በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ ሐምሌ ፲፪ ቀን ፳፻፭
ዓ.ም)፡-
ባለፉት ጊዜያት ፈቃደ እግዚአብሔርን እንዳንረዳ ያደረጉንን ሁለት ምክንያቶች ተመልክተን ነበር፡፡ በዚህ ክፍል ደግሞ ከችግሮቹ ውስጥ ሦስቱን አቀርባለሁ፡፡ በሚቀጥለውና በመጨረሻው ክፍል ግን ፈቃደ እግዚአብሔርን እንዴት እንደምንረዳ አይተን ጽሑፉ ይጠናቀቃል፡፡ መልካም ንባብ!
3) ፈቃደ እግዚአብሔርን በራስ መረዳት ልክ መወሰን
ፈቃደ እግዚአብሔርን ለመረዳትና ለመቀበል እንድንቸገር የሚያደርገን አንዱና መሠረታዊው ችግር ደግሞ ብዙ ነገሮችን በራሳችን መረዳት መጠን የመወሰን ችግር ነው፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ጥንቱንም ስለ እምነታችንም ሆነ ስለቤተ ክርስቲያናችን ያለን ግንዛቤ በእኛ ጭንቅላት ውስጥ በተወሰነው ልክ ብቻ መሆኑ ይመስለኛል፡፡ ከዚህ በፊት ስለ አምልኮተ እግዚአብሔር ባሉን ዕወቀቶች ላይ ተመሥርተን ብቻ የሆነ ነገር እናደርግና እግዚአብሔር የምንሻውን ለምን አይፈጽምልንም በማለት የምንጠይቅ ብዙዎች ነን፡፡ ለምሳሌ ሳዖል ንጉሠ እሥራኤል ለእግዚአብሔር የሚቀርበውን የመሥዋዕት ዓይነት በማወቁ ከተማረኩት ውስጥ ደኅና ደኅናውን ለእግዚአብሔር በማምጣቱ ብቻ እግዚአብሔርን የሚያስደስት መስሎት ነበር፡፡ ነገር ግን ምንም እንኳ ያመጣቸው እንስሳት ለመሥዋዕተ እግዚአብሔር ሊሆኑ የሚችሉ ቢሆኑምና እግዚአብሔርም መሥዋዕት የሚወድ ቢሆንም በእነዚህ ላይ ተመሥርቶ ብቻ ፈቃዱ ይሆናል ብሎ ማቅረብ አይገባውም ነበር፡፡ ልናደርግ የምናስበው ነገር ከዚህ በፊት በሌሎች ተደርጎ የተወደደና ድርጊቱም ጥሩ ቢሆንም እንኳ በዚህ ላይ ተወስነን ብቻ ድርጊቱን በመፈጸም ፈቃደ እግዚአብሔርን ፈጽመናል ማለት አይቻልም፡፡ አንድ ገዳማዊ አባት ‹‹ በራሴ ፈቃድ ተስቤ ከሱራፌል እንደ አንዱ መሆን ከምችል በእግዚአብሔር ፈቃድ ከምድር ትሎች እንደ አንዱ ብሆን ይሻለኛል›› ያለው ምንም ከሱራፌል እንዳንዱ ሆኖ እግዚአብሔርን ማመስገንን የመሰለ ትልቅ ነገር ባይኖርም ፈቃዱ ካልሆነ መተውን ያህል የተሻለ ነገር ስለሌለ ነው፡፡ የመንፈሳዊነትና የቅድስና ብቃት ትልቁ መለኪያም ሁልጊዜም በራስ ዕውቀት፣ መረዳትና ልክ ተመሥርቶ እግዚአብሔርን አስደስታለሁ ብሎ መድከም ሳይሆን አስቀድሞ የእግዚአብሔር ፈቃድ የሆነውን ለመቀበል መዘጋጀትና መጸለይ ነው፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት ‹‹ አንተ አምላኬ ነህና ፈቃድህን ለማድረግ አስተምረኝ ፤ ቅዱስ መንፈስህም በጽድቅ ምድር ይምራኝ ›› /መዝ 143 ፤ 10/ እያለ እንደጸለየውና በሕይወቱም በዚሁ ሲመራ እንደኖረው እርሱን መምሰል ተገቢ ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላካችንም ‹‹እንደ ልቤ የሆነ ሰው ፈቃዴንም ሁሉ የሚያደርግ የእሴይን ልጅ ዳዊትን አገኘሁ ›› /ሐዋ 13 ፤22/ ሲል የመሰከረለት ዳዊት ከራሱ ሀሳብና ዕውቀት ወጥቶ የሚፈጸመውን ሁሉ በእግዚአብሔር ፈቃድ ላይ ተመሥርቶ ይፈጽም ስለነበረ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በደማስቆ ጎዳና በተአምራት ከተመለሰ በኋላ ‹‹ ጌታ ሆይ፥ ምን አደርግ ዘንድ ትወዳለህ?›› /ሐዋ 9 ፤ 6/ ሲል የጠየቀው ትልቁ ነገር የራስ ፈቃድን ትቶ የእግዚአብሔር የሆነውን መከተል ስለሆነ ነው፡፡ ጌታም ‹‹ይህ በአሕዛብም በነገሥታትም በእስራኤልም ልጆች ፊት ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ነው ›› /ሐዋ 9 ፤ 15/ ሲል ያዘጋጀውና የመሰከረለት ሰው የራሱን ፈቃድ ትቶ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመፈጸም ከተነሣሣ ከዚህ የሚበልጥ ምንም ዓይነት ውድ ሥጦታ ስለሌለ ነው፡፡
አንድ ሰው የራሱን ፈቃድ
ከተወ ያልቶወውና የቀረለት ምንም ነገር የለምና፡፡
በሕይወታችን ውስጥ በሀብት፣ በሥልጣንና የመሳሰለው በጎ ነገር በገጠመን ጊዜ የሆነልንን ወይም የተደረገልንን ነገር ፈቃደ እግዚአብሔር ነው ብሎ ለመቀበል አንቸገርም፡፡ በእንዲህ ያለው ጊዜ ማንም ኃጥእ ቢሆን ፈቃደ እግዚአብሔርን ለመቀበል አይቸገርም፡፡ ከባድ የሚሆነው በመከራ፤ በድህነትና በውርደት ወይም በሕማምና በችጋር ውስጥ ስንሆን ነው፡፡ ከባድ ሊሆን የሚችልበት ምክንያት ደግሞ እኛ ነገሮችን የምንለካው በራሳችን ዕውቀት ላይ በመመሥረታችንና ከግንዛቤያችንም ድንበር ፈቀቅ ለማለት እንኳን ዝግጁ ባለመሆናችን ነው፡፡ ቅዱሳንን ከእኛ የተለየ የሚያደርጋቸውም በመከራና በፈተና ጊዜ ሰውነታቸው ሳይሰቀቅ፣ ፊታቸው ሳይከፋና ልቡናቸው ሳያዝን ልክ በጎውን ሁሉ በሚቀበሉበት መጠን ክፉውንም ለመቀበል መቻላቸውና ከዕወቀታቸውና ከግንዛቤያቸው በላይ የሆነውን ሁሉ ‹‹ ፈቃዱ ነው›› ብለው የመቀበላቸው ብርታት ከፍተኛ መሆኑ ነው፡፡ አንድ አባትም ‹‹ በማግኘትና በደስታ ጊዜ ከሚቀርብ ዕልፍ ዝማሬና ምስጋና ይልቅ በፈተናና በመከራ ጊዜ የምትቀርብ አንዲት ተመስገን እጂግ ታላቅ ዋጋ አላት›› ያሉት ለዚህ ነበር፡፡
ከራስ ዕውቀትና ግንዛቤ ተጽእኖ ተላቅቆ ፈቃደ እግዚአብሔር መሆኑን መቀበል እንደምንናገርለት ቀላል አይደለም፡፡ እንኳን እኛና በተጥባበ ነገር የተሞላ ጭንቅላት ያለን የዚህ ዘመን ክርስቲያን ነን ባዮች ደካማ ሰዎች ቀርቶ ጌታችን ከዋለበት እየዋሉ ካደረበት እያደሩ የተማሩትና ተአምራ ለማድረግና አጋንንትን ለማስወጣት በቅተው የነበሩት ሐዋርያት እንኳን ተቸግረው ነበር፡፡ ለምሳሌ ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታችን በአይሁድ እጅ ተላልፎ እንደሚሰጥና እንደሚሞት በገለጸበት ጊዜ ‹‹ ጌታ ሆይ አይሁንብህ›› በማለቱ ‹‹ ወደ ኋላዬ ሂድ፥ አንተ ሰይጣን፤ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አታስብምና ዕንቅፋት ሆነህብኛል›› /ማቴ 16 ፤23/ ተብሎ የተገሰጸው ቅዱስ ጴጥሮስ ፈቃደ እግዚአብሔርን በራሱ መረዳት ወስኖ በማሰቡ ነበር፡፡ በፈቃዱ ሊቀበላት ያላትን የሞት ጽዋ ይቀበል ዘንድ በምሴተ ሐሙስ ተላልፎ በአይሁድ እጅ በሚያዝበት ዕለትም ቀናኢው ቅዱስ ጴጥሮስ ሰይፍ አንሥቶ የማልኮስን ጆሮ እስከመቁረጥ ደርሶ ነበር፡፡ ቀድም ብለን ካየነው ከዚያ ተግሣጽ በኋላም ይህን ያደረገው ነገሮችን በራሱ ዕውቀት ላይ ተመሥርቶ ከማድረግ ገና ነጻ ስላልወጣ ነበር፡፡ ጌታም ‹‹ ሰይፍ የሚያነሡ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉና ሰይፍህን ወደ ስፍራው መልስ። ወይስ አባቴን እንድለምን እርሱም አሁን ከአሥራ ሁለት ጭፍሮች የሚበዙ መላእክት እንዲሰድልኝ የማይቻል ይመስልሃልን? ›› /ማቴ 26 ፤ 52-53/ ሲል የመለሰለት ቅንዓቱን ጠልቶበት ሳይሆን እንዲህ ያለ በጻድቅና በእውነት ላይ የሚደረግ ክፉ ነገርም ብታዩ ፈቃደ እግዚአብሔር ከሆነ ተቀበሉት፤ በተሳሳተ መንገድም አትመልሱ ለማለት ነው፡፡ በርግጥም ጌታ ለቅዱስ ጴጥሮስ እንደነገረው ግፍና መከራ በምንም መንገድ እንዳይፈጸሙ መከላለከል ብቻ ጠቃሚና አስተማማኝ ቢሆን ኖሮ እግዚአብሔር ሰዎች እስኪነግሩት የሚጠብቅ ሊሆን አይችልም ፤ ቅዱስ ጴጥሮስ እንዳደረገውም ሰይፋችንም ሆነ ሌላው ነገራችንም አያስፈልገውም ነበር፡፡ እንደተጻፈውም እግዚአብሔር በዚህ መንግድ የሚደረጉትን ቢውድ ኖሮ የሰማይ መላእክት አያንሱትም ነበር፡፡ እረ አንድ መልአክም ብቻ ይበቃው ነበረ፡፡ ነገር ግን እኛ አሁንም በራሳችን ዕውቀትና ግንዛቤ ከመታጠር ለመውጣት አቅም ስለሌለን ቅዱስ ጴጥሮስ ያን ጊዜ እንዳደረገው ያለችንን ሰይፍም ሆነ ጎራዴ ዱላም ሆነ ምናምን ይዘን ከመንደፋደፍ አልቦዘንንም፡፡ በዚህ መንገድ የእግዚአብሔርን ፈቃድ መፈጸም ግን አይቻልም፡፡ ስለዚህም ከዚያ ከሐዋርያት ዘመን ጀምሮ ከፈቃደ እግዚአብሔር እንድንለይ እያደረገን ያለው አንዱና መሠረታዊው ችግር በራስ ዕውቀትና ግንዛቤ ላይ ታጥሮ ለማገልገል መጣደፍ መሆኑን መገንዘብና ራስን በዚህ ከመታጠር ነጻ ለማውጣት መጣር ተገቢ ነው፡፡
4ኛ) የተለየ ምልክት መፈለግ
ፈቃደ እግዚአብሔርን በተመለከተ ውይይትም ሆነ ትምህርት በሚሰጥበት ጊዜ ተደጋግሞ የሚነሣው ጥያቄ ‹‹ ፈቃደ እግዚአብሔር መሆኑን በምን አውቃለሁ›› የሚለው ነው፡፡ ጥያቄው በራሱ ክፉ ባይሆንም መነሻውን ስንመረምረው ግን በብዙዎቻችን ውስጥ የሚኖር አንድ መሠረታዊ ችግርን ያመለክታል፡፡ እርሱም ፈቃደ እግዚአብሔርን በሆነ ምልክት የማወቅ መሻት ነው፡፡ አብዛኛዎቻችን በተሳሳተ መንገድና ለተሳሳተ ዓላማ ሱባኤ እስከመግባት የሚያደርሰን በውስጣችን በስሱም ቢሆን የተደበቀው ምልክት የማየት ፍላጎት ነው፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ እሥራኤል ብዙ ጊዜ ምልክትን ሲሹ እንመለከታቸዋለን፡፡ በርግጥ በብሉይ ኪዳን ዘመኑ ዘመነ ረድኤት ስለነበረ ምልክት መሻት የሚያስነቅፍ አልነበረም፡፡ ምክንያቱም የሰው ዘር ገና ከኃጢአት ባርነት ነጻ ያልወጣ ስለነበር እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር መሆኑን ወይም ፈቃደ እግዚአብሔር መሆኑንና አለመሆኑን ለማወቅ ምልክትን ይጠቀሙ ነበር፡፡ ለምሳሌ እሥራኤል ከአማሌቅ ጋር ጦርነት ተፋጥጠውና ፈርተው በነበሩበት ጊዜ ዮናታን ወልደ ሳዖል ለጋሻጃግሬው ‹‹ እነሆ፥ ወደ ሰዎቹ እናልፋለን እንገለጥላቸውማለን፤ እርሱም፦ ወደ እናንተ እስክንመጣ ድረስ ቆዩ ቢሉን በስፍራችን እንቆማለን፥ ወደ እነርሱም አንወጣም። ነገር ግን፦ ወደ እኛ ውጡ ቢሉን እግዚአብሔር በእጃችን አሳልፎ ሰጥቶአቸዋልና እንወጣለን ምልክታችንም ይህ ይሆናል ›› /1ኛ ሳሙ 14 ፤ 8 - 10/ የሚል ምልክት እንደሚጠቀሙ ነግሮት ነበር፡፡ በርግጥም በምልክቱ መሥራት ፈቃደ እግዚአብሔር መሆኑን አውቀው ጦርነት ውስጥ ገብተው አሸንፈዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር
የጌዴዎንን ጸምርና ጠል ምልክት የመሰሉ ብዙ ምልክቶች ተገልጸው ይገኛሉ፡፡
በዘመነ ሐዲስ ግን ሰው በእግዚአብሔር ቃል ሰው መሆን የጎሰቆለ ባሕርዩ ታድሶ የተገፈፈው ጸጋ ስለተመለሰለት አማኑኤል ተብሎ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ስለሆነ የተለየ ከእኛ ጋር የመኖሩ ምልክት አያስፈልግም፡፡ እርሱ በዘመነ ሥጋዌው እንዳስተማረው ምልክትን መሻትም የከፉነትና የአመንዝራነት መገለጫዎች ሆነዋል /ማቴ 12 ፤ 39/ ፡፡ ሆኖም ግን እስካሁን ድረስ ይህ ፍትወት ከሰው ፈጽሞ ስላልተወገደ ማድረግ የፈለግነውን ነገር የሚያረጋግጥልን ምልክት ብዙ ጊዜ እንሻለን፡፡ የፈለግነውን ባጣን ጊዜም እናዝናለን፡፡ ሌላው ቀርቶ መጥፎ ድርጊት እየፈጸሙ ነው በምንላቸው ሰዎች ላይ እንኳን አንድ መቅሰፍት ወርዶ እኛ የምንቃወመውን እግዚአብሔር የሚቃወመው ነው ለማለት የሚያስችል ፍላጎታችን እጂግ ከፍተኛ ነው፡፡ ይህንኑ ድካማችን የሚያውቅ ሰይጣንም ከዚሁ ድብቅ ፍላጎታችን ጋር ተጣጥሞ ሊተረጎም የሚችል ክስተት ሲያሳየን የእኛን ትክክለኛነት የሌሎቹንም ስሕተትነት እግዚአብሔር ያረጋገጠልን አድርገን እንድንወስደውና ቀስ በቀስም በምልክት የምንመራ ሰዎች እንድንሆን ምልክትንም እንድንጠብቅ ይገፋፋናል፡፡ ነገሩን በቀላሉ ለመረዳት ይህን የመሰለ ድርጊት የተደጋገመላቸውን ሰዎች መመልከቱ በቂ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ነገር የተደጋገመላቸው ሰዎች ከትንሽ ጊዜ በኋላ ራሳቸውን የበቁ አድርገው ይወስዳሉ፤ ለገጠመኞቻቸውን ሁሉ ትርጓሜ በመስጠት ምልክቶች አድረገው ይወስዳሉ፤ ነገሮችንም ሁሉ ከዚያ ምልክታቸው እንደማይወጡ ያምናሉ፡፡በዚህም ሳይወሰኑ የእነርሱን ምልክት፣ መልእክትና የመሳሰለውን የማይቀበሉ ሁሉ ኃጥኣንና የእግዚአብሔርን መንገድ የሚቃወሙ ሰዎች አድርገው ይወሰዳሉ፡፡ ‹‹ ወዳጆች ሆይ፥ መንፈስን ሁሉ አትመኑ፥ ነገር ግን መናፍስት ከእግዚአብሔር ሆነው እንደ ሆነ መርምሩ፤ ብዙዎች ሐሰተኞች ነቢያት ወደ ዓለም ወጥተዋልና ›› / 1ኛ ዮሐ 4፥1/ የተባለውንም ረስተው የሚመራቸውን መንፈስ እንኳ ሳይመረምሩ የማያውቁት መንፈስ ባሪዎች ሆነው ለመገዛትና ከነበሩበትና ከእውነተኛው መንገድ እስከመውጣት ይደርሳሉ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ መናፍስትን መለየት ራሱ ልዩ ጻጋ መሆኑን /1ኛ
ቆሮ 12 ፤10/ ቢገልጽም መናፍስትን ለይቶ ከጉዳታቸው ለመጠበቅ የሚደረግ ነገር አይታይም፡፡ የዚህ ሁሉ ጥፋት መነሻ ግን ምልክትን የማየት ከፍተኛ ድብቅ ፍላጎት መኖሩ ነው፤ ፈቃደ እግዚአብሔርን ላለመረዳት ዋናውና ትልቁ እንቅፋትም ይኼው ሁሉን በምልክት የማረጋገጥ ፍላጎት ነው፡፡
በርግጥ በሐዲስ ኪዳንም ቢሆን ምንም ዓይነት ምልክትና ጠቋሚ መልእክት አልነበረም፤ ፈጽሞም አይደረግም ለማለት አይደለም፡፡ ለምሳሌ ቅዱስ ጴጥሮስ ቆርኔሌዎስን ለማጥመቅ አልሔድም ብሎ እንዳያስቸግር አስቀድሞ እግዚአብሔር በራእይ ገልጾለት ነበር፡፡ /ሐዋ 10 / ይህን የመሰሉ ብዙ መገለጦችም በቅዱሳን ሕይወት ውስጥ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ዓይነት ምልከቶችና መገለጦች ግን ከላይኞቹ እጂግ በብዙዉ ይለያሉ፡፡በመጀመሪያ ደረጃ ቅዱስ ጴጥሮስም ሆነ ሌሎቹ እንዲህን ዓይነት ምልክቶችን በመሻት የሚደክሙት ድካም አልነበረም፡፡ ከዚያም አልፎ እግዚአብሔር ያደረባቸው መሆኑንና ያም ቢሆን ግን ከሥጋዊ ደማዊ ጠባያቸው ተነሥተው ሳያውቁ የእግዚአብሔርን ሥራ እንዳይቃወሙ ወይም ደግሞ ፈቃዱን በከፍተኛው መዓርግ በብቃትም ጭምር የሚረዱ መሆናቸውን ለመግለጽ የሚደረጉላቸው እንጂ ያን ምልክት ባያዩ ግራ የሚገባቸውና የሚያደርጉትን የማያውቁ ሆነው አይደለም፡፡
በእኛ ዘንድ ያለውና ከእግዚአብሔር እያራቀን ያለው ግን በእጂጉ ሌላ ነው፡፡ በእኛ ዘንድ ትዳር መሠርቶ መኖር ከሚፈልገው አንሥቶ
ሥራ መቀየር እስከሚፈልገው ድረስ ልዩ ምልክትን ማየት ይሻል፡፡ ከግብዝነታችንም የተነሣ እኛ የተውነው መሥሪያ ቤት ሲዳከም ወይም እኛ ያላጨነው ሰው ተጎድቶ በማየት እኛ የእግዚአብሔር በመሆናችን ከዚያ እንደተረፍን በመንገር ብቃታችን ለማሳየት ስንል ይህን ዓይነት ምልክት የምንሻው እንኳ ቁጥራችን ጥቂት የሚባል አይመስለኝም፡፡ ከዚህም የተነሣ ምልክት መሻትን ወይም ራስን አጽድቆ ማየትን የተንተራሱ ብዙ ታላቅ ኃጢአቶችን እንሠራለን፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው ራሱን ከብዙዎች በሆነ ምክንያት ለይቶ እነርሱ ሲጎዱ እርሱ ተርፎ በማየት የእግዚአብሔር ወዳጅ መሆኑን ለማረጋገጥ የሚሻ ከሆነ ሀሳቡ ላዩን ሲያዩት ራስን የእግዚአብሔር አድርጎ የመቁጠር ስሜት ብቻ ቢመስልም በጥላው የተሸከመው ትልቅ የገዳይነት ኃጢአት አለበት፡፡ ሰውየው ይህን የሚያስበው የራሱን ብቃት ለማሳየት ቢመስለውም በዚያ የተለዩ ሆኖ የመታየት ምልክት መሻት ግን ብቻውን አይደለም፡፡ ምንም እንኳ በዚህ ዓይነት ሀሳብ ውስጥ ገዳይ ወይም እኛ በሌለንበት አደጋውን ያደርሳል ብለን የምናስበው ሌላ አካል ቢሆንም ሀሳቡን እያሰበ ያለው አደጋ ያደርሳል ብለን የምንስለው ራሱ ሳይሆን እኛው በመሆናችን የአደጋ ጣዩ ፈጣሪዎች እኛው ነን ማለት ነው፡፡ አደጋ ፈጣሪውን ከፈጠርነው ደግሞ አደጋ አድራሾቹም እኛው እንሆናለን፤ በዚህም ሳናውቀው የበቃንና መንፈሳዊ የሆንን በሚመስል ሕይወት ውስጥ ገዳይነትንና ወንጀለኝነትን እናስድጋታለን ማለት ነው፡፡ ጊዜ የገጠማት ጊዜም በአርበኝነት ሰበብ ብቅ ብላ ሀሳቧን ወደ ገቢር የምትለውጥ ፍትወትን ትልቅ መኖሪያ ሠራንላት ማለት ነው፡፡ የዚህ ሁሉ ወንጀል ዋሻ ሆና የምታገለግለው ግን ያችው ‹‹ ምልክትን›› የመሻት ኃጢአት ናት፡፡ ይህ ችግር ደረጃው ይለያይ እንደሆነ እንጂ በዓለም ያለነውን ብቻ ሳይሆን በገዳም ከሚገኙትም ቢያንስ ጥቂቶቹን ጭምር የሚያንገላታ መምህር ከደቀመዝሙር ጋርም የሚያላጋ ትልቅ ፈተና ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላካችንም እሥራኤልን በኃይልና በተግሣጽ ‹‹ ዘርሽና ትውልድሽ ከከነዓን ምድር ነው ፤ አባትሽ አሞራዊ ነበረ እናትሽም ኬጢያዊት ነበረች / ሕዝ 16፥3 / የሚላቸው ምንም በአምልኮተ እግዚአብሔር ቢኖሩ በውስጣቸው ሊወጣ ያልቻለ ድብቅ የእምልኮ ጣዖትና የጥንቆላ ፍላጎት ስለነበረባቸው ነው፡፡ አሁንም እኛ ምንም ክርስቲያን የሆንን ቢመስለንም በውስጣችን ተደብቀው የሚያነገላቱ የጥንቆላ፤ ምልክትን የመሻት፣ ያለ መንፈሳዊ ግብር ቶሎ የመብቃት፣ የተለዩ መንፈሳዊ መስሎ የመታየትና የመሳሰሉት አደገኛ ነገሮች አሉብን፡፡ በእነዚህ ተይዘን ደግሞ ፈቃደ እግዚአብሔርን ልናውቅ በዚያም ልንመራ አንችልም፡፡
5ኛ) እግዚአብሔርን መሣሪያ የማድረግ ፍላጎት
ለዚህ ጽሑፍ ፈቃደ እግዚአብሔርን ላለማወቅ እንደ መጨረሻ ምክንያት የምናየው እግዚአብሔርን ለእኛ ሀሳብ መሣሪያ አድርጎ የመጠቀምን ፍላጎት ነው፡፡ በብዙዎቻችን ዘንድ ከእግዚአብሔር እንዳንታረቅና ፈቃዱን በመፈጸም እንዳንኖር ከሚያደርጉን ነገሮች አንዱ ቀደም ብለን በጠቀስነው በራስ መረዳት መጠን ነገሮችን ከወስንን በኋላ የሚከተለው እኛ የምንቃወመው ወይም የምንጠላው ነገር እንዲጠፋ እግዚአብሔርን እንደ መሣሪያ የመጠቀም ፍላጎት ነው፡፡ ሙሴ ከጠራቸው ሰባ ሁለት ሰዎች ውስጥ በሰፈር የቀሩት
ኤልዳድና ሞዳድ በሰፈር ትንቢት በተናገሩ ጊዜ የቀናው ብላቴናው ኢያሱ ‹‹ ጌታዬ ሙሴ ሆይ፥ ከልክላቸው አለው /ዘኁ 11 ፤ 28/ ሲል ሙሴን መሣሪያ አድርጎ መከልከል እንደፈለገው ወይም የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ወደ ጌታ የሚሔደው ሕዝብ ወደ ዮሐንስ ከሚሔደው መብልጡ አስከፍቷቸው እንደተናገሩት / ዮሐ 3 ፤30 /ብዙዎቻችን በእኛ ሀሳብ መሠረት የማይሔደው ሁሉ ምንም መልካምና ከእኛ ጋር ካለው የተሻለም ቢሆን አያስደስተንም፡፡ በዚህ ጊዜ ከላይ እንዳየናቸው ታሪኮች ከምንቀርባቸው ሰዎች ጀምሮ እግዚአብሔርንም ጭምር እንደ መሣሪያ ተጠቅመን የሐሳባችን በላጭነት ወይም የእኛን የበላይነት ማሳየት እንሻለን፡፡ ልክ አይሁድ ጾምን ቅዱስ ጳውሎስን ለመግደል መሣሪያ አድርገው ሊጠቀሙበት
እንደሞከሩት ማለት ነው /ሐዋ 23 ፤ 14 /፡፡ በእኛም ዘመን የነገሮቹን እውነተኛ ሁነት ሳንመረምርና የእግዚአብሔርንም ሃሳብ ሳንረዳ‹‹ እግዚአብሔር እንዲህ ቢያደርጋቸው፣ ይህን ቢጨምርባቸው፣ ... ›› እያልን ለክፋታችንና ላለማስታዋላችን እግዚአብሔርንም እንደ መሣሪያ ልንጠቀምበት እንሻለን፡፡ በመራገም ጊዜ ብቻ ሳይሆን በስብከትና በጽሑፍም ጊዜ ለሀሳባችን የሚስማሙ ጥቅሶችን በመፈለግ እግዚአብሔር ሀሳባችንን የሚደግፈው ለማስመሰልና ኅሊናችን ከሚያመጣብን ወቀሳ በእግዚአብሔር ቃል ለመደበቅ የምንሽሎከለከው ቁጥራችን ጥቂት አይደለም፡፡ ከዚህም አልፎ ያንን ሀሳባችንና ነገራችን ተመልክቶ እንደ ቀናኢነትና እውነተኝነትም ቆጥሮ ሌሎቹን ቢያጠፋልን ወይም አንድ ነገር ቢያደርግልን ደስታውን አንችለውም፡፡ እግዚአብሔርን እንደ መሣሪያ የመጠቀም ፍላጎት ማለትም ይኼው ነው፡፡ እንዲህ ያለው ነገር ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው ለዚህ ዓለም የሚመች ቢሆንም ( እንደ መሠልጠን ወይም እንደ ሁሉን አወቅም ሊያስቆጥር ይችላል) ለመንፈሳዊ ሕይወት ግን ጠቃሚ አይደለም፡፡ ‹‹ ነገር ግን ለዓለም ከሚመች ከከንቱ መለፍለፍ ራቅ፤ ኃጢአተኝነታቸውን ከፊት ይልቅ ይጨምራሉና፥ ቃላቸውም እንደ ጭንቁር ይባላል፤ ›› /2ኛጢሞ 2፥16/ ሲል እንደገለጸው የዚህ ዓይነት አገላለጽ እንደ ጭንቁር የሚባላ እንጂ እግዚአብሔርን የሚያስደስት ነገር አይደለም፡፡ ሳናውቀውም ቢሆን
‹‹ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና ›› /ዮሐ 3 ፤ 15/ ተብሎ ከተገለጸውና እግዚአብሔር ለኃጥአን ካለው ፈቃድ ጋር እንጋጫለን፤ የእግዚአብሔርንም የማዳን ሀሳብ እንቃወማለን፡፡ በዚህም ምክንያት ከዋናው እግዚአብሔር ለዓለም ወይም ለኃጥኣን ካለው ሀሳብ ወይም ፈቃድ መቃወም ስለምንጀምር በየትኛውም መንድ ከእግዚአብሔር ፈቃድ እየወጣን እንሔዳለን፡፡ ቀደም ብለን እንዳየነውም የዚህ ሁሉ መሠረታዊ ምክንያቱ እግዚአብሔርን ለሀሳባችን እንደመሣሪያ ለመጠቀም ካለን ፍላጎት የሚመነጭ ነው፡፡ሌላው ቀርቶ ሱባኤ በተሳሳተ መንገድ እስከመግባት የሚያደርሰን ይኼው እኛ ከምንፈልገው አንጻር እግዚአብሔርን አንድ ነገር አድርጎ የማየት ፍላጎታችን ታላቅ በመሆኑ ነው፡፡ እንዲህ ያለው ነገር ግን ቀደም ብለን ካየነው አይሁድ ቅዱስ ጳውሎስን ለመግደል እንደ ጾሙት ያለ ጾምና ሱባኤ ነው፡፡ በአጭሩ የእግዚአብሔርን ስም እየጠሩና ለቤቱም በሚደረግ ቅንዓት የሚያንቦገቡጋቸው ሀሳቦች ውስጥ ሌላውን የማጥቃትና የማሰደድ ሀሳቦችን መሰንዘር ለድክመታችን ወይም ከአእምሮ ወቀሳችን ለማምለጥ እግዚአብሔርን መሣሪያ ማድረግ እንጂ የእግዚአብሔር መሆናችንን አያሳይም፡፡ ይልቁንም በዚህ ሰበብ ሳናውቀው የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንቃወማለን፡፡ ታዲያ የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንዴት እናውቃለን? የጽሑፋችን መጨረሻ የሆነውንና ፈቃዱን የማወቂያ መንገዶቹን በሚቀጥለው እትም እናያለን፤ ይቆየን፡፡
© ይህ ጽሑፍ በቀጥታ ከዲ/ን
ብርሃኑ አድማስ የምጽሐፈ ገጽ አድራሻ የተወሰደ ነው፡፡
kale hiywet yasemalen
ReplyDelete