Tuesday, September 2, 2014

አዲሱ ዓመት - ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዳስተማረው (ክፍል ፪)




(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ነሐሴ ፳፯ ቀን፣ ፳፻፮ ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
የቀጠለ…

 ከገቢረ ኀጢአት ሳይወጡ አዲስ ዓመት ሲመጣ መደሰት፣ ብዙ መብልና መጠጥ ማዘጋጀት፣ አዲስ ልብስም መልበስ ጥቅም የለውም፡፡ ነፍሳችን በኀጢአት እየተጨነቀች፣ ነፍሳችን ተርባና ተጠምታ ሳለ፣ የተዳደፈ የኀጢአት ልብስም ተጆቡና ሳለ አዲስ ዓመት ማክበር ለእኛ ምን ጥቅም ይሰጠናል? እንዲኽ ከገቢረ ኀጢአት ሳይወጡ አዲስ ዓመትን ማክበር ማለት ለእኔ እንደ ልጆች የዕቃ ዕቃ ጨዋታ ነው፡፡

 ክርስቶስ ከዚኹ ሥራ አውጥቶናል፡፡ ከሕፃንነት አዕምሮ ወደ ማወቅ አሸጋግሮናል፡፡ ከምድራውያን ለይቶ ከሰማያውያን ጋር ደባልቆናል፡፡ ስለዚኽ “መልካሙን ሥራችኁን ዐይተው በሰማያት ያለውን አባታችኁን እንዲያከብሩ ብርሃናችኁ እንዲኹ በሰው ፊት ይብራ” እንደተባለ አፍአዊ ሳይኾን መንፈሳዊውን ብርሃን ልናበራ ይገባናል /ማቴ.5፡16/፤ በአዲሱ ዓመት፡፡ ይኽም ብርሃን ተስፋ መንግሥተ ሰማያትን የሚያስገኝ ነው፡፡
 ወዳጄ ሆይ! ቤቱ ቆሽሾ ሳለ ውጫዊ በሩን ብቻ ለማሽቀርቀር ለምን ትጨነቃለኽ? ነፍስኅ በኀጢአት ተዳድፋ ሳለ ሥጋኽን ብቻ ለማስደሰት ለምን ትሮጣለኽ? አስቀድመኽ ቤቱን (ነፍስኽን) ለማስዋብ አትሽቀዳደምምን? አስቀድመኽ ለነፍስኽ የምታስብ ከኾነ ከሰው እጅ ሳይኾን ከክርስቶስ እጅ ሹመት ሽልማት ትቀበላለኽ፡፡ ኹል ጊዜ “የማደርገው ነገር እግዚአብሔር ይከብርበታልን?” ብለኽ አስብ እንጂ እንዲኹ በዘልማድ የምትመላለስ አትኹን ብዬ እመክርኻለኁ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሲመክረን፡- “እንግዲኽ የምትበሉ ወይም የምትጠጡ ብትኾኑ ወይም ማናቸውም ነገር ብታደርጉ ኹሉን ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት” ያለንም ስለዚኹ ነውና በአዲሱ ዓመት በድርጊቶቻችን ኹሉ እግዚአብሔርን ለማክበር እንዘጋጅ /1ኛ ቆሮ.10፡31/፤ አዲስ ዓመት ማክበር ማለት ይኼ ነውና፡፡
 ለመኾኑ ለእግዚአብሔር ክብር ሲባል መብላት ወይም መጠጣት ማለት ምንድነው? ድኻውን ወደ ቤታችን ስንጠራው፤ በማዕዳችንም ክርስቶስ አብሮ ሲኖር ለእግዚአብሔር ክብር በላን ወይም ጠጣን ይባላል፡፡
 ሐዋርያው የመከረን ግን በመብላችን ወይም በመጠጣችን ብቻ እግዚአብሔርን እንድናከብረው አይደለም፡፡ ጨምሮም “ማናቸውም ነገር ብታደርጉ ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት” አለን እንጂ፡፡ ስለዚኽ ወደ ሸንጐም ብንሔድ፤ ወደ ቤተ ክርስቲያንም ብንሔድ ለእግዚአብሔር ክብር ልናደርገው ይገባናል፡፡ እነዚኽን ለእግዚአብሔር ክብር ማድረግ የምንችለውስ እንዴት አድርገን ነው? ወደ ቤተ ክርስቲያን፣ ወደ ሥርዓተ ቅዳሴው፣ ወደ ጉባኤው፣ ወደ ሌላውም አግልግሎት ስንሔድ አካሔዳችን እግዚአብሔር የሚከብርበት መኾን አለበት፡፡ እግዚአብሔር የማይከብርባቸው ብዙ ምልልሶች አሉና በአዲሱ ዓመት ወደ ቤተ ክርስቲያን መመላለሳችን ለእግዚአብሔር ክብር መኾን አለበት፡፡
 ከቤት ቁጭ ማለትን የምንመርጥ ከኾነም ለእግዚአብሔር ክብር ልናደርገው ይገባናል፡፡ “ምን ማለት ነው?” ልትል ትችላለኅ፡፡ ከቤት ወጥተን ክፋት ወደ መላበት ሥፍራ፣ ክርክርና ክስ ወደ ሰፈነበት ሸንጐ፣ ዘፈን ስካርና ገቢረ ኀጢአት ወደሚደገስበት ነፍስንም ወደሚያውክ ስፍራ ከመሔድ ተቈጥበን ከቤት ቁጭ ብንል ለእግዚአብሔር ክብር አደረግነው ይባላል፡፡ ስለዚኽ ከቤት ውስጥ ቁጭ ማለትም ወደ ቤተ እግዚአብሔር መሔድም እኩል ለእግዚአብሔር ክብር ማድረግ ይቻለናል ማለት ነው፡፡
 በአዲሱ ዓመት ብናመሰግንም ብንገሥፅም ለእግዚአብሔር ክብር መኾን አለበት፡፡ “ለእግዚአብሔር ክብር ሲባል ማመስገንና መገሠፅ ሲባልስ ምን ማለት ነው?” ብሎ የሚጠይቅ ሰው ሊኖር ይችላል፡፡ እንበልና በመሥሪያ ቤታችን ቁጭ ብለናል፡፡ እጂግ ክፋትን የተመሉ ሰዎችም በፊታችን ይመላለሳሉ፡፡ እነዚኽ ሰዎች በውስጣቸው በትዕቢት፣ በቁጣ፣ እንዲኹም ይኽን በመሳሰሉ ጥገኛ ተሐዋስያን የተመሉ ናቸው፡፡ ነገር ግን እጂግ ውድ የኾኑ አልባሳትን ለብሰዋል፡፡ አከባቢውን የሚለውጡ ውድ የኾኑ ሽቶዎችን ተቀብተዋል፡፡ ይኽን እያየን ሳለ አንድ ሰው መጥቶ፡- “እንዴት የታደለ ሰው እንደኾነ ዐየኸውን? ደስ አይልም?” ሊለን ይችላል፡፡ እንዲኽ የሚላችኁን ሰው ገሥፁት፤ ምክሩት፤ ወይም ዝም በሉት፡፡ ቢቻላችኁ እዘኑለት (አልቁስለት)፡፡ ተግሣፅን ለእግዚአብሔር ክብር ማድረግ ማለትም ይኼ ነው፡፡
 ተግሣፅ ሲባል ሰዎች ከነበሩበት የተሳሳተ አመለካከት ወጥተው ወደ ቀና አስተሳሰብ እንዲመጡ ማድረግ ነው፡፡ ከእንግዲኽ ወዲኽ ክፋትን ሳይኾን ምግባር ትሩፋትን እንዲያደንቁና እነርሱም ራሳቸው ለዚያ የተዘጋጁ እንዲኾኑ ማድረግ ነው፤ ተግሣፅ፡፡
 ከላይ እንደነገርኳችኁ “እንዴት የታደለ ሰው እንደኾነ ዐየኸውን? ደስ አይልም?” ለሚላችኁ ሰው እንዲኽ በሉት፡- “ወዳጄ! ይኽ ሰው ንዑድ ክቡር ነው የምትለኝ ስለምንድነው? እጂግ ግሩምና ድንቅ የኾነች ሠረገላ (በዚኹ በ21ኛው መ/ክ/ዘ. የግል አውሮፕላን ወይም ሃመር መኪና ልንለው እንችላለን!) ስላለው ወይም ብዙ ሠራተኞችን (ብዙ ኩባንያዎችን ልንለው እንችላለን!) ስለሚያስተዳድር፣ እጂግ ውድ ውድ የኾኑ ፋሽን ልብሶችን ስለሚለብስ፣ በየዕለቱም የተለያዩ የመጠጥ ዓይነቶችን ስለሚጠጣና ቅንጡ የኾነ ሕይወትን ስለሚመራ ነውን? እውነት እውነት እልኻለኁ! ለዚኽ ሰውዬስ የዕድሜ ዘመን ዕንባ ያስፈልገዋል ብዬ እነግርኻለኁ፡፡ አንተ ርሱን የምታደንቀው አፍአዊ ነገሩን ብቻ በማየት ነው፡፡ አንተ ርሱን የምታደንቀው ግሩምና ድንቅ የኾነችውን ሠረገላው፣ ወይም ወርቃማው መጋለቢያውን፣ ወይም ልብሱን ዐይተኽ ነው፡፡ ይኽ ግን ለእኔ ምንም ነው፡፡ እስኪ ንገረኝ! ከዚኽ ሰው በላይ ጐስቋላ ሰው ማን አለ? ሠለገላው፣ መጋለቢያው፣ ልብሱ፣ እና ሌላው ሃብቱ እየተደነቀለት ሳለ ርሱ ግን ምንም ሳይመሰገን ቢሞት ከርሱ የባሰ ጐስቋላ ሰው ማን አለ ትለኛለኽ? ከዚኽ ዓለም ወደዚያኛው ዓለም ይዞት የሚሔድ ብዕል (ሃብት) ከሌለው ከዚኽ ሰው በላይ ድኻ ማን አለ? ከአፍአ ሲታይ እጂግ የሚያምርበት ከውስጡ ግን የተለሰነ መቃብር ከኾነው ከዚኽ ሰውዬ በላይ ጐስቋላ ሰው ማን አለ? የእኛ የክርስቲያኖች ትክክለኛ ሃብት ጌጣ ጌጥ፣ ወይም ሠራተኞቻችን ወይም ልብሳችን ወይም ሠረገላዎቻችን አይደሉም፡፡ የእኛ ትክክለኛ ሃብት ምግባር ትሩፋታችን ነው፡፡ የእኛ ሃብት በእግዚአብሔር ማመናችንና መታመናችን ነው፡፡”
 ዳግመኛም እጅግ ድኻ፣ በጓደኞቹ ዘንድ ዕድሜውን በሙሉ እንደ ፋራና ያልዘመነ ሰው የሚቈጠር፥ ግን ደግሞ በምግባር በትሩፋት ያጌጠ ሰውን ብታዩ ይኽ ሰው ንዑድ ክቡር ሰው ነው ብዬ እነግራችኋለኹ፡፡ ምንም በዚኽ ምድር ላይ ያፈራውና ያጠራቀመው ሃብት ባይኖሮውም በሰማያት ዘንድ ድልብ ሃብት አለውና ይኽ ሰው በእውነት ንዑድ ክቡር ነው ብዬ እነግራችኋለኹ፡፡
 ይኽን አመለካከት ስለያዛችኁ ብቻ ጓደኞቻችኁ፡- “ኧረ በሥሉስ ቅዱስ! ይኽ ሰውማ እጅግ የተረገመ ሰው ነው!” ቢልዋችኁ፥ “እንደዉም እንደዚኽ ሰው ንዑድ ክቡር የለም፡፡ ወዳጅነቱ ከኃላፊውና ጠፊው ሃብትና ንብረት ሳይኾን ከእግዚአብሔር ጋር ነውና ንዑድ ክቡር ነው፡፡ ዕድሜውን በሙሉ ሲያከማች የነበረው እንደ እኛ አፍአዊውን ሳይኾን ብልና ዝገት የማያገኘውን ብዕል ነበርና ንዑድ ክቡር ነው፡፡ የዚኹ ሰው ሀብቱ በትዕቢት፣ በቁጣ፣ በዘፈን፣ በስካርና በገቢረ ኀጢአት ያልቆሸሸ ንጽሐ ልቡናው ነውና ንዑድ ክቡር ነው፡፡ እስኪ ንገረኝ! ይኽ ሰው ግሩምና ድንቅ የኾነች ሠረገላ፣ በወርቅ የተሽቆጠቆጠ መጋለቢያ፣ ውድ ውድ የኾኑ አልባሳት ስለሌለው የተጐዳ ይመስልኻልን? ርስት መንግሥተ ሰማያትን ከማግኘት በላይ ሌላ ምን ሃብት አለ ብለኽ ልትነግረኝ ትችላለኽ?” ብላችኁ መልሱላቸው፡፡
 እግዚአብሔር የሚወዳችኁ እናንተም የምትወዱት ሆይ! በአዲሱ ዓመት ብቻ ሳይኾን ዘወትር እንዲኽ እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ የምንገሥፅ፣ ወይም የምናመሰግን ከኾነ ሹመት ሽልማታችን ብዙ ነው፡፡
 ልጆቼ! ይኽን ኹሉ የምነግራችኁ እንዲኹ ስሜታችኁን ለማርካት አይደለም፡፡ ይልቁንም በአዲሱ ዓመት ብቻ ሳይኾን በየዕለቱ አስተሳሰባችንን እንዲኽ የምናስተካልለው ከኾነና እኛም እንደዚኹ በምግባር በትሩፋት ለማጌጥ የምንሽቀዳደም ከኾነ ሹመት ሽልማታችን ብዙ የብዙም ብዙ መኾኑን ለማስረዳት ነው፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ክቡር ዳዊት ስለዚኹ ጕዳይ ምን እንደሚል እስኪ አብረን እናድምጠው፡- “በአንደበቱ የማይሸነግል፣ በባልንጀራው ላይ ክፋትን የማያደርግ፣ ሰርቆ ቀምቶ እናት አባቱን የማያሰድብ፣ እኩይ ምግባር በፊቱ የተናቀለት፣ እግዚአብሔርንም የሚፈሩትን የሚያከብር፣ ለባልንጀራው ምሎ የማይከዳ፣ ገንዘቡን በአራጣ የማያበድር፣ ከድኻው መማለጃን የማይቀበል፣ እንዲኽ የሚያደርግ ሰው በመከራ ሥጋ መከራ ነፍስ ለዘለዓለም አይታወክም” /መዝ.15፡3-5/፡፡ ይኽም ማለት ክፋትን በመጸየፍ በጐውንም በማመስገን እግዚአብሔርን የሚያከብር ሰው ነፍሱ ለዘለዓለም አትታወክም ማለት ነው፡፡ ዳግመኛም ይኼ ክቡር ዳዊት በሌላ ሥፍራ እንዲኽ አለ፡- “አቤቱ ባለሟሎችኅ በእኔ ዘንድ እንደምን እጅግ ንዑዳን ክቡራን ናቸው! አስቀድመው ከነበሩት ባለሟሎችኅ ይልቅም እኒኽ ፈጽመው ጸኑ!” /መዝ.139፡17/፡፡
 እግዚአብሔር ያከበረውን ግን አትገሥፁ፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር በጽድቅ በቅድስና ሕያዋን የኾኑትን ያከብራልና፡፡ በሰው ዓይን እዚኽ ግቡ የማይባሉ ድኾች ቢኾኑም በእግዚአብሔር ዘንድ ንዑዳን ክቡራን ናቸውን እነዚኽን አትገሥፁ፡፡ እግዚአብሔር ያላከበረውን ግን ገሥፁት፡፡ ምንም ያኽል በወርቅ ላይ ቆሞ በወርቅ ላይ ቢተኛም ምግባር ትሩፋትን ሳይይዝ በገቢረ ኀጢአት የፀናውን፣ በሚቀጥለው ዓመትም ይኽን ለማድረግ የሚያቅደውን ሰው ገሥፁት፡፡ በአጭር ቃል ስታመሰግኑም ስትገሥፁም ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት፡፡ አዲስ ዓመትን ማክበር ማለት እንደዚኽ በኹለንተናችን አዲስ ሰው ኾኖ በመዘጋጀት ነውና፡፡
ይቀጥላል…

No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount