Showing posts with label ብሒል ወምክረ አበው. Show all posts
Showing posts with label ብሒል ወምክረ አበው. Show all posts

Friday, May 16, 2014

ምክረ አበው ቁጥር 5



(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ግንቦት ፰ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
1.  ጥያቄ፡- “ለሰው አፍ ከኮሶና ከነገር ማናቸው ይመራል?"
      ምላሽ፡- "ሲገባ ኮሶ ይመራል፤ ሲወጣ ግን ነገር ይመራል፡፡
2.  ሐሳብህ ብዙ የሚመኝ አንዱን ይዞ የማይሠራ ሲሆንብህ ሰይጣን በጐም ሥራ እንዳትሠራ ባለመሥራትህም እንዳትደነግጥ መልካምን በማሳሰብ እየከለከለ በጥበብ ሰንሰለቱ እንዳሰረህ ዕወቅ፡፡ ስለዚህ አንተ አንድ ሁነህ ሐሳብህን ብዙ አታድርግ፡፡ የምትኖርበትን የማትለቀው አንድ ሥራ ያዝ እንጂ ምኞትህን በየቀኑ አትለዋውጠው፡፡ አንዱን መያዝ አንዱን መልቀቅ የዕብደትና የዝሙት ነውና፡፡

Sunday, October 28, 2012

ምክረ አበው ቁጥር አራት


ልጆቼ! ሓኪሞች ብትሆኑ፣ መሀንዲሶች ብትሆኑ፣ የሽመና ሠራተኞች ብትሆኑ፣ መርከበኞችም ብትሆኑ መልካም ነው፡፡ ይህን ጥበብ መማራችሁም ጥሩ ነው፡፡ እኔ ግን ከዚህ የበለጠ ጥበብ አሳያችኋለሁ፡፡ በዚህ (በተማራችሁት ምድራዊ) ጥበባችሁም ሌላ ጥበብ ትማሩበት ዘንድ እማልዳችኋለሁ፡፡ ሰማያዊን ጥበብ! ከላይ በገልጽኩላችሁና እናንተ በተማራችሁት ጥበብ ተጠቅማችሁ ገንዘብ ማግኘታችሁ አይቀርም፡፡ በዚህ ገንዘባችሁ ግን ድሆችን መርዳት ልመዱበት፡፡ ይህ የምነግራችሁን ጥበብ እንደ ቀላል የምታዩት አትሁኑ፡፡ መሀንዲሶች ብትሆኑ በምህንድስና ጥበባችሁና እውቀታችሁ በዚህ ምድር የሚያማምሩ ቪላ ቤቶችን ልትሠሩ ትችላላችሁ፡፡ በምነግራችሁ ጥበብ ግን
በመንግሥተ ሰማያት ውስጥ የዘላለም ቤታችሁን ትሠራላችሁ፡፡ በዚህ ምድር ለምትሠሩት ቤታችሁ በጣም ብዙ ወጪ ብዙም ድካም ይጠይቃችኋል፡፡ በምነግራችሁ ጥበብ ግን ብዙ ልፋት የለውም፡፡ ወጪአችሁ መልካምና ፈቃደኛ መሆን ብቻ ነው፡፡ በዚህ ምድር ለምትሠሩት ቤት የተለያዩ ዓይነት ብረቶችና ማቅለጫዎች እንዲሁም የከበሩ ድንጋዮችን ትጠቀማላችሁ፡፡ በምነግራችሁ ጥበብ ግን ይህ ሁሉ አያስፈልጋችሁም፡፡ የሚያስፈልጋችሁ ብሎን ወይንም ብረት ወይንም የከበረ ድንጋይ ሳይሆን መልካም ምግባራችሁና በጎ ፈቃዳችሁ ብቻ ነው፡፡

Wednesday, September 19, 2012

ምክረ አበው -ቁጥር ሦስት


1. ከዕለታት በአንድ ቀን አባ ፓምቦ አባ እንጦንስን “ማድረግ ያለብኝ ነገር ምንድነው?” ብሎ ይጠይቋል፡፡ አባ እንጦንስም እንዲህ ሲል መለሰለት “በራስህ ጽድቅ አትታመን፤ ላለፈው አትጨነቅ፤ ይልቁኑ አንደበትህንና ሆድህን ግዛ፡፡”
2. አባ እንጦንስ በአንድ ወቅት እንዲህ አለ፡- “በዚህች ምድር ላይ ስንኖር ሕይወታችንንም ሆነ ሞታችን ከባልንጀራችን ጋር ነው፡፡ ወንድማችንን ገንዘብ ካደረግነው እግዚአብሔርን ገንዘብ እናደርጓለን፤ ወንድማችንን ካስቀየምነው ግን በክርስቶስ ላይ ኃጢአትን እንሠራለን፡፡”

Wednesday, August 8, 2012

የምክር ቃል ከቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ!


 ክርስቶስን ትለብስ ዘንድ በውኃ ስሙን እየጠራህ ተጠምቀሃል፡፡ በጥምቀትም የጌታህ ዙፋን አካልህ እንደሆነ ማኅተሙም በግንባርህ ላይ እንደታተመ ልብ በል፡፡ ከእንግዲህ አንተ የሌሎች ሌሎችም የአንተ ጌቶች አይደሉም የጌታ እንጂ፡፡
በርህራሄው ዳግም የፈጠረን ጌታ ኢየሱስ አንድ ነው፡፡ በመስቀሉ ላይ በፈፀመው ቤዛነት በኩል እኛን ያዳነን እርሱ አንድ ነው፡፡ ሕይወታችንን በጽድቅ የሚመራት እርሱ ብቻ ነው፡፡ ትንሣኤያችንን የሚፈጽምልን እርሱ ነው፡፡ እንደ ሥራችንም ዋጋችንን የሚከፍለን እርሱ ነው፡፡ በሥራዎቹ ቸርና ሩህሩህ የሆነውን አባት እንዳታስቆጣው፡፡
በባልንጀራህ ላይ የምትቆጣ ከሆነ የአንተ ቁጣ በእግዚአብሔር ላይ ነው፡፡ በባልንጀራህ ላይ ቂምን በልብህ የያዝክ ከሆነ ቂምህ በጌታ ላይ ነው፡፡ ባልንጀራህን በከንቱ የምትቆጣው ከሆነ ኃጢአት በአንተ ላይ ይስለጠንብሃል፡፡ ልብህን የፍቅር ማደሪያ ካደረከው በምድር ላይ አንዳች ጠላት አይኖርህም፡፡
አምላክህ ክርስቶስ ስለ ገዳዮቹ በመስቀሉ ላይ ሳለ ይቅርታን ለመነ፡፡ እንዴት አንተ ፍጥረትህ ከትቢያ የሆነ ቁጣን በፈቃድህ በራስህ ላይ ታቀጣጥላለህ? አንተ በክርስቶስ ደም ወደ እርሱ ቀርበሃል፤ በሕመሙም ድነሃል፡፡ በአንተ ፈንታ ለኃጢአት ስራዎችህ ምትክ ሆኖ ስለ አንተ መተላለፍ እርሱ ሞቷል፡፡ አይሁድ በመዘበት በፊቱ ላይ ምራቃቸውን ሲተፉበት መታገሱ ሰዎች ቢያፌዙብህ እንኳ እንድትታገሳቸው አርአያ ሊሆንህ ነው፡፡ መራራና ሆምጣጣ የሆነውን ወይን መጎንጨቱ ከቁጣ ትሸሽ ዘንድ ነው፡፡ በጅራፍ ተገርፎ፣ በሰንሰለት ታስሮ መጎተቱ ስለ ጽድቅ ስትል መከራን እንድትቀበል ነው፡፡ 
(ምንጭ፡- ስብከት ወተግሳጽ ዘቅዱስ ኤፍሬም፣ በመ/ር ሽመልስ መርጊያ፣ ገጽ 65-66)

FeedBurner FeedCount