በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፥ ጥቅምት ፱ ቀን፥ ፳፻፮ ዓ.ም.፤ የጽሑፉ ምንጭ፡ አዲስ ጉዳይ መጽሔት፣ ቅጽ 7፣ ቁ.183፣ መስከረም
18 ቀን፣ 2006 ዓ.ም.)፡- “የአምላክህ የእግዚአብሔር ቍጣ እንዳይነድድብህ ከምድርም ፊት እንዳያጠፋህ፥ በዙሪያችሁ ያሉት አሕዛብ የሚያመልኩአቸውን ሌሎችን አማልክት አትከተሉ”
/ዘዳ.6፡15/ ተብሎ እንደተጻፈው እንኳን ሰው እግዚአብሔርም ይቆጣል፡፡ እግዚአብሔር የሚቆጣ መሆኑንና ተቆጥቶም የሚቀጣ መሆኑን
ብዙ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅሶች አሉ፡፡ “ከቍጣው ጢስ ወጣ፥ ከፊቱም የሚበላ እሳት ነደደ፤ ፍምም ከእርሱ በራ”
/መዝ.18፡8/፤ “የእግዚአብሔር ቍጣ በሕዝቡ ላይ ነድዶአል እጁንም በላያቸው ዘርግቶ መትቶአቸዋል፤”
/ኢሳ.5፡25/ የሚሉትን የመሰሉ በመቶዎች የሚቈጠሩ ጥቅሶችን ከመጽሐፍ ቅዱስ እናገኛለን፡፡ እንዲሁም ከቅዱሳን ሰዎች ደግሞ ከታላቁ
ነቢይ ከሙሴ ጀምሮ ያሉ ነቢያት ሐዋርያትና አበውም ሁሉ የሚቈጡባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡ ለምሳሌ ቅዱስ ጳውሎስ ችሎት ፊት ቀርቦ
እየተናገረ ባለበት ሰዓት ሊቀ ካህናቱ አፉን እንዲመቱት ሲያዝ፡- “አንተ በኖራ የተለሰነ ግድግዳ፥ እግዚአብሔር አንተን ይመታ ዘንድ አለው፤ አንተ በሕግ ልትፈርድብኝ ተቀምጠህ ሳለህ ያለ ሕግ እመታ ዘንድ ታዛለህን?”/ሐዋ.23፡3/
ሲል በቁጣ ቃል ተናግሮ ነበር፡፡ ስለዚህ ቁጣ በሁላችንም ሊገኝ የሚችልና በራሱም ከተፈጥሮአችን ጋር የሚቃረን ነገር አይደለም ማለት
ነው፡፡
ቁጣ በተፈጥሮአችን ውስጥ ያለና ከውጭ መጥቶ የተጨመረብን ካልሆነ መኖሩም
በራሱ ክፉ ካልሆነ ለውስጣችን የሚያገለግል መሣሪያ ነው ልንለው እንችላለን፡፡ በዚህ መንገድ የምናየው ከሆነ ጥቅሙንም ሆነ ጉዳቱን
ለመረዳት አያስቸግረንም፡፡ ምክንያም እጅ የሰውነት ክፍል ሆኖ በራሱም ባይሆን ለስርቆት፣ ለዱላ፣ ለግዲያና ለመሳሰሉት ሊያገለግል
መሆኑ ብቻ እጅን ጎጂ እንደማያሰኘው ይልቁንም የምንጠራቸው ድርጊቶች ሁሉ አጠቃላይ ሰውየው የደረሰበትን የአስተሳሰብና የመፍትሔ
ዓቅም ማሳያዎች እንደሚሆኑት ሁሉ ቁጣም እንዲሁ ነው፡፡ እንደ እጅ ገዝፎ ባናየውም በማንነታችን ውስጥ ያሉ ሰዎች ለፈለጉት ሊጠቀሙበት
የሚችሉት መሣሪያ ነው፡፡
ሆኖም ቁጣ ሲባል
ለአብዛኞቻችን በጭንቅላታችን ቅድሚያ የሚመጣው ጉዳቱ ነው፡፡ ምክንያም አብዛኞቻችን የምናየው እንደ ጦር መሣሪያ ሲጎዳ እንጂ ሲያድን
እንዳልሆነ ነው፡፡ በሠለጠኑትና የአንድን መሣሪያ አጠቃቀም በአግባቡ በሚያውቁት ሃገሮችና ሰዎች ጠመንጃም የሃገርንና የከተማን ሰላም
መጠበቂያ መሣሪያ ሆኖ እንደሚያገለግል ቢታወቅም በወታደርና በፖሊስ እጅ በየዕለቱና በየመንገዱ የሚያዩት መሣሪያ አይደለም፡፡ ልክ
እንዲሁ ቁጣም በብልህ ሰዎች ዘንድ የሌለ እስኪመስል ድረስ አይታይ እንጂ የራሳቸውን ከተማ ሰውነታቸውን በመጠበቅ ግን መኖሩ የታወቀ
ነው፡፡ በአብዛኞቻችን ዘንድ ግን አጠቃቀሙን ስለማናውቀው ልክ ሞኝ ሰው እንደያዘው ጠመንጃ በየሰዓቱ ስናባርቀው ራሳችን ረብሸን
ሌላውንም ስንረብሽበትና በፊታችን የተገኘውን ሁሉ ስናቆስልበት እንኖራለን፡፡
ቃሉ ሲጠራ ቀድሞ ጉዳቱ ወደ አእምሮአችን የሚመጣብንም ስለዚሁ ነው፡፡
በክርስትና አምልኮት
ውስጥ ተገቢውን ሕይወት የሚኖሩ ሁሉ በእጅጉ እንደሠለጠነና መሣሪያውን ለመጠበቂያ እንጂ ለማሸበሪያ እንደማይጠቀምበት ወታደር ወይም
ፖሊስ መሣሪያው እንዳላቸው ቢታወቅም የሚጠቀሙበት በጠላት ዲያብሎስና ኀጢአት ላይ ስለሆነ ወንድሞቻቸውንና እኅቶቻቸውን ሲረብሹ አይታዩም፡፡
አብዛኞቻችን ግን መሣሪያውን የነፍሳችን ከተማ ራሳችን ከኀጢአትና ከዲያብሎስ ለመጠበቅ ሳይሆን ለፍላጎቶቻችን ከተሸነፍን በኋላ ፍላጎታችን
ለማሳካት ዕንቅፋት የመሰለን ላይ ሁሉ የምንባርቀው አላዋቂ የያዘው መሣሪያ አድርገነዋል፡፡ እኔም በዚህ ጽሑፍ ለማሳየት የምሞክረው
ቁጣ ማንኛችንም ላይ ያለ መሆኑን ተረድተን ሊጠቅመን ወደሚችል አጠቃቀም ለመለወጥ የሚረዳውን ልምምድ ነው፡፡
በመጀመሪያ ደረጃ
ቍጣን ባልተፈለገ መንገድ እንድንጠቀምበት የሚገፋፉን መንሥኤዎች ማወቅ ተገቢ
ነው፡፡ መፍቀሬ ጥበብ ሰሎሞን “ቅንአት ለሰው የቍጣ ትኩሳት ነውና” /ምሳ.6፡34/ ሲል እንደገለጸው የቍጣ አንዱ መነሻው ቅንአት
ነው፡፡ ከዚህም ይልቅ ትዕቢት፣ በተለይም በውይይትና በጋራ ሥራ ወቅት የእኔ ሐሳብ ብቻ ተቀባይነት ይኑረው የምንልና ለሌላው ሰው ለሐሳቡም ሆነ ለማንነቱ ተገቢውን ክብር የማንሰጥ ሰዎች
ለቍጣ በከፍተኛ ደረጃ እንጋለጣለን፡፡ ምክንያቱም ከራሳችን ሐሳብና አመለካከት የተሻለ ሐሳብና አመለካከት ወይም ደግሞ እኛ ካለን
ዕውቀት የተሻለ ዕውቀት የሚል (መኖሩን በደንብ ያልተረዳነው) አስተሳሰብ በውስጣችን ካለ ቍጣ መምጣቱ አይቀሬ ነው፡፡ አባ መክሲሞስ፡-
“ለዝና፣ ለደስታና ለብልጽግና ያለውን ሐሳብ ያልገራ ሰው ከቍጣ ሊድን፤ ወደ እውነተኛ ፍቅርም ሊደርስ አይችልም” ያለው ለዚህ ነው፡፡
“…ቍጣን መጐተት ጠብን ያወጣል” /ምሳ.30፡33/ ተብሎ እንደተጻፈውም ቍጣ ከኖረ ዘንድ ደግሞ ጠብ ጥላቻ አለፍ ሲልም መጠቃቃት
መበቃቀልና መለያየት ይወለዳሉ፡፡ በምድር ካሉ ጥፋቶችም አብዛኛዎቹ የዚህ ውጤት ናቸው፡፡ በተለይ ለዚህ የተጋለጠው ሰው ኀላፊነቱ
ትልቅ ሲሆን ደግሞ የሚያደርሰው ጥፋትም ያን ያክ ሰፊና ታላቅ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ ያህል አንድ የሃገር መሪ ለቍጣ ቶሎ የሚጋለጥ
ከሆነ ከላይ እስከታች የአርድ አንቀጥቅጥ መንገድ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ በደንብ አድርገን እናውቀዋለን፡፡ ምክንያቱም ሥልጣኑን
እንደ ማይክራፎን አጉልቶ ስለሚያሰማን፡፡ ያ ሰው ትሑትና እውነተኛ ቢሆን አሁንም ሥልጣኑ ትሕትናውንና እውነተኝነቱን አጉልቶ ያሳየን
ነበር፡፡ ማይክራፎን ሥራው የተጠቃሚዎችን ድምፅ አጉልቶ አርቆና አጩኾ ማስደመጥ ነውና፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞንም፡- “የንጉሥ ቍጣ እንደ
ሞት መልእክተኛ ነው፤ ጠቢብ ሰው ግን ያቈላምጠዋል” /ምሳ.16፡14/ ፤ “የንጉሥ ቍጣ እንደ አንበሳ ግሣት ነው፤ የሚያስቈጣውም
ሰው የራሱን ነፍስ ይበድላል” /ምሳ.20፡2/ ሲል ደጋግሞ አረጋግጦልናል፡፡
አባ ዮሐንስ ዘሰዋስው
እንዳለው በሰዎች ላይ የሚደረግ ቍጣ ከጠፋ ግን ልጆቹ ብዙ ስሕተቶች ሊኖሩ አይችሉም፤ ያለ አባት ሊወለዱ አይችሉምና፡፡ ስለዚህ
የቍጣ መንሥኤዎቹን ለማጥፋት የሚታገል ሰው ቍጣ የተባለውን መሣሪያ እንዲህ ማንነቱን ለመጉዳት የሚነሣሱበትን የውስጥ ጠላቶቹን ለማጥፋት
ይጠቀምበታል፡፡ የመሣሪያውን አፈሙዝ ወደ ዲያብሎስና ወደ ኀጢአት ማለትም መጀመሪያ ራሱን የሚዋጉትን ስሜቶች ለማጥፋት ካዞረው የነፍሱን
ከተማ ራሱን ለመጠበቅ ስለሚጠቀምበት ሌላውን ሊጎዳበት አይነሣሣም፡፡ አንድ ገዳማዊ አባት ስለ ቍጣ ምንነት በተጠየቁበት ወቅት፡-
“ቅዱሳን መላእክት ሰዎች ቍጣቸውን በርኩሳት መናፍስትና በዚህ ዓለም ከንቱ ምኞት ላይ እንዲያዞሩ ሲረዱ ዲያብሎስ ደግሞ ቍጣችንን
በሰዎች ላይ እንድናደርግና ከወገኖቻችን ጋር ጦርነት እንድንከፍት ይገፋፉናል” ብለው ነበር፡፡ አባ ኤስድሮስም አጋንንት ልምን ይፈሩሃል
ተብሎ ሲጠየቅ “እኔ የምጋደለው ሰዎችን እንዳልቈጣ ስለሆነ ነው” ብሎ ነበር፡፡ ሌላ አባትም ሰዎች ላይ ያለውን ቍጣ ለማጥፋት ዐሥራ
አራት ዓመት እንደተጋደለ ተናግሯል፡፡ ሰሎሞንም፡- “ሰውን ጠቢብ አእምሮውን ከቍጣ ያዘገየዋል፤ ለበደለኛውም ይቅር ይል ዘንድ ክብር
ይሆንለታል” /ምሳ.19፡11/ ብሏል፡፡ ስለዚህ ቍጣ በሕይወታችን ውስጥ የሚኖር ከሆነ አፈሙዙን ወደማን ማዞር እንዳለብን መረዳትና
ከሰዎች ጋር ለማጋጨት የሚዳርጉንን ስሜቶች መቈጣጠር ተገቢ ይሆናል፡፡
ሰዎች በሰዎች ላይ የሚቃጡት ቍጣ መፍትሔ ካላመጣንለት
ግን ጉዳቱ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ቅዱስ ባስልዮስ እንዳለው በሰዎች ላይ የሚቃጣ ቍጣ ምክንያታዊነትን ሁሉ ስለሚያጠፋ ሰብአዊ ተፈጥሮአችንን
እንኳ ጥያቄ ውስጥ የሚጥል ነውና፡፡ ነቢዩ ኢዮብም፡- “ሰነፉን ሰው ቍጣ ይገድለዋል፤ ሰነፉንም ቅንአት ያጠፋዋል” /ኢዮ.5፡2/
የሚለው ለዚሁ ነው፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞንም፡- “ድንጋይ ከባድ ነው፤ ሸክሙ ጽኑ ነው፤ ከሁለቱ ግን የሰነፍ ቍጣ ይከብዳል፡፡ ቍጣ ምሕረት
የሌለው ነው፤ መዓትም እንደ ጎርፍ ነው፤ በቅንአት ፊት ማን ይቈማል?” /ምሳ.27፡3-4/ ሲል በሰው ላይ የሚቃጣ ቍጣ ምን ያህል
አጥፊ እንደሆነ ገልፆልናል፡፡ ስለዚህ (ከዚህ ዓይነቱ) ቍጣ መራቅ ለሰው ሁሉ ጠቃሚና የሰውነት ሙሉነት መገለጫ ነው፡፡ ዳዊት፡-
“ከቍጣ ራቅ፤ መዓትንም ተው፤ እንዳትበድል አትቅና” /መዝ.37፡8/ ሲል ከነምክንያቱ በመጥቀስ ይመክረናል፡፡ ገዳማውያን አበውም
አንድ ሰው (ከዚህ ዓይነቱ) ቍጣ ራሱን ነጻ ሊያወጣባቸው የሚችላቸውን መንገዶች በማመልከት ከቍጣ እንድንርቅ አበክረው ይመክራሉ፡፡
እንደ አበው ምክር፡- “አንድ ሰው ልቡ ለቍጣ በሚናውፅበት ጊዜ ዝምታን የመጀመሪያ መከላከያ መሣሪያው አድርጎ መጠቀም ይኖርበታል፡፡
በማስከተልም በነፍሱ ወይም በኅሊናው የሚረማመዱ አደገኛ ሐሳቦችን ዝም ማሰኘት ወይም በአፉ ዝም ብሎ በእነዚያ ሐሳቦቹ ከሚያደርገው
ውይይት መቆምና የውስጥ ዝምታን በፍጥነት ማስከተል አለበት፡፡ በመጨረሻ የሚረብሹ የንግግርና የሐሳብ ነፋሶችን በፀጥታ ጐጆ ውስጥ
ሆኖ ማሳለፍ ከቍጣ ነጻ ሊያወጣው ይችላል” ይሉናል፡፡ እነዚህን መንገዶች የምንከተል ከሆነ በርግጥም ቍጣን ጠላታችን ዲያብሎስንና
በውስጣችን የሚፈጠሩ ክፉ ሐሳቦችን ለመዋጋት በመጠቀም ወደ ሰዎች ከመቃጣት እንድናለን፤ አላዋቂ እንደያዘው ጠመንጃም በየመንገዱ
አናባርቀውም፡፡ •
my dear brother ገብረ እግዚ ለምን your commentary of st jhon gospelመጽሃፉን ለማህበረ ቅዱሳን አቅርበህ እንዲያሳትሙልህ አታረግም ...ይሄ ትምህርት በመጽሃፍ መልክ ለሁሉ እንዲደርስ ካለኝ ጉጉት ነው!
ReplyDelete