(መቅረዝ ዘተዋሕዶ ነሐሴ ፲፬ ቀን ፳፻፬ ዓ.ም)፡- አምላክን የወለደች የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ነገረ ዕርገቷን እግዚአብሔርን አጋዥ በማድረግ እንናገራለን፡፡
ተወዳጆች ሆይ! “አቤቱ ወደ ማረፍያህ ተነሥ፤ አንተም የመቅደስህ ታቦትም” እያለ መሰንቆውን ንጽሕት ክብርት ስለምትሆን
ስለ ድንግል ማርያም ሲደረድር፣ ሲዘምር፣ ሲያመሰግን ስሙት፡፡ ሁሉም ምሳሌዎች ይገቧታልና ነብያትም መዝሙረኛውን መስለው በብዙ ሕብረ
አምሳል አመስግነዋታል፡፡ ፍቁራን ሆይ! ከአዳም ጀምረው እስከ ዛሬ ድረስ በየዘመኑ የተነሡት ሁሉ እንደምን እንደተባበሩ የምንሰማ
እንሁን፡፡ ነቢዩ ሰሎሞን “በየትውልዱ በጻድቃን ሕሊና ትመላለሳለች” እንዳለ ሁሉም መዋትያን ቢሆኑም ምስጋናዋ ግን አይሞትም፡፡
ልጇ ወዳጇም ምስጋናዋን በየዕለቱ ያዘጋጃል፤ የወንጌልን መንገድ በሚያቀኑ ልጆቹም ምስጋናዋን በአእምሮአቸው ሹክ ይላቸዋል፡፡ ሰማይና
ምድር የማይወስኑትን አምላክ በማሕፀኗ የተሸከመች ናትና፤ ኪሩቤል ሱራፍኤል ዙፋኑን በረዐድና በመንቀጥቀጥ የሚሸከሙትን ሰማያዊ መለኮት
በዠርባዋ ያዘለች በክንዷም የታቀፈች ናትና፤ ሰማይና ምድር ከፊቱ የሚሸሹለትን የባሕርይ አምላክ እርሱን ከንፈሮቹን የሳመች ናትና፤
ፍጥረታትን ሁሉ በዝናብ አብቅሎ በፀሐይ አብስሎ የሚመግበውን እግዚአብሔር ወልድ የድንግልና ጡቶቿን ያጠባች ናትና ብጽዕት፣ ንዕድት፣
ክብርት ነሽ ይሏት ዘንድ ሹክ ይላቸዋል፡፡ አዎ! ሥጋቸውን፣ ነፍሳቸውንና ሕሊናቸውን ከኃጢአት ያነጹት ሰዎች ሁሉ ክብራቸው ከድንግል
ማርያም ክብር ጋር አይተካከልምና “ወላዲተ አምላክ ቅድስት ድንግል ማርያም ሆይ! መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል አንቺ ከሴቶች ሁሉ ተለይተሸ
የተባረክሽ ነሽ፤ የማሕፀንሽ ፍሬ ኢየሱስ ክርስቶስም የተባረከ ነው ብሎ እንዳመሰገነሽ እኛም ዋሕድ ቃል እግዚአብሔር ከሥጋሽ ሥጋ፣
ከነፍስሽ ነፍስን ነሥቶ በተዋሕዶ ፍጹም ሰው ሆኗልና ምልዕተ ጸጋ፣ ምልዕተ ክብር፣ ምልዕተ ውዳሴ እመቤታችን ሆይ ደስ ይበልሽ”
እያሉ ውዳሴዋን ይናገራሉ፡፡ አስቀድመን እንደተናገርን በቅዱሳን ላይ የቅዱሳን ቅዱስ እግዚአብሔር ያድራል፤ ከእመቤታችን ግን በግልጽ
ተወለደ፡፡ ቅዱሳንን ይመግባቸዋል፤ ድንግል ግን ሁሉን የሚመግበውን በጡቶቿ አሳደገችው፡፡ ለቅዱሳን ኃይላቸው እርሱ ነው፤ ድንግል
ግን በጀርባዋ አዘለችው፡፡