Wednesday, February 24, 2016

ትንቢተ ዮናስ - የመጨረሻው ክፍል



(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ የካቲት 16 ቀን 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

ምዕራፍ አራት

ሰብአ ነነዌ ስለዳኑ በሰማያት ሐሴት ኾኗል፡፡ እግዚአብሔር ደስ ተሰኝቷል፡፡ መላእክት እርስ በእርሳቸው፡- “እንኳን ደስ ያለህ! እንኳን ደስ ያላችሁ! በአንዲት ቀን ብቻ መቶ ሀያ ሺሕ የነነዌ ሰዎች ወደ እግዚአብሔር ተመልሰዋልይባባላሉ፡፡ ዮናስ ግን ፈጽሞ አዝኗል፡፡ ከአፍአ (ከውጭ) ሲታይ ዮናስ አሕዛብ ስለዳኑ የተበሳጨ ይመስላል፤ ኾኖም ግን ደጋግመን እንደተናገርን ዮናስ እንዲህ የሚያዝነው ወገኖቹ እስራኤል ከእግዚአብሔር ኅብረት መለየታቸውን አይቶ ነው፡፡ ዮናስ በሕይወት ከመኖር ይልቅ ሞትን የሚመርጠው ወገኖቹን እስራኤልን እጅግ ከመውደዱ የተነሣ ነው፡፡ ቅዱስ ጀሮም ነቢዩ ዮናስ ለምን እንዲህ ፈጽሞ እንዳዘነ ሲናገር፡- “ዮናስ እጅግ አዘነ፡፡ ኾኖም አንዳንድ ሰዎች እንደሚሉት ሰብአ ነነዌ ስለዳኑ አልነበረም፡፡ የአሕዛብ መዳን የወገኖቹ የእስራኤል መጥፋት መኾኑን ስላወቀ እንጂ፡፡ ከነቢያት ተለይቶ የወገኖቹን የእስራኤልን መጥፋት እንዲናገር በመመረጡ እንጂ፡፡ በመኾኑም ወገኖቹ እስራኤል ከሚሞቱ እርሱ ቢሞት ተመኘ፡፡ ይኸውም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእስራኤል መጥፋት አይቶ እንዳለቀሰው ነው /ማቴ.2337/ ሐዋርያት በሥጋ የሚዛመድዋቸው ወገኖቻቸው ከክርስቶስ አንድነት ተለይተው በመቅረታቸው ስለ እነርሱ የተረገሙ እንዲኾኑ እንደጸለዩት ነው /ሮሜ.94-5/” ብሏል /St. Jerome, Commentary on the Book of Jonah, IV:1/፡፡

ዮናስ በዚያች ሰዓት የሚያስበው ስለወገኖቹ ስለ እስራኤል ብቻ ነበር፡፡ በዚያች ሰዓት የሚያለቅሰው ከዘለዓለም አንሥቶ ቃል ኪዳን የተገባላቸው ወገኖቹ ከእግዚአብሔር ልጅነት ተለይተው ስለወጡ ስለ እስራኤል ብቻ ነበር፡፡አቤቱ በሀገሬ ሳለኹ ተናግሬ የለምን? ስለዚህ ነገር (የወገኖቼን ጥፋት እንዳላይ) ኰብልዬ ወደ ደሴት የሄድኹ አይደለምን? መሐሪ ይቅር ባይ እንደኾንኽ፣ ከመዓት የራቅህ ቸርነትህ የበዛ እንደኾነ፣ በዚህም እስራኤል ጠፍተው አሕዛብ እንዲድኑ አውቃለሁና፡፡ አሁንም አቤቱ ነፍሴን ለያት፡፡ በሕይወት ኖሬ የወገኖቼ የእስራኤል ጥፋት ከማይ እኔ ሞቼ እነርሱ በሕይወት እንዲኖሩ እሻለሁናእያለ ይጸልይ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ግን እስራኤላውያን ጌታ ሊያድናቸው ስላልወደደ ሳይኾን በፈቃዳቸው የሚጠፉ መኾናቸውን ስለሚያውቅ፡- “ዮናስ ሆይ! ወገኖችህ እስራኤል እንዲህ በፈቃዳቸው በመጥፋታቸው አዘንህን?” አለው፡፡ማዘንህ ትክክል አይደለምአላለውም፤ እስራኤል የሚመለስ ልቡና እንደሌላቸው ያውቃልና፡፡ መዳን የሚሰብኩላቸውን የነቢያቶቹን ደም ሲያፈሱ እንደኖሩ ያውቃልና፡፡ በኋለኛው ዘመንም አንድያ ልጁን የሚሰቅሉት መኾናቸውን ያውቃልና፡፡ በእርግጥም እግዚአብሔር ሰብአ ነነዌን ያዳናቸው እስራኤልን ጠልቶ አልነበረም፡፡ እግዚአብሔር ፊቱን ወደ አሕዛብ ያዞረው ሰብአ እስራኤል አልሰማ ስላሉ ነው፡፡ እግዚአብሔር ፊቱን ወደ አሕዛብ ያዞረው እስራኤል በፈቃዳቸው ስለሞቱ ነው፡፡ ወገኖቼ እናስተውል! እንደ አይሁድ ልቡናችንን የምናደነድን ከኾነ መዳን ከእኛ ቤት ይርቃል፡፡ መዳን ወደ ሌሎች ይሄዳል፡፡ ልባችን ደንዳና ከኾነ ኖኅም ቢኾን፣ ዳንኤልም ቢኾን፣ ኢዮብም ቢኾን እኛን ማዳን አይቻለውም /ሕዝ.14 14/፡፡ ዮናስ አዘነ፡፡ ነነዌንም ትቶ ከከተማይቱ በስተ ምሥራቅ በኩል ተቀመጠ፡፡ በዚያም ለራሱ ዳስ ሠርቶ ከጥላው በታች ተቀመጠ፡፡ ሐዘኑም ከልክ አለፈና በእግዚአብሔር እንዲያኮርፍ አደረገው፡፡ እስራኤል በፈቃዳቸው እንደሚሞቱ አልታይ አለው፡፡ እንኳን እርሱ ራሱ ሙቶላቸው እውነተኛው ዮናስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሙቶላቸውም የማይድኑ መኾናቸውን አልታይ አለው፡፡ ከእግዚአብሔር በላይ ለእስራኤል የቀና መሰለ፡፡ ጭራሹንም የዳኑት የነነዌ ሰዎች ዳግም መከራ እንዲያገኛቸው ተመኘ፡፡ ሰው ወዳጁ ጌታ ግን ዮናስን ከዚህ ሊያወጣው ፈለገ፡፡ ኹል ጊዜ እንደሚያደርገውም የዮናስ ማኩረፍ ሳይመለከት ዝቅ ብሎ ያናግረው ጀመር፡፡ ዮናስ በታላቅ ሐዘን ከከተማይቱ ወጥቶና ከከተማይቱ በስተምሥራቅ በኵል ተቀምጦ ሲያየው እግዚአብሔር ቀረበው፡፡ ተወዳጆች ሆይ! የእግዚአብሔር ፍቅር ታስተውላላችሁን? እኔና እናንተ ከራሳችን መረዳት ወጥተን ከእርሱ ጋር እንድንታረቅ አባታችን እንዲህ ነው የሚያናግረን! እንዲህ ነው የሚፈልገን! እንዲህ ነው እንደ ሕፃን የሚያባብለን!
ስለዚህም ወደ ዮናስ ቀረበ፡፡ መቅረብ ብቻም ሳይኾንከእኔ በላይ ለእስራኤል የቀናህ ቢመስልህም አሁንም ልጄ ነህ፤ ሰብአ ነነዌን እንዳዳንኳቸው አንተንም ካለህበት ኹናቴ እፈውስኻለሁ፤ ወደ ተርሴስ ስትሄድ አብሬህ እንደነበርኩ አሁንም ከአንተ ጋር ነኝ፤ ወደ ባሕሩ ስትጣል አብሬህ እንደነበርኩ አሁንም አልለይህምይለው ነበር፡፡ ምን ዓይነት ፍቅር ነው? ምን ዓይነት መውደድ ነው? ከዮናስ ጋር ለመታረቅ ብሎም በምሳሌ ሊያስረዳው ወደደ፡፡ አስቀድሞምቅል ይብቀልብሎ አዘዘ፡፡ የዮናስን ራስ ፀሐይ እንዳያገኘውም ጐጆውን ሸፈነለት፡፡ ቅል በቅሎ ጐጆውን ስለሸፈነለትም ዮናስ ፈጽሞ ደስ አለው፡፡ በማግሥቱ ግን እግዚአብሔር ትል ቈርጦ ይጥላት ዘንድ አዘዘ፤ የበቀለችው ቅልም ደረቀች፡፡ ዳግመኛም ፀሐይ በወጣች ጊዜ የሚያቃጥል ነፋስ ይመጣ ዘንድ አዘዘ፡፡ የዮናስን ራስ እስኪዝል ድረስ ዋዕየ ፀሐይ መታው፡፡ በዚያን ጊዜ ዮናስ ሰውነቱ ተቈጣች፡፡ ይህቺ ቅል የእስራኤል ምሳሌ ናት፡፡ እስራኤል ስትለመልም አይቶ ዮናስ ደስ አለው፡፡ ወገኖቹ እስራኤል ወደ ክርስቶስ የሚያደርሳቸውን ሕግና ነቢያትን ሲሰጣቸው አይቶ ደስ አለው፡፡ ከከተማይቱ በስተ ምሥራቅ ወጥቶ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ በሕዝብና በአሕዛብ የሚወጣውን ፀሐይ (ክርስቶስን) አይቶ ደስ አለው፡፡
ዮናስ እስራኤል እንድትለመልም ምንም አላደረገም፡፡ ይህን ያደርግ የነበረው እግዚአብሔር ነውና፡፡ ከግብጽ ባርነት አውጥቶ እንዲለመልሙ (ከፍ ከፍ እንዲሉ) ያደረጋቸው እግዚአብሔር ነው፡፡ በበረሀው ጉዞ ዋዕየ ፀሐይ እንዳያገኛው በደመና ሲጋርዳቸው የነበረው እግዚአብሔር ነው፡፡ በጨለማ ዕንቅፋት እንዳይመታቸው በብርሃን ዓምድ ሲመራቸው የነበረው እግዚአብሔር ነው፡፡ ሥጋ አማረን ባሉ ጊዜ መናን ከሰማይ አውርዶ ሲመግባቸው የነበረው እግዚአብሔር ነው፡፡ ውኃ ጠማን ሲሉ ከዓለት ውኃ እያፈለቀ ሲያጠጣቸው የነበረ እግዚአብሔር ነው፡፡ ሕግን የሰጣቸው እግዚአብሔር ነው፡፡ ወደ ተስፋይቱ ምድር መርቶ ያስገባቸው እግዚአብሔር ነው፡፡ ነቢያትን የላከላቸው እግዚአብሔር ነው፡፡ ለዚህች ቅል (ለእስራኤል) ያላደረገውስ ምን አለ /ኢሳ.53-4/? እስራኤል ግን ይህን ኹሉ ረስተው በእግዚአብሔር አመፁ፡፡ ፈጣሪያቸውን ተዉ፡፡ እንዲህም ስለኾነ እግዚአብሔር ዮናስንስለዚች (ዓመፀኛ) ቅል (እስራኤል) ትቈጣ ዘንድ ይገባሃልን?” ይለው ነበር፡፡ ዮናስ ግን ወገኖቹ እስራኤላውያን ወደ ክርስቶስ የሚያደርሳቸውን ሕግንና ነቢያትን ይዘው ሳለ ዳግም ሲደርቁ (ሲጠፉ) ማየትን ስላልወደደእነርሱ ከሚጠፉ እኔ ብጠፋ ይሻለኛልአለ፡፡ እግዚአብሔርም፡- “አንተ ትበቅል ዘንድ ላልደከምህባት፣ ላላሳደግሃትም፣ በአንድ ሌሊት በቅላ በአንድ ሌሊት በደረቀች (በጠፋች፣ የንስሐም ፍሬ ላልሰጠች) በቅሊቱ (በእስራኤል) አዝነሃል፡፡ እኔስ የንስሐን ፍሬ ላገኘኹባቸው ለሰብአ ነነዌ (በአጠቃላይ ለአሕዛብ) ላዝን አይገባኝምን?” እያለ ከባርያው ጋር ይከራከር ነበር፡፡ ዮናስም የአምላኩን ምክር ተቀብሏል፡፡ ወገኖቼ! የእግዚአብሔር ትሕትና ትመለከታላችሁን? እንደምን አድርጎ ዮናስን እንዳስረዳው ትገነዘባላችሁን?

ማጠቃለያ

ከዚህ የትንቢተ ዮናስ መጽሐፍ እጅግ ብዙ ነገሮችን ተመልክተናል፡፡ የዮናስ ሕይወት ምን እንደሚመስል፣ ለወገኖቹ ለእስራኤል የነበረው ቅናት፣ የሰብአ ነነዌ የንስሐ ፍሬ እንደምን እንኾነ አይተናል፡፡ በዚህ መጽሐፍ የተረዳነውና እግዚአብሔር ለልጆቹ ያለው ፍቅር ግን በጭራሽ የዚህ ዓለም ቋንቋ ሊገልጸው እንደማይችል ነው፡፡ እንደተመለከትነው እግዚአብሔር ልጆቹን በብርቱ ይፈልጋቸዋል፡፡ ሰዎች ወደ ንስሐ እንዲመጡ ኹኔታዎችን ያመቻችላቸዋል፡፡ አስቀድሞ የመርከበኞችን ነፍስ ፈለገ፤ አገኛትም፡፡ ቀጥሎ የዮናስን ነፍስ ፈለጋት፤ አገኛትም፡፡ አሁንም የሰብአ ነነዌን ነፍስ ፈለጋት፤ የእነርሱንም አገኛት፡፡ የመንፈስ ቅዱስ እንዚራ የተባለው ያዕቆብ ዘሥሩግ ይህን ሲመለከት በልደት ድርሳኑ እንዲህ ነው ያለው፡- “ሰውና እግዚአብሔር ተጣሉ፡፡ ሰው ከፈጣሪው ጋር ሊታረቅ ስላልቻለም ፈጣሪ ራሱን ዝቅ አድርጎ ይፈልገው ነበር፡፡እግዚአብሔር እንዲህ ዝቅ ብሎ ልጆቹን ሲፈልግ እንደተዋረደ አልቈጠረውም፡፡ ከዚያ ይልቅ ልጆቹን ፈልጐ ሲያገኛቸው ደስ ብሎት በትከሻው ተሸከማቸው እንጂ፡፡
ተወዳጆች ሆይ! ዛሬ ከአምላካችን ርቀን የምንገኝ እኛን ለመፈለግ አባታችን ማንን ልኳል? እግዚአብሔር እኮ ፍለጋ ላይ ነው፡፡ ልባችን ያርፍበት ዘንድ እየፈለገ ነው፡፡ የዚህን ዓለም ጣጣ በማሰብ የዛለው ልባችን ያርፍበት ዘንድ እየፈለገ ነው፡፡ የባቢሎንን ግንብ በመሥራት የደከመው ልቡናችን እርሱ ያርፍበት ዘንድ እየፈለገ ነው፡፡ እንደ ሰብአ ነነዌ ተመልሰን በሰማያት ታላቅ ደስታ ይኾን ዘንድ እየፈለገን ነው፡፡ ፍሪዳውን አዘጋጅቶ እየጠበቀን ነው፡፡ እንግዲያውስ ከአምላካችን ርቀን ኑሮ አይመችምና እንመለስ፡፡ ሞትም ቢኾን፣ ሕይወትም ቢኾን ከእርሱ ጋር ይሻለናልና ወደ ቤታችን እንመለስ፡፡ ወደ አምላካችን መመለስ አማራጭ ሳይኾን ምርጫችን ይኹን፡፡ ይህን እንድናደርግ ሰውን በመውደዱ ሰው የኾነ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይርዳን፡፡ የዮናስ አምላክ በረከት ከኹላችን ጋር ይኹን፡፡ አነቃቅቶ ላስጀመረን አተጋግቶም ላስፈጸመን ለእግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይግባው አሜን፡፡

3 comments:

  1. ቃለ ሕይወት ያሰማልን

    ReplyDelete
  2. ቃለ ሕይወት ያሰማልን እግዚአብሔር ጸጋውን ያብዛላችሁ

    ReplyDelete
  3. ቃለ ሕይወት ያሰማልን,እግዚአብሔር ይመስገን ጸጋውን ያብዛላችሁ ።


    ReplyDelete

FeedBurner FeedCount