Monday, September 22, 2014

ሥነ ፍጥረት (ለሕፃናት)



(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ መስከረም 12 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ልጆች እንደምን ከረማችኁ? የዕረፍት ጊዜአችኁ እንዴት አለፈ? መልካም ልጆች፡፡ እንግዲኽ ዘመነ ማርቆስ አልፎ አኹን ዘመነ ሉቃስ ገብተናል፡፡ ለአዲሱ ዓመት ያደረሰንን አምላክ እያመሰገንን በዚኽ ዓመት ደግሞ ጊዜያችንን በአግባቡ ተጠቅመን፣ በትምህርታችንም በርትተን ለጥሩ ውጤት መብቃት አለብን እሺ፡፡ ምክንያቱም ጊዜውን በአግባቡ የማይጠቀም ልጅ መጨረሻው አያምርም እሺ ልጆች፡፡ ስለዚኽ ጊዜአችንን በአግባቡ መጠቀም አለብን፡፡ ለዚኽም እግዚአብሔር ይርዳን፡፡

 ልጆች መቼም ጠፍቼባችኁ እንደ መክረሜ ሳትታዘቡኝ አትቀሩም፡፡ እስኪ እንደ እናንተ ጐበዝ እንድኾን ለእመብርሃን ንገሩልኝ፡፡ “እንደ እኛ ጐበዝ እንዲኾን እና በአግባቡ እንዲያስተምረን እርጂው” እያላችኁ ጸልዩልኝ፡፡ እሺ ልጆች? እሺ እንዳላችኁኝ እመብርሃን እሺ ትበላችኁ!!!

ልጆች! እግዚአብሔር ቢረዳን ከዛሬ ዠምሮ ተከታታይነት ያለው ትምህርት ስለምንማማር በጽሞና ተከታተሉ፡፡ ዛሬ የምዠምረው ትምህርትም የሥነ ፍጥረት ትምህርት ነው፡፡

ልጆች! በሳምንት ስንት ቀናት አሉ? እስኪ ሰማቸውን ተናገሩ፡፡ ጐበዞች! ልክ ናችኁ፡፡ በሳምንት ሰባት ቀናት አሉ፡፡ ስማቸው ደግሞ ሰኞ፣ ማግሰኞ፣ ረቡዕ፣ ሐሙስ፣ ዓርብ፣ ቅዳሜ እና እሑድ ይባላሉ፡፡ 

 ለዛሬ እግዚአብሔር በመዠመሪያዎቹ ሦስት ቀናት ምን ምን እንደፈጠረ እንማማራለን፡፡ 

ልጆች! ይኽ እኛ የምረግጠው ምድር፣ ቀና ብለን የምናየው ሰማይ ማን ፈጠረው? መቼ ተፈጠሩ?

የመዠመሪያው ቀን

እግዚአብሔር የምንረግጠውን ምድርና ቀና ብለን የምናየውን ሰማይ ከመፍጠሩ በፊት ብቻውን ይኖር ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ በጣም ቸር ስለኾነ ክብሩን ሊያካፍለን ፈለገና እኛን ፈጠረን፡፡

 ልጆች እግዚአብሔር የፈጠራቸው ፍጥረታት ብዙ ናቸው፡፡ በመዠመሪያው ቀንም መሬትን፣ ውኃን፣ እሳትን፣ ነፋስን፣ መላዕክትን፣ ጨለማን እና ብርሃንን ፈጠረ፡፡ ይኽቺ እግዚአብሔር ፍጥረታትን ለመፍጠር የመዠመሪያ ያደረጋት ቀንም እሑድ ትባላለች፡፡ 

 ደግሞ እንዴት እንደ ፈጠራቸው ታውቃላችኁ? በማሰብ እና በመናገር ብቻ፡፡ አይደንቅም ልጆች?! በጣም ይደንቃል፡፡ በማሰብ እና በመናገር መፍጠር የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ 


 ኹለተኛው ቀን
ልጆች ኹለተኛይቱ ቀን ሰኞ ትባላለች፡፡ እግዚአብሔር በዚኽች ዕለት እሑድ የተፈጠረውና ከምድር እስከ ሰማይ ድረስ ሙልት ብሎ የነበረውን ውኃ በ4 ከፋፈለው፡፡ አንዱን እጅ ከጠፈር በላይ አደረገው፡፡ ኹለተኛው እጅ ለምድር ንጣፍ አደረገው፡፡ ሦስተኛ እጅ በምድር ዙርያ እንደ መቀነት ጠመጠመው፡፡ አራተኛው እጅ ደግሞ በዚኽ ቀና ብለን በምናየው ሰማይ አደረገው፡፡ ይኽ ቀና ብለን የምናየው ጠፈር ውኃ ነው እሺ ልጆች፡፡


ሦስተኛው ቀን

እግዚአብሔር ፍጥረታትን የፈጠረባት ሦስተኛዋ ቀን ማግሰኞ ትባላለች፡፡ በዚኽች ዕለት ምድር ከውኃ ጋር ተቀላቅላ ስለ ነበር ኃይለኛ ነፋስ አመጣና አደረቃት፡፡ ከሥር እና ከዙርያዋም ውኃ አደረገላት፤ ያንንም ባሕር አለው፡፡


ከዚኽ በኋላ ባዶ የነበረችው ምድር አትክልት፣ አዝርዕት እና ዕፅዋት አስገኘች፡፡ ልጆች! አትክልት ምንድነው? አዝርዕትስ? ዛፎችንስ በደምብ ታውቃላችኁ? ልዩነታቸው ምን እንደኾነ ወላጆቻችኁን ጠይቋቸው እና ይነግሯችኋል እሺ፡፡ ጐበዞች፡፡ 

 ልጆች! የዛሬውን ትምህርታችን ከመጨረሳችን በፊት እስኪ የሚከተሉትን ጥያቄዎችን መልስ ስጡባቸው፡፡ ወላጆች! ልጆች ጥያቄውን በትክክል መመለሳቸውን አይታችኁ አርሙላቸው፡፡

1.  እግዚአብሔር የምንረግጠውን ምድርና ቀና ብለን የምናየውን ሰማይ ከመፍጠሩ በፊት ማን ጋር ይኖር ነበር?.....................
2.  መላዕክት የተፈጠሩት በስንተኛው ቀን ነው?.................
3.  በማሰብ እና በመናገር መፍጠር የሚችለው ማን ብቻ ነው?...................
4.  ከምድር እስከ ሰማይ ድረስ ሙልት ብሎ የነበረውን ውኃ በ4 የተፋፈለው በስንተኛው ቀን ነው?..................
5.  ማግሰኞ ዕለት ከውኃ ጋር ተቀላቅላ የነበረችው ምድር የደረቀችው በምንድነው?....................

 በሉ ልጆች! ለዛሬ በዚኽ ይበቃናል፡፡ በቀጣይ ክፍል እስከምንገናኝ ድረስ ደኅና ሰንብቱ፡፡ እግዚአብሔር በሰላም ያገናኘን፡፡ አሜን!!!

No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount