በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ- በድጋሜ የቀረበ ጽሑፍ)፡- በአሁኑ ጊዜ በምንኖረው ሕይወት ከፍተኛ ግራ መጋባት ከሚፈጥሩብን ነገሮች ውስጥ ፈቃደ እግዚአብሔርን የተመለከተው ቀዳሚ ሥፍራ የሚወስድብን ይመስለኛል፡፡የምናዝንባቸው፣ የምንበሳጭባቸው፣ መደረጋቸውን መቀበል እስከሚያቅተን ድረስ የምንረበሽባቸው ድርጊቶች በተፈጸሙ ጊዜ መፈተናችን ይጨምራል፡፡ ነገሮቹ በቤተ ክርስቲያን አካባቢ ሲሆኑ ደግሞ የበለጠ እንፈተናለን፡፡ እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ወይ እምነታችን የተሳሳተ ካለበለዚያም እግዚአብሔር የእኛን ጸሎት መስማት ያቆመ ይመስለናል፡፡ እንደዚህ ዓይነት ስሜቶች ደግሞ መቋሚያቸው ይህ ብቻ አይደለም፤ ከፍተኛ ጥራጣሬ ላይ ጥለውን ብቻ ሳይሆን ደስታችንንም ሰርቀውብን አጎረምራሚና ወቃሽ አድረገውን፤ በቤተ ክርስቲያናችንና በአንዳንድ የቤተ ክርስቲያን አካላትም ላይ እንድናኮርፍ አድርገውን በአጠቃላይ መንፈሳዊ ሕይወታችንም ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥረውብን ያልፋሉ ወይም እኛን ወደ ሌላ ሕይወት ያሳልፉናል፡፡ በተለይ በእነዚህ ጊዜያት ‹‹ የእግዚአብሔር ፈቃድ›› ነው ተቀበሉ የሚል ሰው ከገጠመን ልናደምጠው እንቸገራለን፤አንዳንዴማ ልባችንን ዘልቆ ከገባው ሐዘን የተነሣ የሚናገርን ሰው ሞኝነቱ ብቻ ሳይሆን በእኛ ኅሊና የተሳለው አላዋቂነቱም እየታየን ብስጭታችን ሊጨምር ይችላል፡፡ ለመሆኑ ክፉ ሰዎች ግፍ ሲፈጽሙ ፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ማታለልና ተንኮል ሲፈጸም ይህን ሁሉ ፈቃደእግዚአብሔር ነው ብሎ መቀበል ይቻላልን? የፈቃደ እግዚአብሔር ድንበሩስ ምንድን ነው? ክፉ ሰዎች ሲሾሙ፣በሀገርና በሕዝብ ላይ አስከፊ ነገር ሲፈጸም ፣ አደጋና ጥፋት ሲደርስስ ፈቃደ እግዚአብሔር ነው ማለት ይቻላል? የምንፈልገው መልካም ነገር የማይፈጸመውስ ለምንድን ነው? እግዚአብሔር በጎው እንዲፈጸም አይወድምን? ወይስ ፈቃዱ የሚሆነው መቼ ነው?እነዚህ ሁሉ ለመንፈሳዊ ሕይወታችን ጥያቄዎች ሆነው የሚያስቸግሩበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡ ጉዳዮቹን በቀጥታ ከማየታችን በፊት ፈቃደ እግዚአብሔርን ለመቀበል የሚፈትኑን ነገሮች እናስቀድም፡፡
ስለ ፈቃደ እግዚአብሔር የተሳሳቱ አስተሳሰቦች
1) ክፉው ከእግዚአብሔር አይደለም
የፈቃደ እግዚአብሔርን ምንነት እንዳናውቅ የሚጋርዱ ብዙ የተሳሳቱ አስተሳሰቦች በውስጣችን ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ከእነዚህ ውስጥ አንዱና ዋነኛው ክፉው ከእግዚአብሔር አይመጣም የሚለው ነው፡፡ቅዱሳት መጻሕፍት ግን ይህም ቢሆን ከእግዚአብሔር ነው ይሉናል፡፡ ‹‹ ደዌና ጥዒና(ጤና)፣ ሞትና ሕይወት፣ ብልጽግናና ችግር መገኛቸው ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው››/ሲራ 11፤14-16/፡፡ በትንቢተ አሞጽም ላይ ‹‹ ወይስ ክፉ ነገር በከተማ ላይ የመጣ እንደ ሆነ ያደረገው እግዚአብሔር አይደለምን?›› /አሞ 3፡6/ ይላል፡፡ በአጭሩ ክፉ ነገር ከእግዚአብሔር ይመጣል፡፡ለምን እንደሚመጣ ምክንያቱን ለጊዜው አቆይተን የክፉ ወይም የማንፈልጋቸው ነገሮች መፈጸም የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው እንዴት ሊባልይችላል? የሚለውን እንመልከት፡፡
እግዚአብሔር ክፉ አድራጊውን ክፉ እንዲሆን አላደረገም፤ አያደርግምም፡፡ በሚፈጽሙት ማንኛውም ክፉ ነገርም ፈጻሚዎቹን መጠየቁም አይቀርም፡፡ ለእያንዳንዱ እንደሥራው የሚከፍል አምላክ ነውና፡፡ ክፉው በሚደርስባቸው ሰዎች ላይ ግን የሚፈጸምባቸውን ነገር እንዳይደርስባቸው ሁልጊዜም አይከላከልላቸውም፡፡ይህም የሚሆነው ስለ ሦስት ምክንያቶች ነው፡፡ የመጀመሪያውና ዋናው ከበጎ ብቻ የማንማርና የማንጠቀም ሰዎች ስላለን ነው፡፡ ሰዎች በባሕርያችን ደካሞች ስለሆንን ብዙ ጊዜ በጎውን ነገር ባገኘን ጊዜ እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት አንችልም፡፡ ለእኛ መልካም የመሰለን የሚደረግ ከሆነም ያ ነገር ሌሎቹን የሚጎዳ እንኳ ቢሆን ስለሌሎቹ አንጨነቅም፡፡ ሌላው ቀርቶ መልካም የመሰለንና እስኪደረግልን የጓጓንለት ነገር በተፈጸመ ጊዜ ከፈነጠዝን በኋላ ያሰብነውን ያህል እንዳልተጠቀምን በተረዳን ጊዜ እንደገና እግዚአብሔርን ለመውቀስ ወደ ኋላ አንልም፡፡ ምክንያቱም ጥቅም የሚገኝ የሚመስለን እኛ በጎ ነው ብለን በምናስባቸው ነገሮች መፈጸም ብቻ ስለሚመስለን ነው፡፡ መጥፎ ከምንላቸውና ከማይጠቅሙ ነገሮች ጥቅም እንደሚገኝ ካለማወቃችን በላይ እግዚአብሔር ከነዛ የሚገኘውን ጥቅም ሊሰጠን ሲፈቅድም በመቃወማችን ብቻ ሳንጠቀም እንቀራለን፡፡ ሆኖም የሚጠቅሙን እስከሆነ ድረስ እግዚአብሔር ክፉ የምንላቸውንም ማምጣቱ አይቀርም፡፡
በአንድ ወቅት በአንድ የቁሪት (ለራሳቸው የሚሆነውን ምግብና ምርት በየራሳቸው ሠርተው በሚኖሩበት) ገዳም ውስጥ በሚኖሩ አባቶች የተፈጸመው ታሪክ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ሊሆን ይችላል፡፡ በገዳሙ ከሚኖሩ አባቶች ውስጥ ሁሉም በሚባልበት ሁኔታ ምርታቸው በቂ ስለማይሆንላቸው ይቸገራሉ፡፡ በተለይ ድርቅ በሚሆንበት ጊዜ የሚላስ የሚቀመስ አስከማጣት ስለሚደርሱ ድርቅ እንደ እሾህ ይፈራሉ፡፡ ከዚህ የተነሣ በየዓመቱ እግዚአብሔር ድርቅ እንዳያመጣ ብቻ ሳይሆን ጊዜውን ጠብቆ እንዲያዘንም፣ ነፋሳቱንእንዲያፈራርቅና አስፈላጊውን ሁሉ እንዲያደርግላቸው በምሕላ በሱባዔ እግዚአብሔርን በኅብረት ይለምናሉ፡፡ ይሁን አንጂ በአብዛኛው ድርቅ ይመታቸዋል፡፡ እነርሱም ብዙ ጊዜ በእግዚአብሔር ላይ ያጎረመርማሉ፡፡ አንድ ነገር ደግሞ ሁልጊዜም ያስገርማቸዋል፡፡ በገዳማቸው ከሚኖሩት አባቶች የአንዱ ምርት ሁልጊዜም ከፍተኛ ነው፡፡ ድርቅም ቢሆን ዝናብም ቢበዛ፣ ተምችና አንበጣ ቢመጣ፣ ውርጭና በረዶ ቢፈራረቅ የዚህ አባት ምርት ሁልጊዜ ተመሳሳይ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት አንዳንዶቹ ከመደነቅም አልፈው ይህ ሰው ምን የተለየ ነገር አለው እያሉ ወደ መጠራጠርም ሔደው ነበር፡፡ አንድ ቀን ግን ጠየቁት፡፡እርሱም ምስጢሩን ነገራቸው፡፡ እኔ ለሱባኤ ስንሔድ እግዚአብሔርን የምለምነው እኛ የምንፈልገውን ሳይሆን የሚጠቅመንን እንዲያደርግልን ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ድርቅ በሆነ ጊዜም እግዚአብሔር ድርቁን ያመጣው ከዝናቡ ይልቅ ድርቁ ቢጠቅመን ነው ብየ ከልቤ አምናለሁ፡፡ስለዚህ በአንዳንዱ ዓመት በዝናባማ ጊዜ ከማገኘው የተሻለም በድርቁ ጊዜ አገኛለሁ፡፡ በዚህም ድርቁ የመጣው በእግዚአብሔር ፈቃድ እንደሆነ አምናለሁ፡፡ በሌላውም ጊዜ ቢሆን ማንኛውም ነገር ሲከሰት አላጉረመርምም፤ ምክንያቱም ባይጠቅመን ኖሮ እግዚአብሔር አያመጣውምና አላቸው፡፡ እነርሱም የችግራቸው ምንጭ ድርቁ ወይም ሌላው ሳይሆን እነርሱ ክፉ የመሰላቸውን ድርቁን በእግዚአብሔር ፈቃድ እንደሆነ አለማመናቸው መሆኑን ተረድተው ለንስሐ በቁ፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን በነቢዩ በኢሳይያስ አድሮ ‹‹ብርሃንን ሠራሁ፥ ጨለማውንም ፈጠርሁ ደኅንነትን እሠራለሁ፥ ክፋትንም እፈጥራለሁ እነዚህን ሁሉ ያደረግሁ እግዚአብሔር እኔ ነኝ›› /ኢሳ 45፤7/ የሚለንም በክፋት ፈጣሪነቱ ለመመካት ወይም ‹‹ ምን ታመጣላችሁ›› ለማለት ሳይሆን ከሚደርስብን ክፉ ነገርም መጠቀም የምንችል መሆናችንን ለመንገር ነው፡፡ በርግጥም እግዚአብሔር በብርሃኑ ብቻ ሳይሆን በጨለማውም የብርሃኑን ያህል እንደጠቀመን እንደሚጠቅመንም ማመን ይገባናል፡፡
ክፉው እንዲገጥመን ፈቃዱ የሚሆንበት ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ነጻ ፈቃድን ሊሸራርፍ ስለማይወድ ነው፡፡ እግዚአብሔር ክፉዉንና በጎውን፣ ሩቁንና ቅርቡን የሚለይ አእምሮ ሰጥቶ ከፈጠረንና እያንዳንዳችንም እንደ ሥራችን እንደሚከፈለን ከነገረን በኋላ በእያንዳንዷ ሥራችን ላይ ጣልቃ እየገባ ይህንን ወይም ያንን አድርጉ፣ አታድርጉ አይልም፤ እንድናደርግ ወይም እንዳናደርግም አያስገድድም፡፡ ይህ ሁሉ እንዲሆን ፈቃዱ ነው የሚባለውም በክፉው ነገር መፈጸም የሚደሰት ሆኖ ሳይሆን ክፉዎችን ለይቶ ያሰቡትን እንዳያደርጉ ስለማይከለክል ነው፡፡ ነጻ ፈቃዳችንን ተጠቅመን እንድነሠራ አንድ ጊዜ ለሁላችንም ፈቅዷልና፡፡ አንዳንድ ሊቃውንት ይህንን ፈቃዱን የእግዚአብሔር የፍጹምነቱ መገለጫ አድርገው የሚያቀርቡትም ፍትሑን ረስቶ ፈቃዳችንን ጨልጦ ገርኝቶ አስትቶ እንደ ቁስ አካል በሠሪው ፈቃድ ብቻ የማይጠቀምብን (ምንም እንኳ ከየትኛውም ድርጊታችን የሚጠቀመው ነገር ባይኖርም ነጻነታችንን የማይጋፋ) መሆኑን ስለሚያሳይ ነው፡፡
ከዚህም አልፎ ክፉው ሳይደርስብን ብቻ ሳይሆን ደርሶብንም መጠቀም እንደምንችልና ሰዎች ሌሎችን ለመጉዳት ሆነ ብለው ከሚፈጽሙት ክፉ ድርጊት እንኳ እግዚአብሔር ወዳጆቹን እንዴት ፍሬያማ ማድረግ እንደሚችልና ሁሉን ቻይ መሆኑንም የሚያስተምረንም ከእነዚህ መሰል ድርጊቶች ነው፡፡ ለምሳሌ በኢዮብ የደረሰውን መከራ ስንመለከት እንዴት እግዚአብሔር እንዲህ ያደርጋል ሊያሰኘን ይችላል፡፡በተለይ በቅዱስ መጽሐፍ ሳይጻፍ በእኛ ዘመን ለሁላችን በታወቀ ሁኔታ ተፈጽሞ ቢሆን ኖሮ ‹‹ እግዚአብሔር ወዴት አለ?›› ልንል ሁሉ እንችላለን፡፡ ኢዮብ ግን ያለው ‹‹እግዚአብሔር ሰጠኝ የሳባም ሰዎች ወሰዱብኝ›› ሳይሆን ‹‹ እግዚአብሔር ሰጠ እግዚአብሔር ነሣ›› ነው፡፡ ይህን ያለው የሳባ ሰዎችን እግዚአብሔር ልኳቸዋል ወይም በክፋታቸውና በግፋቸው እግዚአብሔር ይደሰታል ብሎ ሳይሆን ፈቃዳቸውን እንዲፈጽሙ ያልከለከላቸው እነርሱ ካደረሱብኝ ግፍም እግዚአብሔር የሚሰጠኝ በጎ ነገር አለ ብሎ ከልቡ በማመኑ ነው፡፡ በርግጥም ኢዮብ ከነበረው ሁለት እጥፍ ያገኘውና ከቀደመ ክብሩ ወደ ሚበልጥ ክብር የተሸጋገረው እግዚአብሔር በክፉውም ውስጥ ያለውን የማዳን ኃይል በማመኑ ነው፡፡
በአንድ ወቅት በአንድ ገዳም በሚኖሩ አባቶችም ተመሳሳይ ታሪክ ተፈጽሞ ነበር፡፡ በገዳሙ ካሉት አባቶች አንዱ ብዙ ተአምራቶችን የሚያደርጉ በተለይ አጋንንትን በማስወጣት በፈውስ ታላቅ ሀብት የነበራቸው አባት ነበሩ፡፡ገዳማቸው ደግሞ ብዙ ጊዜ በሽፍቶች ይዘረፋል፤ ይቃጠላል፤ መነኮሳቱም ይደበደባሉ፤ ብዙ መከራም ይቀበላሉ፡፡ ከዚህ የተነሣም ብዙዎቹ ያማርራሉ፤ ያዝናሉ፣ ያለቅሳሉ፡፡ ይህ ተአምራት ሚያደርግ አባት ግን ምንም አይልም፡፡ በሁኔታው የተገረሙት መነኮሳቱም ለምን ዝም ይላል ብለው በአበ ምኔቱ እንዲጠየቅ አደረጉት፡፡ ያ አባትም እነዚህ ሁሉ መከራዎች የሚመጡብን የእግዚአብሔር ፈቃዱ ስለሆነ ነው፡፡የሚደጋገሙብን ግን እናነተ ፈቃዱ ነው ብላችሁ ስለማታምኑና ከአንዱም ለመማር፣ ከመከራ ከሚገኘው ጸጋም ለመሳተፍ ፈቃደኞች ስላልሆናችሁ ነው፡፡ መከራውን ያላቆመውም እግዚአብሔር ከዚህ የምታገኙት ጥቅም እንዳይቀር ቸል ባይላችሁ ነው አለው፡፡ አበ ምኔቱም እግዚአብሔር ለዚያ አባት ተአምራት ማድረግን የሰጠው ክፉዉንም ሁሉ ፈቃደ እግዚአብሔር ነው ብሎ በመቀበሉ እንደሆነ ተረድቶ ተመለሰ ይላል፡፡ ስለዚህ ክፉ ነገር ሁሉ ለመንፈሳዊ ሕይወታችን ጎጂ ብቻ ሳይሆን ጠቃሚም ነገር ነው ማለት ነው፡፡ ይህ ማለት ግን እንዲያው እንደ ፊልምና ልቦለድ ወይም እንደ ነነዌ እሳት አይተነው ደንግጠን ወይም አዝነን ብቻ በዚያው የሚቀርልን ነው ማለት አይደልም፡፡ በትክክል ደርሶብን ሥጋችንንም ቆንጥጦን ተሰምቶን አንዳንድ ጊዜም እንደ ኢዮብ አስጨንቆንም የሚያልፍ መሆኑን መርሳት የለብንም፡፡
ወደ ሦስተኛው ከመሸጋገራችን በፊት ግን ከላይ በተጠቀሱት ሁለቱ ምክንያቶች የሚጠቀሙት እነማን እንደሆኑ ጠቆም አድርጌ ልለፍ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህን አስመልክቶ በጻፈው መልእክቱ ‹‹ እግዚአብሔርንም ለሚወዱት እንደ አሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግእናውቃለን›› /ሮሜ 8፤28/ ብሏል፡፡ ስለዚህ ከክፉው እንኳ ሳይቀር መልካም ፍሬ ማፍራት የሚቻላቸው ክፉው የደረሰባቸው ሁሉ አይደሉም ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ‹‹ ነገር ሁሉ ለበጎ›› የሚሆንላቸው ‹‹እግዚአብሔርን የሚወዱትና እንደ አሳቡም የተጠሩት›› ብቻ ናቸው፡፡ከዚህ በተረፈ ጥቅሱን ስላስታወስንና የተረበሹ ሰዎችን ለማረጋጋት ስንል ‹‹ ነገር ሁሉ ለበጎ ነው›› ስላልን ብቻ ነገር ሁሉ ለበጎ ሊሆን አይችልም፡፡ እግዚአብሔርን የሚወዱት ደግሞ ትዕዛዙን የሚጠብቁት ናቸው፡፡ እኛ ትእዛዙን ሳንጠብቅ ወይም እግዚአብሔርን ሳንወድ ልክ እንደ መለወጫ ማሽን ክፉውን በጎ የሚያደርግልን ኃይል ሊመጣ አይችልም፡፡ ስለዚህ ነገር ሁሉ ‹‹ ክፉውም ጭምር›› ለበጎ እንዲሆንልን የምንፈልግ ከሆነ የመጀመሪያው ደረጃ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ሳንልከሰከስ መጠበቅ ይገባናል፡፡ ሁሉተኛውና ከባዱ ግን ‹‹ እንደአሳቡም የተጠሩት›› የሚለው ነው፡፡ ነገሩ እንደ አሳቡ እንደ ፈቃዱ መኖር ማለት ነው፡፡ ይህም በአጭሩ ከላይ በበረሐውያን አባቶች መፈጸሙን እንዳየነው ድርቁንም ውርጩንም ሕማሙንም ድብደባ መከራውንም እግዚአብሔር እንድቀበለው ፈቃዱ ከሆነ እርሱ ይሻለኛል ብሎ የሚቀበል ልቡና ወይም ፍጹም እምነት ላይ መድረስን ይጠይቃል፡፡ በአጭር ቃል ከክፉው ለመጠቀም እንዲህ ያለ እምነትና ተእዛዛተ እግዚአብሔርን መፈጸምን ወይም እግዚአብሔርን መውደድን ገንዘብ ሳያደርጉ የሚያገኙት ነገር አይደለም ማለት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ክፉ ነገር ደርሶብን ሳንጠቀም እንቀራለን፤ መጠቀም ስላልቻልንና ይሔ ስላልገባንም ደግሞ ገና አልገባቸውም ተብሎ አይቀርልንም ማለት ነው፡፡
ሦስተኛው እግዚአብሔር ክፉ ነገርን የሚያመጣበት ምክንያት ደግሞ ከኃጢአታችን የተነሣ ለመቅጣት ነው፡፡ ለምሳሌ ወዳጁን ዳዊትን እንዴት እንደቀጣው ማስታወስ እንችላለን፡፡‹‹ ... ናታንም ዳዊትን አለው። ያ ሰው አንተ ነህ። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በእስራኤል ላይ ንጉሥ ልትሆን ቀባሁህ፥ ከሳኦልም እጅ አዳንሁህ ፤የጌታህንም ቤት ሰጠሁህ፥ የጌታህንም ሚስቶች በብብትህ ጣልሁልህ፤ የእስራኤልንና የይሁዳን ቤት ሰጠሁህ፤ ይህም አንሶ ቢሆን ኖሮ ከዚህ የበለጠ እጨምርልህ ነበር። አሁንስ በፊቱ ክፉ ትሠራ ዘንድ የእግዚአብሔርን ነገር ለምን አቃለልህ? ኬጢያዊውን ኦርዮን በሰይፍ መትተሃል፥ ሚስቱንም ለአንተ ሚስት ትሆን ዘንድ ወስደሃል፤ እርሱንም በአሞን ልጆች ሰይፍ ገድለሃል። ስለዚህም አቃልለኸኛልና፥ የኬጢያዊውንም የኦርዮን ሚስት ለአንተ ሚስት ትሆን ዘንድ ወስደሃልና ለዘላለም ከቤትህ ሰይፍ አይርቅም። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ከቤትህ ክፉ ነገር አስነሣብሃለሁ ሚስቶችህንም በዓይንህ ፊት እወስዳለሁ፥ለዘመድህም እሰጣቸዋለሁ፥ በዚህችም ፀሐይ ዓይን ፊት ከሚስቶችህጋር ይተኛል። አንተ ይህን በስውር አድርገኸዋል እኔ ግን ይህን በእስራኤል ሁሉ ፊትና በፀሐይ ፊት አደርገዋለሁ ›› /2ኛ ሳሙ 12፤ 6 - 12/ ተብሎ እንደተጻፈው በዳዊት ላይ የመጣው ነገር ሁሉ ከክፉ ሥራው የተነሣ ነው፡፡ እግዚአብሔርም በማያሻማ መንገድ ‹‹ እነሆ፥ ከቤትህ ክፉ ነገር አስነሣብሃለሁ›› ያለው ለመቅጣትም ክፉ ነገርን የሚያመጣ እርሱ ስለሆነ ነው፡፡ እንዲያው በዚህ ዓይነት የበቀል ጊዜ ክፉ ሰዎችን ወደጆቹን እንዲቀጡ ያነሣሣቸዋል፡፡ ለምሳሌ ያህል‹‹ በተጎበኛችሁበት ቀን፥ መከራም ከሩቅ በሚመጣበት ዘመን ምን ታደርጉ ይሆን? ለረድኤትስ ወደ ማን ትሸሻላችሁ? ክብራችሁንስ ወዴት ትተዉታላችሁ?›› / ኢሳ 10፤3/ እያለ የሚዘልፋቸውን እሥራኤልን ሊቀጣ በወደደ ጊዜ ስላስነሣው ስለ አሦር ‹‹ ለቍጣዬ በትር ለሆነ፥ የመዓቴም ጨንገር በእጁ ላለ ለአሦር ወዮለት! እርሱንም በዝንጉ ሕዝብ ላይ እልካለሁ፥ ምርኮውንና ብዝበዛውንም ይወስድ ዘንድ እንደ አደባባይም ጭቃ የተረገጡ ያደርጋቸው ዘንድ በምቈጣቸው ሰዎች ላይ አዝዘዋለሁ። እርሱ እንዲሁ አያስብም፥ በልቡም እንዲህ አይመስለውም፤ነገር ግን ማጥፋት፥ ጥቂት ያይደሉትንም አሕዛብን መቍረጥ በልቡ አለ ›› / ኢሳ 10፤ 5-7/ እያለ የሚናገረው ተበቃዩን አስነሹም እርሱ ስለሆነ ነው፡፡ ይህ ማለት ግን ደግ የነበረውን ሰው ለመበቀል ሲል እርሱ አከፍቶታል ማለት አይደለም፡፡ ‹‹ጥቂት ያይደሉትንምአሕዛብን መቍረጥ በልቡ አለ›› ተብሎ እንደ ተጻፈው በሰውየው ዘንድ ማጥፋ ወይም ክፋት ነበረ፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ያን ክፉ ሰው ቀደም ብለን እንደገለጽነው ክፋቱን ይፈጸም ዘንድ ካለመከልከሉ በላይ ልቡን ሌሎቹን ከማጥፋት እግዚአብሔር ሊቀጣቸው ወደ ፈቀደው ወደ እሥራኤል አነሣሣው ማለት ነው፡፡ ‹‹ እርሱ እንዲህ አያስብም፤ በልቡም እንዲህ አይመስለውም›› የተባለውም ሰውየው ቀድሞ ይህን የመሰለ ክፋት ማድረግ በልቡ ስላለ ባጠፋ ጊዜ እግዚአብሔር በእኔ አድሮ አጠፋ ብሎ ሊያስብ አይችልም፤ ምክንያቱም ክፋቱ የራሱ ነውና፡፡እግዚአብሔር ግን ይህን ክፋቱን እርሱ ሊቀጣቸው በወደደው ሕዝብ ላይ እንዲፈጽም በማድረግ አሦርም ክፋቱን እግዚአብሔርም ቅጣቱን በአንድ ሕዝብ ላይ አደረጉ ማለት ነው፡፡ ለዚህም ነው እግዚአብሔር አሥራኤልን በአሦር መቅጣቱ አሦርን ከፍርድ ነጻ የማያደርገው፡፡‹‹ ለቍጣዬ በትር ለሆነ፥ የመዓቴም ጨንገር በእጁ ላለ ለአሦር ወዮለት!›› /ኢሳ 10፤5/ ተብሎ የተጻውም ለዚህ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር የቀጭወቻችን ወይም መከራ የሚያመጡብን ሰዎች ከሐዲነትና ክፋት እኛን ጻድቅ አያደርገንም ወይም ደግሞ መከራውንና ስቃዩን የማይገባን ሊያደርገው አይችልም፤ እግዚአብሔር ለእነርሱ ፈቅዶ እኛን እንድንቀጣ ማድረጉም ቀጭዎቹን ጻድቃን ወይም እግዚአብሔርንም የተሳሳተ አያደርገውም፡፡ ስለዚህም ክፉ ሰዎችን አስነስቶ የሚቀጣ፣ መከራና ስቃይ የሚያመጣም እግዚአብሔር ነው ማለት ነው፡፡
አማኞች የሆኑ ሰዎች ግን ከዚህም መንፈሳዊ ፍሬን ሊያጭዱ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ከላይ በጠቀስነው የቅዱስ ዳዊት ታሪክ ውስጥ ቅዱስ ዳዊት ተነግሮትና ጥፋቱንም አምኖ የተቀበለው ስለሆነ በሁለት መንገድ ተጠቅሟል፡፡ በመጀመሪያ ቅጣቱን ወይም መቅሰፍቱን ይገባኛል ብሎ ስለተቀበለ መንግሥቱ ጸንቶለታል፤ እጂግ ከከፋ መከራም ድኗል፡፡ ሁለተኛውና ዋናው ጥቅሙ ግን እግዚአብሔር ለሁሉም እንደ ሥራው ይከፍላልና ኃጢአቱ የምታመጣበትን ፍዳ በምድር ላይ በመቀበሉ ስለ ኃጢአቱም ሥርየት በማግኘቱ በሰማይ ሊገጥመው ከሚችለው የዘላለም ቅጣት አመለጠ ማለት ነው፡፡ ስለዚህም በምድር የገጠመችው ቅጣት ሊነጻጸር ከማይችል ዘላለማዊ የነፍስ ቅጣት ስላዳነችው ከፍተኛ ተጠቃሚ ሆኖአል፡፡ ‹‹ እንደ አሳቡም ለተጠሩት››የሚለው የሐዋርያው ቃል ከተፈጸመላቸው ሰዎችም አንዱ ዳዊት ነው፡፡ እንደርሱ የእግዚአብሔርን አሳብ ወይም ፈቃድ የሚቀበል ሰው አልነበርምና፡፡ይህም ሳዖልን ያህል አሳዳጁን ሁለት ጊዜ ለመግደል ተመቻችቶ ባገኘው ጊዜ ከዘፈረ ልብሱ እየቆረጠ ማድረግ የሚችል መሆኑን እያሳየ ለፈቃደ እግዚአብሔር ሲል (ቀብቶ ያነገሠውን አልገድልም) ብሎ የተወ በርግጥም እንደ እግዚአብሔር አሳብ የሚኖር ሰው ነበርና፡፡እንኳን እግዚአብሔር ለቀባው ለሳዖል ይቅርና ለፍልስጤማውያንም ‹‹ ልሂድን? እነዚህንስ ፍልስጥኤማውያን ልምታን? ብሎ እግዚአብሔርን ጠየቀ እግዚአብሔርም ዳዊትን፦ ሂድ፥ ፍልስጥኤማውያንን ምታ ቅዒላንም አድን አለው›› /1ኛ ሳሙ 23፤2/ ብሎታል፡፡እግዚአብሔርም ለዳዊት ‹‹እንደ ልቤ የሆነ ሰው ፈቃዴንም ሁሉ የሚያደርግ የእሴይን ልጅ ዳዊትን አገኘሁ›› /ሐዋ 13፤22/ ሲል የመሰከረለት የዳዊት ጦርነትና ግድያ የእግዚአብሔርን አሳብ የተከተለ እንጂ እንደነ አሦር በጭካኔና ለራሱ ገናንነት ሲል የሚያደርገው ስላልነበረ ነው፡፡
በዚህ ዘመን የምንኖር እኛ ፈቃደ እግዚአብሔር ሳናውቅ አሳቡንም ሳንረዳ የምንኖረውና የምንቸገረውም ስለ ክፉ ነገሮች ካለን የተሳሳተ አሳብ የተነሣ ነው፡፡ እኛ እንደ ምቾትን እንደ ነዌ ጽድቅንም ወይም በአብርሃም እቅፍ መቀመጥንም እንደ አልዓዛር የምንፈልግ ሰዎች ነን፡፡ ይህ ደግሞ ከባድ ነገር ነው፡፡ ለመጽደቅ የግድ እንደ አልዓዛር መደኸየት በደዌ መሰቃየትም የማያስፈልግ ቢሆንም ቢያንስ ግን ስለ ኃጢአታችን የሚመጣውን መከራና ስቃይ ለመቀበል ፈቃደኞች ካልሆንን ስለጠላነው ብቻ ክፉው እንዴት ሊቀር ይችላል? ክፉዎችንስ በክፋት እንዴት ልናስወግዳቸው እንችላለን? ዘዴያችን እንደ ፖለቲከኞች፣ ሀሳባችን እንደ ብልጦች ሆኖ ጽድቃችን እንደነ ዳዊት እንዴት ሊሆን ይችላል? ኃጢአታችን እንደ ሰዶም እንደ ገሞራ ሰዎች፣ ቸልተኝነታችንም እንደ ኖኅ ዘመን ሰዎች መሆኑ ፍጥጥ ብሎ እየታየ መሪዎቻችን እንደ ዳዊት እንደ ሰሎሞን በረከቱና ሰላሙስ እንደ ብሔረ ሕያዋን እንዴት ሊሆን ይችላል? የምንሠራውን ሥራና ያለንበትን ሕይወት እንደ ጽድቅ ቆጥሮ እግዚአብሔርን እንበደለኛ ከመቁጠርስ የሚበልጥ ምን ድፍረት አለ? ትልቁ ፈቃደ እግዚአብሔርን ላለማወቃችን መጋረጃ የሆነብንም ይሔው እየደረሰብን ነው የምንለውን ክፉ ነገር ፈቃደ እግዚአብሔር ነው ብለን መቀበል አለመቻላችን ነውና ክፉውን ከእግዚአብሔር ነው ለማለት እንጀምር፡፡ ሌሎቹን ምክንያቶችና ፈቃደ እግዚአብሔርን ማወቅ የምንችልባቸውን መንገዶች በሚቀጥለው ዕትም እናያለን፤ ይቆየን፡፡
© ይህ ጽሑፍ በቀጥታ ከዲ/ን ብራሃኑ አድማስ የምጽሐፈ ገጽ አድራሻ የተወሰደ ነው፡፡
No comments:
Post a Comment