Sunday, April 24, 2016

ስግደት - ክፍል 2



በዲ/ን ሕሊና በለጠ ዘኆኅተ ብርሃን
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሚያዝያ 16 ቀን፣ 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
በክፍል አንድ ጽሑፍ ስለ ስግደት ምንነት በወዲቅ በአስተብርኮ በአድንኖ የሚሰገዱ የስግደት አይነቶችን ለእግዚአብሔር ብቻ የሚሰገድ የባሕሪይ ስግደትን ለቅዱሳን የሚሰገድ የጸጋ ስግደትን መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት አድርገን አይተናል፡፡ ለቅዱሳን እንድንሰግድ ያስተማረን እግዚአብሔር መሆኑንም በመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃነት ተመልክተናል፡፡
በዚህ በሁለተኛው ክፍል ትምህርታችን ደግሞ የሚሰገድባቸውና የማይሰገድባቸው ጊዜያት ለመላእክት፣ ለቅዱሳንና ለቅዱሳን ንዋያት የሚሰገድ ስግደትን የእግዚአብሔር መልአክ ባለራእዩ ዮሐንስን አትስገድልኝ የማለቱን ምሥጢር እናያለን፡፡

የሚሰገድባቸውና የማይሰገድባቸው ጊዜያት
ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን በሃይማኖት ይዘትም (Content of Faith) ሆነ በሃይማኖት ሥርዐት (Expression of Faith) ፍጽምት ነች፡፡ የሃይማኖት ይዘቷ (ዶግማዋ) ይህ ይቀረዋል ተብሎ የማይጨመርበት በእግዚአብሔር አንድ ጊዜ ፍጹም ሆኖ ለቅዱሳን የተሰጠ ነው፡፡ (ይሁዳ 3) እግዚአብሔርን የምታመልክበት ሥርዐትም እንዲሁ መንፈስ ቅዱስ በመራቸው ቅዱሳን ሰዎች የተቀነነ ቅዱስ ሥርዐት ነው፡፡ ጊዜንና ቦታን በመዋጀትም (ግንዛቤ ውስጥ በማስገባትም) እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ሥርዐትን እንድትሠራ ቀኖና አለ፡፡
ከዚህ አንጻር ስግደትንም በተመለከተ መች ሊሰገድ እንደሚገባና መች እንደማይሰገድ ሥርዐትን ሠርታልናለች እንጂ እንዲሁ በዘፈቀደ እንዲተገበር ቸል አላለችም፡፡
. የሚሰገድባቸው ጊዜያት የሚከተሉት እንዲሰገድባቸው የታዘዙ ጊዜያት ናቸው፤
1. በጸሎት ጊዜ ስግደትን ከሚያነሣ አንቀጽ ሲደርስ
ፍትሐ ነገሥቱ እንዲህ ይላል፡- “የሚሰገድባቸው ጊዜያቶችና ቁጥሮች በቤተ ክርስቲያን ተጽፈዋል፡፡ የሚጸልይ ሰው በጸሎት ጊዜ ስግደትን ከሚያነሣ አንቀጽ ሲደርስ ለልዑል እግዚአብሔር ይስገድፍት. መን. አን. 14 . 536
ለጸሎት በምንዘጋጅበት ጊዜ ከሚያስፈልጉ 6 ነገሮችም አንዱ ስግደት መሆኑን ፍትሐ ነገሥቱ ከላይ በተጠቀሰው አንቀጽ ከቁጥር 528-535 ድረስ ይገልፃል፡፡ ስለዚህ በጸሎት ጊዜ ስግደትን የሚያነሣ ንባብ ስናገኝ እንዲሁም ስግደትን የሚያነሣ ንባብ ባናገኝም መስገድ ከስድስቱ የጸሎት ይዘቶች አንዱ ነውና መስገድ ይገባል፡፡
2. በጾም ወራት
ጾም የሚቀደሰው በጸሎት በምጽዋት በዕንባና በስግደት ነው፡፡ ስለዚህ በጾም ወራት ጾማችንን ቅዱሱ የሚቀበለው ቅዱስ ጾም ለማድረግ መስገድ ተገቢ ነው፡፡
3. በሰሙነ ሕማማት
ሰሙነ ሕማማት በጾም በጸሎት በስግደት የሚከበር ልዩ በዓል ነው፡፡ ጾሙም ስግደቱም ጸሎቱም የሚበረታበት የመጨረሻው የዐቢይ ጾም ሳምንት ነው፡፡ (ስለ ሰሙነ ሕማማትና ስግደት እግዚአብሔር ቢፈቅድ በቀጣይ ክፍል በዝርዝር እንጽፋለን)
4. በቅዳሴ ጊዜ
በቅዳሴ ጊዜ መስገድ እንደሚገባስግዱ ለእግዚአብሔር በፍርሐትንስግድአድንኑ አርእስቲክሙ ቅድመ እግዚአብሔር አምላክነበንስሐ ውስጥ ያላችሁ ራሳችሁን ዝቅ ዝቅ አድርጉእና የመሳሰሉት የቅዳሴ ይዘቶችና ምንባቦች (ዜማዎች) ምስክር ናቸው፡፡ እዚህ ቅዳሴ ምሥጢርነቱና አምልኮነቱ ሲገለፅ አንዱ ይዘቱ ስግደት መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡
5. በንስሐ ጊዜ
በንስሐ ውስጥ ያላችሁ ራሳችሁን ዝቅ ዝቅ አድርጉየሚለው ንባብ በንስሐ ውስጥ መስገድ እንደሚገባ የሚያመለክት ነው፡፡ (ራስን ዝቅ በማድረግ መስገድ በክፍል አንድ እንዳየነው አድንኖ እንደሚባል ልብ ይሏል፤) ሌላው ሊታወስ የሚገባው ጉዳይ የንስሐ አባቶች በንስሐ ውስጥ ላሉ ልጆቻቸው ስግደትን ቀኖና አድርገው መስጠታቸው ነው፡፡ ስለዚህ ስግደት የንስሐ ሕይወት አንዱ አካል ነው፡፡
6. ስንሳለም
ቤተ ክርስቲያንን ስንሳለም መስገድ ተገቢ ነው፡፡ ስንሳለም እንዲህ እያልን ነው፡-
ሰላም ለኪ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን፣ አምሳለ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት፣ ማኅደረ መለኮት፣ ምስኣል ወምስጋድ ወመሥተሥርየ ኃጢአት
ስንሳለም በምንናገረው አጭር ጸሎት ውስጥ “...ምስአል ወምስጋድማለታችን መስገድ እንደሚገባን የሚጠቁም ነው፡፡ መስቀልን መጽሐፍ ቅዱስን ቅዱሳት መጻሕፍትን ቅዱሳት ሥዕላትን ቅዱሳት ቦታዎችን ...ወዘተ ስንሳለም በተመሳሳይ መልኩ መስገድ ተገቢ ነው፡፡
 . የማይሰገድባቸው ጊዜያት
የሚሰገድባቸው ጊዜያት እንዳሉት ሁሉ የማይሰገድባቸው ጊዜያትም አሉ፡፡ እነዚህ ስግደት የተገዘተባቸው ጊዜያት የሚከተሉት ናቸው፡፡
1. በዕለተ እሑድ
ከአልቦ ነገር ወይም ከምንም (ex-nihilo – from nothingness) የተፈጠረ ፍጥረት ሁሉ ክርስቶስ ዳግም ሲመጣ ጠፍቶ ወደ ምንምነት ሲቀየር ከማይጠፉ ከአምስቱ ፍጥረታት አንዷ ሰንበት ናት፡፡ ጌታ የተነሣባት ዳግምም የሚመጣባት ዕለት ናት፡፡ በዚህና በሌሎች ምክንያቶችም ሰንበተ ክርስቲያን እሑድ በዓል ነች፡፡ ስለዚህ በዕለተ እሑድ መስገድ የተከለከለ ነው፡፡
ይህንን ፍትሐ ነገሥቱ እንዲህ በማለት ይገልፀዋል፡- “ከአድንኖና ከአስተብርኮ በቀር እስከ ምድር መስገድን የሚተዉባቸው የታወቁ ጊዜያቶች እነዚህ ናቸው፡፡ ኒቅያ 20 በዕለተ እሑድና በበዓለ ሃምሳ ወራት፣...” ፍት.መን. አን. 14 . 537
ይህንን ይበልጥ ሲያጸናው በሰንበታትና በበዓላት አንቀጹ እንዲህ ሲል ደግሞታል፡- “በእሑድና በተከበሩት በዓላት ቀን ስግደት አይገባም፤ እነዚህ የደስታ ቀኖች ናቸውናፍት. መን. አን. 19 . 715
2. በበዓለ ሃምሳ ወራት
በዓለ ሃምሳ የፍስሐና የሰላም ጊዜ ነው፡፡ ስሙ እንደሚጠቁመው ሃምሳውም ቀን በሙሉ በዓል ነው፡፡ በዓል ስለሆነም እንደ ፋሲካና እንደ ልደት እንበላበታለን እንጂ ረቡዕና አርብ ቢሆን እንኳን አንጾምበትም፡፡ በበዓልነቱ ጾም እንደተሻረበት ስግደትም እንዲሁ ይሻርበታል፡፡ ከላይ እንዳየነው ፍትሐ ነገሥቱም በፍት.መን. አን. 14 . 537 በእሑድ መስገድን ሲከለክል በበዓለ ሃምሳም እንዲሁ ከልክሏል፡፡
3. በጌታችን በዓላት
ፍትሐ ነገሥቱበእሑድና በተከበሩት በዓላት ቀን ስግደት አይገባም፤ እነዚህ የደስታ ቀኖች ናቸውና” (ፍት.መን. አን. 19 . 715) ካለ በኋላየተከበሩት በዓላትያላቸው የትኞቹን እንደሆነ ሲዘረዝር ትስብእት/ጽንሰት ልደት ጥምቀት ሆሣዕና ትንሣኤ ዕርገት በዓለ ሃምሳ ደብረ ታቦር በማለት ከጌታ ዘጠኝ ዐበይት በዓላት 8ቱን ይገልፃል፡፡ ሳይገለፅ የቀረው ስቅለት ነው፤ ያልተገለፀበትም ምክንያት በስቅለት ስግደት ስለማይከለከል ነው፡፡ (ይህንን በክፍል ሦስት በዝርዝር ለማየት እንሞክራለን) ስለዚህ ከስቅለት በቀር በጌታ ዐበይት በዓላት (በተቀሩት 8) ስግደት የተከለከለ ነው፡፡
ፍትሐ ነገሥቱ ይህንን ሲያጸና በአንቀጽ 14 እንዲህ ብሏል፡- “መስገድን የሚተዉባቸው የታወቁ በዓላት እነዚህ ናቸው.... ኒቅያ 32 በጌታችን በዓላትና በእመቤታችን በዓላትፍት.መን. አን. 14 . 536-537፡፡
4. የእመቤታችን በዓላት
ከላይ ያየነው የፍትሐ ነገሥት ንባብ በፍት. መን. አን. 14 . 536-537 ድረስ በጌታ በዓላት መስገድ እንደተከለከለው ሁሉ በእመቤታችን በዓላትም መከልከሉን ይጠቁመናል፡፡ ይህንን ሥርዐት እንዴት እንደምንተገብርና የማይሰገድበት የእመቤታችን በዓል የትኛው እንደሆነ ከታች 6 ቁጥር እንመለከተዋለን፡፡
5. ሥጋውንና ደሙን ከተቀበሉ በኋላ
የሥርዐት ምንጫችን የሆነው ፍትሐ ነገሥት አሁንም በዚህ ዙሪያ እንዲህ ብሏል፡- “መስገድን የሚተዉባቸው የታወቁ በዓላት እነዚህ ናቸው... ሥጋውንና ደሙን ከተቀበሉ በኋላይላል፡፡ ፍት. መን. አን. 14 . 536-537፡፡
ሥጋውንና ደሙን ከተቀበልን በኋላ ከሚሰገድለት እንጂ ከማይሰግደው ጋር አንድ መሆናችንን ለማጠየቅና ለቅዱስ ሥጋውና ለክቡር ደሙ ክብር ስንል ዝቅ ብለን አንሰግድም፡፡
6. 12 21 29
ከሌሎቹ የግዝት ወቅቶች ይልቅ እነዚህ ዕለታት በአብዛኛው ምዕመን የታወቁ ናቸው፡፡ ዕለታቱን የግዝት ያደረገው ሥርዐት ምንጭ ከላይ ያየናቸው የፍትሐ ነገሥት ምንባባት ናቸው፡፡
29 በዓለ ወልድ ብለን የጌታን በዓላት እንደምናስብ ይታወቃል፡፡ በፍትሐ ነገሥትም የጌታችን በዓላት እንደማይሰገድባቸው ሲጠቀስ ምንም እንኳን በአንቀጽ 19 9 ዐበይት በዓላት ስምንቱን ቢገልፅም አንቀፅ 14 ግን ከላይ እንዳስነበብነውየጌታችን በዓላት የእመቤታችን በዓላትብሎ ማለፉን መርጧል፡፡
የጌታችን በዓላት የተባሉ 9 የጌታ በዓላት ውጪ 9 ንዑሳን በዓላትም አሉ፡፡ እነዚህም ስብከት ብርሃን ኖላዊ ግዝረት ልደተ ስምዖን ቃና ዘገሊላ ደብረ ዘይት ጌና መስቀል ናቸው፡፡ ፍትሐ ነገሥቱ በእነዚህ ዙሪያ የዘረዘረው ግልፅ ነገር የለም፡፡ ሆኖም የጌታ በዓላት ስለሆኑና በጌታ በዓላት ደግሞ ስግደት ስለተከለከለ አባቶቻችን እነዚህን የጌታ (የወልድ) በዓላት በአንድነት ወር በገባ 29 በዓለ ወልድ ብለን እንድናስብና፣ ዕለቱም ስለ በዓላቱ የግዝት ዕለት እንዲሆን የተደረገ ይመስላል፡፡ ስለዚህ አይሰገድበትም፡፡
ከዘጠኙ ዐበይትና ከዘጠኙ ንዑሳን በዓላት ውጪ ሰሙነ ሕማማትና ሰሙነ ትንሣኤም የጌታ በዓላት በመባል ይታወቃሉ፡፡ ሰሙነ ሕማማት በስግደት እንዲከበር ቤተ ክርስቲያን ታዛለች፡፡ (ይህን በዝርዝር በክፍል 3 እናያለን)፡፡ ሰሙነ ትንሣኤን ግን ከሰሙነ ሕማማት በተለየ ሁኔታ እናከብረዋለን፡፡ ሰሙነ ትንሣኤ የሚባለው ከትንሣኤ በኋላ ያለው እስከ ዳግም ትንሣኤ ያሉትን ቀናት የያዘው ሳምንት ነው፡፡ ሰሙነ ሕማማትን በፍጹም ሐዘን በጾም በስግደት እንዳከበርበው ሁሉ ሰሙነ ትንሣኤን ደግሞ በፍጹም ደስታ እንድናከብረው ትዕዛዝ አለ፡፡ ስለዚህ ሰሙነ ሕማማትን ስቅለትን በዋናነት በማሰብ በብዙ ስግደት ስናከብር ሰሙነ ትንሣኤን ደግሞ ትንሣኤውን በማሰብ በብዙ ደስታ ካለ ስግደት እናከብረዋለን፡፡
ፍትሐ ነገሥቱ የማይሰገድባቸውን ጊዜያት ሲጠቅስየጌታችን በዓላት የእመቤታችን በዓላትማለቱን ከላይ ጠቅሰናል፡፡ የጌታን ንዑሳን በዓላት ወር በገባ 29 አስበን እንደማንሰግደው ሁሉ የእመቤታችንንም በዓላት 21 አስበን አንሰግድም፡፡ ስለዚህ ወር በገባ 21 ሁሌም የግዝት በዓል ነው፤ አይሰገድበትም፡፡
12 የቅዱስ ሚካኤል በዓል እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የቅዱስ ሚካኤል በዓል ከሌሎች የመላእክት በዓላት ተለይቶ መከበሩ ለምንድነው ቢሉየቅዱስ ሚካኤል በዓል መላእክትን ወክሎ ወርኃዊ ሆኖ እንዲከበር ታዟል” (በዓላት .. ብርሃኑ አድማስ ገጽ 124)፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን 12 እንዳይሰገድና እንደ ታላላቅ በዓላት በደስታ እንዲከበር ሥርዐትን ሠርታለች፡፡
የሚሰገድባቸውና የማይሰገድባቸው ዕለታት ሲገጥሙ ምን ይደረጋል? ለምሳሌ የግዝት በዓላት በሰሙነ ሕማማት ቢውሉ ምን ይደረጋል? የዘንድሮው ስቅለትም 21 ነው፤ ታዲያ እንሰግዳለን ወይስ አንሰግድም? የእነዚህን መልስ የያዘውንና ሰሙነ ሕማማት ላይ ያተኮረውን የስግደት የመጨረሻ ጽሑፍ በቀጣይ ክፍል ይጠብቁ፡፡
(የእግዚአብሔር መልአክ ባለራእዩ ዮሐንስን አትስገድልኝ የማለቱን ምሥጢርና ለመላእክት ስግደት እንደሚገባ የሚያስረዳውን ትንታኔ ጽሑፉ በጣም ስለረዘመ በዚህኛው ክፍል ላካትተው አልቻልኩም፡፡ በቀጣይ ክፍል ያገናኘን፡፡)
ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን፡፡

4 comments:

  1. መምህር እያንዳንዳችን ክርስቲያኖች ልንማረው የሚገባነን አስተምረውናልና ቃለ ሕይወት ያሰማልን፡፡ቁጥሮችን በተመለከተ ግን የቤተ ክርስቲያናችን ቢጠቀሙ እጅግ ጥሩ ነው ፡፡ እናንተ መምህራን ከተዋችሁት ትውልዱን ማን ያስተምረዋል ? ታሪክ ብቻ ሁኖ ይቀራል እንጂ ባይሆን ግልጽ እንዲሆን በቅንፍ ቢቀመጥ ትምህርት ይሆነናል ፡፡ እግዚአብሔር አምላክ የአገልግሎት ዘመንዎን ያርዝምልን ይባርክልን አሜን !!!መምህር እያንዳንዳችን ክርስቲያኖች ልንማረው የሚገባነን አስተምረውናልና ቃለ ሕይወት ያሰማልን፡፡ቁጥሮችን በተመለከተ ግን የቤተ ክርስቲያናችን ቢጠቀሙ እጅግ ጥሩ ነው ፡፡ እናንተ መምህራን ከተዋችሁት ትውልዱን ማን ያስተምረዋል ? ታሪክ ብቻ ሁኖ ይቀራል እንጂ ባይሆን ግልጽ እንዲሆን በቅንፍ ቢቀመጥ ትምህርት ይሆነናል ፡፡ እግዚአብሔር አምላክ የአገልግሎት ዘመንዎን ያርዝምልን ይባርክልን አሜን !!!

    ReplyDelete
  2. ቃለ ህይወት ያሰማልን

    ReplyDelete
  3. ቃለ ህይወት ያሰማልን መምህር ፈጣሪ እግዚአብሔር ያሠቡትን መልካም ነገር ሁሉ ያሣካሎት!!

    ReplyDelete
  4. ቃሌ ሕይወት ያሰማልን

    ReplyDelete

FeedBurner FeedCount