በስመ አብ
ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ አምላክ አሜን
እንኳን ለእመቤታችን ለቅድስትድንግል ማርያም በዓለ ልደት በሠላም አደረሳችሁ!
ድንግል ማርያም በቅ/ገብርኤል ሠላምታ(ክፍል 1)
በታሪክ ፍሰት
ውስጥ ድንግል ማርያም ከቅዱስ ገብርኤል የተቀበለችውን ያህል ሠላምታ የከበረ ሠላምታ አይገኝም። መልአኩ ያቀረበላት ይህ ተወዳጅ
ሠላምታ የዓለምን መዳን ዜና ያዘለ የአርሷንም የክብሯን መጠን ያሳየ ነበረ። የእመቤታችን የልደቷም ምሥጢር ፍቺ የጌታ መወለድ ነው።
ጌታ ቅድመዓለም
ከአብ ለመወለዱ ጡት የምታጠባው ምድራዊት እናት፣ ድኅረ ዓለም ከድንግል ማርያም ለመወለዱ ለዘር ምክንያት የሚሆን ምድራዊ አባት
የለውም። ባለሁለት ልደቱ ጌታ ግን አንድ ነው። ባለበገናውም፡-
“በአባትህ ስም ስንጠራህ
ወልደ ማርያም
በላይ ነህ” በማለት ተቀኝቶለታል። ይህም የአብ የማርያም ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ
የበላይ አስተዳዳሪ፣ ገ™ ነህ ማለት ነው።
ከዚህ ቀጥለን
የመልአኩ የቅዱስ ገብርኤል ቃለ ብሥራት ከጌታ ፍቅር ባሻገር ክብረ ማርያምንም ወለል ያደርግልናልና በጥቂቱ
እንዳስሰው!
“በሰድስተኛውም
ወር መልአኩ ገብርኤል ናዝሬት ወደምትባል ወደገሊላ ከተማ ከዳዊት ወገን ለሆነው ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደታጨች ወደ አንዲት ድንግል
ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ”ስድስተኛው ወር…. ይህ
ወር ቅድስት ኤልሣቤጥ በስተርጅናዋ ዘመን ጸንሳ” ነቀፌታዬን ከሰው መካከል ያሰወግድልኝ ዘንድ ጌታ በተመለከተበት ወራት
እንዲህ አድርጎልኛል” ስትል ራሷን ከሰወረችባቸው ከ5ቱ ወራቶች ቀጥሎ የሚመጣ ነው።
ናዝሬት ገሊላ… ናዝሬት
በገሊላ አውራጃ ይገኙ ከነበሩ ከተሞች መካከል አንዷ የሆነች፣ ብዙ የማይጠበቅባትና የተናቀች ነበረች (ዬሐ1.47)ከዳዊት ወገን ለሆነው ለዮሴፍ ..ዮሴፍ በመልአኩ” የዳዊት ልጅ “ተብሎ ተጠርቷል(ማቴ
1÷20)። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በወንጌላዊው ማቴዎስ የትውልድ አቆጣጠር የዳዊት ልጅ የተባለው በአሳዳጊው በዮሴፍ በኩል
በተዘረዘረው ትውልድ ነው። (ማቴ.21÷9) (ማቴ. 12÷23) (ማር.10÷47)ወደታጨች… መታጨት፡- መታሰብ፣ መመደብ፣
መመረጥ ማለት ነው።
የእመቤታችን ለዩሴፍ መታጨት ለጋብቻ ከመታጨት ወይም በእንግሊዘኛው betrothal ከሚባለው የተለየ
ነው። የእመቤታችን መታጨት መመረጥን የሚወክል ነው። መጽሐፍ ቅዱስም መታጨትን “መመረጥ” እያለ በቀጥታ እንደሚተረጉም መረዳት እንችላለን
(2ኛ ቆሮ 11÷2) (ሆሴ 2÷21)። የድንግል ማርያምና የዮሴፍንም ስንመለከት “እጮኝነቱ” መመረጥ በሚለው ትርጓሜ የሚነበብ እንጂ
ሌላ መላምት የሚቀርብበት አይደለም። ቅዱስ ዮሴፍና እመቤታችን ለጋብቻ የማይሆን የዝምድና ትስስር፣ የእድሜ አለመመጣጠን የሚያግዳቸው
ከመሆኑም ባሻገር እንዲህ የሚያስቡትን መጽሐፍ ቅዱስ “የተሰናከሉ” መሆናቸውን በግልጽ አማርኛ አስቀምጧል (ማር. 6÷3)። የኪንግ
ጀምስ የእንግሊዘኛው መጽሐፍ ቅዱስም የሚመሰክረው ይህንኑ ነው። በአማርኛ “እጮኛ” የሚለውን እንግሊዘኛው” espouse” ብሎ ጠርቶታል።
ይህም “አንድን ዓላማ ወይም አሳብ የሚደገፍን አካልን “ ያመለክታል። ለጋብቻ መታጨትን የሚመለክት ቢሆን ኖሮ የድንግል
ማርያም ለዮሴፍ መታጨት “befrothed” ተብሎ ይጻፍ ነበር። /long man dictionary of
contemporary English 1987).
ወደ አንዲት ድንግል … ልዩ
ድንግል በመሆን አንድ ናትና “አንዲት!” ብሎ ገለጻት። ሌሎች በሥጋ ድንግል ይሆኑ ይሆናል። እርሷ ግን በሥጋም በኀሊናም
ድንግል ናት “ርግቤ መደምደሚያዬ አንዲት ናት፣ ለወለደቻትም የተመረጠች ናት” (መኀመኀ.6÷9)። ጠቢቡ በትንቢት መንፈስ
ሆኖ፡-ርግቤ አላት
የየዋሕነቷን
መደምደሚያዬ አላት
የሞትን ታሪክ የሚደመድመውን ትውልዳለችና ለወለደቻትም የተመረጠች
ናት፡- የተወለደ ሁሉ ምርጥ አይደለም። ድንግል ማርያም ግን እንኳን ለወለደቻት ለወለደችውም የተመረጠች ናት።
ከእግዚአብሔር
ዘንድ ተላከ፡- ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላከ የሚናገረው እውነት ነውና ::
የድንግሊቱም ስም
ማርያም ነበረ፡- ማርያም ማለት ጸጋወሀብት ማለት ነው። ለጊዜው ለእናት ለአባቷ ልጅ ሆና ተሰጥታለች በፍጻሜው ግን የጸጋ እናት
ሆና ለልጆቿ ሁሉ ተሰጥታለችና። መልአኩም ወደ
እርሷ ገብቶ ደስ ይበልሽ፣ ጸጋን የሞላብሽ ሆይ፣ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፣
ደስ ይበልሽ…ይህንቃል
የተናገራት ቅዱስ ገብርኤል ቢሆንም መልአክቱ የመጣው ግን ከሰማይ ነው። ጌታ ደስ ይበልሽ አላት። ደስ ይበልሽ ያላት በመጀመርያ
ድኅነተ ዓለም ስለደረሠ ሲሆን ቀጥሎ ደግም እርሱን ለመውለድ ክብር በመመረጧ ነው። አንዳንዶች ግን ጌታን ደስ ያሰኙት እየመሰላቸው
“ደስ ይበልሽ” ያላት እናቱን “ይሰድቡለታል”!
ጸጋን የሞላብሽ
ሆይ
ከቅዱስ ሕዝብ ወገን ጸጋ ያለው እንጂ ጸጋ የሞላበት የለም። አንድ ሁለት ጸጋ ይሞላበት ይሆናል፣ ጸጋ ሁሉ ግን አይሞላበትም። የጸጋ
ስጦታ ልዮ ልዩ ነውና (1ቆሮ. 12÷4)። ድንግል ማርያም ግን “ ምልዕተ ጸጋ” የሚለው ማዕርጓ ጸጋ ሁሉ እንደሞላባት
የሚያሳየን ነው። እንዴት በሉ?
1ኛ- ጌታ ከነ ጸጋ ስጦታው ሁሉ ጋር በማኀፀኗ በማደሩ ነው። ታዲያ አባቶች ” የጸጋ ግምጃ ቤት” ቢሏት ተሳስተው
ይሆን?
2ኛ- ፍጹሙ ጸጋ እርሱን ጌታን መውለድ ነውና።
ጌታ ከአንቺ ጋር
ነው
አንዳንዶች ጌታ በዮሐንስ ወንጌል ላይ..” አንቺ ሴት ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? “ ብሏታል። ስለዚህ ማርያም ማርያም አትበሉ
ሲሉ ብዙ ጊዜ ሰምተናል (ዮሐ. 2÷4)። አንድን ጹሑፍ ላልተጻፈበት ዓላማ ማዋል አለመታደል ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘይቤ “ከአንቺ
ጋር ምን አለኝ” ማለት “ከአንቺ ጋር ምን ጠብ አለኝ?” ማለት እንደሆነ ግልጽ ቢሆንም መልአኩ ግን በቀጥተኛ መልዕክት “ጌታ
ከአንቺ ጋር ነው”ይላታል። “ጌታ ከአንቺ ጋር ነው” የሚለው የእግዚአብሔር መልእክተኛ ከሆነ “ጌታ ከእርሷ ጋር ምን አለው?” የሚለውስ
የማን መልእክተኛ ነው ትላላችሁ? ተወዳጆች ሆይ፡- ጌታ ከእርሷ ጋር ባይሆን ዛሬ እኛ ከእርሱ ጋር አንሆንም ነበር፣ የእርቃችን
ሰነድ፣ የአብሮነታችን ምስጢር፣ የመገናኛ ድንኳናችን ናት። አማኑኤል ትርጓሜውም “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር” የተባለው
ከእርሷ ሰው ሆኖ አይደለምን? (ማቴ.1÷23)። ፍቅርን እየወደደ የፍቅርን ሀገር የሚጠላ ማነው? ፍቅር ጌታን እየወደደ ሀገረ ፍቅር
ድንግል ማርያምንስ የሚጠላ ማነው? እርሱ ይመለካል፣ እርሷን ብጽዕት እንላለን! እርሱ ታላቅ ገናና ነው፣ እርሷ ታላቅ ሥራ ተደርጎባታል
(ሉቃ.1÷49)። እርሱ አምላክ ነው፣ እርሷ እናቱ ናት። የልባችን መሻት እንዲሞላ እርሱ ከእርሷ ጋር እንደሆነ
እርሷም ከእርሱ ጋር ናት።
ሴትየዋ በዕድሜ የገፉ ናቸው፣ አንዱ በመንገድ አስቁሞ “ቃል ላካፍልዎት” ይላቸዋል። እርሳቸውም “ተወኝ
ባክህ ልጄ ልደትዬን ተሣልሜ እየተመለስሁ እንደመሆኔ ደክሞኛል” ይሉታል፣ እርሱም “ ማናት ደግሞ ልደትዬ” ?
ይላቸዋል፣ “ድንግል ማርያም ናት“ይሉታል። እርሱም “ጌታ እኮ ከአንቺ ጋር ምን አለኝ!“ ብሏታል ሲል ደንግጠው
“ እናቱን?” አሉ “አዎ”! አላቸው። እርሳቸውም “ለእናቱ ያልሆነ ለእኔ ይሆናል ብለህ ነው” ብለው እንደቆመ
ጥለውት ሄዱ። እባካችሁ ለእናቱ የማይሆን ኢየሱስ እኛ ቤት የለም!
ወሰብሐት
ለእግዚአብሔር