በቅዱስ ዮሐንስ
አፈወርቅ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ መጋቢት 22 ቀን 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ
አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ተወዳጆች
ሆይ! እነሆ እግዚአብሔር ፈቃዱ ኾኖ በዚህ ሳምንትም “ወደ ኦሎምፒያስ የተላኩ
መልእክታት እና ሌሎች” በተሰኘ አዲስ የሊቁ መጽሐፍ ተገናኝተናል፡፡ እርሱ እስከ ወደደ ድረስም እስከ አሁን በተተረጎሙት
ሳንረካ ብዙ ለመተርጎም ወደ ፊት እንሔዳለን፡፡ የሊቁ ሥራዎች ለዚህ ትውልድ ዓይነተኛ መድኃኒቶች ናቸውና፤ እንዲሁ ለማወቅ ያኽል
ብቻ ተነብበው በመጻሕፍት መደርደሪያ ላይ የሚቀመጡ ሳይኾኑ መንፈሳዊ ሕይወታችን እንዲጎለምስ ዕለት ዕለት ልናነባቸው የሚገቡ ናቸውና፤
በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ላይ እስከ ምን ድረስ ጠንካራ ክርስቲያኖች ልንኾን እንደሚገባን የሚያሳዩ ናቸውና፡፡
ሊቁ፥
በዚህ መጽሐፍ ላይ ሦስት ዋና ዋና ርእሶችን ይዞልን ቀርቧል፡፡ በመጀመሪያው ርእስ ላይ የእግዚአብሔር ከአእምሮ የሚያልፍ አሠራርና
ፍቅር፥ ጓደኞቹ የቤቱን ጣራ ነድለው ባወረዱት ሽባ አንጻር እናያለን፡፡ እንዲሁ የበይ ተመልካቾች ግን አንኾንም፤ የድርሻችንን ዘግነን
እንወስዳለን እንጂ፡፡ በኹለተኛው ዐቢይ ርእስ “ሰው ራሱን ካልጎዳ በስተቀር ማንም እርሱን ሊጎዳው እንደማይችል” በማለት የሰው
ብቸኛና እውነተኛ ጠላቱ እርሱ ራሱ እንደ ኾነ ያስረዳናል፤ ማስረዳት ብቻም ሳይኾን መፍትሔዉንም ያመላክተናል፡፡ በሦስተኛው ዋናው
ርእስ ላይ ወደ አምስት የሚኾኑ ንኡሳን አርእስት አሉ፡፡ እጅግ በጣም አስደናቂ ወደኾነችው ወደ ዲያቆናዊት ኦሎምፒያስ የላካቸው
መልእክታት ናቸው፡፡ በእነዚህ መልእክታት ውስጥ እጅግ በጣም ብዙ አሳቦች ተነሥተዋል፡፡ በዚህ ዘመን ያሉ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ካህናትና
አገልጋዮች ከእነዚህ የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ደብዳቤዎች እጅግ በጣም ብዙ ቁም ነገሮችን ያገኛሉ፡፡ ራሳቸውንና አገልግሎታቸውን
ይመዝናሉ፡፡ ምእመናንም በአስደናቂዋ ሴት አንጻር ራሳችንን እንመለከታለን፡፡ አሻቅበን ማየት ከተቻለንም ከዲያቆናዊቷ ከኦሎምፒያስ
ምን ያኽል ርቀት ላይ እንዳለን እናያለን፡፡ የዘመኑ ባለጸጎችም ከዚህች ባለጸጋ ሴት የድርሻችሁን ትወስዳላችሁ፡፡
አሁን
እዚህ የማቀርብላችሁ ትምህርትም በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት መሠረት ይህ ሳምንት “መጻጉዕ” እንደ መባሉ ሊቁ በዚህ መጽሐፍ ስለ
መጻጉዕ ካስተላለፈልን ትምህርት የተቀነጨበ ነው፡፡ መልካም የምክርና የተግሣጽ ጊዜ ይኹንልዎት!