በየአመቱ በዕለተ ሰኑይ ብቻ (ሰኞ ቀን ብቻ) የሚጀምሩ ሦስት አጽዋማት አሉ፡፡ እነርሱም ዓቢይ ጾም፣ ጾመ ነነዌ እና ጾመ ሐዋርያት ናቸው፡፡ እነዚህ አጽዋማት ምን ጊዜም ቅበላቸው እሁድ ሲሆን የሚገቡት ደግሞ ሰኞ ቀን ነው፡፡ በየትኛውም አመት ይህን ዕለት አይለቁም፡፡
ስለዚህ የ2004 ጾም ሐዋርያት ግንቦት 27 የፊታችን ሰኞ ይገባል፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ በየግላችንም ያጋጠሙንን መንፈሳዊና ሥጋዊ ውጊያዎች በማሰብ ድል የምናደርግበትን ኃይል ፈጣሪያችን ይሰጠን ጾሙን ከወትሮው በበለጠ ጥንቃቄ ልንጾመው ይገባናል፡፡
የጾሙን ታላቅነት ተረድተን እንድንጾመው የትመጣውን፣ ትንቢቱን፣ ምሳሌውንና ምሥጢሩን መረዳት አጋዥ ስለሚሆነን አስቀድመን ስለጾሙ እንማር ዘንድ በአጭሩ አቅርቤዋለሁ! የምችለውን ያህል እጽፍ ዘንድ ብርታቱንና ጥበቡን የሰጠኝ አምላከ ቅዱሳን ሐዋርያት ክብር ምስጋና ይድረሰው! አሜን!
ጾመ ሐዋርያት በራሳቸው በሐዋርያት የተጀመረ ጾም እንደመሆኑ መጠን በአንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን ማለትም ከዛሬ አንድ ሺህ ዘጠኝ መቶ ዓመታት በፊት ጀምሮ ሲጾም የኖረ ጾም ነው፡፡ ለዚህም የመጽሐፍ ቅዱስ፣ የአዋልድ መጻሕፍትና የታሪክ በርካታ ምስክሮች አሉ፡፡ ስለዚህ ጾሙን እንደ እንግዳ ነገር መቁጠርና ዘመን አመጣሽ አድርጎ ማየት የራስን አላዋቂነት ያሳያል፡፡ ይህን ማለት ያስፈለገው ጥቂቶች ጾሙን ድሮ ያልነበረና ዘመን አመጣሽ አድርገው ስለሚናገሩ ነው፡፡
ጾመ ሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን ዕድሜያቸው ለጾም የደረሱ ምእመናን በሙሉ እንዲጾሙአቸው ካወጀቻቸው ሰባት የአዋጅ አጽዋማት መካከል አንዱ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በጌታችንና በአምላካችን በኢየሱስ ክርስቶስ አንደበት ቀን የተቀጠረለት፣ ትንቢት የተነገረለትና ምሳሌ የተመሰለለት ጾም መሆኑ ከአጽዋማት ሁሉ ለየት ያደርገዋል፡፡
ጌታችን ስለዚህ ጾም ትንቢተ በመናገር፣ ምሳሌ በመመሰል ሰፊ ትምህርት የሰጠው ፈሪሳውያን ወደ እርሱ ቀርበው ‹‹ደቀ መዛሙርትህ የማይጦሙት ስለ ምንድር ነው?›› ብለው በጠየቁት ጊዜ ነው፡፡ እርሱም ሲመልስ እንዲህ አላቸው፡- ‹‹ሚዜዎች ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊያዝኑ ይችላሉን? ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወራት ይመጣል፤ በዚያ ጊዜም ይጦማሉ፡፡ በአረጀ ልብስ አዲስ እራፊ የሚያኖር የለም፤ መጣፊያው ልብሱን ይቦጭቀዋልና፤ መቀደዱም የባሰ ይሆናል፡፡ በአረጀ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም፤ ቢደረግ ግን አቁማዳው ይፈነዳል፤ የወይን ጠጁም ይፈሳል፡፡ አቁማዳውም ይጠፋል፡፡ ነገር ግን አዲሱን የወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ ያኖረዋል ሁለቱም ይጠባበቃሉ፡፡›› (ማቴ9.14-17)
በመቀጠል
እስከ መጨረሻ የምንመለከተው ከላይ የሰፈረውን የማቴዎስ ወንጌል አጭር ገጸ ንባብ ሐሳብ በመሆኑ መለስ እያሉ ታሪኩን ማንበብ ወይም በልብ ከመዘገቡ በኋላ ቀጣዩን ክፍል ማንበብ ምሥጢሩን ለመረዳት ያግዛል፡፡