(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ መስከረም 19 ቀን፣
2007 ዓ.ም.)፡- በስመ
አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
እንደምን ናችኁ ልጆች? ትምህርት በደምብ ዠመራችኁ? እንዴት ነው ታድያ ትምህርት?
በጉጉት እየተከታተላችኁ ነው አይደል? ጐበዞች፡፡ አኹን የምትማሩት ትምህርት ለወደፊት ኑሮአችኁ መሠረት በመኾኑ ተግታችኁ ተማሩ፤
እሺ?! እግዚአብሔር ብርታትን እንዲሰጣችኁ፣ የእናንተንና የቤተ ሰቦቻችኁ ጤንነት እንዲጠብቅላችኁም ዘወትር ጸልዩ፡፡ እግዚአብሔር
ጸሎታችኁን እንዲሰማችኁም ለወላጆቻችኁና ለታላላቆቻችኁ በቅንነት ታዘዙ፡፡ ይኽን ካደረጋችኁ፥ ዕቅዳችኁና ምኞታችኁ ይሳካላችኋል፡፡
ልጆች! ባለፈው ሳምንት የተማርነውን ታስታውሳላችኁ? እስኪ ምን ምን ተማርን?
ጐበዞች!!! ጥያቄውንስ ሠራችኁት? ስንት አመጣችኁ? እናንተ ጐበዞች ስለኾናችሁ ደፍናችኁታል አይደል? በጣም ጐበዞች፡፡ ለዛሬ ደግሞ
እግዚአብሔር ረቡዕ፣ ሐሙስ እና ዓርብ ምን ምን እንደፈጠረ እንማራለን፡፡ እግዚአብሔር ልቡናችንን ይክፈትልን፡፡ አሜን!!!
አራተኛው
ቀን
ልጆች አራተኛይቱ ቀን ረቡዕ ትባላለች፡፡ እግዚአብሔር
በዚኽ ቀን ፀሐይን፣ ጨረቃን እና ከዋክብትን ፈጠረ፡፡ ፀሐይ በሰማይ ላይ ኾና ቀን ቀን ታበራልናለች፡፡ ጨረቃና ከዋክብት ደግሞ
ማታ ማታ ያበሩልናል፡፡
አምስተኛ
ቀን
አምስተኛው ቀን ሐሙስ ይባላል፡፡ በዚኽ ቀን እግዚአብሔር በውኃ ውስጥ የሚኖሩትን እንስሳት ፈጠረ፡፡ በውኃ ውስጥ
የሚኖሩት እንስሳት ዓሣ፣ አዞ እና የመሳሰሉት ናቸው፡፡
ትንሽ ቈይቶም ርግብ፣ ቁራ፣ አሞራ እና ሌሎች ወፎችን ፈጠረ፡፡ ደግሞ እንዴት
እንደ ፈጠራቸው ታውቃላችኁ? “አንቺ ውኃ! እነዚኽን እንስሳት አስገኚ” ሲላት ውኃይቱም “እሺ” ብላ በውኃ ውስጥ የሚኖሩትን እንስሳት
እና ወፎችን አስገኘች፡፡ እግዚአብሔር የማይችለው ምንም የለም፡፡
ስድስተኛ
ቀን
ስድስተኛዋ ቀን ዓርብ ትባላለች፡፡ እግዚአብሔር
መፍጠር የጨረሰውም በዚኽች ዕለት ነው፡፡
በዚኽ ዕለት መዠመሪያ ድመት፣ ውሻ፣ በግ፣ በሬ፣ አንበሳ፣ ቀበሮ፣ እና ሌሎች
የምድር እንስሳትን ፈጠረ፡፡ የፈጠራቸውም “አንቺ ምድር! እነዚኽን እንስሳት አስገኚ” ሲላት ነው፡፡ ምድርም “እሺ” ብላ እነዚኽን
የምድር እንስሳትን አስገኘች፡፡ አይገርምም ልጆች! በጣም ይገርማል፡፡ እንደዚኽ ማድረግ የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ ስሙ
የተመሰገነ ይኹን፡፡
በመጨረሻም እግዚአብሔር ሰውን ከምድር አፈር ፈጠረው፡፡ የሕይወት እስትንፋስም
እፍ አለበትና ሕያው ኾነ፡፡ ከዚኽ በኋላ እግዚአብሔር፥ አዳም እንቅልፉ እንዲመጣ አደረገና አስተኛው፡፡ ከዚያ በኋላ ከአዳም ጐን
አንዲት አጥንት ወሰደና ሔዋንን ፈጠራት፡፡
ልጆች! እግዚአብሔር በእጁ የሠራው ፍጥረት ሰው
ብቻ ነው፡፡
ልጆች! በሉ እንደተለመደ ትምህርታችንን ከመጨረሳችን በፊት የሚከተሉትን ጥያቄዎች
መልሱ፡፡ ወላጆች! ልጆች ጥያቄውን በትክክል መመለሳቸውን አይታችኁ አርሙላቸው፡፡
1. አምላካችን
እግዚአብሔር በቀን እና በሌሊት እንዲያበሩልን የፈጠራቸው እነማንን ነው? ………………… ……………… …………….
2. በውኃ
ውስጥ ከሚኖሩ እንስሳት ኹለት ጥቀሱ ……….. …………..
3. በምድር
ከሚኖሩ እንስሳት ሦስት ጥቀሱ ………… ……………
4. እግዚአብሔር
አምላካችን ዓርብ ምን ምን ፈጠረ? ………… ……………
በሉ ልጆች! ለዛሬ በዚኽ ይበቃናል፡፡ በቀጣይ ክፍል እስከምንገናኝ ድረስ ደኅና ሰንብቱ፡፡ እግዚአብሔር በሰላም ያገናኘን፡፡
አሜን!!!
No comments:
Post a Comment