Thursday, February 12, 2015

ቅዱሳት መጻሕፍት ስለማንበብ

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሐሙስ የካቲት 5 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
እስኪ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ መጽሐፍ ቅዱስን ላለማንበብ ምክንያት ይደረድሩ ለነበሩ ሰዎች ይሰጣቸው የነበረውን ተግሣፅ ከዚኽም ከዚያም ያሰባሰብኩትን አንድ ላይ አድርጌ ላካፍላችኁና ራሳችንን እንመርምርበት፡-
·        መጽሐፍ ቅዱስ የለንም የሚሉ ነበሩ፡፡ ይኽም በጣም ውድ ስለኾነ ነው፡፡ 4ኛው ... አንድን ሙሉ መጽሐፍ ቅዱስ ለመግዛት የአንድ ዓመት ደመወዝ ነበርና፡፡ ሊቁ ግንይኽ ምክንያት አይኾንም፡፡ ብያንስ መጽሐፍ ቅዱስ ሙሉው ባይኖራችኁም ከወንጌል አንዱን ብቻ መግዛት ትችላላችኁ፤ ርሱንም ዘወትር ማንበብ ትችላላችኁይላቸው ነበር፡፡ይኽን ማድረግ ባትችሉ እንኳን ዘወትር ወደዚኽ ጕባኤ በመምጣት በነጻ መማር ትችላላችኁ፡፡ ብያንስ ወደ ቅዳሴው ኑ፡፡ እዚያ የሚነበበውንና የሚተረጐመውን በሥርዓት አዳምጡ፡፡ ወዮ! እዚኽ ስትመጡ ትቁነጠነጣላችኁ፤ ሙቀቱ ብርዱ ትላላችኁ፡፡ ወደ ገበያ ቦታ፣ ወደ ተውኔት፣ ወደ ስታድዬም ስትሔዱ ግን ምንም አይመስላችኁም፡፡ ዶፍ ዝናብ ቢዘንብባችኁ፣ ሙቀቱ አናትን የሚበሳ ቢኾን፣ በውኃ ጥም ብትያዙ ትቋቋማላችኁ፡፡ ታድያ ምን ዓይነት ይቅርታ ይኾን የሚደረግላችኁ?” ይላቸው ነበር፡፡
 
·        ባለጸጐቹም ቢኾኑ ልክ በዚኽ ሰዓት ሃመር መኪና እንደሚይዙት በቤታቸው እጅግ ያማረና የተሸቆጠቆጠ መጽሐፍ ቅዱስ ቢኖራቸውም አንድም ቀን ገልጠው አያነቡትም ነበር፡፡ ለእነዚኽ ሰዎች የሚሰጣቸው ተግሣፅ፡- “መጽሐፍ ቅዱሱን እንዲኽ በሚያምር መልኩ እቤታችኁ ቢቀመጥ ግን ደግሞ ባታነቡት ምን ይጠቅማችኋል? እንዲኽ ማድረጋችኁስ ባለጸግነታችኁን ለማሳየት ካልኾነ በቀር ምን ፋይዳ አለው? ስለምን መጽሐፍ ቅዱስን የሀብት መለኪያ ታደርጉታላችኁ?”
አንዳንዶቹ ማንበብ አንችልም ይሉት ነበር፡፡ ርሱ ግንይኽ ምክንያት ነው፤ ሌላ ሰውም ቢኾን እንዲያነብላችኁ ማድረግ ትችላላችኁይላቸው ነበር፡፡
·        አንዳንዶቹሥራ ይበዛብናል፤ መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ ጊዜ የለንምይሉ ነበር፡፡ ርሱ ግን ይኽ ምክንያት እንደማይኾን ይነግራቸው ነበር፡፡ቀኑን ሙሉም ቢኾን የፈረስ ግልቢያን ለመመልከት ጊዜ ለማያጥረው ሰው መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ ጊዜ የለኝም ቢል ማን ያምኗል? የፈረስ ጋላቢዎቹን ዝርዝርና ማንነታቸውን እስከ በጥልቀት የሚያውቁ የሐዋርያትን የነቢያትን ስም ግን የማያውቁ ቢኾኑ ማን ያምናቸዋል?” አቤት! ሊቁ በዚኽ ዘመን ቢኖር ኳሱን፣ ፊልሙን፣ ዘመዱን ለማየት በካፌው ለመቀመጥ ጊዜ ያለን ቅዱሳት መጻሕፍትን ለማንበብ ግን ጊዜ የሌለን ምን ብሎ ይገሥፀን ነበር?
·        አንዳንዶቹ ደግሞእኛ መነኮሳት አይደለንምይሉ ነበር፡፡ ሊቁ ግንእንደዉም እናንተ ናችኁ የበለጠ ማንበብ ያለባችኁ፤ ምክንያቱም መነኮሳቱማ ብዙውን ሰዓታቸው በጸሎት በትሕርምት ስለሚያሳልፉት የጠላት ፍላጻን መከላከል ይችላሉይላቸዋል፡፡ልጆቻችን ወደ ዓለማዊ ትምህርት ቤት ስንልካቸው ምን ያኽል እንደምንጨነቅላቸው ግልጽ ነው፡፡ ታድያ ለምንድነው በዋናው ላይ ውኃ የሌላቸው ጐድጓዶች የምናደርጋቸው?” “ልጄ ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲሔድ፤ መጽሐፍ ቅዱስንም እንዲያነብ አልፈልግምይሉ ስለነበርእነዚኽ ልጆቻችኁ ቤተ እግዚአብሔር ቢሔዱ የመዠመሪያዎቹ ተጠቃሚዎችኮ እናንተው ናችኁ፡፡ ቀድመው የሚማሩት እናትና አባትህን አክብር የሚል ነውናይላቸዋል፡፡
·        አንዳንዶቹ ደግሞየማነበው አይገባኝምይሉት ነበር፡፡ ይኽ ግን ምክንያት አይደለም፡፡ የማይገባን ሊኖር ይችላል፡፡ ርሱን ለጊዜው ማለፍ፡፡ የሚበዛው ግን የሚገባን ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በሰው ቋንቋ እንጂ በመለኮታዊ ቋንቋ የተጻፈ አይደለምና፡፡ እግዚአብሔር እኛን ከመውደዱ የተነሣ ያናገረን በሕፃንኛ (with a baby talk) ነው፡፡
          ስለዚኽ ቅዱሳት መጻሕፍትን ላለማንበብ ምንም ምክንያት መደርደር አያስፈልግም፡፡ ማንበብ የማይችልና ስልቹ ቤተ ሰብ ቢኖር እንኳን ማንበብ የሚችለው ሊያነብላቸው ይገባል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በተቀመጠበት ስፍራ ዲያብሎስ መቅረብ የማይቻለው ከኾነ ዕለት ዕለት ቃሉን ብናነበውና በልቡናችን፣ በከንፈራችን፣ በምግባራችን ብናስቀምጠውማ ዲያብሎስ በየትኛው ዓቅሙ ሊቀርበን ይችላል?፡፡ ወንድሞቼ! ይኽን ታውቁ ዘንድ እወዳለኁ! ለብዙ አሕዛብ ክርስቲያን አለመኾን ብቻ ሳይኾን ለብዙ ምስኪን ምእመናን መጥፋት ምክንያታቸው እኛው ነን፡፡ እኛ ቅዱሳት መጻሕፍትን በቅጡ ብናነብ ኖሮ እነዚኽ ነፍሳት አይጠፉምና፡፡ ክርስቲያኖች ነን እያልን ክርስቶስን በገቢር እንሰድባለን፤ ደግሞም እናሰድባለንና፡፡ ብዙ መናፍቃን ቃሉን ሲሸቃቅጡበት እኛ ግን ለጥ ብለን ተኝተናል፡፡ እንኳንስ በጽቅድ ይቅርና በአንዲት ጥቅስ እንኳን መቆም አቅቶናል፡፡ ለብዙ ሰዎች ዘፋኞች፣ ሴተኛ አዳሪዎች፣ ለመንፈሳዊ ሕይወታቸው ቸልተኛ መኾን ተጠያቂዎቹ እኛው ነን ይላል፡፡ ለብዙ ሕፃናት መጥፋት እኛው ተጠያቂዎቹ እኛው ነን፡፡
ወንድሞቼ! ስለምናገረው ንግግር ብታደንቁኝ ምን ያደርግልኛል? ስለ አሰባበኬስ ብታጨበጭቡልኝ እኔ ምን እጠቀማለኹ? እኔ የምጠቀመው ደግሞም የምማጸናችሁ በጽሞና እንድታደምጡኝና የምነግራችሁን ቃለ እግዚአብሔር ለማድረግ ስትፋጠኑ ብቻ ነው፡፡ እንዲኽ ስታደርጉ ነፍሴ ስለ እናንተ ሐሴት ታደርጋለች፡፡ የምናገረውን ሳታደርጉ ስለ ንግግሬና ስለ አሰባበኬ ብቻ የምታደንቁ ከኾነ ግን ጥቅም የለውም፡፡ እንዲኽ ብዬ እየገሠፅኳችሁ ሳለ ከንቱ ጥላቻን እንዳላተርፍ እፈራለኁ፡፡ እንድታውቁት የምፈልገው ግን እንዲኽ ማለቴ እናንተን ጠልቻችኁ አይደለም፡፡ ኹላችንም እንድንድን ስለምሻ እንጂ፡፡
ዕለት ዕለት ቅዱሳት መጻሕፍትን የሚያነብ ሰው ንዑድ ክቡር ነው፡፡ መጻሕፍትን የማያነቡ ብዙ ሰዎች ሕገ እግዚአብሔርን ካለማወቅ የተነሣ ክሕደት የተባለ ክፉ ልጅን ወልደዋልና፡፡ ኃጢአት የተባለ ክፉ ዛፍም ዳግም በተወለደው ሰውነታቸው ላይ አብቅለዋልና፡፡ ደጋግመው ቅዱሳት መጻሕፍትን የሚያነቡ ግን ቢወድቁ እንኳ ተመልሰው ይነሣሉ፡፡ ወንድሞቼ! እናንተም ቅዱሳት መጻሕፍትን ከማንበብ ቸል አትበሉ፡፡ በጣም ተቸግራችኁ ለተከታታይ ዐሥር ቀናት ብቻ ይኽን ብትለማመዱት ከዚያ በኋላ ልምድ ይኾንላችኋል፡፡ 


2 comments:

FeedBurner FeedCount