በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ለጌታችንና
ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ካላቸው እይታ አንጻር የሥነ መለኰት ምሁራን አይሁድን በሦስት ምድብ ይመብዋቸዋል፡፡ አንደኛው
ምድብ የአለቆች፣ የካህናትና የፈሪሳውያን ምድብ ሲሆኑ እነርሱም ለክርስቶስ ፍጹም ጥላቻ የነበራቸው ናቸው፡፡ ሁለተኛው ምድብ
ደግሞ በኢየሩሳሌም ውስጥ የሚኖሩና በአንደኛው ምድብ ባየናቸው ቡድኖች ጥላቻ ግራ የተጋቡ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች የአለቆቻቸውን
ጥላቻ ቢያውቁም ጌታ በሚያደርጋቸው ገቢረ ተአምራት ፍጹም የሚማረኩ ናቸው፡፡ ጌታን ለአለቆቻቸው አሳልፈው እንዳይሰጡት
በሚያስተምራቸው ትምህርት፣ በሚያሳያቸው ፍቅር፣ በሚያደርግላቸው ምልክት ልባቸው የተወሰዱ ናቸው፡፡ ሦስተኛው ምድብ ደግሞ
ከኢየሩሳሌም ውጪ የሚኖሩ ናቸው፡፡ እነዚህ ከኢየሩሳሌም ውጪ የሚኖሩ አይሁዳውያን ለገቢረ በዓል ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጡ
በክርስቶስ እጅግ የተማረኩና በምድብ አንድ ያየናቸውን አለቆች ስሜት የማያውቁ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች አለቆች ክርስቶስን
ሊገድሉት እንደሚፈልጉ ሲሰሙ በእጅጉ የተደናገጡና በአለቆቹ ክፉ ሥራ ግርምት ውስጥ የገቡ ናቸው /Fr.Tadros Malaty,Commentary
on the Gospel of John,pp359/፡፡
አሁን
ወንጌላዊው እየነገረን ያለው የሁለተኛው ምድብ የሆኑ ሰዎች ስሜት ነው፡፡ “እንግዲህ ከኢየሩሳሌም ሰዎች አንዳንዶቹ እንዲህ አሉ፡- ሊገድሉት የሚፈልጉት ይህ አይደለምን? እነሆም፥ በግልጥ ይናገራል አንዳችም አይሉትም። አለቆቹ ይህ ሰው በእውነት ክርስቶስ እንደ ሆነ በእውነት አወቁን? ነገር ግን ይህን ከወዴት እንደ ሆነ አውቀናል፤ ክርስቶስ ሲመጣ ግን ከወዴት እንደ ሆነ ማንም አያውቅም” እንዲል /ቁ.25-27/። እንዲህ
ማለታቸው ነበር፡-“አለቆቻችን እንገድለዋለን ብለው የሚዝቱበት ይህ አሁን በድብቅ ያይደለ በይፋ በስውር ያይደለ በግልጥ
የሚያስተምራቸው አይደለምን? እነሆ፡- ከእናንተ ሕግን የሚያደርግ አንድ ስንኳ የለም
ብሎ በግልጥ ይናገራል /ቁ.19/፤ ሆኖም ግን አንዳች ስንኳ አይሉትም፡፡ ወይስ ይህ ሰው በእውነት ክርስቶስ እንደሆነ አውቀዋል
ማለት ነው? ይህ አሁን የሚናገረው ሰውዬ (ሎቱ ስብሐትና) ከቤተ ልሔም እንደተወለደ የቀራጩ የዮሴፍም ልጅ እንደሆነ እናውቃለን
/ማቴ.2፡4/፡፡ ክርስቶስ ሲመጣ ግን ኢሳይያስ፡- ትውልዱን ማን ይናገራል ብሎ እንደተናገረ ማንም አያውቅም” /ኢሳ.53፡8፣ Saint Cyril the Great/፡፡
የእነዚህ
ሰዎች ችግር ነቢዩ ኢሳይያስ የተናገረው ቃል ለቀዳማዊ ልደቱ ከማድረግ ይልቅ ለደኃራዊ ልደቱ አድርገው መረዳታቸው ነው፡፡
ነቢያቱ ግን እንዲህ የቀዳማዊ ልደቱ አይመረመሬነት እንደተናገሩ ሁሉ /ኢሳ.53፡8/ ሰው ሆኖ ከድንግል እንደሚወለድም በግልጽ
ቦታውን ሳይቀር ጨምረው ተናግረዋል /ኢሳ.7፡14፣ ሚክ.5፡2/፡፡
ከዚህ በኋላ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመቅደስ ሲያስተምር፡- “እኔንም ታውቁኛላችሁ ከወዴትም እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ፤ እኔም በራሴ አልመጣሁም ነገር ግን እናንተ የማታውቁት የላከኝ እውነተኛ ነው፤ እኔ ግን ከእርሱ ዘንድ ነኝ እርሱም ልኮኛልና አውቀዋለሁ” ብሎ ጮኸ /ቁ.28-29/። እንዲህ ማለቱ ነበር፡- “ጀሮ ያለው መስማትን ይስማ፤ ነቢያት አብዝተው እንደነገሯችሁ ከወዴት
እንደሆንኩ (ናዝሬት ገሊላ እንዳደግኩ)፣ ከወዴት እንደተወለድኩ (ከቤተልሔም እንደተወለድኩ)፣ ከማን ወገን እንደተወለድኩ (ከዳዊት
ወገን እንደተወለድኩ) ታውቃላችሁ፡፡ ሆኖም ግን ከአብ ባሕርይ ዘእምባሕርይ አካል ዘእምአካል የተወለድኩትን ቀዳማዊ ልደቴን ጨምረው
የነገርዋችሁን አታውቁም ብዬ በእውነት እነግራችኋለሁ፤ ይህን ከማመን ይህን ከመቀበል በፍቃዳችሁ ተከልክላችኋል ብዬ በእውነት
ያለ ሐሰት እነግራችኋለሁ/St. John Chrysostom, Hom
50./፡፡ በእኔ
ፈቃድ ብቻ ያይደለ በበአባቴም ፈቃድ ሰው ሆኛለሁና እርሱን ብታምኑበት እኔም ከእውነት የተወለድኩ እውነት እንደሆንኩ ባወቃችሁ ባመናችሁ
ነበር፡፡ ደጋግሜ እንደነገርኳችሁ እኔ በህልውና ያየሁትን ነገርኳችሁ እንጂ አብን በባሕርይው ያየው አንድ ስንኳ የለም
/ዮሐ.1፡18/፡፡ እኔ ልገልጽለት ያልፈቀደ፣ በእኔ ያላመነ ሁሉ አብን ሊያየው ሊያውቀው የሚችል እንደሌለ በእውነት
እነግራችኋለሁ፤ ወልድን ያየ ግን አብን አይቷል ብዬ በእውነት ያለ ሐሰት እነግራችኋለሁ” /ዮሐ.14፡9፣ Augustine, On the Gospel of St. John, tractate 31/፡፡
ፈሪሳውያን ግን እንዲህ ስለተናገረ ሊይዙት ይፈልጉ ነበር፤ ከማር በሚጣፍጠው መለኰታዊ ቃሉ የሕዝቡን ልብ እንደወሰደ ወደ እውነትም እንደመለሰ ሲያውቁ
ሊገድሉት ይፈልጉ ነበር፡፡ ነገር
ግን ጊዜው ገና ስላልደረሰ የሚሰቀልበት ሰዓት ስላልደረሰ በመለኰታዊ ሥልጣኑ ይህን እንዳያደርጉ ከለከላቸው፤ ስለዚህ ማንም እጁን አልጫነበትም /ቁ.30/።
የፈሪሳውያን ቁጣ እየበዛ በሄደ ቁጥር ሕዝቡም
እውነቱን እየተረዳ እያወቀ መጣ፡፡ ነገር ሁሉ ግልጽ እየሆነለት መጣ፡፡ ስለዚህ ከሕዝቡ ብዙዎች አመኑበት፡፡ ያመኑትም ሕዝብ እንዲህ
ብለው ተነጋገሩ፡- “አይሆንም አይደረግም እንጂ አለቆቻችን
ይመጣል ብለው የሚነግሩን ክርስቶስ
በመጣ ጊዜ ይህ አሁን ያመንንበት ክርስቶስ ካደረጋቸው ምልክቶች በላይ ተአምራትን ያደርጋልን?” /ቁ.31/፡፡ የሚደንቅ ነው! ሕሙማነ ሥጋ በተአምራት ሕሙማነ ነፍስም በትምህርት ሲፈውሳቸው በዙርያ
የነበሩ ድሆች አመንዝሮችና ቀራጮች አመኑበት፡፡ እናውቃለን ከሚሉት እረኞች ይልቅ የተበደሉት ሰዎች ዳኑበት፡፡ ቁስላቸውን
ፈወሱበት፡፡ ስብራታቸውን ጠገኑበት፡፡ ተስፋቸውን ቀጠሉበት፡፡ ከውድቀታቸው ተነሡበት፡፡ አለቆች ነን ባዮቹ ግን አንዳችም
ሳይጠቀሙ ከነደዌአቸው ቀሩ፤ ወደ ሐኪማቸው ከመቅረብ ተከለከሉ፤ ይባስ ብለውም ሊገድሉት ፈለጉ፡፡
ሕዝቡ ሰለ ክርስቶስ እንደዚህ ሲነጋገሩ ሲሰሙም ሎሌዎቻቸውን ላኩ /ቁ.32/። ሰው ወዳጁ ጌታ … ሰው አፍቃሪው ንጉሥ
ግን እንዲህ አላቸው፡-“ፈሪሳውያን ሆይ! በዚህ ዓለም ከእናንተ ጋር ብዙ እንደምቆይ ስለምን
ትቆጣላችሁ? ሸክም እንደሆንኩባችሁ አውቃለሁ፡፡ ክፋታችሁን በእውነት
ስለምናገርባችሁ አውቃለሁ፡፡ ሰላም እንደነሣኋችሁ አውቃለሁ፡፡ ሆኖም ግን እኔ ሳልፈቅድላችሁ ማድረግ አትችሉምና ጊዜዬ ሳይደርስ
እኔን ለመግደል በከንቱ የምትደክሙ አትሁኑ፡፡ በቅናትና በቁጣ ተነሳሥታችሁ እኔን ለመግደል የምትቻኮሉ አትሁኑ፡፡ ድኅነተ ዓለም
የምፈጽምባትን የእኔን ሰዓት፣ በእኔ ዘላለማዊ ዕቅድ ውስጥ ያለችውና መከራ መስቀልን የምቀበልባት ያቺ ሰዓት ስትደርስ በፈቃዴ፣
ወድጄ ራሴን እሰጣችኋለሁ፡፡ ከዚያን ጊዜ በኋላ ግን ሥራችሁ ክፉ ነውና ፈጽሞ አታገኙኝም፤ በጨለማ መኖርን የምትወዱ ናችሁና
ወደ ብርሃን መውጣት የማትፈልጉ ናችሁና ስለዚሁ በእናንተ ዘንድ የማድር የምዋሐድ አይደለሁምና አታገኙኝም፡፡ አንድም ጥጦስ
መከራ ሲያደርስባችሁ ትሹኛችሁ፤ አታገኙኝም፡፡ አንድም ጻድቃንን ልፈርድላቸው ኃጥአንን ልፈርድባቸው በመጣሁ ጊዜ አምነንበት
ቢሆን ብላችሁ ትፈልግኛላቹ፤ አታገኙኝም፡፡ መንገዱም እውነቱም እኔ ነኝና በእኔ ሳታምኑ ተድላ ደስታ ወዳለባት መንግሥተ ሰማያት
መምጣት አይቻላችሁምና አታገኙኝም፡፡ ፈሪሳውያን ሆይ! ጥቅም በሌለው ምክር ራሳችሁን የምታጎሳቁሉ አትሁኑ፡፡ አለቆች ሆይ! መከራ
ነፍስ የሚያመጣባችሁ ነውና ቁጣችሁን ወደ ሰገባው መልሱት፡፡ በተወደደ ሰዓት ሰማሁህ በመዳንም ቀን ረዳሁህ ይላልና እነሆ
የተወደደ ሰዓት አሁን ነው፤ እነሆ የመዳን ቀን አሁን ነው /2ቆሮ.6:2/፡፡ አትሳቱ! ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ
ያጭዳልና የዘለዓለምን ሕይወት ታጭዱ ዘንድ በመንፈስ የምትዘሩ ሁኑ /ገላ.6፡7-8/፤ በእኔ እመኑ በአባቴም እመኑ፡፡ እኔስ ሞታችሁን
እገድል ዘንድ እናውቀዋለን ከምትሉት ሆኖም ግን ከማታውቁት ከአባቴ ዘንድ መጥቻለሁና፣ ሕይወት ይሆንላቸው ዘንድ ለወደዱ ሕይወትን
እሰጣቸው ዘንድ ሰው ሆኛለሁና ሞት በእኔ ላይ ሥልጣን የለውም፡፡ ሰዓቱ ሲደርስ ግን የሲዖል የምሥጢር በሮችን እሰባብራለሁ፡፡ ምርኮን
እማርካለሁ፡፡ ስለዚህ እናንተ እንደምታስቡት ፈጥነንም እናስወግደው እንደምትሉት በመቃብር በስብሼ የምቀር አይደለሁም፡፡ ከሙታን
ተለይቼ እነሣለሁ እንጂ፡፡ መነሣትም ብቻ ሳይሆን ደቀመዛሙርቴ እያዩኝ በይባቤ መላዕክት በቅዳሴ በብርሃን በሥልጣን ዐርጋለሁ
/መዝ.46፡5/፡፡ ያኔ ሰዎች ዕርገቴን አይተው ያደንቃሉ፤ መላእክትም፡-“ይህ በእጅህ መካከል ያለ ቁስል ምንድነው?” ይሉኛል፤
እኔም “በወዳጆቼ ቤት የቆሰልኩት ቁስል ነው” እላቸዋለሁ /ቁ.33-34፣ ዘካ.13፡6፣ St. Augustine: On the Gospel of St. John, tractate
31:9/፡፡
ከዚህ
በኋላ አይሁድ፡- “እኛ እንዳናገኘው ይህ ወዴት ይሄድ ዘንድ አለው? በግሪክ ሰዎች መካከል ተበትነው ወደሚኖሩት ሊሄድና የግሪክን ሰዎች ሊያስተምር አለውን? እርሱ። ትፈልጉኛላችሁ አታገኙኝምም እኔም ወዳለሁበት እናንተ ልትመጡ አትችሉም የሚለው ይህ ቃል ምንድር ነው?” ብለው እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ /ቁ.35-36/።
ቸርነትህ የበዛ አፍቃሪያችን ሆይ! በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበን፡፡ ቀን ሳለልን
በብርሃን እንድንመላለስ እርዳን፡፡ ዓለምን ለማሳለፍ በመጣህ ጊዜ ያ የቀመስነውና የለመድነው የፍቅር ፊትህ በምግባራችን ክፋት
እንዳይለወጥብን ዛሬ ላይ በምግባር በትሩፋት እንድንመላለስ እርዳን፡፡ ሙሽራችን ሆይ! ዘይታችን አልቆ ከውጭ ከሚቀሩ ቆነጃጅት
እንዳንሆን ደግፈን፡፡ የአባቴ ብሩካን ከምትላቸው ወዳጆችህ ጋር ደምረን፡፡ አሜን በእውነት አሜን!!!!!!!