Thursday, February 5, 2015

በእንተ አትሕቶ ርእስ



በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
(መቀረዝ ዘተዋሕዶ፣ ጥር 28 ቀን፣ 2007 ..)- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
  እግዚአብሔርን የምትወዱት አንድም እግዚአብሔር የሚወዳችኁ ልጆቼ! ትሕትናን ገንዘብ ማድረግ ምን ያኽል ጥቅም እንዳለው፥ በአንጻሩ ደግሞ ትዕቢትን ገንዘብ ማድረግ ምን ያኽል ጕዳት እንዳለው ታውቁ ዘንድ እወዳለኁ፡፡ ምንም ያኽል ምግባር ትሩፋት ቢኖረን፣ ብንጾም፣ አሥራት በኵራት ብናወጣ፣ ሌላም ብዙ የብዙ ብዙ ምግባራትን ብናደርግ ትሕትና ግን ከሌለን ከንቱ ነን ብዬ እነግራችኋለኁ፡፡ ምንም ያኽል ኃጥአን ሳለን ነገር ግን የተሰበረ ልቡና ካለን፥ በምግባር በትሩፋት አሸብርቀው ሳለ ትዕቢተኞች ከኾኑት ሰዎች ይልቅ በእግዚአብሔር ዘንድ ተወዳጆች ነን ብዬ እነግራችኋለኁ፡፡ ከቀራጩ በላይ ማን ኃጢአተኛ ነበር? /ሉቃ.189-14/፡፡ ነገር ግን ይኽ ኃጢአተኛ ሰው ዓይኑን ወደ ሰማይ ቀና አድርጐ ሊያይ ባለመውደዱ፣ በምትመሰገንበት በቤተ መቅደስኅ መቆም የማይቻለኝ ኀጥእ ነኝ በማለቱ ከማይቀማው፣ ከማይበድለው፣ ከማያመነዝረው፣ በሳምንት ኹለት ጊዜ ከሚጾመው፣ ከገንዘቡ ኹሉ አሥራት ከሚያወጣው ፈሪሳዊው ይልቅ በእግዚአብሔር ዘንድ ባለሟልነትን አገኘ፡፡ ይኽስ እንዴት ሊኾን ቻለ?

ይኽን ያኽል ምግባር ትሩፋትን ገንዘብ አድርጐ የነበረው ፈሪሳዊው የክፋት ኹሉ ስር የኾነውን ትዕቢት በልቡናው አኑሮ ስለነበር ነው ብዬ በእውነት እነግራችኋለኁ፡፡ ብጹዕ ጳውሎስም ይኽን በማስመልከት ሲናገር፡- “ነገር ግን እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሥራ ይፈትን፤ ከዚያም በኋላ ስለ ሌላው ሰው ያልኾነ ስለ ራሱ ብቻ የሚመካበትን ያገኛልአለ /ገላ.64/፡፡ ፈሪሳዊው ግን ይኽን አላደረገም፡፡ ይልቁንም ሌላውን ሰው ኹሉ እየኰነነ፥ በሕይወት ካለ ሰው ይልቅም እጅግ ጻድቁ ርሱ ብቻ እንደኾነ እያሰበ ወደ ቤተ መቅደሱ መጣ እንጂ፡፡ ይኽ ፈሪሳዊ ራሱን ያነጻጸረው ከዐሥር፣ ወይም ከአምስት ወይም ከኹለት ወይም ከአንድ ሰው ብቻ አይደለም፤ በዚኽ ዓለም ከሚኖሩ ሰዎች ርሱን የሚተካከለው ማንም እንደሌለ በአደባባይም ጭምር ተናገረ እንጂ፡፡ የሚተካከለው እንደሌለ ብቻም አይደለም፤ ዳግመኛም በሰው ኹሉ ላይ ፈረደ እንጂ፡፡ ይኽን በማድረጉም በሽቅድድሙ መም ላይ ወደቀ፡፡ ብዙ ዕቃዎችን የጫነች መርከብ ብዙ አስቸጋሪ የሚባሉ ማዕበላትን ተሻግራ ከወደቡ ጫፍ ልትደርስ ጥቂት ብቻ ሲቀራት ከዐለት ጋር ተላትማ እንደምትሰጥምና ጭናው የነበረው ኹሉ እንዳልነበረ እንደሚኾን ኹሉ ይኽ ፈሪሳዊም ብዙ ከጾመ፣ ሌላም ብዙ በጐ ምግባራትን ከያዘ በኋላ አንደበቱን ባለመግዛቱ ምክንያት የነበረውን ሀብተ ሥጋ ሀብተ ነፍስ ኹሉ አጣ፡፡ ምንም እንኳን ወደ ቤተ መቅደሱ ለጸሎት መምጣቱ በጐ ምግባር ቢኾንም ባደረገው ነገር ስለተመጻደቀበት፣ ራሱን ከፍ ከፍ ስላደረገበት ባዶውን ወደ ቤቱ ሔደ ብዬ በእውነት እነግራችኋለኁ፡፡


  እጅግ የምወዳችኁ ልጆቼ! ምንም ያኽል የምግባር ማማ ላይ ብንወጣም ከኹሉም ይልቅ ጐስቋሎች እንደኾንን ልናስብ ይገባናል፡፡ ትዕቢትን ከልቡናችን ነቅለን ካልጣልን በቀር ምንም መንበረ ጸባዖትን ብንደርስም ጠልፎ እንጦርጦስ ይወረውረናል ብዬ በእውነት ያለ ሐሰት እነግራችኋለኁ፡፡ ዳግመኛም ትሕትናን በልቡናችን ውሳጤ የምናኖር ከኾነ ምንም ያኽል በኃጢአት ሸለቆ ብንወድቅም መንበረ ጸባዖትን ታደርሰናለች ብዬ በእውነት ያለ ሐሰት እነግራችኋለኁ፡፡ ከፈሪሳውያን ይልቅ ቀራጮች በእግዚአብሔር ዘንድ ባለሟልነትን ያገኙት ልበ ትሑታን ስለነበሩ ነው፡፡ ትዕቢት፣ ልቡናንም ከፍ ከፍ ማድረግ ከዲያብሎስ ይልቅ የከፋን እንኾን ታደርገናለች፡፡ ፈያታዊ ዘየማን ከሐዋርያት አስቀድሞ ገነት የገባው ልበ ትሑት፣ ኃጢአቱን ዐውቋት ይናዘዛት ስለነበር ነው፡፡ ኃጢአታቸውን ዘወትር የሚያስቡ ደግሞም የሚናዘዝዋት ሰዎች ንዑዳን ክቡራን ናቸው፡፡ ምንም ያኽል በጐ ምግባር እንደሠሩ የሚያውቁ፥ ነገር ግን ምንም በጐ ምግባር እንዳልሠሩ ኾነው ልቡናቸውን ዝቅ ዝቅ የሚያደርጉ ሰዎች ሹመት ሽልማታቸው እንዴት የበዛ ይኾን? ኃጢአተኛ ኾኖ ሳለ ራሱን ዝቅ ዝቅ የሚያደርግ ሰው በትዕቢት ከተያዘ ጻድቅ ሰው ይልቅ ንዑድ ክቡር ነው፡፡ እንግዲኽ ኃጢአተኛ ኾኖ ሳለ ራሱን ዝቅ ዝቅ የሚያደርግ ሰው ይኽን ያኽል ንዑድ ክቡር ከኾነ፥ ጻድቅ ኾኖ ሳለ ራሱን ዝቅ ዝቅ የሚያደርግ ሰው ደግሞ ከዚኽ ይልቅ እንዴት ይከብር ይኾን? የምግባሩ መዓዛ፣ የትሩፋቱ በጐ ጠረን እስከየትኛው ሰማይ ይወጣ ይኾን? አዎ! የዚኽ ሰው የምግባሩ ዕጣን መንበረ ጸባዖት ይደርሳል፡፡ በእውነት ያለ ጥርጥር በማዕከለ ሠራዊተ መላእክት ይገባል፡፡ ከዚኹ በተቃራኒ በበጐ ምግባር ያጌጠ ሰው ትዕቢተኛ በመኾኑ ብቻ ይኽን ያኽል ጉዳት የሚያመጣበት ከኾነ፥ በኃጢአት ዐዘቅት ተዘፍቀው ሳሉ ትዕቢትን የሚጨምሩ ሰዎች እንደምን ይዋረዱ ይኾን?
 የምወዳችኁ ልጆቼ! ይኽን ኹሉ የምላችኁ በጐ ማድረግን ቸል እንል ዘንድ አይደለም፤ ከኹሉም አስቀድመን ልቡናን ከፍ ከፍ ማድረግ አስወግደን ልበ ትሑታን እንኾን ዘንድ ስለምሻ ነው እንጂ፡፡ ትሕትና የጥበብ ኹሉ መሠረት ናት፡፡ ምንም ያኽል በጐ ምግባር ቢኖረን፣ ምጽዋትም ቢኾን፣ ጸሎትም ቢኾን፣ ጾምም ቢኾን፣ ሌላም ብዙ የብዙ ብዙ ምግባር ቢኖረን የእነዚኽ ምግባራት መሠረት የሚኾን ትሕትናን ካልያዝን ቤታችን በአሸዋ እንደተሠራ ቤት ከንቱ የከንቱ ከንቱ ነው፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላ መውደቁ አይቀሬ ነው፡፡ እነዚኽ በጐ ምግባራቶቻችን ያለ ትሕትና ብቻቸውን መቆም አይችሉም፡፡ ምንም ያኽል ትዕግሥተኞች ብንኾን፣ ደናግላን ብንኾን፣ ፍቅረ ንዋይ የጠፋልን ብንኾን፣ ሌላም እናንተ የምትጠቅሱት በጐ ነገር ቢኖረን ትሕትና ግን ከሌለን እነዚኽ ኹሉ ጥቅም የላቸውም፤ በእግዚአብሔር ዘንድም ንጹሐን መሥዋዕቶች አይደሉም፡፡ ስለዚኽ እጅግ የምወዳችኁ ልጆቼ! በቃላችንም፣ በግብራችንም፣ በሐሳባችንም ትሕትናን ገንዘብ እናድርግና ከላይ የጠቀስናቸውን በጐ ምግባራት በርሷ መሠረትነት እናንፃቸው (እንገንባቸው) ብዬ እማልዳችኋለኁ፡፡






2 comments:

FeedBurner FeedCount