Monday, February 22, 2016

ትንቢተ ዮናስ - ክፍል ሦስት



(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ የካቲት 15 ቀን 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

ምዕራፍ ሦስት

ዓሣው ዮናስን በአንጻረ ነነዌ ተፋው፡፡ እግዚአብሔርም ልክ እንደ መጀመርያው፡- “ተነሥተህ ወደዚያች ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ፤ እኔ ከዚህ ቀደም አስተምር ብዬ እንደነገርኩህ አስተምራቸውአለው፡፡ ዮናስም መጀመርያ እንዳደረገው ከጌታ ፊት ለመሸሽ አልሞከረም፡፡ እግዚአብሔር እንዳዘዘው ተነሥቶ ሄደ እንጂ፡፡ ተወዳጆች ሆይ! እስኪ የእግዚአብሔርን ፍቅር ቆም ብለን እናሰላስለው፡፡ ዮናስ ለወገኖቹ ለእስራኤል አዝኖ አልታዘዝ ብሎ ነበር፡፡ ባለመታዘዙ ምክንያትም ወደ ሌላ ኃጢአት ገብቶ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ግን አሁንም ይወዷል፡፡ ወደዚያች ወደ ታላቂቱ ከተማሌላ ነቢይ ልላክአላለም፤ከእንግዲህ ወዲህ ዮናስን አልፈልገውምአላለም፡፡ እግዚአብሔር ዮናስን በቃል እንኳ የገሰጸው አይደለም፡፡ ዳግመኛምዮናስ ሆይ! ትእዛዜን ተላልፈህ የሸሸኸው ስለምንድነው?” አላለውም፡፡ በተግባር የደረሰበት ኹሉ በቂ ነውና፡፡ በመኾኑም አሁን ተጨማሪ የቃል ተግሳጽ አላስፈለገውም፡፡ ዳግመኛ በቃላት ቢገስጸው ዮናስ ምን ያክል ስሜቱ ሊጐዳ እንደሚችል ሰው ወዳጁ ጌታ ያውቃልና፡፡ እግዚአብሔር ስሜታችንን ምን ሊጐዳው እንደሚችል ጠንቅቆ ያውቃል፤ በመኾኑም ይጠነቀቅልናል፡፡ ስሕተታችን ምን እንደኾነ በራሳችን አውቀን እንድንመለስ ኹኔታዎችን ያመቻችልናል እንጂ እየመላለሰ እንደ ሰው አይነዘንዘንም፡፡ ስሙ የተመሰገነ ይኹን! ወገኖቼ! ገና ስንጀምር እንደተናገርነው ይህቺ ከተማ ድሀ የሚበደልባት ጣዖት የሚመለክባት የሞት ከተማ ናት፡፡ ክፋትዋ ጽርሐ አርያም የደረሰ ነው፡፡ እግዚአብሔር ግን አሁንም ይወዳታል፡፡ እግዚአብሔር ግን አሁንም ያፈቅራታል፡፡ እግዚአብሔር የሚጠላው ፍጥረትስ ማን አለ? የቅዳሴ ማርያም ጸሐፊ አባ ሕርያቆስ እንደተናገረው እግዚአብሔር ያፈቅራል፤ እግዚአብሔር ባለሟል ያደርጋል፤ እግዚአብሔር ዝቅ ብሎ እንደ ሰው ያናግራል፡፡ መልካም ስላገኘብን አይደለም፤ ባሕርዪው ፍቅር ስለኾነ እንዲሁ ያፈቅናል እንጂ፡፡ እግዚአብሔር ኃጢአተኛውን ይፈልገዋል፡፡ እግዚአብሔር ደካማውን ይፈልገዋል፡፡ እርሱ የሚጠላው ኃጢአትን እንጂ ኃጢአተኛውን አይደለምና፡፡ እግዚአብሔር የሚጸየፈው የነነዌን ኃጢአት እንጂ የነነዌን ሰዎች አይደለም፡፡ እግዚአብሔር የሚጸየፈው እኛን አይደለም፤ ኃጢአታችንን እንጂ፡፡ አባት ልጁን እንዴት ይጠላል?

ዮናስ ትልቅ ትምህርት ቤት ውስጥ ገብቶ ስለወጣ አሁን እሺ በእጄ ብሎ ታዘዘ፡፡ ከነፋሱ ተምሯል፤ ከማዕበሉ ተምሯል፤ ከዓሣው ተምሯል፡፡ ስለኾነምአሜንብሎ ታዘዘ፡፡ ወደ ታላቂቱ ከተማ፣ ከበር እስከ በር ያለው ዙርያዋ በእግር የሦስት ቀን ጐዳና ወደሚኾን ሰፊዋ ከተማ፣ መቶ ሀያ ሺሕ የሚያህል ሕዝብ ወደ ሚኖርባት ከተማ የአንድ ቀን መንገድ ያህል ገባ፡፡እስከ ሦስት ቀን ድረስ ነነዌ ትጠፋለችብሎም ሰበከ፡፡ ተጨማሪ የለውም! በቃ! “እስከ ሦስት ቀን ድረስ ነነዌ ትጠፋለችብቻ፡፡ የነነዌ ሰዎችም በዚህች አጭር ቃል ብቻ እጅግ የሚያስደንቅ ፍሬ አፈሩ፡፡ እግዚአብሔር የተናገረውን አመኑ፡፡ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ማቅ ለበሱ፡፡ ልባቸው ተሰበረ፡፡ ልብሳቸውን ትተው አመድ ነስንሰው ንስሐ ገቡ፡፡ ንጉሡም (ስልምናሶር) ይኸን ሰምቶ ከዙፋኑ ወረደ፤ ማቅ ለበሰ፤ አመድ ነሰነሰ፤ ንስሐ ገባ፡፡ ሰውና እንስሳ፣ ላምና በግ ከምግብ ተከለከሉ፡፡ ወደ ሣር አልተሰማሩም፡፡ ውሀ አልጠጡም፡፡ ኹሉም ጾሙ፤ እንስሳቱም ጭምር፡፡ ሰዎች ኹሉ ማቅ ለበሱ፡፡ አንድ ኹነው ወደ እግዚአብሔር በብርቱ ጮኹ፡፡ ኹሉም ክፉ ሥራቸውን፣ ቅሚያንና ስርቆትን ተዉ፡፡ በእጃቸው የሚሠሩትን ጣዖት ተዉ፡፡እግዚአብሔር ያዝንልን እንደኾነ ማን ያውቃል? ፈርዶ ያመጣውን መቅሰፍቱን ይመልስ እንደኾነ ማን ያውቃል? ከእንግዲህ ወዲህ አንሞት እንደኾነ ማን ያውቃል?” አሉ፡፡ በጣም የሚያስደንቀው ዮናስንስሐ ብትገቡ እግዚአብሔር ይቅር ይላችኋልእንኳን አላላቸውም፡፡ ስለ እግዚአብሔር ይቅርታ ምንም አላስተማራቸውም፡፡ ስለ ንስሐ ጥቅም ምንም አልሰበካቸውም፡፡እስከ ሦስት ቀን ድረስ ነነዌ ትጠፋለችአላቸው እንጂ ሌላ ተጨማሪ ትምህርት አልሰጣቸውም፡፡ እነርሱ ግን ተግባራዊ ምላሽ ሰጡ፡፡ የከተማይቱ ሕዝብ በሙሉ ወደ ታላቁ አምላክ ጮኸ፡፡ ወደ መሐሪው ጌታ ዕንባውን እየረጨ አለቀሰ፡፡ ኹሉም ስለ ኃጢአቱ ማቅ ለበሰ፡፡ ንጉሡ ሳይቀር ምድራዊዉን ልበሱ ጣለናከእናቴ ሆድ ዕራቆቴ ወጣኹአለ፡፡ ባዶነቱን ገለጸ፡፡ ንጉሥ ቢኾንም ወራዳነቱን መሰከረ፡፡ እግዚአብሔርም ከክፉ ሥራቸው እንደተመለሱ አየ፤ ሐዘናቸውን ተመለከተ፡፡ጾማቸውንና ጸሎታቸውንአይደለም፡፡እንደተመለሱእንጂ፡፡ ማመናቸው፣ ጸሎታቸው፣ ጾማቸው የመመለሳቸው ፍሬ ነበር፡፡ ስለኾነም በእርሳቸው ላይ ያደርገው ዘንድ ከተናገረው ክፉ ነገር ከማድረግ ተመለሰ፤ ክፉ ነገር አላደረገባቸውም፡፡ ታላቁ የቤተ ክርስቲያናችን ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዲህ ይላል፡- “ሰብአ ነነዌ ጾሙ፤ የእግዚአብሔር ምሕረትንም አገኙ፡፡ ሰብአ አይሁድም ጾሙ፤ ኾኖም ምንም አላገኙም፤ እንዳውም ተወቀሱ እንጂ /ኢሳ.583/፡፡ እንግዲያውስ እኛም እንደምን መጾምና ንስሐ መግባት እንዳለብን ከሰብአ ነነዌ እንማር፤ እግዚአብሔርም ይምረናል፤ በእኛ ላይ ከተናገረው ክፉ ነገርም ከማድረግ ይመለሳል” /Conc. Stat. 3:8/፡፡
እግዚአብሔር ደጋግሞ ይህችን ከተማታላቅ ከተማብሎ ጠርቷታል፡፡ ታላቅነቷ መቶ ሀያ ሺሕ ሕዝብ መያዟ አይደለም፡፡ ታላቅነቷ ከበር እስከ በር ያለው ዙርያዋ በእግር የሦስት ቀን ጐዳና ስለሚኾን ስፋቷ አይደለም፡፡ ታላቅነቷ ንስሐዋ ነው፡፡ ታላቅነቷ እጅግ አስደናቂ የኾነና ፈጣን መመለሷ ነው፡፡ ሎጥ የሰዶም ከተማ በእሳትና ዲን እንደምትጠፋ ሲናገር የገዛ አማቾቹ የሚያፌዝባቸው መሰላቸው /ዘፍ.1914/፡፡ ሰብአ ነነዌ ግን የማያውቁትን ዮናስን ሰሙት፡፡ አመኑት፡፡ ለእስራኤል እልፍ ጊዜ በእልፍ ነቢያት እንደተናገሩት አይደለም፡፡ አንዱን ነቢይ፣ በአንዲት ሐረግ ስብከቱ ሰሙት፤ አመኑት እንጂ፡፡ እግዚአብሔርም ራራላቸው፤ ፊቱን መለሰላቸው፤ እደ መዓቱን መልሶ እደ ምሕረቱን ዘረጋላቸው፡፡ 
ከእናንተ መካከል እንዲህ ብሎ የሚጠይቅ ሰው ሊኖር ይችላል፡- “የሰብአ ነነዌ የመመለስ ምሥጢር ምን ነበር?” የመመለሳቸው ምሥጢር የልባቸው ዝግጁ መኾን ነበር፡፡ የልባቸው ዝግጁ መኾን ነቢይ እንዲላክላቸው አደረጋቸው፡፡ የልብ ዝግጁነት በንስሐ ላይ እንዲህ ታላቅ የኾነ ሚናን ይጫወታልና፡፡ የሰብአ ነነዌ ንስሐ እንዲሁ ከውጭ ለታይታ አልነበረም፤ ከውስጥ ከልብ የሚመነጭ እንጂ፡፡ እንዲህም ስለኾነ ጌታ አመስግኖአቸዋል፡፡ ለትውልድ መፈራረጃ እንደሚኾኑም ተናግሮላቸዋል /ማቴ.1241/፡፡ ለካስ ፈሪሐ እግዚአብሔር ባለበት የጊዜ ርዝማኔ ትርጕም የለውም፤ ፈሪሐ እግዚአብሔር ከሌለን መቶ ዓመት ቆመን ብንጸልይም ትርጕም የለውም፡፡ ዋናው ነገር የልብ መመለስ ነውና፡፡ ወገኖቼ ልብ እንበል! ሰብአ ነነዌን ባሰብኩ ቁጥር እደነቃለኹ፡፡ ኹሉም ተመለሱ፤ ኹሉም ተጸጸቱ፤ ኹሉም ማቅ ለበሱ፤ እግዚአብሔርም ሰማቸው፡፡ መቶ ሀያ ሺሕ ነፍሳት ወደ በረታቸው ተመልሰው ገቡ፡፡ በሰማይ ዘንድ በአንድ ኃጥእ ሰው ንስሐ መግባት ብቻ ታላቅ የኾነ ደስታ የሚኾን ከኾነ መቶ ሀያ ሺሕ የነነዌ ሰዎች ንስሐ ሲገቡ በሰማይ እንዴት ያለ ታላቅ ደስታ ኾኖ ይኾን?

No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount