በገብረ እግዚአብሔር ኪደ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ ሐምሌ ፲፱ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም)፡ ውድ ጠያቂያችን! እንደምን ሰነበቱ?
ዳግም እንድንገናኝ፣ መንፈሳዊ ጭውውትም እንድናደርግ የፈቀደልን ለቸርነቱ ስፋት ለፍቅሩም ልኬት የሌለው ደግ ፈጣሪያችን ጌታችን
ኢየሱስ ክርስቶስ የተመሰገነ ይኹን፤ አሜን፡፡ እነሆ ለዛሬ ደግሞ ብዙ ስስ ልብ ያላቸው ወገኖች (በተለይም የይሖዋ ምሥክሮችና ሙስሊሞች)
ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ፍጡር ነው” ለማለት ከሚጠቅስዋቸው ቃላተ መጻሕፍት ቀዳሚውን ይዘን ቀርበናል፡፡ እርሱም
“እግዚአብሔር የመንገዱ መጀመሪያ አደረገኝ፥ በቀድሞ ሥራው መጀመሪያ”
/ምሳ.፰፡፳፪/ የሚለው ነው፡፡ እንኪያስ እኛም ከአማናዊው መርከብ እንሳፈርና ከሊቃውንቱ ጋር ሆነን የምሥጢሩን ጽዋዕ እንቅዳ፤
በጥርጣሬ ፀሐይ ደርቆ የተጠማው ልቦናችንም ከማየ ሕይወት እናጠጣው፡፡
“እግዚአብሔር የመንገዱ መጀመሪያ አደረገኝ፥ በቀድሞ ሥራው መጀመሪያ” /ምሳ.፰፡፳፪/፡፡
ይህ ጥቅስ በዘመነ አርዮስ
(፪፻፶፯-፫፻፴፮ ዓ.ም.) አብዝተው ከተጠቀሱ ጥቅሶች አንዱ ነው፡፡ ይኸውም አርዮስ ለመጀመርያ ጊዜ “ወልድ በመለኮቱ ፍጡር ነው”
ለማለት የጠቀሰው በመኾኑ ነው፡፡ እንደ አርዮስ አመለካከለት፡- “እግዚአብሔር ፈጣሪነት እንጂ ወላዲነት የለውም፡፡ ቀዳሚ የሌለው
አብ ብቻ ነው፤ ከርሱ በቀር ኹሉም የተፈጠረ ነው፡፡” እንደ አርዮስ አባባል “መወለድና መፈጠር ሞክሼ ቃላት ናቸው፡፡ በአብ ህልውና
ውስጥ “ጥበብና ቃል” የሚባሉ ኀይላት ነበሩ፡፡ ከእነዚህ ሌላ ደግሞ እግዚአብሔር በራሱ ፍቃድ ዓለምን ለመፍጠር ስላሰበ መሥፈሪያና
መለኪያ እንዲኾነው ሌላ ጥበብ ፈጠረ፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስም ጥበብ /፩ኛ ቆሮ.፩፡፳፬/፣ ወልድ /ማቴ.፳፰፡፳/፣ ቃል /ዮሐ.፩፡፩/፣
አርአያ /ቈላ.፩፡፲፭/ እየተባለ ይጠራል፡፡ በባሕርዩ ፍጡር ስለኾነ ያልነበረበት ጊዜ ነበር፡፡ ከመፈጠሩ በፊት አልነበረም፡፡ በፈቃደ
እግዚአብሔር ከኢምንት ከዓለማት በፊት የተፈጠረ ነው፡፡ ሰው መኾኑ ራሱ የባሕርዩን ተወራጅነት ያመለክታል፡፡ ቃል ሰው ለመኾን የበቃው
ቅሉ የመታዘዝ ግብር ቢኖርበት ነውና” ይላል፡፡ አርዮስ እንዲህ ከላይ እንዳየነው የወልድን ፍጡር መኾን ተንትኖ ያበቃና እንደገና
ደግሞ ከፍጡራን የለየ አስመስሎ እንደሚከተለው ይናገራል፡- “ነገር ግን ከሌሎች ፍጡራን ይበልጣል፡፡ ለአብ ፍጡሩም ልጁም ነው፡፡
በኋላም በመዋዕለ ሥጋዌ ባሳየው ታዛዥነትና የተጋድሎ ጽናት ከእግዚአብሔር ቡራኬን፣ ጸጋን ተቀብሎ እንደ ጻድቃን እንደ ሰማዕታት
ሱታፌ አምላክነትን አገኘ፡፡” “ስለዚህ” ይላል አርዮስ “ስለዚህ ወልድ
ፍጡር ሲኾን በገድል፣ በትሩፋት አምላክ ለመኾን፣ አምላክ ለመባል የበቃውን እርሱን እኛም አምላክ ነው ብለን ልንጠራው
ደግሞም አምላክ ነው ብለን ልናመልከው እንችላለን” ይላል፡፡
“የማስተምረው ትምህርት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያለው ነው” ለማለት ለዛሬ
መነሻችን አድርገን የተነሣነውንና በምሳሌ ሰሎሞን “(ትቤ ጥበብ) እግዚአብሔር ፈጠረኒ
ቀዳሜ ኵሉ ተግባሩ- (ጥበብ) እግዚአብሔር የመንገዱ መጀመርያ አደረገኝ (አለች)” የሚለውን ንባብ መላልሶ ይጠቅሰው
ነበር፡፡
ይህ የአርዮስ ትምህርት ግን ፍጹም ክሕደት ነው፡፡ ምንም እንኳን እንዲህ ዓይነቱ
ትምህርት በምሥጢረ ሥላሴ ትምህርቱ የተዘበራረቀና የተምታታ ሐሳብ የነበረው አርጌንስ (Origen) በመጠኑም ቢኾን አንሥቶት የነበረ
ቢኾንም እንደ አርዮስ ግን ፍጥጥ ብሎ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የወጣ አልነበረም፡፡ ነገር ግን ይህ ትምህርት አስቀድመን እንደተናገርን
ፈጽሞ ክሕደት እንደኾነ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ያስተምራሉ፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ ይህን ሲያስረዳ እንዲህ ይላል፡- “…
እግዚአብሔር ራሱ ዓለምን ለመፍጠር እስካለመቻል ደርሶ ደካማ አይደለምና፡፡ ወይም ዓለምን ለመፍጠር እስካለመፍቀድ ደርሶ ትዕቢተኛ
አይደለምና፡፡… ቃል (ወልድ) በገድል በትሩፋት ለራሱ አምላክ ለመኾን የሚጥር ከኾነ እኛን የጸጋ አማልክት እንድንኾን ማድረግ እንዴት
ይቻለዋል? /ማቴ.፲፡፴፬/፡፡ በስጦታ ያገኘውን አምላክነት ለሌላ ሊቸረው ሊለግሰው አይችልም፤ ከራሱ አይተርፍምና፡፡… ስለዚህ ወደ
እኛ ወርዶ ራሱን ያሻሻለ አይደለም፤ ይልቁንስ መሻሻል የሚያስፈልገውን ሰው አሻሻለ እንጂ” ይላል /የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም
መድረክ፣ በአቡነ ጐርጐርዮስ ካልዕ የተዘጋጀውን መጽሐፍ ይመልከቱ/፡፡
ቅዱስ አትናቴዎስ ትምህርቱን ሲቀጥል፡- “ለመኾኑ ወልድ ፍጡር ነው፤ ከመፈጠሩ
በፊት ያልነበረ ነው ካሉ በኋላ አምላካዊ ክብርና ስግደት ይገባዋል፤ የሚሉ አርዮሳውያን ስማቸውን ቀይረው ክርስቲያን መባላቸው ስለምን
ይኾን? ለምንስ አሕዛብ (አረማውያን) አይባሉም፤ ምክንያቱም አረማውያን እውነተኛውን አምላክ ትተው ጣዖታትን ፍጡራንን ስላመለኩ
አረማውያን ተብለዋልና፡፡ እነ አርዮስም ስግደትና አምለኮት ለፍጡር ይገባል ብለው ካወጁ አረማውያን ናችሁ ያሰኝባቸዋልና” ይላል
/Contra Arianos, 1134.35/፡፡ በሌላ አንቀጽም፡- “ክርስቶስ ፍጡር ነው የሚሉ መናፍቃን እኛን ክርስቲያኖችንም መምለኪያነ
ፍጡር ማለታቸው ነው፡፡ ክርስቲያኖች ግን መምለኪያነ ፍጡር አይደሉም፤ ዕሩቅ ብእሲን አያመልኩም” ይላል /ዝኒ ከማሁ፣ ገጽ ፻፭/፡፡
አርዮስን ለማውገዝ ሳይኾን ከዚህ አደገኛ ስሕተቱ አርመውና ዘክረው ለመመለስ
ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በ፫፻፳፭ ዓ.ም. በኒቅያ ተሰብስበው ነበር፡፡ በጉባኤው ላይ በነበረው ክርክር አርዮስና ተባባሪዎቹ የግሪኮችን
ፍልስፍናና ከመጽሐፍ ቅዱስም ለእነርሱ እንደሚመች አድርገው የተረጐሟቸውን (ለምሳሌ ምሳ.፰፡፳፪ን) እየጠቀሱ ስለ ወልድ ፍጡርነት
ለማስረዳት እሰጥ አገባ ይሉ ነበር፡፡ በጉባኤው የነበረው አትናቴዎስ ሐዋርያዊ ግን፡- “ኢየሱስ ክርስቶስ መድኃኒት ነው፤ አዳኝ
ነው፡፡ ማዳኑን ካመንህ የባሕርይ አምላክነቱን ማመን አለብህ፡፡ የሚያድን እግዚአብሔር ብቻ መኾኑን መጽሐፍ ቅዱስ መስክሯልና /ማቴ.፩፡፳፩፣
ኢሳ.፵፭፡፳፩/፡፡ በቅዱሳት መጻሕፍት ምስክርነት የወልድ አምላክነት ከሰው ልጆች የመዳን ምሥጢር ጋር የተያያዘ ነው፡፡ እርሱ አምላክ
ካልኾነ ደግሞ እኛንም ማዳን አይችልም ማለት ነው፡፡ በእርሱ መዳናችንን ካመንን ግን ያዳነን እርሱ አምላክ መኾኑን ማወቅና ማመን
አለብን፤ ፍጡር ፍጡራንን ማዳን አይቻለውምና፡፡ ራሱ መዳን የሚያስፈልገው ስለኾነ፡፡ ለምሳሌ በሉቃስ ወንጌል የተማርነው የጠፋው
ልጅ ምሳሌ መላውን የሰው ዘር የሚመለከት ነው /ሉቃ.፲፭፡፲፩/፡፡ ፈላጊውም ቃል የእግዚአብሔር ልጅ ነው፡፡ ቃል (ወልድ) ፍጡር
ከተባለ የጠፋው እርሱ ራሱ ነዋ!” አለ፡፡ አትናቴዎስ ይህን በተናገረ ጊዜ ኦርቶዶክሳውያን አባቶች በደስታ ተዋጡ፡፡ አርዮስና መስሎቹ
ግን አመድ ለበሱ /ዝኒ ከማሁ፣ ገጽ ፻፲፬/፡፡
ለመነሻ ያህል ይኽን ካልን የጥቅሱን ትርጓሜ ወደ መናገር እንለፍ፡፡ ትርጓሜ ሲባል ግን እንዲሁ በዘፈቀደና እኛ እንደሚመቸን አድርገን ተራቅቀንና ተፈላስፈን የምንናገረው
አይደለም፡፡ የምትተረጕመው ቤተ ክርስቲያን ብቻ ነች፡፡ ለምን? ያልን እንደኾነ ልቧ ክርስቶስ ስለኾነ /፩ኛ ቆሮ.፪፡፲፮/፡፡ የክርስቶስ
ሐሳብ ደግሞ ክርስቶስን ሳይይዙ ማወቅ አይቻልም፡፡ አሁን ወደ ሊቃውነቱ ትርጓሜ እንግባ፡፡ ሊቃውንቱ እንደሚነግሩን “እግዚአብሔር የመንገዱ መጀመሪያ አደረገኝ፥ በቀድሞ ሥራው መጀመሪያ” /ምሳ.፰፡፳፪/ የሚለው አንቀጽ በኹለት መልኩ የሚተረጐም ነው፡፡ ይኸውም፡-
፩ኛ) ምዕራፉ
በአጠቃላይ ደግሞ መጽሐፉ፣ ጥበብን (ማስተዋልን) እንደ ሰው እንድትናገር በማድረግ የእርሷንም ታላቅነትና ክቡርነት የገለጸበት ነው፡፡
ገና ከምዕራፉ መጀመርያ አንሥተን ስናነብ “በውኑ ጥበብ አትጮኽምን? ማስተዋልስ ድምፅዋን አትሰጥምን?” ይላል
/ቁ.፩/፡፡ ቀጥሎም ጥበብ ለሰው ልጆች ምን እንደምትል በሰውኛ ዘይቤ እንድትናገር ያደርጋታል፡- “እናንተ ሰዎች፥ (ባለ አእምሮ
የምኾን እኔ) እናንተን እጠራለሁ፥ ድምፄም ወደ ሰዎች ልጆች ነው። እናንተ አላዋቂዎች፥ ብልሃትን አስተውሉ ፤ እናንተም ሰነፎች ጥበብን በልባችሁ ያዙ” ትላለች
/ቁ.፬-፭/። አሁንም ትንሽ ወረድ ብለን ስናነብ “ዋጋው እጅግ ብዙ ከኾነ ቀይ ዕንቍ ይልቅ ጥበብ ትበልጣለችና የዚህ ዓለም ክብር ኹሉ አይተካከላትም” ይላል ጠቢቡ /ቁ.፲፩/። ቀጥሎም ጥበብ ራሷ በሰውኛ ዘይቤ
እንድትናገር ይሆንና፡- “እኔ ጥበብ በሰው ልቡና
ምክር፣ ዕውቀት ኾኜ በብልሃት ተቀምጫለሁ፥ ዕውቀትንም ጥንቃቄንም አስተማርሁ።
እግዚአብሔርን የሚፈራ ክፋትን ይጠላል፤ ትዕቢትንና እብሪትን ክፉንም መንገድ ጠማማውንም አፍ እጠላለሁ።
ምክር የእኔ ገንዘብ ነው፤ ትእዛዝ የእኔ ገንዘብ ነው፤ ማስተዋል (ዕውቀት) የእኔ ገንዘብ ነው፤
ብርታትም (ጽናትም) የእኔ ገንዘብ ነው። ነገሥታት በእኔ ምክር ይነግሣሉ፤ ሹማምቶችም በእኔ አእምሮ
የቀናውን ነገር ይደነግጋሉ
(ይጽፋሉ)። አለቆች በእኔ ትእዛዝ ይከብራሉ፡፡
ክቡራንና የምድር ፈራጆችም በእኔ ብርታት
ጠላትን ወግተው ይይዛሉ፡፡ እኔ ጥበብ የሚወዱኝን እወዳለሁ፡፡ እኔን የሚፈልጉኝ ባለሟልነትን ያገኛሉ፡፡ ብዙ ባለጸግነትና ክብር
በእኔ ዘንድ አለና” ትላለች /ቁ.፲፪-፲፰/። ከዚህ በኋላ ነው እንግዲህ
እንኳንስ በፍጡራን ዘንድ ቀርቶ በፈጣሪም ዘንድ እንዳለች ለማስረዳት ጠቢቡ ሰሎሞን “(ትቤ ጥበብ) እግዚአብሔር ፈጠረኒ ቀዳሜ ኵሉ
ተግባሩ- (ጥበብ) እግዚአብሔር የመንገዱ መጀመርያ አደረገኝ (አለች)” የሚለው፡፡ በምዕራፍ ፫ ቁጥር ፲፱ ላይም፡- “እግዚአብሔር
በጥበብ ሣረራ ለምድር- እግዚአብሔር በባሕርይ
ጥበቡ ምድርን መሠረተ (ፈጠረ)፤ በባሕርይ
ማስተዋሉም (ዕውቀቱም) ሰማያትን አጸና (አዘጋጀ)” ያለው ይህን የመሰለ ነው /ምሳሌያተ ሰሎሞን ወልደ ዳዊት ትርጓሜ፣ ገጽ ፴፯-፴፰ና
፳፬/።
፪ኛውና
ምሥጢራዊው ትርጓሜው ግን የእግዚአብሔር ጥበብ የተባለው ክብር ይግባውና ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መኾኑ ሊቃውንቱ
ያስተምራሉ /፩ኛ ቆሮ.፩፡፳፬/፡፡ “እግዚአብሔር ፈጠረኒ
ቀዳሜ ኵሉ ተግባሩ- እግዚአብሔር የመንገዱ መጀመርያ አደረገኝ” ማለቱም “በሐዲስ ተፈጥሮ ከሚፈጥራቸው ምእመናን አስቀድሞ እግዚአብሔር
ፈጠረኝ” ሲል ነው ይሉናል፤ ዓይናማዎቹ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት፡፡ እዚህ ጋር ታላቅ የኾነ ጥንቃቄ ገንዘብ ልናደርግ ይገባናል፡፡
ይኸውም “ፈጠረኝ” የምትለዋን ኃይለ ቃል ብቻ ይዘን ወደ ስሕተት እንዳንነጕድ ነው፡፡ ገና ስንጀምር “ከአማናዊው መርከብ እንሳፈርና
ከሊቃውንቱ ጋር ሆነን የምሥጢሩን ጽዋዕ እንቅዳ፤ በጥርጣሬ ፀሐይ ደርቆ የተጠማው ልቦናችንም ከማየ ሕይወት እናጠጣው፡፡ ያልነውም
ስለዚሁ ነውና፡፡
ኢትዮጵያውያኑ ሊቃውንት ይህን አንቀጽ ምን ማለት እንደኾነ ሲተረጕሙት “ፈጠረኝ ማለቱ ድኅረ ዓለም በሥጋ መፈጠሩን ቅድመ ዓለም በልበ ሥላሴ መታወቁን ሲያጠይቅ ነው እንጂ
ፍጡር ሆኖ አይደለም” ይሉናል /አንድምታውን ይመልከቱ/፡፡ በርግጥም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተዋሐዳት ሰውነትም ብትኾን ፍጡር መባሏ ገና በልበ ሥላሴ ሳለች፣
ሳይዋሐዳት እንጂ ከተዋሐዳት በኋላ አይደለም፡፡ ከተዋሕዶ በኋላማ ምንታዌ (ኹለትነት) የለም፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ አንድ ነው /ዮሐ.፫፡፲፮/፤ የሰው ልጅ አንድ ነው /ዮሐ.፫፡፲፫/፤ አማኑኤል አንድ ነው /ማቴ.፩፡፳፩/፤
ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ነው /ኤፌ.፬፡፬/፡፡ ይህች አካላዊ ቃል ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል
ማርያም ነሥቶ የተዋሐዳት ሰውነት በሐዲስ ተፈጥሮ፣ በቀደመ ማንነት በጥምቀት ለተፈጠርን በኩራችን ናት፡፡ የምእመናን የመልካም ምግባራችን፣
የትሩፋታችን በኩር ናት /ኤፌ.፪፡፲/፡፡ እግዚአብሔር ፈጠረኝ ማለቱ ትርጓሜው ይኼ ነው፡፡
እስኪ ሊቃውንቱ ራሳቸው አምልተው አስፍተው ይንገሩን፤ እኛም እንስማቸው፡፡
የመናፍቃን መዶሻ የተባለው የአሌክሳንድርያው ሊቅ ቅዱስ ቄርሎስ እንዲህ ሲል ይቀጥላል፡- “(በመጽሐፈ) ምሳሌ ስለ ተጻፈው ቃል
አስቀድመን እንደተናገርን ይህን ተናገርን፡፡ ከፍጥረቱ አስቀድሞ እግዚአብሔር
ፈጠረኝ ያለውን ይህን ቃል ከእኛ ወገን ብዙዎች አምነው ሰው ስለመኾኑ ይናገሩታል /ምሳ.፰፡፳፪/፡፡ በወንጌል ቃል ሥጋ ኾነ ተብሎ
እንደተጻፈ /ዮሐ.፩፡፲፬/፡፡ ጥበብ ተፈጠረ፡፡ ይኸውም ቃል ነው፡፡
ከፍጥረቱ አስቀድሞ የነበረ ቃል ሥጋ በመኾኑ ይህ አምላክ ያለ መለወጥ ከንጽሕት ድንግል ከነሣው ሥጋ ጋር አንድ አካል አንድ ባሕርይ
ኾኗልና የእግዚአብሔር ፍጥረቶች ከጥበብ ተገኝተው በባሕርያቸው ጸንተው ይኖራሉና፡፡ አሁን ግን ጥበብ ከፍጥረት አስቀድሞ የነበርኩ
እኔን ጌታ ፈጠረኝ አለች፡፡ የተገዥ (የአዳምን) ባሕርይን ገንዘብ ልታደርግ ሰው ኾነች፡፡ አብ ፈጠረኝ አላለችም፤ ጌታ ፈጠረኝ
አለች እንጂ፡፡ ወልድ አባቱን ብቻ ለማመልከት በሚናገርበት ጊዜ አባቴ ይሏል፤ የተገዥ (የአዳም) ባሕርይን በማድረጉ እርሱ ራሱ
ሰው ኾነ፡፡ ስለዚህም ጌታ ፈጠረኝ አለ፡፡ አባቴ ፈጠረኝ አላለም /ዮሐ.፲፡፲ና ፴፣ ፊል.፪፡፯፣ ፩ኛ ዮሐ.፭፡፳/፡፡ የጌታ ፍርዱ
በሚገባ ኾነ፡፡ ፍጥረቶቹ እርሱን ወደ ማወቅ ይደርሱ ዘንድ የሰው ባሕርይ በዲያብሎስና በሠራዊቱ ቁራኝነት ተይዞ ደክሞ ነበርና፣
በፍዳም ተይዞ ይቀር ዘንድ አይገባምና፣ ስለዚህ ተጐድቶ የነበረው ይድን ዘንድ እግዚአብሔር የሰውን ባሕርይ አሰበ፡፡ ድኅነት ከማንም
ሊገኝ አልተቻለምና ስለዚህ አምላክን በወለደች በድንግል ማርያም ማኅፀን ሰው ይኾን ዘንድ ጥበቡ የሚኾን አንድ ልጁን ሰደደ /ዮሐ.፲፯፡፳፩፣
ሮሜ.፲፡፲፬-፲፱፣ ፩ኛ ጴጥ.፪፡፳፫፣ ዕብ.፪፡፲/፡፡ ጥበብ የሚኾን ቃል የተጐዳ ሰውን ያድን ዘንድ ሳይለወጥ ነፍስ ያለችውን ሥጋ
ነሣ፡፡ ለራሱ እጠቀም ብሎ ሰው የኾነ አይደለም፤ ሥጋ ልዩ ልዩ ኀይሎችን በማድረግ ይገለጥ ዘንድ ነው እንጂ፡፡ ‘የእግዚአብሔር
ሥልጣን የእኔ ነው፤ ስለ ድኅነተ ምእመናን አዋሐደኝ፡፡ ነዳያንን ደስ አሰኛቸው ዘንድ፣ በሥጋ በነፍስ ደዌ የተያዙትን አድናቸው
ዘንድ፣ ለተማረኩት ነጻነትን እሰብክላቸው ዘንድ፣ ዕውሮች ያዩ ዘንድ፣ እግዚአብሔር ሰው የኾነበትን ዘመን የምሕረት ዘመን እለው
ዘንድ ሰው አደረገኝ’ ተብሎ ስለ እርሱ ብቻ እንደ ተነገረ /ኢሳ.፷፩፡፩-፫፣ ሉቃ.፬፡፲፯-፳፣ ማቴ.፲፩፡፬-፮/፡፡ ዳግመኛም ቅዱስ
ጴጥሮስ ስለ ኢየሱስ እርሱ ከእግዚአብሔር ተገኝቶ በጽኑ ሥልጣን ከኀሊነት እንደ ተዋሐደ፣ ሰው ኾኖም ዲያብሎስ ድል የነሣቸውን እንደ
አዳናቸው ተናገረ፡፡ ቀብዐኒ ተብሎ እንደ ተነገረ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ኾነ፡፡ ሞተ፤ ተነሣ መባሉም ለሙታን ለሕያዋን ገዢ ይኾን
ዘንድ ነው እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ ሰው እንደ ኾነ ሞተ፤ ተነሣ፤ ስለ እርሱ የተጻፈውን ይፈጸም ዘንድ /ሐዋ.፲፡፴፰፣ ኤፌ.፩፡፲፩፣
ዕብ.፪፡፲፰/፡፡ መጻሕፍት እንደተናገሩ ለፍጥረቱ መሪ፣ የትሩፋት ጀማሪ ይኾን
ዘንድ ሰው ኾነ፡፡ ጥበብም ጌታ ፈጠረኝ ያለችው በድንግል ማኅፀን ሊዋሐደው ሥጋን ስለፈጠረ እንደኾነ ያስረዳል፡፡ እነሆ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፤ ስሙም አማኑኤል ይባላል፡፡ ትርጓሜውም እግዚአብሔር
ከእኛ ጋር አንድ የኾነ ማለት ነው ተብሎ የተነገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ድንግል ወንድ ሳታውቅ ፀነሰች፡፡ እግዚአብሔር ከእኛ
ጋር አንድ ይኾን ዘንድ ወለደች፡፡ በመውለድዋ እግዚአብሔር ከሰው ጋር አንድ ይኾን ዘንድ /ምሳ.፰፡፳፪፣ ኢሳ.፯፡፲፬፣ ማቴ.፩፡፲፰-፳፣
ሉቃ.፩፡፴፬/፡፡ ዳግመኛም መድኅን ክርስቶስን ከድንግል ስለ መወለዱ በዚህ ነቢይ ኢሳይያስ አፍ ‘ብዙ ሥራ እሠራ ዘንድ፣ የያዕቆብንም
ወገን አጸና ዘንድ ስለዚህ በማኅፀን ተጸነስኩ’ አለ፡፡ ስለዚህ ሥራ
እግዚአብሔር ለፈጠረው ፍጥረት መሪ፣ የትሩፋት ጀማሪ ይኾን ዘንድ ቃል ሥጋ ኾነ /ኢሳ.፵፱፡፭-፯/፡፡ ፈጥኖ በንስሐ ወደ እግዚአብሔር የሚመለስ ኹሉ በማኅፀን የተፀነሰ የእርሱን ፍለጋ ይከተላል፤ የሚፈጽማቸውን
ወደ እግዚአብሔር ለሚያቀርቡ ምግባራት ጀማሪ ይኾን ዘንድ ሰው ኾነ፤
ለትሩፋት ጀማሪ ሊኾን ሰው የኾነ ርሱ ነው፡፡ ዳግመኛም የያዕቆብን ወገን
አንድ ለማድረግ እሥራኤልንም ለማዳን አገልጋይ እኾነው ዘንድ በማኅፀን የፈጠረኝ እግዚአብሔር ርሱ ይወደኛልና ጌትነቱም በእግዚአብሔር
ዘንድ የነበረ ነውና ጌታ ኀይል ይኾነኛልና የእሥራኤልን ወገኖች በሃይማኖት ልታጸናልኝ የያዕቆብንም ምርኮ ልትመልስልኝ የእኔ ልጅ
ይሉህ ዘንድ ይህ ላንተ ድንቅ ነገር ነው፡፡ አሁንም እስከ ምድር ዳርቻ ያሉትን ታድን ዘንድ ለአሕዛብ ኹሉ መተማመኛ አደረግኩህ
አለኝ አለ /ኢሳ.፵፱፡፭-፯/፡፡ ይህ በቅድስት ድንግል ማርያም ማኅፀን
የተፈጠረበት (ሰው የኾነበት) ምክንያት እሥራኤልን ብቻ ለማዳን አይደለም፤
እስከ ምድር ዳርቻ ያሉ አሕዛብን ኹሉ ለማዳን ነው እንጂ፡፡ ከዲያብሎስ ቁራኝነት ያዳናቸው፣ ከክሕደታቸው ተመልሰው የባሕርይ አምላክ
እግዚአብሔርን ባመለኩት ጊዜ በወንጌል ዕውቀትን የገለጸላቸው እሊህ ናቸው /ኢሳ.፵፭፡፲፬-፲፯፣ ቈላ.፩፡፲፪-፲፬፣ ማቴ.፭፡፳፩-፵፪፣
ሃይማኖተ አበው ዘቄርሎስ ፸፮፡፲-፳፪/፡፡
ቀጥሎ ያለውን
ምንባብ ማለትም ምሳሌ ፰ ቁ.፳፫ እስከ ፴፩ ያለውን ሲተረጕሙም ኢትዮጵያውያኑ ሊቃውንት “ሰማይን ሳይፈጥር፣ ምድርንም ሳይፈጥር፣
ወንዞችንም ሳይፈጥር፣ የውሆች ምንጮች ተመጥነው ሳይፈጠሩ፣ ተራሮች ሳይጸኑ፣ ኮረብታዎችም ሳይከናወኑ ስለ ሥጋ ፈጠረኝ አልኩ እንጂ
አካል ዘእም አካል ወለደኝ” ይላሉ፡፡ በምሥጢራዊው ትርጉሙን ሲያስቀምጡም “ጥምቀትን ሳይሠራ፣ ጥሙቃን ሳይፈጠሩ፣ ሊቃነ ጳጳሳት
ኤጲስ ቆጶሳት ሳይፈጠሩ አካል ዘእም አካል ወለደኝ ማለት ነው” ይሉናል፡፡ እንቀጥል፤ “መንደር መንድረው የሚኖሩ ሰዎች ሳይፈጠሩ፣
ጠፈር ጸንቶበት የሚኖር አድማስ ሳይፈጠር ወለደኝ፡፡ ሰማያትን ባዘጋጀ ጊዜ አብሬው ነበርሁ፡፡ ነፋሳት ማደርያው ሰማይን በነፋስ
ባጸና ጊዜ አብሬው ነበርሁ፡፡ አካለ ደመናትን ባጸና ጊዜ፣ የውሆችን ምንጮች አነዋወር ባጸና ጊዜ፣ ለባሕር ለውቅያኖስ ድምበር ባኖረ
ጊዜ፣ የምድር መሠረት ነፋሳትን ባጸና ጊዜ፣ በሥነ ፍጥረት መፈጠር በየጊዜው ደስ ይለኝ ነበር፡፡ በየጊዜው በየወገን በየወገኑ ፍጥረት
በተፈጠረ ጊዜ ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ይህን ዓለም ፈጥሮ በጨረሰ ጊዜ ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ይልቁንም ከፍጥረቱ ኹሉ ሰው ይበልጣልና
በሰው መፈጠር ደስ ይለኝ ነበር” ማለት ነው ይላሉ /ምሳሌያተ ሰሎሞን ትርጓሜ ገጽ ፴፰ ይመልከቱ/፡፡
የቆጵሮሱ ኤጲስ ቆጶስ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ደግሞ “መልሕቅ” በተባለ መጽሐፉ ይህን
አንቀጽ ሲተረጕመው እንዲህ ይላል፡- “የተወለደ ሲኾን እንደምን ተፈጠረ? ካልተፈጠረስ ባልተወለደም ነበር፡፡ ቀዳማዊ አምላክ ሲኾን
እንደምን ተፈጠረ ይባላል? እኛም የምንወልደውን የምንፈጥረው አይደለም፡፡ የምንሠራውንም የምንወልደው አይደለም፡፡ እኛ ፍጡራን ነን፤
የምንወልዳቸው እነርሱም ዳግመኛ ፍጡራን ናቸው፡፡ ያልተፈጠረ የእግዚአብሔር ቃል ግን መወለዱ ከፍጡር አባት አይደለም፡፡ እርሱም
የተፈጠረ አይደለም፡፡ ከተፈጠረስ በኋላ ከተወለደ ቀድሞ እንደምን ተፈጠረ? ዳግመኛ ከተፈጠረ በኋላ እንደምን ተወለደ? ተፈጠረ መባሉ ሰው በመኾኑ ይፈጸማል፡፡ ስለዚህም አስቀድሞ ደኃራዊ ልደቱን ተናገረ፡፡ ቅሩባን የሚኾኑ
የሰዎችን ደስ ሊያሰኝ ወድዶ፤ ስለዚህም የሰውነቱን ነገር ይናገር ጀመር” ይላል /ሃይ.አበ. ፶፮፡፲፰-፳/፡፡
በጉባኤ ኒቅያ
ተሰብስበው የነበሩት ሊቃውንት ዛሬ በየዕለቱ የምንጸልየውና “አንቀጸ ሃይማኖት” በተባለው አንቀጻቸው ላይ “ሰማይንና ምድርን የፈጠረ
/ዮሐ.፩፡፫/፤ የሚታየውንና የማይታየውን ዓለም ሳይፈጠር ከእርሱ ጋር በነበረ /ሚክ.፭፡፪/ አንድ የአብ ልጅ በሚኾን /ዮሐ.፫፡፲፮/
በአንድ ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እናምናለን /ዮሐ.፫፡፲፯/፡፡ ከብርሃን የተገኘ ብርሃን /ዕብ.፩፡፫/ ከእውነተኛ አምላክ የተገኘ
አምላክ /ዕብ.፩፡፭/ የተወለደ እንጂ ያልተፈጠረ /ምሳ.፰፡፳፪-፳፭/ …” ብለው ያጸደቁት ስለዚሁ ነው፡፡
አጽድቀዋል፤ ወስነዋል ሲባል ግን ሰዎች ተሰብስበው “ይህን ማመን አለብን”
ብለው በድምፅ ብልጫ ተስማምተው የጋራ መግለጫ ሰጡ ማለት አይደለም፡፡ በቀላል ምሳሌ ለማስረዳት ያህል አንድ ገበሬ በእህሉ አጠገብ
ወይም እህሉን መስሎ አዝመራውን የሚጐዳ አረም ሲበቅል ከእህሉ መካከል ነቅሎ እንደሚጥል ኹሉ ቤተ ክርስቲያንም በዓይኗ አይታ፣ በጀሮዋ
ሰምታ፣ በእጅዋ ዳስሳ በምታውቀውና በምታምነው እውነት አጠገብ የራሷን እውነት መስሎ ራሷን የሚጐዳ ከኾነ የመናፍቃንን አረም ነቅላ
ለመጣል ጉባኤ ታደርጋለች፡፡ አረሙን ነቅላ ትምህርተ አዝመራዋን ትከላከላለች፡፡ በዚህ ጉባኤ የኾነውም እንደዚህ ነው፡፡
ለዛሬ እንዳበዛነው
ቢገባንም በዚህ እናብቃ፡፡ በቀጣይ ደግሞ ሌላ ማብራርያ የሚያስፈልገውን ጥቅስ ይዘን እንቀርባለን፡፡ እስከዚያው ግን ሰላም ወሰናይ!!!
No comments:
Post a Comment