በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሐምሌ ፲፭ ቀን፣ ፳፻፭ ዓ.ም)፡- አንድ ምክርና ታሪክ አካፋይ የሆነኝ
ወዳጄ ጋር ስለ ሙስና ስናወራ የድሮ ሙሰኞች ብያንስ ይሉኝታ ነበራቸው ሲል የተረከልኝ ታሪክ “በርግጥም” አሰኝቶኛል፡፡ እርሱ እንደነገረኝ
ከሆነ አሁን በቅርቡ በደርግ ዘመን አንድ ትልቅ ሰው ሦስት ጊዜ ሎተሪ ደርሷቸው ነበር ይባላል፡፡ እንደሚባለው ከሆነ ሰውዬው ብርቱ
ሙሰኛ ነበሩ፡፡ ነገር ግን ይሉኝታ ስለነበራቸው በማንአለብኝነት በሦስት ሺሕ ደመወዝ የአራት ሚልዮን ብር መኖሪያ ቤትና ባለ ስድስትና
ምናምን ፎቅ እንደሚሠሩት እንደ አሁኖቹ አንዳንድ ሰዎች ዝም ብለው በድፍረት አይሠሩም ነበር፡፡ ሰውዬው በወዳጆቻቸው በኩል ሎተሪ
የደረሰውን ሰው በብርቱ ጥንቃቄ አስፈልገው ራሱን ከማሳወቁ በፊት በትርፍ ይገዙትና እርሳቸው ደረሳቸው እየተባለ ዜና ይወጣላቸዋል፡፡
ለካስ ይህም ብልሃት ኖሯል፡፡ ታድያ እንደ ነገረኝ ከሆነ እስከ ሦስት ጊዜ ሎተሪ ደርሰዋቸዋል ይባላል፤ እኒያን ባለ ይሉኝታ ሰው፡፡
የረሱት ነገር ቢኖር ሦስት ጊዜ ትልልቅ ገንዘብ በሎተሪ የወጣላቸው አስብለው ስማቸውን በድንቃ ድንቅ የዓለም መዝገብ ማሰፈር ብቻ
ይመስለኛል፡፡ ቢያደርጉት ኖሮ ብያንስ በዕድል ለምናምን ሰዎች ትልቅ ማስረጃም ይሆኑ ነበር፤ ግን አላደረጉትም ብሎኛል፡፡ ዛሬ ግን
እንዲህ ያለ ይሉኝታ እንኳ ጠፍቷል፡፡ እንኳን በዓለሙ ሰዎች ዓለሙን ትተናል ከምንለውና ገቢያችን እንትን ከሆነው እንኳ በዓይነቱ
ልዩ የሆነ ቤት ሠርቶ እንኳን ሊታፈር ደግሶ ማስመረቅ ከተለመደ ሰንብቷል፡፡ ነገሩ ድሮ እንኳን ሰው ሰይጣኑም አፋራም ነበር ይመስለኛል፡፡
ምክንያቱም ዛርና ጥንቆላ እንደዛሬው በባሕታውያንና በአጥማቂ ወይም በመሳሰለው ስም ይነግድ እንደነበር አልሰማሁም፡፡ እዚያው በየሠፈራቸው
አንዴ ገብስማ ዶሮ ሌላ ጊዜም ሌላ እያሉ ይሠሩ ነበር እንጂ እንዲህ እንደ ዛሬው ለይቶላቸው አንዳንድ መንፈሳዊ ቦታዎች ላይ ሳይቀር
ገብተው በቃሁ ነቃሁ አይሉም ነበር፡፡ ታድያ ብዙ ጊዜ ፕሮፌሰር መስፍን ከሀገር ፍቅር ቲያትር የሰማሁት ብለው በአንድ መድረክ ላይ
ሲናገሩት የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ያሰማኝ “ማፈር ቀረ፤ መሽኮርመም ቀረ” ትዝ ይለኛል፡፡ በርግጥም ነገሩን ሁሉ ለሚያስተውል ነውርም፣
ማፈርም፣ ይሉኝታም ተሰብስበው ገደል የገቡና ቃላቱ ብቻ የተረፉ ይመስላሉ፡፡