Showing posts with label ትንቢተ ዮናስ - ክፍል ሦስት. Show all posts
Showing posts with label ትንቢተ ዮናስ - ክፍል ሦስት. Show all posts

Monday, February 22, 2016

ትንቢተ ዮናስ - ክፍል ሦስት



(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ የካቲት 15 ቀን 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

ምዕራፍ ሦስት

ዓሣው ዮናስን በአንጻረ ነነዌ ተፋው፡፡ እግዚአብሔርም ልክ እንደ መጀመርያው፡- “ተነሥተህ ወደዚያች ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ፤ እኔ ከዚህ ቀደም አስተምር ብዬ እንደነገርኩህ አስተምራቸውአለው፡፡ ዮናስም መጀመርያ እንዳደረገው ከጌታ ፊት ለመሸሽ አልሞከረም፡፡ እግዚአብሔር እንዳዘዘው ተነሥቶ ሄደ እንጂ፡፡ ተወዳጆች ሆይ! እስኪ የእግዚአብሔርን ፍቅር ቆም ብለን እናሰላስለው፡፡ ዮናስ ለወገኖቹ ለእስራኤል አዝኖ አልታዘዝ ብሎ ነበር፡፡ ባለመታዘዙ ምክንያትም ወደ ሌላ ኃጢአት ገብቶ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ግን አሁንም ይወዷል፡፡ ወደዚያች ወደ ታላቂቱ ከተማሌላ ነቢይ ልላክአላለም፤ከእንግዲህ ወዲህ ዮናስን አልፈልገውምአላለም፡፡ እግዚአብሔር ዮናስን በቃል እንኳ የገሰጸው አይደለም፡፡ ዳግመኛምዮናስ ሆይ! ትእዛዜን ተላልፈህ የሸሸኸው ስለምንድነው?” አላለውም፡፡ በተግባር የደረሰበት ኹሉ በቂ ነውና፡፡ በመኾኑም አሁን ተጨማሪ የቃል ተግሳጽ አላስፈለገውም፡፡ ዳግመኛ በቃላት ቢገስጸው ዮናስ ምን ያክል ስሜቱ ሊጐዳ እንደሚችል ሰው ወዳጁ ጌታ ያውቃልና፡፡ እግዚአብሔር ስሜታችንን ምን ሊጐዳው እንደሚችል ጠንቅቆ ያውቃል፤ በመኾኑም ይጠነቀቅልናል፡፡ ስሕተታችን ምን እንደኾነ በራሳችን አውቀን እንድንመለስ ኹኔታዎችን ያመቻችልናል እንጂ እየመላለሰ እንደ ሰው አይነዘንዘንም፡፡ ስሙ የተመሰገነ ይኹን! ወገኖቼ! ገና ስንጀምር እንደተናገርነው ይህቺ ከተማ ድሀ የሚበደልባት ጣዖት የሚመለክባት የሞት ከተማ ናት፡፡ ክፋትዋ ጽርሐ አርያም የደረሰ ነው፡፡ እግዚአብሔር ግን አሁንም ይወዳታል፡፡ እግዚአብሔር ግን አሁንም ያፈቅራታል፡፡ እግዚአብሔር የሚጠላው ፍጥረትስ ማን አለ? የቅዳሴ ማርያም ጸሐፊ አባ ሕርያቆስ እንደተናገረው እግዚአብሔር ያፈቅራል፤ እግዚአብሔር ባለሟል ያደርጋል፤ እግዚአብሔር ዝቅ ብሎ እንደ ሰው ያናግራል፡፡ መልካም ስላገኘብን አይደለም፤ ባሕርዪው ፍቅር ስለኾነ እንዲሁ ያፈቅናል እንጂ፡፡ እግዚአብሔር ኃጢአተኛውን ይፈልገዋል፡፡ እግዚአብሔር ደካማውን ይፈልገዋል፡፡ እርሱ የሚጠላው ኃጢአትን እንጂ ኃጢአተኛውን አይደለምና፡፡ እግዚአብሔር የሚጸየፈው የነነዌን ኃጢአት እንጂ የነነዌን ሰዎች አይደለም፡፡ እግዚአብሔር የሚጸየፈው እኛን አይደለም፤ ኃጢአታችንን እንጂ፡፡ አባት ልጁን እንዴት ይጠላል?

FeedBurner FeedCount