Wednesday, September 19, 2012

ምክረ አበው -ቁጥር ሦስት


1. ከዕለታት በአንድ ቀን አባ ፓምቦ አባ እንጦንስን “ማድረግ ያለብኝ ነገር ምንድነው?” ብሎ ይጠይቋል፡፡ አባ እንጦንስም እንዲህ ሲል መለሰለት “በራስህ ጽድቅ አትታመን፤ ላለፈው አትጨነቅ፤ ይልቁኑ አንደበትህንና ሆድህን ግዛ፡፡”
2. አባ እንጦንስ በአንድ ወቅት እንዲህ አለ፡- “በዚህች ምድር ላይ ስንኖር ሕይወታችንንም ሆነ ሞታችን ከባልንጀራችን ጋር ነው፡፡ ወንድማችንን ገንዘብ ካደረግነው እግዚአብሔርን ገንዘብ እናደርጓለን፤ ወንድማችንን ካስቀየምነው ግን በክርስቶስ ላይ ኃጢአትን እንሠራለን፡፡”
3. በአንድ ወቅት አንድ ወንድም አባ እንጦንስን “ጸልይልኝ?” በማለት ይጠይቋል፡፡ እንጦንስምአንተ ራስህ ጥረት የማታደርግና ወደ እግዚአብሔር የማትጸልይ ከሆነ እኔም ሆንሁ እግዚአብሔር ምሕረት ልናደርግልህ አንችልምአለው፡፡
4. አባ ዮሐንስ ሐጺር አንድ ቀን እንዲህ አለ፡- “እኔ ልክ ከትልቅ ዛፍ ሥር ተቀምጦ ሳለ ብዛት ያላቸው አውሬዎችና እባቦች ወደ እርሱ መጥተው ሊያጠቁት ሲሉ በፍጥነት ዛፉ ላይ ወጥቶ በማምለጥ የሚድን ሰውን እመስላለሁ፡፡ ምክንያቱም ይህ ሰው ፈጥኖ ዛፉ ላይ በመውጣት እንደዳነ ሁሉ እኔም በባእቴ ውስጥ ተቀምጬ ሳለሁ ክፉ ሐሳቦች ሲዋጉኝ ፈጥኜ ወደ እግዚአብሔር በመጠጋት ከጠላቴ አመልጣለሁና፡፡”
5. ለመለወጥ ጥረት ስለምታደርግ ነፍስ አባ ዮሐንስ ሐጺር ለአንድ መነኰሴ ያስተማረበት ምሳሌ እንደሚከተለው ተጽፎ ይገኛል፡-“በከተማ መካከል ብዙ ወዳጆች ያሏት አንዲት ቆንጆ ሴተኛ አዳሪ ነበረች፡፡ የከተማዋ ከንቲባ ወደ እርሷ ቀርቦ፡- መልካም ሴት እንደምትሆኚ ቃል ከገባሽልኝ አሁኑኑ አገባሻለሁ ይላታል፡፡ እርሷም በሐሳቡ ተስማምታ ቃል ስለገባችለት ወደ ቤቱ ይዟት ሄደ፡፡ ወዳጆቿ ድጋሚ ሊያገኟት ስለ ፈለጉ እንዲህ እያሉ ይመካከሩ ነበር፡- የከተማው ከንቲባ ወዳጃችንን ወደ ቤቱ ወስዷታል፡፡ በግልጽ ወደ ቤቱ ከሄድን ስለሚያውቅብንና ስለሚያስፈርድብን በቤቱ ጓሮ ዞረን እናፏጭላት፡፡ የፉጨታችንን ድምጽ ለይታ ስለምታውቃቸው ከቤቷ ወርዳ ትመጣለች፡፡ ለማንኛውም ግን እርሷ ትምጣልን እንጂ እባ አንጣላም አሉ፡፡ በመጨረሻ እንደተመካከሩት በቤቱ ጓሮ ዞረው ሲያፏጩላት ጀሮዎቿ ቆሙ፡፡ ይሁን እንጂ ወደ እነርሱ ልትወርድ ስላልፈለገች ፈጠን ብላ ወደ እንግዳ መቀበያው አዳራሽ ገባችና በሮቹን ዘጋግታ ከውስጥ ተቀመጠች፡፡
  ልክ እንደዚሁ ነፍሳችን በዚህች ሴት ስትመሰል ወዳጆቿ ደግሞ ምኞቶቻችን ይመስላሉ፡፡ ከንቲባው የሚመሰለው በምንወደው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ በቤቱ ውስጥ ያለው የእንግዳ መቀበያ አዳራሽ በዘላለማዊ ቤታችን ወይም በመንግሥተ ሰማያት ሲመሰል የሚያፋጩላት ሰዎች ደግሞ በርኩሳን መናፍስት ይመሰላሉ፡፡ በመጨረሻም ይህን ምሳሌ ነፍሳችን ሁል ጊዜ እግዚአብሔር ከተጠጋች በእርሱ ኃይል እንደምትኖር ያስረዳናል፡፡
6. አባ ዳንኤል እንዲህ አለ፡- “ሥጋ የሚበረታው ነፍስ በደከመችበት መስፈርያ መጠን ሲሆን ነፍስም የምትበረታው ሥጋ በደከመበት መስፈርያ መጠን ነው፡፡
7. አባ አርሳኔዎስ በበአቱ ውስጥ ተቀምጦ ሳለ ርኩሳን መናፍስት ክፉኛ ሊነዘንዙት ጀመሩ፡፡ በዚህ ጊዜ ከበአቱ ውጪ በደጃፉ ላይ ቆመው የነበሩት ደቀመዛሙርቱ እንዲህ እያለ ወደ እግዚአብሔር ሲጸልይ ይሰሙታል፡- “ጌታዬ ሆይ! በፊትህ ምንም ዓይነት መልካም ሥራ ባልሠራም እንደ ቸርነትህ አቁመኸኛል! ስለዚህ ከአሁን በኋላ መልካም መሥራትን ስለምጀምር እባክህ አትተወኝ!”
 (ምንጭ፡- የበረሃ አባቶች ምክሮች በአያሌው ዘኢየሱስ የተተረጎመ)!

1 comment:

  1. kale hiwoten yasemalen girum new le hiwot yemhihon senq new

    ReplyDelete

FeedBurner FeedCount