው በበሽታ ተያዘ እንጂ እንደምን ከበረ፤ ተደሰተ እንሏለን?
   ከደዌ ዘሥጋ ይልቅ ደዌ ዘነፍስ እጅግ አደገኛ ነው፡፡ በሥጋው የታመመ ሰው ለሐኪም አልታዘዝ ቢል ደዌው እየጠናበት ይኼዳል፡፡ በነፍስ የታመመ ሰውም ለዚኽ ከዳረገው ነገር እንዲወጣ ሲነገረው እሺ ካላለ ኹለንተናው እየመረቀዘ ይኼዳል፡፡ ተወዳጆች ሆይ! ሥጋ እየታመመ ሲኼድ እንደምን ሰውነት እንደሚደክም እናውቋለን፤ እንደምን ዓቅም እንደሚያጣ እንረዷለን፡፡ ክብርና ደስታ በሚመስል ነገር ነፍሳችንን ስናዋርዳትና ስናሳምማትማ እንደምን አትደክም? እንደምን ዓቅሟን አታጣ? ለዚኽ ኹሉ ምንጭስ ክብር ወይም ደስታ ነው ብለን ያሰብነው በተለይ ደግሞ በዚኽ ወራት እጅግ የሚዘወተረው ጭፈራው፣ መዝናናቱ፣ ሃብቱ፣ ንብረቱ አይደለምን? እንኪያስ ደጋግመን እንደተናገርነው ሰማያዊ ስፍራችንን አንልቀቅ፡፡ ክርስቶስ በመጣ ጊዜ እውነተኛው ትንሣኤያችንና ክብራችን ይገለጥ ዘንድ የእኛ ባልኾነ አገላለጥ አንገለጥ፡፡ የዚኽን ወራት ዓላማ አንሳተው፡፡
ይቀጥላል…

No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount