Showing posts with label የምክር ቃል ከቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ. Show all posts
Showing posts with label የምክር ቃል ከቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ. Show all posts

Wednesday, August 8, 2012

የምክር ቃል ከቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ!


 ክርስቶስን ትለብስ ዘንድ በውኃ ስሙን እየጠራህ ተጠምቀሃል፡፡ በጥምቀትም የጌታህ ዙፋን አካልህ እንደሆነ ማኅተሙም በግንባርህ ላይ እንደታተመ ልብ በል፡፡ ከእንግዲህ አንተ የሌሎች ሌሎችም የአንተ ጌቶች አይደሉም የጌታ እንጂ፡፡
በርህራሄው ዳግም የፈጠረን ጌታ ኢየሱስ አንድ ነው፡፡ በመስቀሉ ላይ በፈፀመው ቤዛነት በኩል እኛን ያዳነን እርሱ አንድ ነው፡፡ ሕይወታችንን በጽድቅ የሚመራት እርሱ ብቻ ነው፡፡ ትንሣኤያችንን የሚፈጽምልን እርሱ ነው፡፡ እንደ ሥራችንም ዋጋችንን የሚከፍለን እርሱ ነው፡፡ በሥራዎቹ ቸርና ሩህሩህ የሆነውን አባት እንዳታስቆጣው፡፡
በባልንጀራህ ላይ የምትቆጣ ከሆነ የአንተ ቁጣ በእግዚአብሔር ላይ ነው፡፡ በባልንጀራህ ላይ ቂምን በልብህ የያዝክ ከሆነ ቂምህ በጌታ ላይ ነው፡፡ ባልንጀራህን በከንቱ የምትቆጣው ከሆነ ኃጢአት በአንተ ላይ ይስለጠንብሃል፡፡ ልብህን የፍቅር ማደሪያ ካደረከው በምድር ላይ አንዳች ጠላት አይኖርህም፡፡
አምላክህ ክርስቶስ ስለ ገዳዮቹ በመስቀሉ ላይ ሳለ ይቅርታን ለመነ፡፡ እንዴት አንተ ፍጥረትህ ከትቢያ የሆነ ቁጣን በፈቃድህ በራስህ ላይ ታቀጣጥላለህ? አንተ በክርስቶስ ደም ወደ እርሱ ቀርበሃል፤ በሕመሙም ድነሃል፡፡ በአንተ ፈንታ ለኃጢአት ስራዎችህ ምትክ ሆኖ ስለ አንተ መተላለፍ እርሱ ሞቷል፡፡ አይሁድ በመዘበት በፊቱ ላይ ምራቃቸውን ሲተፉበት መታገሱ ሰዎች ቢያፌዙብህ እንኳ እንድትታገሳቸው አርአያ ሊሆንህ ነው፡፡ መራራና ሆምጣጣ የሆነውን ወይን መጎንጨቱ ከቁጣ ትሸሽ ዘንድ ነው፡፡ በጅራፍ ተገርፎ፣ በሰንሰለት ታስሮ መጎተቱ ስለ ጽድቅ ስትል መከራን እንድትቀበል ነው፡፡ 
(ምንጭ፡- ስብከት ወተግሳጽ ዘቅዱስ ኤፍሬም፣ በመ/ር ሽመልስ መርጊያ፣ ገጽ 65-66)

FeedBurner FeedCount