Sunday, July 21, 2013

ማፈር ቀረ!!!

በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሐምሌ ፲፭ ቀን፣ ፳፻፭ ዓ.ም)፡- አንድ ምክርና ታሪክ አካፋይ የሆነኝ ወዳጄ ጋር ስለ ሙስና ስናወራ የድሮ ሙሰኞች ብያንስ ይሉኝታ ነበራቸው ሲል የተረከልኝ ታሪክ “በርግጥም” አሰኝቶኛል፡፡ እርሱ እንደነገረኝ ከሆነ አሁን በቅርቡ በደርግ ዘመን አንድ ትልቅ ሰው ሦስት ጊዜ ሎተሪ ደርሷቸው ነበር ይባላል፡፡ እንደሚባለው ከሆነ ሰውዬው ብርቱ ሙሰኛ ነበሩ፡፡ ነገር ግን ይሉኝታ ስለነበራቸው በማንአለብኝነት በሦስት ሺሕ ደመወዝ የአራት ሚልዮን ብር መኖሪያ ቤትና ባለ ስድስትና ምናምን ፎቅ እንደሚሠሩት እንደ አሁኖቹ አንዳንድ ሰዎች ዝም ብለው በድፍረት አይሠሩም ነበር፡፡ ሰውዬው በወዳጆቻቸው በኩል ሎተሪ የደረሰውን ሰው በብርቱ ጥንቃቄ አስፈልገው ራሱን ከማሳወቁ በፊት በትርፍ ይገዙትና እርሳቸው ደረሳቸው እየተባለ ዜና ይወጣላቸዋል፡፡ ለካስ ይህም ብልሃት ኖሯል፡፡ ታድያ እንደ ነገረኝ ከሆነ እስከ ሦስት ጊዜ ሎተሪ ደርሰዋቸዋል ይባላል፤ እኒያን ባለ ይሉኝታ ሰው፡፡ የረሱት ነገር ቢኖር ሦስት ጊዜ ትልልቅ ገንዘብ በሎተሪ የወጣላቸው አስብለው ስማቸውን በድንቃ ድንቅ የዓለም መዝገብ ማሰፈር ብቻ ይመስለኛል፡፡ ቢያደርጉት ኖሮ ብያንስ በዕድል ለምናምን ሰዎች ትልቅ ማስረጃም ይሆኑ ነበር፤ ግን አላደረጉትም ብሎኛል፡፡ ዛሬ ግን እንዲህ ያለ ይሉኝታ እንኳ ጠፍቷል፡፡ እንኳን በዓለሙ ሰዎች ዓለሙን ትተናል ከምንለውና ገቢያችን እንትን ከሆነው እንኳ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ቤት ሠርቶ እንኳን ሊታፈር ደግሶ ማስመረቅ ከተለመደ ሰንብቷል፡፡ ነገሩ ድሮ እንኳን ሰው ሰይጣኑም አፋራም ነበር ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ዛርና ጥንቆላ እንደዛሬው በባሕታውያንና በአጥማቂ ወይም በመሳሰለው ስም ይነግድ እንደነበር አልሰማሁም፡፡ እዚያው በየሠፈራቸው አንዴ ገብስማ ዶሮ ሌላ ጊዜም ሌላ እያሉ ይሠሩ ነበር እንጂ እንዲህ እንደ ዛሬው ለይቶላቸው አንዳንድ መንፈሳዊ ቦታዎች ላይ ሳይቀር ገብተው በቃሁ ነቃሁ አይሉም ነበር፡፡ ታድያ ብዙ ጊዜ ፕሮፌሰር መስፍን ከሀገር ፍቅር ቲያትር የሰማሁት ብለው በአንድ መድረክ ላይ ሲናገሩት የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ያሰማኝ “ማፈር ቀረ፤ መሽኮርመም ቀረ” ትዝ ይለኛል፡፡ በርግጥም ነገሩን ሁሉ ለሚያስተውል ነውርም፣ ማፈርም፣ ይሉኝታም ተሰብስበው ገደል የገቡና ቃላቱ ብቻ የተረፉ ይመስላሉ፡፡

 በርግጥ ለነገሥታትና ለመሪዎች፣ ለጠቢባንና ለዳኞች፣ ለሕግና ሕግ አስከባሪዎች ብቻ ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱስ ለመጻፉ፤ ነቢያት፣ ሐዋርያት፣ መምህራንና ካህናት ለመኖራቸው፤ ለጌታም ሰው ለመሆኑ ምክንያት ሙስና በሰው መፈጸሙ ነው፡፡ በኋላማ አዳም ብቻ ሳይሆን ሙስናውም ይበዛ ጀመር፡፡ እግዚአብሔር አዳምንና ሔዋንን “ብዙ ተባዙ፤ ምድርንም ሙሏት” ያላቸው ከዘራቸው ይልቅ ለሙስናቸው እስኪመስል ድረስ ትልቅ የጥፋት ዘር በምድር ተስፋፋ፡፡
 አሁን ያሉ የጸረ ሙስና እንቅስቃሴዎችም እጅግ ከመጠን ያለፉትን ዐይን አውጣ ዝርፊያዎችና አንጻራዊ ክፉ ነገሮችን ለማስቆምና “ሙስና የተፈቀደ ነው” ላለማስባል እንደሆነ እንጂ መሠረታዊ ችግሮችን ለማስወገድ፤ ምክንያቱንና ሰውን ወደ ጥፋት የሚወስዱትን አስተሳሰቦች በመሞገት በእውነት ለመከላከል የሚያደርጉም አይመስሉም፡፡ እጅግ የሚያሳዝነው ደግሞ ሙስና እንዳይኖር ለመጠበቅ ወይም በዚህ የተገኙትን ለማንጻትና ለማስተካከል የተፈጠሩት አካላትም ግንባር ቀደም ሙሰኞች እየሆኑ መምጣታቸው ነው፡፡
 የመጽሐፍ ቅዱስ መኖርም ሆነ የካህናት አገልግሎት መሠረታዊ ዓላማው ሰውን ከየትኛውም ሙስና መጠበቅ፣ በዚያ ውስጥ ያሉትን ደግሞ ማዳን ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ ሚዲያው፣ መረጃ የሚሰጠውና ሌሎቹም ተቋማት ሁሉ መሠረታዊ ግባቸው እውነትን በመግለጥና ለዚያም በቆም ለፍርድ መጣመምን፣ የሀገር ጥፋትን፣ የዜጐች ጉዳትንና የመሳሰለውን መከላከል ስለሆነ ዋና ተግባራቸው ሙስናን በተለያየ መንገድ መከላከል ነበር ማለት ነው፡፡ ችግሩ ግን ሙስና በእርሱ ላይ ሐኪሞች ይሆናሉ ተብለው የተዘጋጁትን ሳይቀር አንድ ላይ ከሕዝብ ጋር ማስተኛት የሚቻለው ብርቱ በሽታ መሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ የሊቀ ካህናት ዔሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ “ጉቦም እየተቀበሉ ፍርድም ያጣምሙ ነበር” /፩ኛ.ሳሙ.፰፡፫/ ተብሎ እንደተጻፈው መጽሐፍ ቅዱስን ተሸክመው በሙስና ያበዱ በዚህም ምክንያት የእግዚአብሔርን ፍርድ አቅርበው ራሳቸውንም ሃገራቸውንም ያጠፉ ሰዎች ነበሩ፡፡ “ንጉሥ በፍርድ ሃገሩን ያጸናል፤ መማለጃ የሚወድድ ግን ያፈርሰዋል” /ምሳ.፳፱፡፬/ ተብሎ እንደተጻፈውም ሃገራቸውንም በሙስና ምክንያት ብቻ አፈረሷት፡፡ በዚህ መንገድ እንደተጻፈው ብዙ ሃገሮች ፈርሰዋል፤ አሁንም ሊፈርሱ ያሉ አሉ፡፡ ሙስና የፍትሕና የእኩልነት ማጥፍያ መንገድ ከመሆን አልፎ ግፍን በሙሰኞች ጥላ ላይ የሚተክል ስለሆነ ፍጻሜው ጥፋት መሆኑ ጥርጥር የሌለበት ጉዳይ ነው፡፡ “ሙስና” የተባለውስ ስለዚህ አይደል?!
 በታሪክ ሙስናን ከባድና ውስብስብ ያደረገው ደግሞ ሙስናን ለማጥፋት የሚደረግ የማስመሰል እንቅስቃሴ ራሱ ዋና መሣርያ እየሆነ መምጣቱ ጭምር ነው፡፡ ሙስና ድርጊት ከመሆን አልፎ መሣርያም ሲሆን ማለት ነው፡፡ ይህ እንቅስቃሴ ሰዎች ለእውነት የቆሙ፣ አጥፊዎችንም ለመሟገት የቆረጡና የእውነት አርበኞች መስለው እውነተኞቹን ሳይቀር ለማጥፋት የሚያገለግል መልካም ልብስ የለበሰ ዘዴ መሆኑ ከታወቀ ዋል እድር ብሏል፡፡ በተለይ በሥልጣን ላይ ያሉ አካላት እነርሱ የሚሠሩትን ሙስና የሚያውቁና የሚያጋልጡ የሚመስሏቸውን ሰዎች አንዳንድ ጊዜም የጠሉትንና የማይደሰቱበትን በዚህ ሰበብ ማጥፋታቸው በምድር ላይ ረዥም ታሪክ ካላቸው ክስተቶች አንዱ ነው፡፡ ለዚህም ድርጊት መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ ጥሩ ምሳሌ አለው፡፡ ለምሳሌ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የሰቀሉት የአይሁድ ሊቃነ ካህናት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች በመጀመርያ በክርስቶስ ላይ ያስነሣቸው ዋናው ምክንያት የክርስቶስ ድርጊትና ትምህርት የእነርሱን ሌብነትና ሙሰኝነት ማጋለጡ ነው፡፡ በተለይ “እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን በጸሎት ርዝመት እያመካኛችሁ የመበለቶችን ቤት ስለምትበሉ ወዮላችሁ፤ ስለዚህ የባሰ ፍርድ ትቀበላላችሁ” /ማቴ.፳፫፡፲፬/ የሚለው እነርሱ በቀጥታ በጸሎት ሰበብ ሳይቀር ምን ያህል ሙስና ውስጥ እንደነበሩ የሚያሳይ ስለነበር እርሱን ቀድሞ ማጥፋት አማራጭ የሌለው መፍትሔ አድርገው ወሰዱት፡፡ በጊዜው ለሚሰማቸው ሕዝብ ግን ንግግራቸውና ቅስቀሳቸው ሁሉ እርሱ ሐሰተኛና አጥፊ፤ እነርሱ ግን ለእውነትና ለጽድቅም የሚቆጩ ለእግዚአብሔርም አምላክነት ለሕጉም የቀኑ በመምሰል ነበር፡፡ ይህን ሁሉ ለመፈጸም ግን መጀመርያ “በእጃቸው ተንኰል አለባቸው፤ ቀኛቸውም መማለጃ ተሞልታለች” /መዝ.፳፮፡፲/ ተብሎ እንደተጻፈው ለይሁዳ ጉቦ ከፍለዋል፤ ሰቅለው ከገደሉ በኋላ እንኳ የክርስቶስን ትንሣኤ ሐሰት ለማስመሰል የተጠቀሙበት ዘዴ ራሱ እንቆምለታለን ባሉት እውነት ስም እየማሉ እውነታውን ላዩት ጉቦ በመክፈል ነገሩን በመገልበጥ ማስወራት ነበር፡፡ ሕዝቡን የሚያባብሉት “ፍርድን አታጣምም፤ ፊት አይተህም አታድላ፤ ጉቦ የጥበበኞችን ዓይን ያሳውራልና፤ የጻድቃንንም ቃል ያጣምማልና ጉቦ አትቀበል” /ዘዳ.፲፮፡፲፱/፤ “ግፍ ጠቢቡን ያሳብደዋል፤ ጉቦም ልቡን ያጠፋዋል” /መክ.፯፡፯/፤ “የዝንጉዎች ጉባኤ ሁሉ ለጥፋት ይሆናል፤ የጉቦ ተቀባዮችንም ድንኳን እሳት ትበላለች” /ኢዮ.፲፭፡፴፬/ የሚሉትንና የመሳሰሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች በመጥቀስና እዉነተኛ በመምሰል ቢሆንም “ከሽማግሎች ጋርም ተሰብስበው ተማከሩና ለጭፍሮች ብዙ ገንዘብ ሰጥተዋቸው። እኛ ተኝተን ሳለን ደቀ መዛሙርቱ በሌሊት መጥተው ሰረቁት በሉ። ይህም በገዢው ዘንድ የተሰማ እንደ ሆነ፥ እኛ እናስረዳዋለን እናንተም ያለ ሥጋት እንድትሆኑ እናደርጋለን አሉአቸው” /ማቴ.፳፰፡፲፪-፲፬/ ተብሎ እንደተጻፈው ድርጊታቸው ለእውነት በመቆም ስም የሚፈጸም ሐሰት፣ ሙስናን በማጥፋት ስም የሚደረግ የለየለት ሙስናም ነበር፡፡ በሌላ ቋንቋ ሙሰኝነታቸው፣ አታላይነታቸው ከድሀውና ከምስኪኑ ሕዝብ መቀበል ብቻ ሳይሆን ይህን ድርጊታቸውን ሊያጋልጥ የሚችለውን በማጥፋና ለዚህም የሚያስፈልገውን ጉቦ ሁሉ ደግሞ በመክፈል፣ እና የተፈጠሩ ወሬዎችን በማስወራትና ብዙውን ሕዝብ ሳይቀር ደጋፊ አድርጎ በማሰለፍ ጭምር የታጀበ ነበር፡፡ በዚህም “ገንዘብ ባደረገው ፊት መማለጃ እንደ ተዋበ ዕንቍ ነው፥ ወደ ዞረበትም ስፍራ ሁሉ ሥራውን ያቀናል” /ምሳ.፲፯፡፰/ ተብሎ የተጻፈው የተፈጸመባቸው “ሙስና ጌጡ” ሊባሉ ከሚችሉት ወገኖች ሊቆጠሩ የሚገባቸው እንደሆነ እንረዳለን፡፡
 ከዚህ ታሪክም ሙስናን በቀጥታ አንድ ጥቅም ለማግኘት ከሚጠቀሙበት ይልቅ እርሱን ሽፋን ወይም መሣርያ አድርገው ጻድቁንና እውነተኛውን ጭምር የሚያጠፉት ምን ያህል አደገኞች እንደሆኑ ለመረዳት ይቻላል፡፡ አይሁድ በዚህም ግን አልተጠቀሙም፡፡ ወዲያው በ፸ ዓ.ም. ጥጦስ ተነሥቶ ኢየሩሳሌምን ወርሮ ሃገሪቱን አፍርሶ ሕዝቡን ገድሎና ማርኮ አጠፋት፡፡ ከዚያ ጊዜ አንሥቶም ሁለት ሺሕ ለሚጠጋ ዓመታት እሥራኤል የምትባል ሃገር እንደ ሃገር ሳትኖር ጠፍታ ኖረች፤ እነርሱም በተሰደዱበት ሳይቀር የዘሩትን ሲያጭዱ፣ ጠንስሰው የጠመቁትን የግፍ ግፍ ጽዋም ሲጨልጡ ኖሩ፡፡ አሁንም እንኳ ከደም መፋሰስ አላቆሙም፡፡ በጻድቅና በእውነተኞች ላይ ግፍና በደል ከሙስና የተነሣ የሚፈጽሙ ሁሉ ጊዜው ስለዘገየ ምንም የማይሆኑ ይምሰላቸው እንጂ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “አትሳቱ፤ እግዚአብሔር አይዘበትበትም። ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና፡፡ በገዛ ሥጋው የሚዘራ ከሥጋ መበስበስን ያጭዳልና፥ በመንፈስ ግን የሚዘራው ከመንፈስ የዘላለምን ሕይወት ያጭዳል” /ገላ.፮፡፯-፰/ ሲል እንደገለጸው ያንኑ የዘሩትን እንደ አዝመራ በብዙ ዕጥፍ ማጨዳቸው የማይቀር ነገር ነው፡፡
 እጅግ ብዙ ተቋማት ተመሥርተው ሙስናን ለመዋጋት ቢያውጁም፤ ትምህርትና ቅስቀሳ ቢደረግበትም፤ ሚዲያውም ሕዝቡም ቢጮኹም ከዚህ በፊት ያስከተለው ጥፋት ቢዘረዘርም ሙስና ግን ልክ እንደሰው ቴክኖሎጂንም የሚጠቀም ሥልጡን መሳይ ግለሰብ እየመሰለ እያደገና እየሰፋ መጣ እንጂ አልቀነሰም፡፡ ነቢዩ ሚክያስ “እጆቻቸውን ለክፋት ያነሣሉ፤ አለቃውና ፈራጁ ጉቦን ይፈልጋሉ፥ ትልቁም ሰው እንደ ነፍሱ ምኞት ይናገራል፤ እንዲሁም ክፋትን ይጐነጕናሉ” /ሚክ.፯፡፫/ ሲል የተናገረው ለእኛ ዘመን ብቻ እስኪመስል ድረስ ትንሹ ትልቁ፣ ከተሜ ገጠሬው፣ ከጥበቃ እስከ ሚኒስትር፣ ሁሉም እንደ ኮንዶሚኒየም በዓቅሙ የሚሰለፍበት ሃገራዊ ጉዳይ ለመሆን በቅቷል፡፡ አሁንስ ወዳጄ እንዳለው ሙስናው መጥፋቱ ቀርቶ ይሉኝታውና ማፈሩ እንኳ በኖረ፡፡ •

© ይህ ጽሑፍ ዲ/ን ብርሃኑ አድማስ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ቅጽ 7 ቁጥር 170 ሰኔ 2005 ዓ.ም. “ሙስናና ሃይማኖት ከኦርቶዶክስ እምነት አንጻር” በሚል ርዕስ ከጻፈው የተወሰደ ነው፡፡                      

No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount