Sunday, September 16, 2012

እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ


  የዮሐንስ ወንጌል 37 ሳምንት ጥናት (ዮሐ.812-20)

     በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

  በምንዝር በያዝዋት ሴት ላይ ለመፍረድ ተሰብስበው የነበሩት አይሁድ ፈሪሳውያን ጌታችን ጸሐፍት ፈሪሳውያን ሆይ! ኃጢአታችሁ ከዚህች ሴት ኃጢአት የባሰ እንደሆነ ተመልከቱ፡፡ ታውቁት ትረዱት ዘንድም አሁን ሕሊናችሁን መርምሩ፡፡ ስለዚህ እናንተው ራሳችሁ ወንጀለኞች ሳላችሁ በዚህች ሴት ላይ የምትፈርዱ አትሁኑ፡፡ ይልቁንም እርሷን ከመውቀሳችሁና ከመክሰሳችሁ በፊት ራሳችሁን የምትወቅሱ ሁኑ፡፡ እርሷ ተወግራ እንድትገደል የምትፈርዱ ከሆነ ግን እናንተም ከዚያ ነጻ አይደላችሁምብሏቸው እነርሱም ይህን ዘለፋ በሰሙ ጊዜ ሕሊናቸው ወቅሷቸው በፊት ከገቡት ጀምሮ በኋላ እስከ ገቡት ድረስ አንድ አንድ እያሉ እየወጡ ሄደው ነበር /.9/፡፡(በዚህ እስ ላይ ይህን ይመልከቱ እኔም አልፈርድብሽም- የዮሐንስ ወንጌል የ36ኛ ሳምንት ጥናት(8፡1-11)

  ሆኖም ግን ተመልሰው መጡ፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ቂመኛ አይደለምና ዳግመኛ አስተማራቸው፡፡ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም” ብሎ ተናገራቸው /ቁ.12/፡፡ እንዴት ያለ ፍቅር ነው? እንደምን ያለ መውደድ ነው? ፍቁራን ሆይ! የጌታን ንግግር ታስተውሉታላችሁን? እንዲህ ማለቱ ነበር፡-“ፈሪሳውያን ሆይ! እናንተ በመጻሕፍተ ኦሪት የዘለዓለም ሕይወት እንዳለችሁ ይመስላችኋል፤ እነርሱንም ትመረምራላችሁ፡፡ እነርሱ ግን ስለ እኔ የሚመሰክሩ ናቸው /ዮሐ.5፡39/፡፡ እንግዲያውስ ወደ እኔ ኑ እንጂ በዚያ የምትቀሩ አትሁኑ! ዳዊት ‘የሕይወት ምንጭ ከአንተ ዘንድ ነውና በብርሃንህ ብርሃንን እናያለን’ እንዳለ /መዝ.36፡6/ የሕይወት ምንጭ እኔ ነኝና ወደ እኔ ቅረቡ እንጂ በጨለማ የምትቆዩ አትሁኑ፡፡ እውነተኛው ብርሃን እኔ ነኝና ወደ ብርሃን (ወደ እኔ) ኑ! በጨለማ ላለ ሰው ብርሃን ያስፈልጓል፡፡ የተጠማ ሰውም የሚያረካ መጠጥ ያስፈልጓል፡፡ እንግዲያውስ የእነዚህ ምንጫቸው እኔ ነኝና ታገኝዋቸው ዘንድ ወደ እኔ ቅረቡ (በእኔ እመኑ)፡፡ ከእናንተ መካከል አንዱ በሌሊት ውኃ ቢጠማው ተነሥቶ ኩራዝን የማያበራ ማን ነው? ኩራዙንም ተጠቅሞ ውኃ ቀድቶ የሚጠጣ አይደለምን? እንግዲያውስ እናንተም በብርሃኔ ብርሃን የሆንኩትን እኔን ያዙና ዳግመኛ ጽምዓ ነፍሰን የማያስጠማ የሕይወትን ውኃ ጠጡ፡፡ ልጆቼ ሆይ! በጨለማ (በድንቁርና) መኖርን ስለምን ትመርጣላችሁ? እናንተን እንዲሁ አፍቅሬ አማናዊው ብርሃን የምሆን እኔ ወደ እናንተ ስመጣ ስለምን ዐይነ ልቡናችሁን በመዝጋት እኔን ከማየት ትከለከላላችሁ? አባቶቻችሁ ከምድረ ግብጽ ለመውጣት ፊት ለፊት የሚመራቸውን ዓምደ ብርሃንን ተከትለው ከባርነት የወጡ አይደሉምን? /ዘጸ.13፡21/ እንግዲያውስ እናንተም ወደ እውነተኛው ሀገራችሁ (ወደ ገነት መንግሥተ ሰማያት) ለመግባት ብርሃን እኔን ተከተሉ፡፡ እኔ የፍልስጥኤም ወይም የገሊላ ወይም ደግሞ የይሁዳ ብቻ ሳልሆን የዓለም ሁሉ ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝ(የሚያምንብኝ) ቢኖር የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል፡፡ ክብርን፣ ዕውቀትን፣ መንግሥተ ሰማያትን ያገኛል እንጂ በሐሳር፣ በጨለማ ፣ በገሃነም አይመላለስም፡፡ የሚከተለኝ ቢኖር በሴሰኛይቱ ሴት እንዳደረጋችሁት ሳይሆን በራሱ ኃጢአት ላይ ስለሚፈርድ በእኔ አምኖ ይኖራል፡፡ ወደ ክሕደት፣ ወደ ገሃነም፣ በሌሎች ላይ ወደ መፍረድ፣ ወደ ክፉ ነገር አይሄድም፡፡ የሕይወትን ውኃ ክብረ መንግሥተ ሰማያትን ታገኛል፡፡ ስለዚህ በእኔ እመኑና ከስሕተት ከክሕደት ውጡ” /St. Cyril of Alexandria on the Gospel of John, 5:2/፡፡ 

   ፈሪሳውያን ግን ይህን ፍቅር ከመረዳት ራቁ፡፡ መድኅን የሆነው ስሙ ከፍ ከፍ ይበልና አፍቃሪያቸውን እንደ “ዕሩቅ ብእሲ” አይተዉት “የሌለውን አምላክነት” ለራሱ የወሰደ መሰላቸው፡፡ ስለዚህ፡- “አንተ ስለ ራስህ ትመሰክራለህን?” ራስህን የምታመሰግን፣ ራስህንም የምታደንቅ ከሆነማ… አሉት፡፡ ሐሰት የባሕርይው ያይደለ አምላክ “ምስክርነትህ (የምትናገረው ሁሉ) እውነት አይደለም” አሉት /ቁ.13/።  የሚደንቀው ግን
መጻሕፍትን እናውቃለን የሚሉ መሆናቸውን ነው፡፡ ሆኖም “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ” ብሎ የተናገረ የሚጠቅሱት አንድ ነብይ ስንኳ የለም፡፡ ታድያ እግዚአብሔር ካልሆነ በቀር “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ” ሊል የሚችል ማን ነው? /ዳን.2፡22/፡፡ በእርግጥም አልተረዱትም (ሊረዱትም አልወደዱም) እንጂ በምልአት ያልተለየውን ዓለም የአብርሃምን ባሕርይ ባሕርይ አድርጎ በሥጋ ማርያም ለድኅነተ ዓለም የመጣው ቃል፣ ለሰውም ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን /ዮሐ.1፡9/ ጌታ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ ከሁሉ በላይ ሆኖ ለዘላለም የተባረከ አምላክ ነው /ሮሜ.9፡5/፡፡

 አይሁድ “ምስክርነትህ (የምትናገረው ሁሉ) እውነት አይደለም” ቢሉትም ጌታ በፍጹም መውደድ ወዷቸዋልና፡- “እኔ ስለ ራሴ ምንም እንኳ ብመሰክር ከወዴት እንደመጣሁ ወዴትም እንድሄድ አውቃለሁና ምስክርነቴ እውነት ነው፤ እናንተ ግን ከወዴት እንደ መጣሁ ወዴትም እንድሄድ አታውቁም። እናንተ ሥጋዊ ፍርድን ትፈርዳላችሁ፤ እኔ በአንድ ሰው ስንኳ አልፈርድም። የላከኝ አብ ከእኔ ጋር ነው እንጂ ብቻዬን አይደለሁምና እኔ ብፈርድ ፍርዴ እውነት ነው። የሁለት ሰዎችም ምስክርነት እውነት እንደ ሆነ በሕጋችሁ ተጽፎአል። ስለ ራሴ የምመሰክር እኔ ነኝ፥ የላከኝም አብ ስለ እኔ ይመሰክራል” አላቸው /ቁ.14-18/፡፡ እንዲህ ማለቱ ነበር፡-“እኔ ስለ ራሴ ብመሰክር ምስክርነቴ እውነት ነው፡፡ ምክንያቱም ከወዴት እንደመጣሁ (አምላክ ወልደ አምላክ መሆኔን) አውቃለሁ፡፡ አምላክ ደግሞ በባሕርዩ ሐሰት የለበትምና ምስክርነቴ እውነት ነው /St.John Chrysostom, Hom.52/፡፡ (ምሳሌ ዘይሀጽጽ ቢሆንም) በምሳሌ ላስረዳችሁ፡፡ ሁለት ሰዎች ይኖራሉ፡፡ አንዱ ማየት የሚችል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ማየት የተሳነው ነው፡፡ ፀሐይ ለሁለቱም እኩል ታበራላቸዋለች፡፡ ስለ ራሷ ብርሃንነት ራሷ ትመሰክርላቸዋለች፡፡ ሆኖም ማየት የተሳነው ሰውየ ፀሓይዋ ብታበራለትም እርሷን ማየት አይችልም፡፡ ልክ እንደዚሁ እውነተኛው የዓለም ብርሃን የምሆን እኔን ላለማየት ዐይነ ልቡናውን ላሳወረ ሰውም አምላክነቴን ብገልጥለትም አልታየውም፡፡ ወዶና ፈቅዶ ልቡናውን አሳውሯልና በጨለማ (እኔን ባለማወቅ በድንቁርና) ይኖራል፡፡ እናንተም ልቡናችሁን በፈቃዳችሁ ስላሳወራችሁት ከወዴት እንደ መጣሁ ወዴትም እንድሄድ አታውቁም። እኔ የአብ የባሕርይ ልጅ ነኝ፤ ለድኅነተ ዓለም በፈቃዴ በአባቴ በፈቃድ በመንፈስ ቅዱስም ፈቃድ መጣሁ ብላችሁም ‘ወልደ ዮሴፍ ነው እንጂ እንደምን ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር አስተካክሎ እግዚአብሔር አባቴ ነው ይለናል?’ ትላላችሁና ከወዴት እንደመጣሁ አታውቁም /ዮሐ.5፡20/፡፡ እናንተ ሥጋዊ ፍርድን ማለትም ላይ ላዩን ብቻ በማየት ‘ሙሴ እንዲህ ብሎ አዘዘን አንተስ ምን ትላለህ?’ ብላችሁ ትፈርዳላችሁ /ቁ.5/፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ስለ እናንተ መዳን ብዬ ሥጋ ብለብስም እንደ ዕሩቅ ብእሲ በማየት አምላክነቴን ባለ ማየት (ባለመቀበል) ‘ምስክርነትህ እውነት አይደለም’ /ቁ.13/ እያላችሁ ትፈርዳላችሁ፡፡ እኔ ግን ዓለም በእኔ አምኖ እንዲድን እንጂ በዓለም እፈርድ ዘንድ አልመጣሁምና በአንድ ሰው ስንኳ (ባመጣችኋት ሴትም ጭምር) አልፈርድም /ዮሐ.3፡17፣ St.John Chrysostom,Ibid/። ብፈርድ እንኳ (አምላክ ነኝና) ልብ ያመላለሰውን ኩላሊት ያጤሰውን መርምሬ ኃጢአትህ ተሠርዮልሃል፤ ኃጢአትሽ ተሠርዮልሻል እያልኩ እውነትን እፈርዳለሁ እንጂ እንደ እናንተ ትደብደብ፤ ትወገር ብዬ አልፈርድም፡፡ የሁለት ሰዎች ምስክርነት እውነት እንደ ሆነ በሕጋችሁ ተጽፎ የለምን? /ዘዳ.17፡6/፡፡ የላከኝ አብ ከእኔ ጋር ነው እንጂ ብቻዬን አይደለሁምና እኔም ብፈርድ ፍርዴ እውነት ነው። ምክንያቱም እኔው ለራሴ ምስክር ነኝ፤ የላከኝ አባቴም ምስክሬ ነው” /ቁ.14-18፣ የቃል ማስረጃ ከሊቀ ሊቃውንት ያሬድ ካሣ (መቐለ)/።
 
   ፈሪሳውያኑም ጌታችን “አባቴ ከእኔ ጋር ነው” ስላላቸው በግዙፉ ዐይናቸው ለማየት ቋምጠው “አባትህ ወዴት ነው?” አሉት።
   እርሱም መልሶ፡- “እኔንም ወይም አባቴንም አታውቁም፤ እኔንስ ብታውቁኝ አባቴን ደግሞ ባወቃችሁ ነበር” አላቸው /ቁ.19/።  እንዲህ ማለቱ ነበር፡-“አስቀድሜ እንደነገርኳችሁ እኔ የዮሴፍ ልጅ እንደሆንኩ ስለምታስቡ እኔን አታውቁኝም፤ የባሕርይ አባቴንም አታውቁትም፡፡ ‘አባቴንም አታውቁትም’ ብዬ ስላችሁ ‘ታድያ ማንን ነው የምናመልከው?’ ልትሉ ትችላላሁ፡፡ እኔም እንዲህ ብዬ እመልስላችኋለሁ፡- የዔሊ ልጆች እግዚአብሔርን አያውቁም ነበር፡፡ ምክንያቱም ምናምንቴዎች ነበሩና /1ሳሙ.2፡12/፡፡ ልክ እንደዚሁ እግዚአብሔርን አመልካለሁ እያለ በኃጢአት የሚመላለስ ሰውም እግዚአብሔርን አያውቅም ብዬ በእውነት ያለ ሐሰት እነግራችኋለሁ፡፡ ነቢያት ስለ እኔ አመጣጥ ሲመሰክሩ ብታምንዋቸው ኖሮ እኔንም ባመናችሁብኝ ነበር፡፡ እኔን ለማሳደድ እኔን ለመግደል ሳይሆን ልቡናችሁ እውነትን የሚሻ ቢሆን ኖሮ አባቴ ስለ እኔ ይገልጥላችሁ ነበር፤ እኔም ስለ አባቴ በገለጥኩላችሁ ነበር /ማቴ.11፡27/፡፡ አሁንም ቢሆን ግን አልረፈደምና በእኔ እመኑ፡፡ ከጨለማ ውጡ፤ በብርሃኔ ብርሃንን እዩ፤ የሕይወትንም ውኃ ምንጭ ጠጡ፡፡ በእኔ በቀር (እኔን ተወላዲ ካላለ) ወደ አብ የሚመጣ (አብን ወላዲ የሚለው) የለም /ዮሐ.14፡6/፤ እኔን ስታውቁኝ ግን እኔና አብ አንድ እንደሆንን ታውቁታላችሁ” /ዮሐ.10፡30 St. Cyril of Alexandria on the Gospel of John,Ibid /፡፡ 

   ጌታ በመቅደስ ሲያስተምር በግምጃ ቤት (መባውን በሚያኖሩበት ሣጥን) አጠገብ ይህን ትምህርት አስተማራቸው፡፡ ጌታችን በዚህ በሣጥኑ አጠገብ ሆኖ ማስተማሩ ያለ ምክንያት አልነበረም፡፡ ካህናተ አይሁድ ለቤተ እግዚአብሔር የሚሰበሰበውን መባ እያነሡ የሚያበላሹት ሆኑ፡፡ ከዚህ በኋላ ንጉሥ ኢዮአስና ሊቀ ካህናቱ ዮዳሄ መክረው ብር የሚያስገባ እጅ የማስገባ ሣጥን አኖሩ፡፡ ሲመላ ዕቃቤት እያስገቡ ያኖሩታል፡፡ ሁለት ሦስት ሆነው እንዳይወስዱትም ጠባቂ አለው /ወንጌል ቅዱስ አንድምታ፣ ገጽ 497/፡፡ ጌታችን በዚህ መባውን በሚያኖሩበት ግምጃ ቤት አጠገብ ሆኖ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ” ብሎ ማስተማሩ ትምህርቱ እዚያው ከተቀመጠው ገንዘብ በላይ ውድ እንደሆነና ሊጠቀሙበት፣ የራሳቸው ሊያደርጉት እንደሚገባ ሲያስረዳቸው ነው /Origen, Commentary on the Gospel of john,19/፡፡  
  እነርሱ ግን “እኔንም ወይም አባቴንም አታውቁም” ስላላቸው ሊይዙት (ሊገድሉት) ወደዱ፡፡ ሆኖም በፈቃዱ የሚሞትበት “ጊዜው ገና አልደረሰምና ማንም አልያዘውም” /ቁ.20/።
 
  ተወዳጆች ሆይ! “አብን አከብራለሁ” እያለ በወልድ ላይ ጽርፈትን (ስድብን) የሚናገር ሰው አብንም ጨምሮ እንደሚሰደብ ታስተውላላችሁን? እኛ ግን ከዚህ የራቅን ይልቁንም ወልድን ከፍ ከፍ የምናደርግ እንሁን፡፡ ወልድን በቃላት “ኢየሱስ ጌታ ነው” በማለት ብቻ ሳይሆን አምላክነቱንም በሚገባ በመመስከር በእውነት እናመስግነው፡፡ በዚህ ብቻም አይደለም፡፡ የዔሊ ልጆች “እግዚአብሔርን አያውቁም” ተብለው እንደተወቀሱ እንዳንሆን ክርስቲያኖች ስንሆን ከክርስትና ጋር የማይሄዱ ነገሮችን ከእኛ ዘንድ በማራቅም እናመስግነው፡፡ ክርስቲያን ማለት ከንግግሩ በላይ በምግባሩ በሰማያት ያለውን አባቱን የሚያከብር ነውና /ማቴ.5፡16/፡፡ ብርሃን ለራሱ ብርሃንን አያበራም፤ ጨው ለራሱ ጨው አይምርም፤ እንዲሁም እርሾ ለሌሎች እንጂ ለራሱ የሚጠቅም አይደለም፡፡ ክርስቲያንም ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ጭምር የሚኖር ነው፡፡ እንዲህ ሲያደርግም “በእውነት ወልድን አከበረው”፤ “እግዚአብሔርን አወቀው” ይባልለታል፡፡ እንግዲያውስ መዝሙረኛው ዳዊት “ከስንፍናዬ የተነሣ ቁስሌ ሸተተ” እንዳለው ከኃጢአት የባሰ የስንፍና ሥራ የለምና እግዚአብሔርን እያስነቀፍን በስንፍና የምንቆይ አንሁን /መዝ.38፡5/፡፡ ከዚህ ሁሉ ስንፍና እንድንርቅ የተወደደ የክርስቶስ መዓዛም እንድንለብስ መንግሥቱንም እንድንወርስ እግዚአብሔር በቸርነቱ ይርዳን አሜን፡፡

3 comments:

  1. ይኸን በማወቅ ድኀነት ባይገኝበትም ፣ የወንጌልን ቃል ለማስረዳት ቀና ስለሆንክልኝና ፈቃደኛነትህንም ባለፈው ስለገለጽክልኝ ፣ የተሟላ ግንዛቤ እንዲኖረኝ በማለት ከአንድ ጥያቄ ጋር ዛሬም ብቅ ብያለሁ ፡፡

    ዘሌዋውያን 2ዐ ፡ 1ዐ በምንዝር ምክንያት የተያዘ አመንዝራና አመንዝራይት እንዲገደሉ ያዛል ፡፡ ፈሪሳውያን ኢየሱስን ለመፈተን ያቀረቡለት ግን ሴቷን አመንዝራ ብቻ ነው ፡፡ ብቻዋን አመነዘረች ማለት አይቻልምና በቤተ ክርስቲያናችን ትምህርት ሴቷ ብቻ ለፍርድ መቅረቧ እንደምን ይገለጻል ? ወንጌል ጸሃፊው ለእምነት የሚያስፈልጉንን ብቻ እንደከተበ የሚለው አንዱ መልስ ነው /ዮሐ 2ዐ ፡ 31/ ፤ ከዚህ የተለየ የምታብራራልኝ ቢኖር እጠብቃለሁ ፡፡

    አመሰግናለሁ

    ReplyDelete
  2. የእግዚአብሔር ፍጹም ሰላም ይብዛልህ! ከማስተካከያ ልጀምር፡፡ “ይኸን በማወቅ ድኅነት ባይገኝም” ያልከው ቢታረም መልካም ነው፡፡ ምክንያቱም ፈሪሳውያኑ በሴትዮዋ ላይ ሲያደርጉት የነበረው “እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ፤ በምትፈርዱበት ፍርድ ይፈረድባችኋልና” የሚለውን የከበረ ወንጌል የሚቃረን ነውና /ማቴ.7፡1/፡፡ በሌላ አገላለጽ የእነርሱ ኃጢአት ከእርሷ ኃጢአት በላይ ነበር፡፡ እኛም ከዚህ ፈራጆች እንደሚፈረድባቸው አውቀናልና እንዲህ ካላደረግን (ካልፈረድን) ለድኅነታችን ይጠቅመናል፡፡
    ወደ ጥያቄህ ስመለስ ከዚያው ከወንጌሉ መረዳት እንደምንችለው ሴቷ ብቻ ለፍርድ መቅረቧ ፈሪሳውያኑ ጌታችንን ለመፈተን ብለው ስላመጧት ነው /ቁ.5/፡፡ በሌላ አገላለጥ እኛ ንጹሐን ነን ይሉ ስለ ነበር ነው፡፡ ሆኖም ጌታችን እንደነገራቸው ንጹሐን አልነበሩም፡፡ ንጹሐን ቢሆኑ ኖሮ “ከእናንተ ኃጢአት ሌለበት ቀድሞ በድንጋይ ይውገራት” ሲላቸው በወገሯት ነበርና /ቁ.7/፡፡
    በመሠረቱ መማንዘር ማለት ከሕጋዊው ባል ወይም ከሕጋዊት ሚስት ውጪ የሚደረግ ግንኝነት ብቻ አይደለም፡፡ ከእውነተኛው ሙሽራ ከእግዚአብሔር ውጪ ከጣዖትና ከኃጢአት ጋር የሚደረግ ግንኝነትም ምንዝርና ነው፡፡ ሐዋረያው እንደሚነግረን ሥጋችን ማኅደረ እግዚአብሔር እንደሆነ የታወቀ ነው /1ቆሮ.6፡20/፡፡ ይህን ሥጋችን ታድያ እውነተኛው ሙሽራችንን ትተን ከአመንዝራ ሴት ጋር ስንተባበር ሥጋችን የክርስቶስ ብልት መሆኑ ቀርቶ የጋለሞታ ብልት ይሆናል /1ቆሮ.6፡15/፡፡ ልክ እንደዚሁ እግዚአብሔርን ትተን ከጣዖታት (ከማንኛውም ዓይነት ኃጢአትም ጭምር) ጋር ስንተባበርም ግልሙትና እንደሆነ የእግዚአብሔር ቃል ይነግረናል /ኤር.3፡6-9/፡፡
    በዚሁ መሠረት ለፍርድ የቀረበችው ሴቷ ብቻ ሳትሆን ፈሪሳውያኑ ራሳቸውም አመንዝሮች ነበሩ ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ስለ ወጋቸው ብለው የእግዚአብሔርን ትእዛዝ የሚተላለፉ /ማቴ.15፡3/፣ በነቢያት ደም የሰከሩ፣ በውጭ አምረው (ጻድቃን መስለው) የሚታዩ በውስጥ ግን በርኩሰት (በግብዝነትና በዓመጸኝነት) ሁሉ የተመሉ፣ ስለ ቀረባቸው ምድራዊ ክብር ብለውም ጌታችንን ለመግደል የሚባክኑ ነበሩና /ማቴ.25-32/፡፡ እግዚአብሔርን እናውቃለን ቢሉም አያውቁትም ነበርና /ዮሐ.8፡19/፡፡ እንደውም የበለጠ ቃሉን በመንፈስ ስንመረምረው ፈሪሳውያኑ ከሴቷ ይልቅ እጅግ ጋለሞቶች ነበሩ፡፡ ሴቷስ ሳያውቁትም ቢሆን ስታመነዝርባቸው ከነበሩት ከሌሎች ባሎቿ አፋትተው ወደ እውነተኛው ባሏ አምጥተዋታል፡፡ እርሷም እውነተኛውን አፍቃሪዋ አግኝታዋለችና ተመልሳ ወደ ቀድሞ ባሎቿ አልሄደችም፡፡ እነርሱ ግን በአመንዝራነታቸው ቀጥለው ከእግዚአብሔር ጋር እንደተፋቱ ቀርተዋል፡፡
    ወንድሜ! እኛም ብዙ አመንዝረን ይሆናል! ሆኖም ጊዜው አልረፈደብንምና እነዚያን ተትን ወደ ክርስቶስ ዞር እንበል፡፡ ይህን እንድናደርግ እኛን በመውደድ የእኛን ባሕርይ ባሕርይ ያደረገው ክርስቶስ ይርዳን አሜን!!

    ReplyDelete
  3. ስለመልስህ አመሰግናለሁ ፡፡
    እንደ ቸርነቱ ብዛት ምሕረቱን ተስፋ አደርጋለሁ እንጅ ፣ በራሴማ ምን መተማመኑ ይኖራልና አመንዝራነቴ በጥርጣሬ ይነገራል ? እርሱ ደካማነታችንን የሚያውቅ ግን ሁሉንም ይሸፍነዋል ፡፡

    የእግዚብሔር ምሕረት ለሁላችንም ይብዛልን ፡፡ አሜን

    ReplyDelete

FeedBurner FeedCount