በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
በ33ኛ ሳምንት ጥናታችን እንደተናገርን አይሁድ የዳስ በዓልን የሚያከብሩት
ሰባት ቀን ሙሉ እንደ አንድ ቀን ነው /ዘሌ.23፡34/፡፡ በበዓሉ እኩሌታ ማለትም በአራተኛው ቀንም ጌታ በሕቡዕ ያይደለ በይፋ
በስዉር ያይደለ በግልጥ ማስተማሩን መገሰጹን ተመልክተናል፡፡ አሁን ደግሞ በበዓሉ በኋለኛው ቀን፣ የደስታ ቀን ብለው በሚያከብሩበት በመካተቻው፣
በመጨረሻው፣ በመሰባበቻው ቀን እንዲህ ብሎ አሰምቶ ተናገረ፡- “ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ። በእኔ የሚያምን መጽሐፍ እንዳለ፥ የሕይወት ውኃ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል” /ቁ.37-38/። እንዲህ ማለቱ ነበር፡- “ማንም ጽድቅን የተጠማ ቢኖር፣ ማንም ሕይወትን
የናፈቀው ቢኖር፣ ማንም መንግሥተ ሰማያትን መውረስ የሚፈልግ ቢኖር፣ ማንም እኔ የምሰጠውን የጽድቅ ውኃ መጠጣት የሚሻ ቢኖር፣ ማንም
እኔ የምሰጠውን ሀብታተ ምሥጢራትን ጸጋውን መቀበል የሚፈልግ ቢኖር… ወደ እኔ ይምጣ፤ በእግረ ሥጋ ሳይሆን በእግረ እምነት ወደ
እኔ ይቅረብ፤ በእግረ በቀል ሳይሆን በእግረ ፍቅር ወደ እኔ ይጠጋ፤ ቀርቦም የምሰጠውን ውኃ ይጠጣ፤ መጥቶም ከዙፋኔ የሚወጣውን እንደ ብርሌም ከሚያንጸባርቀው የሕይወትም ውኃ ከሚሆን ወንዝ
ይጠጣ ይቀበል /Augustine, On the Gospel of St. John, tractate
32:2./፡፡ ሙሴ ከሰጠው ጊዜአዊ ጥምንም ከሚያረካው
ውኃ ተላቆ ይምጣና አማናዊውን የሕይወት ውኃ ምንጭ ዐለት በውስጡ ያኑር፡፡ ይህን እንዴት ማግኘት እችላለሁ ብሎ የሚቸገርም ከቶ
አይኑር፡፡ ነቢያት ይወርዳል ይወለዳል ብለው የተናገሩለት፣ ሱባዔ የቆጠሩለት መሲሕ ክርስቶስ እርሱ ነው ብሎ በእኔ ይመንና መጽሐፍ
እንደተናገረ የሕይወት ውኃ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል (በእርሱ ምክንያት ቃሌ ሲነገር ልጅነት ሲሰጥ ብዙዎች ሲያምኑበት ይኖራል)፤ በፈሳሾች
አጠገብ እንደሚበቅሉ እንደ አኻያ ዛፎች ይሆናል /ኢሳ.44፡3/፤ ከተድላ ፈሳሽ ይጠጣል /መዝ.36፡8/፤ የሕያዋን ምንጭ የሚሆን
መንፈስ ቅዱስ ያድርበታል /ኤር.2፡13/፤ የእግዚአብሔርን ቸርነት ይቀምሳል ያያልም /መዝ.34፡8/፤ በኢዩኤል ነብይ የተነገረው
ትንቢት በእርሱ ላይ ይፈጸማል” /ኢዩ.2፡28-32፣ Saint Cyril the Great, Commentary on the
Gospel of John, Book 5/፡፡
ይህም አስቀድመን
እንደተናገርን ያመኑበት
ሰዎች ሊቀበሉት ስላላቸው ሀብታተ መንፈስ ቅዱስ የተናገረው ነው፡፡ ይህን ያለው ምእመናን በመንፈስ ቅዱስ ስለሚያገኙት
ምሥጢር፣ በመንፈስ ቅዱስ ስለሚገኙት ልጅነት ሲገልጽ ነው፡፡ ኢየሱስ ገና ስላልከበረ (ያስተውሉ! ከዚያ በፊት ክብሩ በሰው ዘንድ አልታወቀም አልተገለጠም ነበር ለማለት እንጂ ሎቱ ስብሐትና ክብር
አልነበረውም ማለት አይደለም፡፡ በብዙዎች ዘንድ ጌታ መሆኑ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑ የታወቀው ከስቅለቱ በኋላ ከትንሣኤም በኋላ
ስለ ሆነ ነው) ስላልተሰቀለ መንፈስ
ገና አልወረደም ነበርና /ቁ.39/። ይህ ማለት ግን መንፈስ ቅዱስ ክርስቶስ ከመሰቀሉ በፊት በሰው ልጆች ላይ አልነበረም ማለት
አይደለም፡፡ መንፈስ ቅዱስ በነቢያት ነበረ፤ መጽሐፍ እንደተናገረ አስቀድሞ በእመቤታችን ላይ ወርዷል፤ ወንጌል እንደመሰከረ
መንፈስ በስምዖን አረጋዊ ላይ ነበረ፤ በነቢይቱ ሀና ላይ ነበረ፡፡ ስለዚህ አሁን እየነገረን ያለው አጠቃላይ በቤተ ክርስቲያን
ላይ ከበዓለ ኃምሳ በኋላ ሊሆን ስላለው ሁኔታ ነው /Augustine, tactate 32:7. /፡፡
ከሕዝቡ አያሌ ሰዎች ይህን ቃል ሲሰሙ፣ “ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ
ይምጣ” የሚል የጌታችን የፍቅር ግብዣ ሲያደምጡ በአራት ምድብ ተከፋፈሉ፡፡ በአንደኛው ምድብ የነበሩት “ይህ በእውነት ሙሴ እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሣልሃል ብሎ የተናገረለት ነቢዩ ነው” አሉ /ዘዳ.15፡18/፤ በሁለተኛው
ምድብ የነበሩት፡- “ነቢዩ አይደለም ይህ ክርስቶስ ነው” አሉ፤ በሦስተኛው ምድብ የነበሩትና አወቅን ጠነቀቅን ያሉት ደግሞ፡- “ክርስቶስ በእውኑ ከገሊላ ይመጣልን? ክርስቶስ ከዳዊት ዘር ዳዊትም ከነበረባት መንደር ከቤተ ልሔም እንዲመጣ መጽሐፍ አላለምን?” በማለት ጌታ በናዝሬት ገሊላ ማደጉ ናዝሬት
ገሊላ የተወለደ ስለመሰላቸው ተደናገሩ /መዝ.132፡11፣ ሚክ.5፡2/። አራተኛው ምድብ ደግሞ ከጸሐፍትና ከፈሪሳውያን ከአለቆቹ ጋር ያበሩና ጌታን ለመግደል የሚያስቡ ሎሌዎች
ናቸው፡፡ እነዚህ ሎሌዎች ክርስቶስን ለመያዝ ወደው ነበር ይዘውም ለአለቆቻቸው አሳልፈው ይሰጡት ዘንድ ሽተው ነበር፡፡ ሆኖም ግን
በቃሉ ተማርከው አምነውበታልና አንድም ጊዜው አልደረሰምና ይህን ማድረግ አልተቻላቸውም /ቁ.40-44፣ Saint Cyril the
Great, Ibid/፡፡
አስቀድመን እንደተናገርን የመጨረሻው ቀን ማለት አይሁድ በደስታ
የሚያከብሩት ቀን ነው፡፡ ዛሬ ግን ጸሐፍትና ፈሪሳውያን የደስታ ቀን ሊሆንላቸው አልቻለም፡፡ የደስታ ምንጭ የሆነውን ክርስቶስን
ሊገድሉበት ፈለጉ እንጂ እርሱን ተቀብለው ደስታቸውን ፍጹም ሊያደርጉት አልቻሉም፡፡ ውስጣቸው በቅንአት ተጠፍሯልና ይህን
የክርስቶስ ፍቅር ማየት አልተቻላቸውም፡፡ የደስታ ቀን በሆነው ዕለት መንፈሳዊ ተግባራቸውን ትተው ሊገድሉት የሚፈልጉትን ክርስቶስ
ይጠባበቁ ነበር፡፡ ሆኖም ግን እንዳሰቡት አልሆነላቸውም፡፡
ሎሌዎቻቸው (አራተኛው ምድብ ያልናቸው ናቸው!) ክርስቶስን ሳይዙ
በመጡ ጊዜ፣ አስረን እናመጣዋለን ብለው ሄደው አምነው እየተደነቁ በመጡ ጊዜ፡- “ለምድነው ያላመጣችሁት?” ብለው ተቈጡዋቸው። ሎሌዎቹ
ግን አሳማኝ ምክንያት ነበራቸው፡፡ አለቆቻቸው ባይቀበልዋቸውም እንዲህ ሲሉ ሳይፈሩ አስረድዋቸው፡- “አለቆቻችን ሆይ! ይህን ሰው ለምን ይዛችሁት አልመጣችሁም ብላችሁ የምቆጡን አትሁኑ፤ ይህ ሰው እንደተናገረው በዓለም ታይቶም ተሰምቶም ከቶ ከቶ አይታወቅም፡፡ እኛ መጻሕፍትን
እናውቃለን ብለን እናስብ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ገና አላዋቂዎች መሆናችንን ዛሬ አይተን ተረድተን መጣን፡፡ እርሱ የሚናገረው
ነገር ፍጹም መለኰታዊ ቃል ነውና፡፡ ይህ ሰው የሚናገረው ማንም ምድራዊ መምህር ሊያስተምረው ሊናገረው የሚቻለውም አይደለምና፡፡
ስለዚህ ይህን ሰው ፈጽመን ልንገድለው አይገባንም፡፡ በአፉ ተንኰል አላገኘንበትምና እንደ ሕጋችን ንጹሕ ሰው ልንገድል አይገባንም፡፡
እንደውም በሰቂለ ሕሊና ስናስተውለው ስናደምጠው እንደ እግዚአብሔር በኃይልና በሥልጣን ይናገራል እንጂ እንደ ዕሩቅ ብእሲ
አይናገርም፡፡ ምክንያቱም ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣ ያለ ነቢይ ሰምተንም አይተንም አናውቅምና፡፡ ታላቁ አባታችን ሙሴ
እንኳን አንድ ቀንም ቢሆን በእኔ የሚያምን መጽሐፍ እንዳለ፥ የሕይወት ውኃ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል ሲል አልሰማነውምና፡፡ ይህ
ሰው ግን ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣ፤ በእኔ የሚያምን መጽሐፍ እንዳለ፥ የሕይወት ውኃ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል እያለ በሥልጣን ይናገራል፡፡
የሚናገረው ሁሉ ዕሩቅ ብእሲ የሚናገረው አይደለም” ብለው መለሱላቸው /ቁ.45-46፣St.
Cyril the Great, Ibid/። ተወዳጆች ሆይ! የክርስቶስን ፍቅር
የምታስተውሉ ሁኑ፡፡ ምክንያቱም እነዚህን አለቆች እጅግ ከማፍቀሩ የተነሣ እንዲጠፉበትም ካለመፈለጉ የተነሣ ይመለሱለት ዘንድ
ልባቸው ደንዳና ሆነ እንጂ ሊያደምጥዋቸው በሚችሉ ሰዎች ሲያስረዳቸው ነበርና፡፡
ስለዚህ አለቆቹ ጭራሽ እንዲገባቸው
አልፈቀዱምና ባሰባቸው፡፡ ሎሌዎቻቸውንም፡- “እናንተ ደግሞ እንደነዚያ ሐዋርያት ሳታችሁን?” አልዋቸው /ቁ.47/፡፡ በክርስቶስ ማመን መሳት ነው አሉዋቸው! የሕይወትን ውኃ ማግኘት መታለል ነው
አሉዋቸው፡፡ ከሞት ወደ ሕይወት መሻገር ሞት ነው አልዋቸው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ሕዝቡን እንዲህ አሳምኖ እንዳይወስድባቸው በመጨነቅ “ለመሆኑ
ከተሳሳቱት ሕዝብ በቀር ከአለቆች
ወይስ ከፈሪሳውያን በእርሱ ያመነ አለን?” ብለው ጠየቁዋቸው /ቁ.48/፡፡ አሁንም ብስጭታቸውን ቀጠሉና አስተምረውት የማያውቁትን ሕዝብ “ሕግን ኦሪትን የማያውቀው ይህ
ሕዝብ ርጉም ነው” ብለው ሕዝቡን መሳደብ ጀመሩ፤ ሎቱ ስብሐትና
ክርስቶስን “ዕሩቅ ብእሲ” አድርገውት ፍጡርን የሚያመልኩ እነዚህ የተረገሙ ናቸው አሉ /ቁ.49/። የአምላካቸውን ድንቅ ሥራ አይተው ያመኑትን ሕዝብ ሕግን የማያውቁ እያሉ ወቀስዋቸው፡፡ እንደ እውነቱ
ከሆነ ሕዝቡ አምላኩን አውቆ ስላመነበት ሊበሳጩ አይገባም ነበር፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ሕግን የማያውቁና የተረገሙ ክርስቶስንም
ከማመን የዘገዩ እነርሱ ራሳቸው ነበሩ /St.
John Chrysostom, Homily 52/፡፡
የሚደንቀው ግን ይህን አላዋቂነታቸው ይነግራቸው ዘንድ እግዚአብሔር
በመካከላቸው ምስክር ማስቀመጡ ነው፡፡ እርሱም በሌሊት ቀድሞ ወደ ጌታ መጥቶ የነበረው የማታው ተማሪ ኒቆዲሞስ ነው /ዮሐ.3፡2/፡፡ ብስጭታቸውን
በሰማ ጊዜ፣ ሕዝቡን አላዋቂ ሲሉት ባደመጠ ጊዜ፡- “ኦሪታችን ሥራውን አስቀድሞ
ከእርሱ
ሳይሰማ ምንስ እንዳደረገ ሳያውቅ ሳይመረምር በሰው ላይ ይሙት በቃ ይፈርዳልን?” አላቸው /ቁ.50-51/። እውነት ነው! ኦሪት “ንጹሑን ሰው አትግደል” ትላለች /ዘዳ.19፡16-21/፡፡ ተራውን ሕዝብ በሕግ
አፍራሽነትና በአላዋቂነት እየፈረጁና እየረገሙ እንጠብቀዋለን የሚሉትን ሕግ የሚያፈርሱት እነርሱ ራሳቸው ነበሩ፡፡ ስለዚህ
አላዋቂዎች እነርሱ መሆናቸውን ኒቆዲሞስ ይነግራቸው ነበር፡፡ እነርሱ ግን አሁንም በኒቆዲሞስ ንግግር ተበሳጩ፡፡ “ለምን ታድያ ከገሊላ
መጣ?” ብለው ከመጠየቅ ይልቅ ኒቆዲሞስን መስደብ ጀመሩ፡፡ “አንተም ደግሞ ከገሊላ ነህን? ነቢይ ከገሊላ እንዳይነሣ መርምር አንብብና እይ”
ማለትን አስቀደሙ /ቁ.52/። ለምን ከገሊላ መጣ ብለው ቢጠይቁ ግን
ክርስቶስ እርሱ ኢየሱስ ናዝራዊ ይባል ዘንድ በናዝሬት ገሊላ ያደገ ነገር ግን በቤተልሔም የተወለደ መሆኑን ባወቁ በተረዱ ነበር
/ማቴ.2፡1 እና 23/፡፡ እነርሱ ግን ለስድብ ተቻኮሉ፡፡ በዚህ ንግግራቸው ኒቆዲሞስን እንደ አላዋቂ አድርገው በማየት
መናቃቸው ነበር /St. John Chrysostom, Ibid/፡፡
በመጨረሻም ምንም ሳይስማሙ ተለያይተው እያንዳንዳቸው ወደየቤታቸው ሄዱ /ቁ.53/።
ተወዳጆች ሆይ! ቅናት ክፉ ነው፡፡ ቅናት ዓይነ ልቡናን ያሳውራል፡፡
ቅናት ክርስቶስን ከማየት ይከለክላል፡፡ ቅናት ከዐለቱ (ከክርስቶስ) የሕይወት ውኃ እንዳንጠጣ ያደርጋል፡፡ ሀብታተ መንፈስ
ቅዱስን እንዳንቀበል ያደርጋል፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን “ጕድጓድን የሚምስ ይወድቅበታል፤ ድንጋይንም የሚያንከባልል ይገለበጥበታል”
እንዳለ ቅናት የሚጐዳው ቅናተኛውን ነው /ምሳ.26፡27/፡፡ ቅናት ስለ እኛ የተቸነከረው በደምም የጨቀየውን ያ የፍቅር እጅ
እንዳንመለከት ያደርጋል፡፡ ቅናት ተድላ መንግሥተ ሰማያትን እንድናጣ ያደርጋል፡፡ ወዮ አባት ሆይ! ራሳችንን እንዳንጐዳ በቅዱስ
መንፈስህ ምራን! ከቅናት ከበቀል ጠብቀን! ፈሪሳዊ ቁጣና ብስጭት ከእኛ የራቀ ይሁን! አሜን!