Wednesday, September 12, 2012

ዜና ሐዋርያት


 በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
   መንደርደርያ ይሆነን ዘንድ እስከ አሁን ባቀረብናቸው ሁለት ክፍሎች (እነዚያን ለማንበብ ይህን ይጫኑ http://mekrez.blogspot.com/2012/08/blog-post_7538.html) ክርስቲያኖች ለባሴ ክርስቶስ (ክርስቶስን የለበሱ) ዘላለማዊ ሕይወትን የያዙ ማለት እንደሆኑና ቅዱሳን ደግሞ ዘላለማዊ በሆነ በክርስቶስ ከፍተኛ የቅድስና ደረጃ ላይ የደረሱ፣ ሞት የማይሠለጥንባቸው ፍጹማን ክርስቲያኖች፣ ሁለንተናዊ ሕይወታቸው በክርስቶስ የሆነ እንደሆኑ ተመልክተናል። ከዚህ በተጨማሪ እኛም እንደ እነርሱ እውነተኞች የተግባር ክርስቲያኖች ለመሆንና በክርስቶስ በሕይወት ለመኖር የቅዱሳንን ሕይወትና ታሪክ ማጥናትና እነርሱን ለመምሰል መጣጣር መተኪያ የሌለው ጉዳይ እንደሆነ ተመልክተናል። እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በሚቀጥሉት ጊዜያት ከቅዱሳን ሐዋርያት ጀምሮ በየዘመናቱ የተነሡ ቅዱሳንን ታሪክ እናቀርባለን። ለዛሬ የቅዱሳን ሐዋርያትን ታሪክ መግቢያ እነሆ!
  ነቢያትን ትንቢት ያናገረ አምላክ፣ ወልደ አብ ወልደ ማርያም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ሰው ሆኖ ከኃጢአት በስተቀር የሰውን ሥራ በመሥራት አደገ፡፡ በሠላሳ ዓመቱም በባርያው በዮሐንስ እጅ ተጠመቀ፡፡ በገዳመ ቆሮንቶስ መዓልትና ሌሊት ጾመ፤ ተራበ፤ ተጠማ፤ በዲያብሎስ ተፈተነ፡፡ ከዚህም በኋላ ወንጌለ መንግሥቱን ማስተማር ጀመረ፡፡ በሚያስተምርበት ወቅትም ለተለያዩ ዓላማዎች ብዙ ሕዝብ ( ገበያ ያህል) ይከተሉት ነበር። ግማሹይሤኒ ላህዩ እምውሉደ ዕጓለ እመሕያው- መልኩ ከሰው ልጆች ሁሉ ያምራልእንዲል /መዝ.452/ መልኩን ለማየት፤ ግማሹ በአምስት እንጀራና በሁለት ዓሣ አምስት ሺህ ሕዝብ ሲመግብ አይተው /ማቴ. 1416/ ሕብስት አበርክቶ ይመግበናል ብለው፤ ግማሹ ልዩ ልዩ ደዌ ያደረባቸውን ሰዎች በተአምራት ይፈውስ ነበርና ከበሽታቸው ለመፈወስ ይከተሉት ነበር /ማቴ.423/ ጌታችንም ከዚህ ሁሉ ሕዝብ መካከል መቶ ሃያ ቤተሰቦችን መረጠ። ምክንያቱ ደግሞ እነርሱ ከዋለበት እየዋሉ ካደረበት እያደሩ ትምህርቱን ሰምተው ተአምራቱን አይተው በሚገባ የሚከታተሉቀለምተማሪዎች ስለነበሩ ነው። ከእነዚህም ውስጥ አስቀድመው የተመረጡት ቅዱሳን ሐዋርያት ሲሆኑ (እርሱም ጸጋን ሰጠ፤ ከቤተሰቦቹም ሐዋርያትን፣ ከእነርሱም ነብያትንና የወንጌል ሰባኪዎችን ጠባቂዎችንና መምህራንን ሾመ። ኤፌ. ፬፣፲፬) በኋላ ፸፪ቱ አርድእት (ከዚህም በኋላ ሌሎች ሰባ ሰዎችን መረጠ ሉቃ. ፲፣፩) ቀጥሎ ደግሞ ፴፮ቱ ቅዱሳት አንስት ተመርጠዋል። ፲፪ + ፸፪ + ፴፮ = ፻፳ መቶ ሃያ ቤተሰብ የሚባሉ እነዚህ ናቸው።
  ሐዋርያ የሚለው ቃልሖረከሚለው የግዕዝ ግስ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙምለማስተማር የተላከማለት ነው፡፡ የአሥራ ሁለቱም ሐዋርያት ስም፡- ጴጥሮስ፣ እንድርያስ፣ ያዕቆብ፣ ዮሐንስ፣ ፊሊጶስ፣ በርተለሜዎስ፣ ቶማስ፣ ማቴዎስ፣ ያዕቆብ ወልድ እልፍዮስ፣ ታዴዎስ የተባለ ልብድዮስ፣ ስምዖን ቀኖናዊ እንዲሁም የአስቆሮቱ ይሁዳ ናቸው /ማቴ.101-4/፡፡    አባቶቻችን ቅዱሳን ሐዋርያት ምንም እንኳን ትውልዳቸው ከ፲፪ቱ ነገደ እስራኤል ቢሆንም የተመረጡት ግን በጌትነት ከሚኖሩ ከመሳፍንትና ከመኳንንት ወይም ከባለጸጎች ወገን ሳይሆን ከድሆች (ብዙዎች ሐዋርያት ዓሣ አጥማጆች ነበሩ) ካልተማሩትና በአጠቃላይ በኅብረተሰቡ ዘንድ ዝቅተኛ ስፍራ ከሚሰጣቸው ወገኖች ነበሩ። የዚህም ምክንያት ሐዋርያውወንድሞቻችን! እንግዲህ እንዴት እንደተጠራችሁ እዩ፤ በሥጋ እጅግ ብዙዎች ዐዋቂዎች አይደላችሁምና፤ ብዙዎች ኃያላንም አይደላችሁምና፤ በዘመድም ብዙዎች ደጋጎች አይደላችሁምና። ነገር ግን እግዚአብሔር ጥበበኞችን ሊያሳፍር የዚህን ዓለም ሰነፎች መረጠ፤ ኃይለኞችንም ያሳፍር ዘንድ እግዚአብሔር የዚህን ዓለም ደካሞች መረጠ። አለን የሚሉትንም ያሳፍር ዘንድ ዘመድ የሌላቸውን የተናቁትን፤ ከቁጥርም ያልገቡትን እግዚአብሔር መረጠብሎ እንደተናገረው ሰው በጥበቡና በኃይሉ በትውልዱም በእግዚአብሔር ፊት መመካት እንደማይገባው በተግባር ለማስገንዘብ ነው (፩ቆሮ. ፩፣፳፮- ፍጻሜ)
  ጌታችን እነዚህን መርጦ ሐዋርያት ብሎ ከሰየማቸው በኋላ (ከዕርገት በኋላ እርሱን ተክተው ሐዋርያት መደበኞች ሆነው አርድእት ደግሞ ሐዋርያትን እየረዱ የሚያስተምሩ ናቸውና!) ለጊዜው በምድረ እስራኤል ብቻ እንዲያስተምሩ ላካቸው፡፡ የዚህ ዓለም ወታደር ወደ ጦር ሜዳ ሲሄድ በቂ ስንቅና ትጥቅ እንደሚሰጠው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ለቅዱሳን ሐዋርያትበአሕዛብ መንገድ አትሂዱ ወደ ሳምራውያን ከተማም አትግቡ።  ነገር ግን ከእስራኤል ወገን ወደ ጠፉት በጎች ሂዱ። ሄዳችሁም መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች እያላችሁ አስተምሩ። ድውያንን ፈውሱ፤ ሙታንንም አንሡ፤ ለምጻሞችንም አንጹ፤ አጋንንትንም አውጡ፤ ያለዋጋ የተቀበላችሁትን ያለዋጋ ስጡብሎ ድውይ የሚፈውሱበት፣ ሙት የሚያስነሡበት፣ ጋኔን የሚያወጡበት፣ ለምጽ የሚያነጹበት ሙሉ ትጥቅ ሰጣቸው፤መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችእያሉ እንዲያስተምሩም ላካቸው /ማቴ. ፲፣፭ - /  በተመሳሳይ ሁኔታ አርድእቱንም እንደላካቸው በሌላ ቦታ ተጽፎ እናገኛለን (ሉቃ. )
 ከዚህም በተጨማሪእነሆ እንደበጎች በተኩላዎች መካከል እልካችኋለሁ፤ እንግዲህ እንደእባብ ብልሆች እንድርግብም የዋሆች ሁኑ። ከክፉዎች ሰዎች ተጠበቁ፤ ወደ አደባባዮች አሳልፈው ይሰጧችኋልና፤ በምኩራቦቻቸውም ይገርፏችኋልናእያለ ወደፊት በስሙ ሲያስተምሩ ዓለም እንደሚጠላቸውና መከራ እንደሚያመጣባቸው፤ ይህንንም መከራ እንዴት እንደሚያሸንፉት ከነመፍትሔው ነገራቸው /ማቴ. ፲፣፲፯ ዮሐ. ፲፭፣፲፰- ፳፭/
  ከዚህ በኋላ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፅንስ የጀመረውን የማዳን ሥራ በሞቱ በቀራንዮ ፈጸመው፡፡ ዓለምን አድኖም መዓልትና ሌሊት በከርሠ መቃብር አድሮ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ ተነሣ። ከትንሣኤው በኋላ ለሐዋርያት በጉባኤም በተናጠልም (ለአንዱ ለሁለቱ) እየተገለጸ ቀን አስተማራቸው። በ፵ኛው ቀን ኃይል፣ ጽንዕ የሚሆናቸው መንፈስ ቅዱስን እንደሚልክላቸው ተስፋ ሰጥቷቸው እስካሁን ያዩትንና የሰሙትን እውነት ለዓለም እንዲመሰክሩ አዝዟቸው ዐረገ። ባረገ በ፲ኛው ቀንም የተናገረውን የማያስቀር ጌታሁሉም መንፈስ ቅዱስን ተሞሉ፤ ይናገሩ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እንዳደላቸው መጠንም እየራሳቸው በሀገሩ ሁሉ ቋንቋ ይናገሩ ጀመሩእንዲል ጰራቅሊጦስን (መንፈስ ቅዱስን) ሰደደላቸው /ሐዋ. / ጰራቅሊጦስ ማለት በፅርእ ቋንቋ የሚያጽናና የሚያስደስት ማለት ነው፡፡
 አባቶቻችን ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ ፸፪ ቋንቋ ተገልጦላቸው በዕውቀት ጐለመሱ፤ ከብልየት ታደሱ፤ ፈሪዎች የነበሩ መከራ ሥጋን የማይፈሩ ጥቡዐን ሆኑ። መዲናቸው ኢየሩሳሌምን በኅብረት ካስተማሩ በኋላ ሑሩ ወመሀሩ- ሂዱና አስተምሩያላቸውን ቃል በመጠበቅ ዓለምን በዕጣ ተከፋፍለው አርድእት ደግሞ ሐዋርያትን ተከትለውአምላክ ከሰማያት ወረደ፤ በድንግልና ተፀንሶ በድንግልና ተወለደ፤ የምሥራችን አስተማረ፤ በአይሁድ እጅ ተገፈፈ ተገረፈ፤ በመስቀል ተሰቀለ፤ ሞተ፤ ተቀበረ፤ መቃብር ክፈቱልኝ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል በኃይሉና በሥልጣኑ በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፤ በክብር በምስጋና ወደ ሰማይ ዐረገ፤ ዳግመኛም ለፍርድ ይመጣልብለው ወንጌልን ለዓለም ሁሉ ሰበኩ፤ ለቤተ ክርስቲያን ሕግ አወጡ፤ ሥርዓት ደነገጉ፡፡ ነቢዩ ዳዊትውስተ ኵሉ ምድር ወጽአ ነገሮሙ ወእስከ አጽናፈ ዓለም በጽሐ ነቢቦሙትርጉሙምድምፃቸው ወደ ምድር ሁሉ ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ወጣብሎ የተናገረው ትንቢት ደረሰ፤ ተፈጸመ (መዝ. ፲፰ )
  ጌታችን በተራራው ስብከቱ ላይ ሲያስተምራቸውእናንተ የምድር ጨው፣ የዓለም ብርሃንና የተራራ ላይ መንደር ናችሁብሏቸው ነበርና በትምህርታቸው በትሩፋታቸው አልጫውን ዓለም በሃይማኖትና በአምልኮተ እግዚአብሔር አጣፈጡት። በኃጢአት ጨለማ ውስጥ የነበረውን የሰው ልጅ በንጽሕናና በቅድስና ወንጌል ብርሃን አበሩት። በድንቁርና ዋሻ ተሰውሮ የነበረውን የአሕዛብን ልብ በዕውቀት ተራራ ላይ አውጥተው ለዓለም ሁሉ እንዲገለጥና እንዲታይ አደረጉት። ይህን ሁሉ ሲያደርጉ የሐዋርያዊ አገልግሎታቸው ዋነኛ መሣሪያዎች ጌታቸውና መምህራቸው እንዳዘዛቸው ጥበብ፣ ትዕግሥት፣ ፍቅርና የዋህነት ነበሩ። በዚህ ሁኔታ የተመረጡለትን ታላቅ አምላካዊ ዓላማ አሳኩ፡፡ በኋላም የጌታቸውን አርአያ ተከትለው ያላመኑ አይሁድና አሕዛብ እኩሉን በገመድ እያነቁ፣ እኩሉንም በደንጊያ እየወገሩ፣ እኩሉንም በሰይፍ እየመቱ በልዩ ልዩ ዓይነት ስቃይ  እያሰቃዩ ገደልዋቸው፡፡ ሐዋርያትም ቁልቁል ተሰቅለው፣ በሰይፍ ተከልለው፣ እንደ በግ ተገፈው፣ በእሳት ተጠብሰው በድንጋይ ተወግረው ሰማዕትነትን ተቀብለው የመከራ ወንዝ የሆነ ይህን ዓለም ተሻገሩ፡፡ ሰውን ከሰው አላገናኝ ያለውን የቋንቋ፣ የጐሣ፣ የቅንዓትና የምቀኝነት ወንዝ ተሻግሮ እምነት፣ ተስፋ፣ ፍቅር ከሚገኝበት ከተማ የሚያደርሰውን ድልድይ ሠርተው ተልእኮአቸውን ጨረሱ፡፡የምሄድበት ጊዜዬ (ለሞት ዕድሜዬ) ደርሷል፡፡ መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ፤ ሩጫውን ጨርሻለሁ፤ ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ፤ ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፤ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለእኔ ያስረክባል፤ ደግሞም መገለጡን ለሚወዱት ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለምበማለት መስክረው አለፉ /፪ጢሞ.፬፡፮-/፡፡
  ሐዋርያት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በአካል በዓይናቸው ያዩ፣ ቃሉን ከእግሩ ሥር ቁጭ ብለው የተማሩና በጆሮዎቻቸው የሰሙ፣ በእጃቸውም የዳሰሱት በአጠቃላይ ዓመት ከ፫ወር ሲያስተምር ከዋለበት እየዋሉ ካደረበት እያደሩ አብረውት የነበሩ፣ በኋላም ክርስቶስ በደሙ የመሠረታትን ቤተ ክርስቲያን አጥንታቸውን ከስክሰው፣ ደማቸውን አፍሰው፣ ሥጋቸውን ቆርሰው ስለገነቧት ቅድስት ቤተክርስቲያን ከፍተኛና ለየት ያለ ቦታ ትሰጣቸዋለች። ለመታሰቢያቸውም የቤተ ክርስቲያን ጣራ ፲፪ ዐምድ (ምሰሶ) እንዲኖረው ሊቃውንት ወስነዋል፡፡ ስለዚህ ሐዋርያት ከጌታችን ያዩትንና የሰሙትን ወንጌል ያስተላለፉ የመጀመሪያዎቹ ሰዎች ስለሆኑ የቤተክርስቲያን መሠረቶች ናቸው። ከእነርሱ አስተምህሮና ትውፊት የወጣች ቤተክርስቲያን ቤተክርስቲያን ልትባል አትችልም። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስምእናንተ ግን የእኛን ፍለጋ ተከተሉ፤ እናንተስ እኛም ብንሆን ወይም መልአክ ከሰማይ ወርዶ እኛ ካስተማርናችሁ ወንጌል ሌላ ቢሰብክላችሁ ውጉዝ ይሁን። አስቀድሜ እንዳልሁ አሁንም ደግሜ እላለሁ ካስተማርናችሁ ሌላ ትምህርት ያስተማራችሁ ቢኖር ውጉዝ ይሁንበማለት ከሐዋርያት ትምህርት የሚወጣውን አስቀድሞ አውግዟል (ገላ. ፩፣ -)፡፡
   እግዚአብሔር ቢፈቅድና ብንኖር በቀጣይ ጊዜ የእያንዳንዱን ሐዋርያ ታሪክና ሐዋርያዊ ጉዞ በተከታታይ ለማቅረብ እንሞክራለን። ለዚህም የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመ ብርሃን አማላጅነት፣ የቅዱሳን ሐዋርያት በረከታቸውና ረድኤታቸው አይለየን አሜን!!
         






3 comments:

  1. ለመንደርደሪያ ንባብ መክፈቻ ይሆን ዘንድ የተሰጠው አድራሻ ጽሁፉን አያቀርብም ፡፡ መፍትሄ ካለው ብትሞክርልኝ
    አመሰግናለሁ

    ReplyDelete
  2. አሁን የተስተካከለ ስለሆነ ጥቆማውን በመጫን ማንበብ ይችላሉ፡፡ እግዚአብሔር ይስጥልኝ!

    ReplyDelete
    Replies
    1. እግዚአብሔር ይስጥልኝ ፡፡ ደርሶኛል
      ስለ ትምህርቱም ቃለ ሕይወት ያሰማልኝ ፡፡

      Delete

FeedBurner FeedCount