Showing posts with label የሐሙስ ፍጥረታት. Show all posts
Showing posts with label የሐሙስ ፍጥረታት. Show all posts

Monday, October 19, 2015

የሐሙስ ፍጥረታት



(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ጥቅምት 9 ቀን 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ትምህርተ ሃይማኖት - ክፍል 17
ሐሙስ የሚለው ሐመሰ ከሚለው ግስ የተገኘ ሲኾን አምስት አደረገ ማለት ነው። ለሥነ ፍጥረት አምስተኛ ቀን ስለኾነ ሐሙስ ተብሏል።
በዚህ ቀን እግዚአብሔር፡- ውኃ ሕያው ነፍስ ያላቸውን ተንቀሳቃሾችን ታስገኝ” ብሎ አዘዘ /ዘፍ.1፥20-21/፡፡ በዚሁም መሠረት በእግራቸው የሚሔዱ፣ በልባቸው የሚሳቡና በክንፋቸው የሚበሩ ሦስት ወገን ፍጥረታትን ፈጠረ፡፡ እነዚህ ፍጥረታት ተፈጥሮአቸው ከአራቱ ባሕርያተ ሥጋ - ማለትም ከመሬት፣ ከውኃ፣ ከእሳትና ከነፋስ - ሲኾን በደመ ነፍስ የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ ደመ ነፍስ ማለትም በደም ነፍስነት፣ በደም ኃይል የሚንቀሳቀሱ፣ ደማቸው ሲቆም ሕይወታቸውም አብሮ የሚቆም ማለት ነው፡፡ ይህም እስትንፋስ እያልን የምንጠራው ነው፡፡ ይህ እስትንፋስ - ማለትም ደመ ነፍስ - በሰውም ዘንድ አለ፡፡
እነዚህ በዚህ ዕለት የተፈጠሩት ፍጥረታት ካለ መኖር ወደ መኖር የመጡት እግዚአብሔር ስላዘዘ እንጂ ውኃው በራሱ ኃይል ያስገኛቸው አይደለም፡፡ ይኸውም እግዚአብሔር ካልፈቀደና ካላዘዘ በስተቀር ምድር አንዲት ቡቃያስ እንኳን ማብቀል እንደማትችለው ማለት ነው፡፡ ምድር እነዚያን ቡቃያዎች ስታበቅል አስቀድሞ ተዘርቶባት አይደለም፡፡ ውኃይቱም እነዚህ ከላይ የጠቀስናቸውን ፍጥረታት ያስገኘችው አስቀድሞ እነዚህን ፍጥረታት ሊያስገኝ የሚችል ንጥረ ነገር በውስጧ ስለያዘች ሳይኾን እንዲሁ እግዚአብሔር ስላዘዛቸውና እነዚህን ፍጥረታትንም የማስገኘት ዓቅም ስለ ሰጣቸው እንጂ፡፡ በሌላ አነጋገር፥ የእነዚህ ፍጥረታት ዋናው መገኛቸው ቃለ እግዚአብሔር ነው፤ ቃሉ ኃይልን የተመላና ሕይወትን የሚያስገኝ ቃል ነውና፡፡

FeedBurner FeedCount